Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትየሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የውይይት መድረኮች ጅማሮ ችግሮች

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድና የውይይት መድረኮች ጅማሮ ችግሮች

ቀን:

በአሳምነው ጎርፉ

በሰኔ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ሪፖርተር ዕትም ላይ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሁለት ላይ ያተኮሩ የተለያዩ ጠንካራ ጽሑፎች ተስተናግደዋል፡፡ አንደኛው የቀጣዩ ዘመን ዕቅድ ሥጋት ሙስና እንደሆነ የሚያሳዩ ነጥቦችን ያተተ ነው፡፡ ሌላኛው በዕቅዱ ላይ የሚወያዩ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችንና ዝግጅቶችን አስመልክተው የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች የሰጡትን መግለጫ ይመለከታል፡፡ ይህን ጽሑፍ እንድመለስበት የጋበዘኝ እውነት ግን የሪፖርተር ርዕሰ አንቀጽ ነው፡፡

ከዕቅድ ዝግጅቱ በላይ ተወያይቶ የጋራ ማድረጉ ላይ ጥብቅ ማሳሰቢያ ያሰፈረው ይህ ጽሑፍ ‹‹… ዕቅዱ ከፍተኛ የሕዝብ ተሳትፎና የባለሙያዎች ግብዓት ያስፈልገዋል›› በማለት በአፅንኦት ገልጾታል፡፡ በተለይ በዕቅድ ውይይቱ ላይ ሊሳተፉ የሚገባቸው የሕዝብ ወኪሎች ከድርጅታዊ አሠራር ውጪ እንዲመረጡ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተባለው በነፃነት እንዲመክሩበት፣ የምሁራንና የባለሀብቶች ግልጽ ተሳትፎ እንዲደረግበት አሳስቧል፡፡ ሥጋቱንም አስቀምጧል፡፡ ይህ የሚሆነው ደግሞ ለሌላ ለምንም ዓይነት ዓላማ ሳይሆን ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ብቻ እንደሆነ በመጠቆም፡፡

- Advertisement -

ዕቅዱ መንግሥት ድህነትን ለመቀነስ ብቻ ሳይሆን ወደ ሌላ ምዕራፍ ትራንስፎርም ለማድረግ ያለመበት እንደመሆኑ ሕዝቡ በግልጽ መምከሩ ፋይዳ አለው፡፡ ገዢው ፓርቲ የራሱ የፖለቲካ ድል አድርጎ ‹‹በድርጅት›› ሒሳብ ብቻ ከሄደበትም ስኬቱ የተሟላ ካለመሆኑ ባሻገር የፕሮፓጋንዳ ትርፍ እንኳን ሊያስገኝ የሚችል አይደለም፡፡ ይህን አስመልክቶ ከሰሞኑ እየተሻሻለ ቢመስልም ገና በቀዳሚዎቹ ቀናት የታየውን ክፍተት እንመልከት፡፡

የዕቅድ ውይይቱ ለግብዓት ወይስ ለሕዝብ ግንኙነት?

በዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ እምነት ብቻ ሳይሆን በገለልተኝነት ሐሳባቸውን በገለጹልኝ በርካታ ወገኖች፣ ሰሞኑን በየክልሉ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አባላት የጀመሩት ውይይት ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ አይመስልም፡፡ ለዚህ አባባል መነሻ የሚሆነው በሁለም መድረኮች ማለት ይቻላል የኢሕአዴግ የድርጅት፣ የፎረምና የሊግ አባላት የተሳተፉበት ብቻ በመሆኑ ነው፡፡ በአጋጣሚ በደቡብ ክልል ሐዋሳ ከተማ የተካሄደውን የወጣቶችና የሴቶች መድረክ ተሳታፊዎችን በግልጽ ለመረዳት ዕድል አግኝቻለሁ፡፡

አብዛኛዎቹ የመድረኩ ተሳታፊዎች በዝቅተኛው የመንግሥትና የድርጅት ዕርከን በኃላፊነት ላይ ያሉ፣ የ1ለ5 ‹‹ግንባር ቀደም መሪዎች›› እና የተለያዩ አደረጃጀት መሪዎች ናቸው፡፡ ይህ እውነት በአማራ፣ በአሮሚያም ሆነ በአዲስ አበባ የተለየ እንዳልሆነ የዓይን እማኞች አረጋግጠውልኛል፡፡

እዚህ ላይ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ለምን በዕቅድ ሰነዱ ላይ ተወያዩ የሚል ጭፍን አስተያየት የለኝም፡፡ ነገር ግን እንዴት በአገር ግዙፍ ዕቅድ ላይ ኢሕአዴግ ብቻ አወያይም ተወያይም ሆኖ ሊያፀድቅ ይፈልጋል ብዬ ስጠይቅ ይጨንቀኛል፡፡ በዚህች አገር የፖለቲካ እምነት፣ የአመለካከት፣ የሃይማኖት፣ የፆታ የሀብትም ይሁን የትምህርት ዝግጅት በመኖሩ፣ ‹‹ብዝኃነት›› ዋነኛ መገለጫዋ እንደሆነ ከመንግሥት በላይ የሚናገር የለም፡፡ መሬት ላይ ባለው አሠራር ግን የተሟላ የሕዝብ ተሳትፎ ማየት አልተቻለም፡፡ ነው ወይስ በቀጣዮቹ መድረኮች ሌሎች ወገኖችን በተናጠል ለማሳተፍ ታቅዶ ይሆን? ባለፉት ቀናት በየዩኒቨርሲቲው የተጀመረው ነፃ ምክክር በአንፃሩ የተሻለ ሆኖ አይቸዋለሁ፡፡

የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይት ሌላው ገጽታ ባለፉት አምስት ዓመታት አፈጻጸምና የቀጣዩቹ ዓመታት ግቦች ላይ አተኩሮ በመንግሥትና የድርጅት ከፍተኛ ኃላፊዎች ገለጻ መስጠት ብቻ ነው እንጂ፣ እስካሁን ባለው ሁኔታ ተጨባጭና ዕቅዱን መልሶ ለማየት የሚያስችል ግብዓትና ግብረ መልስ (Feedback) ከተሳታፊዎች ሲነገር አልታየም፡፡ ይልቁንም ግንባሩ ‹‹ማኅበራዊና መሠረታዊ ናቸው›› የሚላቸው አርሶ አደሮች፣ ሴቶችና ወጣቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ‹‹ከፍተኛ ዕድገት አምጥተናል›› በሚል እንከን የለሽ ማብራሪያ መድረኩን ሲሞሉት ታይቷል፡፡ በብድር፣ በሥራ ቦታ፣ በገበያ ትስስርም ሆነ በመሬት አቅርቦት ምቹ ሁኔታ የተፈጠረላቸውን ብቻ በማሳተፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠረውን ሥራ ፈላጊና ከድህነት መውጣት የሚሻ ወገን ማግኘት ይቻል ይሆን?

የዕቅድ ውይይቱ ሌላኛው እንከን ስለምን በቱባ ባለሥልጣናቱ ብቻ ለውይይት ይቀርባል? ዕውን የፕላንና የፕሮግራም ሙያተኞች የሉንም? የኢኮኖሚክና ሌሎች ሙያዎች ምሁራንስ ስለዕቅዱ ምን ይላሉ? የታወቀ ምላሽ የለም፡፡ ባለሥልጣናቱ በዕቅዱ ላይም ሆነ ባለፈው አፈጻጸም ላይ የሚነሳውን ነፃ አስተያየት ወይም ነቀፌታ ለመቀበልስ ምን ያህል ዝግጁ ይሆናሉ? ተናጋሪውስ እንደምን ከሙያ አንፃር ብቻ ሐሳቡን ‹‹ከፖለቲካ ውጪ›› በሆነ መንገድ በአገራዊ መንፈስ ለመናገር ይደፍር ይሆን? ማለትም ጠቃሚ ነው፡፡

እስካሁን የተካሄዱ የውይይት መድረኮችን በወጉ ላጤነ ሁሉ ኢሕአዴግ በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ከተጠቀመበት ‹‹የንቅናቄ ሥራ›› የተለየ ነገር አላሳየም፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ያለጥርጥር አሁንም ወደጎን ተብለው የሚታለፉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በርክተው እንዲወጡ ማድረጉ አይቀርም፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችንም ሆነ ትምህርት ሊወሰድባቸው የሚገቡ ጉድለቶችንም ለመለየት አያስችልም፡፡ ሌላው ቀርቶ በመንግሥት መዋቅሩም ሆነ በራሱ በማኅበረሰቡ ውስጥ የሚታዩ ስንፍና፣ ልመና፣ ሙስና፣ ጠባብነት፣ ትምክህት፣ አክራሪነትና መሰል እንቅፋቶች በአጠቃላይ ልማቱና ዕድገቱ ውስጥ የሚያሳድሩትን ጫና ለመለየት አይቻልም፡፡ ለዓመታት በድክመት እየተነሳና እየተተቸ ያለው የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጉዳይ አዲስ ፋይል ሳይከፈትለት ተድበስብሶ ማለፉ አይቀርም፡፡ በአሁኑ ውይይት በርካታ ባለሀብቶች የሚያነሱት ዋነኛው የዕድገት መሰናክል ሙስናና የደካማ አገልግሎት አሰጣጥ መሆኑም ግልጽ ሆኗል፡፡

ስለሆነም መንግሥት በቀዳሚዎቹ ቀናት የታየውን ድክመት ፈጥኖ ሊያርም ይገባዋል፡፡ ከሕገ መንግሥት ረቂቅ ጀምሮ ‹‹ሕዝብ›› ማወያየት የጀመረ ድርጅትና መንግሥት፣ በ24 ዓመታት ውስጥ አባልና ደጋፊውን ብቻ እየሰበሰበ ‹‹ሕዝብ›› ቢል ተቀባይነት ከማጣት አያመልጥም፡፡ በዕቅድ ውይይት የብዙኃኑን ድምፅ ከመስማት የቀለለ ተግባርስ ምን አለ? ‹‹ለማለት ያህል›› ብቻ ከማወያየት በላይ ግብረ መልሱን ለአንዳች ጥቅም ማዋል አለበት፡፡

በዚህ መንገድ ከቀጠልን ግን በግራ ዘመም ፖለቲካ (በተለይ ኮሙዩኒዝም ውስጥ) የተለመደው አድርባይነትና መሸፋፈን ሥር ሊሰድ ይችላል፡፡ የሕዝቡ ተሳትፎም ጎዶሎና ያልተማላ መሆኑ አይቀርም፡፡ ይህን አስመልክቶ ሀብታሙ አለባቸው የተባለ ደራሲ በቅርቡ ባሳተመው ‹‹የቄሳር እንባ›› መጽሐፍ ገጽ 53 ላይ የገለጸውን መጥቀስ እወዳለሁ፡፡

‹‹ዋና ዋናዎቹ ማኅበራዊ ምልክቶች ልክ እንደ ተፈጥሯዊ ሕግ ናቸው፡፡ … የመጀመርያው ምልክት አድርባይነት ነበር፡፡ መዋሸት ነውር መሆኑ ይቀራል፡፡ ጭራሽ እንዲያውም የሞራል ምሰሶ ሆኖት ያርፋል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ አድርባይነት እየተንሰራፋ ይሄድና ችግኝ ትከል ሲባል ‹እሺ› በማለት ተራራ ላይ ወጥቶ በጭንቅላቱ ይተክለዋል፡፡ ማታ ነው ድሌ! እያለ በጭፈራ ተራራውን ይወርዳል፡፡ መልሶ በረሃብ ሆዱን እያከከ ይታያል፡፡ በሚዲያ ሲጠየቅ ግን ‹በአስተዋዩ መንግሥታችን አመራር በቁንጣን ልንሞት ነው› ብሎ በአደባባይ ይናገራል…›› መሬት ያለው እውነት ግን ውኃውም እሳቱም፣ ጥጋቡም ረሃቡም፣ ደስታውም ለቅሶውም … መሆኑን የሰው ፍጥረት ሁሉ ሊክደው አይችልም፡፡ እንኳን በአፍሪካ ምድር በአውሮፓና በአሜሪካም ቢሆን ማለት ነው፡፡ ስለዚህ የዕቅድ ውይይቱ ሕዝቡን ለማሳተፍ መሞከሩ መልካም ነው፡፡ ነገር ግን በድፍረት ይተች፡፡ እምነትም ይያዝበት፡፡

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ‹‹ድል›› ብቻ ነው?

አገራችን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ንድፉ ከአምስት ዓመት በፊት ብቅ ስትል ብዙዎች አፈጻጸሙን ተጠራጥረውት ነበር፡፡ በእርግጥም የትሪሊዮን ብር ኢኮኖሚ ለመገንባት የተለጠጠ ዕቅድ ተይዞላቸው የታሰቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ላየ ተግባራዊ የሚሆኑ አይመስልም፡፡ አሥር የስኳር ፋብሪካዎች፣ የማዳበሪያ፣ የግብርና ግብዓት ማምረቻዎች፣ የሲሚንቶ፣ የብረታ ብረት፣ የምግብ ዘይት፣ የጨርቃ ጨርቅና የመድኃኒት ፋብሪካዎች፣ ወዘተ ዝርዝር ብዙ ነበር፡፡

ኢሕአዴግ ገና ከመነሻውም አቅም በፈቀደ መጠን በመንገድ፣ በትምህርት ቤቶች (ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ)፣ በጤና ተቋማት (ሆስፒታሎችን አካቶ) በመገንባት አይታማም፡፡ በአምስት ዓመት የተያዙ የመሠረተ ልማትና ማኅበራዊ ልማቶች ዕውን ይፈጸማሉ ተብለው ነበር፡፡ በዚህ ሒደትም ለሚሊዮኖች የሥራ ዕድል ለመፈጠርና በከፍተኛ ደረጃ ድህነትን ለመቀነስ ግብ ተቀምጧል፡፡

በዚህ ረገድ ብዙዎቹ አፈጻጸሞች አበረታች የሚባል ውጤት እንዳስመዘገቡ መግለጽ አያዳግትም፡፡ ቀላል የማይባል የአፈጻጸም ድክመትና ወደኋላ መቅረት እንዳለ መሻሻል ደግሞ ራስን ከማታለል ውጪ ሌላ ፋይዳ የለውም፡፡ ለምሳሌ የኢንዱስትሪው መስክ የኢኮኖሚውን 15 በመቶ እንዲይዝና በየዓመቱ 12 በመቶ እንዲያድግ መባሉ በከፍተኛ ደረጃ ያልተሳካ ግብ መሆኑን መንግሥት ያምናል፡፡ ለዚህም የግሉ ሴክተር ከኪራይ ሰብሳቢ አስተሳሰብ ወጥቶ ወደ ምርታማነት ባለመግባቱ እንደሆነም ይናገራል፡፡ የመንግሥት ድጋፍና ማበረታቻም በቂ እንዳልነበር በመጥቀስ፡፡

የመንግሥት ኢንዲስትራላይዜሽን መርሐ ግብርም ወደ ተግባር የመገባቱን ያህል ምርት ማስገኘት አልጀመረም፡፡ ለአብነት ያህል በዕቅዱ ላይ ስኳርን አስመልክቶ የተቀመጠው ግብ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ 2.2 ሚሊዮን ቶን ስኳር ወደ ውጭ በመላክ 661 ሚሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማግኘት ነበር፡፡

ነገር ግን እንኳንስ ስኳር ኤክስፖርት ልናደርግ እስከ ቅርብ ወራት ድረስ በትልልቅ ከተሞች በሸማቾች ማኅበራት የሚከፋፈል ስኳር ከውጭ መግዛት የመንግሥት ግዴታ እንደነበር ይታወቃል፡፡ የማይታበለው እውነት የተጀመሩ የስኳር ፋብሪካዎችና የማስፋፊያ ሥራዎች ቢኖሩም ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው የተሟላ ምርት ለመስጠት፣ ቢያንስ ከሁለት እስከ ሦስት ዓመታት የሚፈጅባቸው መሆኑ ነው፡፡

በሲሚንቶ የማምረት አቅምን 27 ሚሊዮን ቶን ለማድረስ ባይቻልም ተቀራራቢ ግምት ይታያል፡፡ ለዚህም በተለይ የግል ባለሀብቱ ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡ የብረታ ብረት የነፍስ ወከፍ ፍጆታና የአገር ውስጥ ምርት ግን ፍፁም ሊቀራረብ አልቻለም፡፡ አሁንም በውጭ ምርት ላይ የተንጠለጠለ ከመሆኑ ባሻገር፣ በአገር ውስጥ ተስፋ የተጣለባቸው ኢንዱስትሪዎች (የሚድሮክ ኮምቦልቻ ዓይነቶች) እዚህ ግባ የሚባል ጅምር አላሳዩም፡፡ በቡና፣ በአበባና በቅባት እህሎች የውጭ ምርት ረገድ ውጤታችን ገና እንቅልፍ አያስወስድም፡፡

በመሠረተ ልማት ረገድ በበጋ በክረምት መንገድ ሥራና ጥገና ከዕቅዱም በላይ የተገኘ ውጤት አለ፡፡ በባቡር ትራንስፖርት ረገድ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ 2,395 ኪሎ ሜትር ተገንብቶ ይጠቃለላል ቢባልም፣ ገና ሥራው በጅምር ላይ ነው፡፡ ለተግባሩ ወደኋላ መቅረት ዋናው የብድር ፈጥኖ አለማግኘት ሲሆን፣ ከጂቡቲ አዲስ አበባም ሆነ ከኮምቦልቻ ሀራ ገበያ መቐለ፣ ወይም ከምዕራብ ኢትዮጵያ የባቡር መስመር ዝርጋታ አገልግሎት ለመጀመር ሌላ አምስት ዓመታትን ይፈልጋል፡፡

በኤሌክትሪክ ኃይል ልማት ረገድ ከአየር ብክለት የፀዳ ስትራቴጂ መኖሩና በተለይ ለውኃ ኃይልና ለንፋስ ኃይል የተሰጠ ትኩረት እንዳለ ቢታወቅም፣ የጊዜ ጉዳይ እንደ ቁምጣ አጥሮታል፡፡ የሀብት ጉዳይም ሌላ ፈተና ሆኖ እየታዩ ነው፡፡ ለምሳሌ በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ በኤሌክትሪክ ኃይል ሽፋን ከ41 በመቶ ወደ 75 በመቶ ለመድረስ ከሁለት ሺሕ ሜጋ ዋት ወደ ስምንት ሺሕ ሜጋ ዋት ለማምረት እንደሚቻል ተቀምጧል፡፡ ይህ ውጤት ለማግኘት ቢያንስ የጊቤ ሦስት ሁለት ሺሕ ሜጋ ዋትና ከታላቁ ህዳሴ ግድብም ከፍተኛ ኃይል ለማግኘት ታስቦ ነበር፡፡ ነገር ግን ሁሉም ገና ሒደት ላይ ናቸው፡፡ በተለይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ገና ሦስትና አራት ዓመታትን አይፈልግም ማለት አጉል ተስፈኝነት ነው፡፡

በአገሪቱ የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች 40 ሚሊዮን (እንደ ዕቅዱ) ይደርስ ይሆናል፡፡ መደበኛ ስልክና የኢንተርኔት ተጠቃሚነት የታሰበውን ያህል ነው? የአገሪቱ አጠቃላይ የመጠጥ ውኃ ሽፋንስ እውን እንደተባለው 98 ከመቶ ደርሷልን? ስንቶቹ ከተሞችና መለስተኛ መንደሮች በውኃ ጥም እየተጠበሱ ነው? አዲስ አበባስ ቢሆን? በግሌ በትምህርቱ መስክ የጥራት ጉድለት ካልሆነ ሽፋኑ ከፍተኛ ውጤት የተገኘበት መሆኑን አልጠራጠርም፡፡ ከዕቅዱ አኳያ ‹‹የጎልማሶች ትምህርት ተሳትፎን 95 በመቶ ለማድረስ›› የተያዘው ግብ ግን ግማሹ እንኳን አልተሳካም፡፡

ከግብርና ምርታማነት አኳያም ቢሆን በእንስሳት ሀብት በተፈጥሮ ሀብትና የሰብል ልማት መሻሻል የታዩባቸው አካባቢዎች አሉ፡፡ በዚያው ልክ እዚህ ግባ የሚባል መሻሻል ያልታዩባቸው ዞኖችና ወረዳዎች ቁጥራቸው ትንሽ አይደለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በተፋሰሰስ ልማት “የመለስ ፓርክ” ተብለው የታጠሩ ሥፍራዎች ሳይቀሩ የተለጠፈባቸው ታፔላ ብቻ ቀርቶ እየታዩ ነው፡፡ ስለሆነም አጠቃላይ ምርታማነቱ በ2002 ዓ.ም. ከነበረበት 17 ኩንታል በሔክታር ወደ 22 ኩንታል በሔክታር ከፍ ብሏል ብሎ መግለጽ ያዳግታል፡፡ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ የቡና ምርትን 831 ሺሕ ቶን ለማድረስ የተነደፈው ዕቅድም በመጠኑ ነው ከግማሽ ያለፈው (500 ቶን)፡፡ የኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ የግብርና ምርምር፣ የሆርቲካልቸር ልማትና የሰፋፊ እርሻ (3.3 ሚሊዮን ሔክታር ለማረስ መታቀዱን ልብ ይሏል) ከተፈተሹም ቀሪ ሥራው በዝቶ ይታያል፡፡

በአጠቃላይ የዕቅዱ ስኬት ሲነሳ ቀሪ ሥራዎችና የጎደሉ ወይም የዘገዩ አፈጻጸማቸው ላይ ግልጽ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ እርግጥ ዕቅዱ ሲነደፍ ከ80 በመቶ በላይ ቢሳካም ትልቅ ስኬት ነው ከመባሉ አንፃር የአገሪቱን የፋይናንስ፣ የአመራርና የፈጻሚ አቅም በተለጠጠ ደረጃ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መገመት አያዳግትም፡፡ ግን የተሳኩትም ሆነ ወደኋላ የቀሩት ተግባራት በመንግሥትም ሆነ በራሱ በሕዝብ መግባባት ሊፈጠርባቸው ይገባል፡፡ ከዝቅተኛው አጠቃላይ የዕድገት ‹አመላካች› 11 በመቶ በታች የሆነ ውጤት መገኘቱስ ምንን ያሳያል? እዚህ ላይ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዕቅዱ በጣም የተለጠጠ ከመሆኑ የተነሳ እንዴት ሊሳካ ይችላል ተብሎ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር፡፡ እሳቸው የተለጠጠ ዕቅድ መሆኑን አምነው ዋናው ነገር ዕቅዱን መጀመር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በመጀመሪያው ዕቅድ 60 በመቶ ማሳካት ከተቻለ እንኳ ትልቅ ስኬት ነው ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ አባባላቸው መታወስ ይኖርበታል ባይ ነኝ፡፡ በአሁኑ ግምገማ ይጠቀስ እላለሁ፡፡

አገሪቱ ለዘመናት ተሸክማው ከኖረችው ድህነት፣ ኋላ ቀርነትም ሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ወጥታ ከፍተኛ ግምት በሚሰጠው የልማት ዕቅድ ላይ ማተኮሯ ማንንም በጎ አሳቢ ዜጋ የሚያኮራ ነው፡፡ ያም ቢሆን የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተግባራት በዕቅድና በአመርቂ ውጤት ካልታጀቡ፣ ሒደቱን ወደኋላ የመመለስ አደጋ ሊፈጥሩ ይችላሉ፡፡ ሁለቱ ጉዳዮች ተያይዘው የሚታዩት የሕግ የበላይነት፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት፣ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል፣ አገራዊ ስሜት መገንባት፣ የሐሳብ ነፃነት፣ የመደራጀትና የመንቀሳቀስ መብት መከበር፣ ወዘተ የመሳሰሉ ቁልፍ ጉዳዮችን የሚሸከሙ በመሆናቸው ነው፡፡

በሰሞኑ ውይይት ላይ እነዚህ ጉዳዮች ራሳቸውን ችለው የምክክር ነጥብ አለመሆናቸውም እንደ ጉድለት መታየት አለበት፡፡ ‹‹ከእነ ቶሎ ቶሎ…›› ቤት ወጥተን የምርና ከልብ ሕዝብ የሚሳተፍበት የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውይይትና ተግባር ይዘርጋ የምለውም ለዚህ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡    

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...