Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ኮሚሽኑ ከምዕራባውያን ጥቅም ይልቅ ለደሃውና ለድምፅ አልባው ሕዝብ ጥብቅና መቆሙ የተሻለ ነው››

አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፣ ተሰናባቹ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር

ከ170 በላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተወካዮች በነበሩበትና ከ1998 እስከ 2002 ዓ.ም. ባገለገለው የፓርላማ አባላት ስብስብ ያለ አንድ ተቃውሞ በ2002 ዓ.ም. ሹመታቸው የፀደቀላቸው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና፣ ባለፉት አምስት ዓመት ከስድስት ወራት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል፡፡ ከዚህ በፊት ለ30 ዓመታት ያህል በተለያዩ ቦታዎች ለዲፕሎማትነት አገልግለዋል፡፡ የኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት አምባሳደር ጥሩነህ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ኃላፊነታቸውን ያስረክባሉ፡፡ ሰለሞን ጐሹ ስለነበራቸው ቆይታ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እየተጫወተ ስላለው ሚናና ስላሉበት ተግዳሮቶች አነጋግሯቸዋል፡፡  

ሪፖርተር፡- በቆይታዬ ጥዬ አልፌያለሁ የሚሏቸው ትሩፋቶች ምንድን ናቸው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ለሚቀጥለው አመራር የማስተላልፈው ነገር ወይም የፈጸምኩት ሥራ ምንድነው? ብዬ ራሴን በምጠይቅበት ጊዜ የተሠሩ ነገሮች ቢኖሩም ብዙ የቀሩ ነገሮች እንዳሉ አስባለሁ፡፡ አንደኛ ኮሚሽኑ እንደ ተቋም በራሱ እንዲቆም ለማድረግ ችያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ኮሚሽኑን በምረከብበት ጊዜ በራሱ የሚያካሂዳቸው ሥራዎች በጣም ውስን ነበሩ፡፡ አብዛኛውን ሥራ በአማካሪዎች ነበር የሚያሠራው፡፡ የተመድ ኤጀንሲዎችም እንዲሁ ውስጥ ገብተው አብረው ሥራውን የሚያከናውኑበት ወቅት ነበር፡፡ የሰው ኃይል እጥረት ነበረበት፡፡ እኔ ስረከበው የኤክስፐርቶች ብዛት ከ20 አይበልጥም ነበር፡፡ መዋቅሩ ግን ያኔም ነበር፡፡ አሁን ተቋሙ ትልቅ ሆኗል፡፡ አሁን ከ200 በላይ ኤክስፐርቶች አሉት፡፡ አዲስ አበባ ብቻ ተወስኖ የነበረው ተቋም አሁን በሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች አሉት፡፡ ያኔ ስለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማንነት ብዙ ሰዎች አያውቁም ነበር፡፡ አሁን ብዙ ኢትዮጵያዊያን በብዛት ያውቁታል፡፡ ከዚያም አልፈው አገልግሎቱን ይጠይቃሉ፡፡ ሁለተኛ ነፃ የፍትሕ አገልግሎት ኢትዮጵያዊያን እንዲያገኙ አድርገናል፡፡ ከዚያ በፊት ነፃ የፍትሕ አገልግሎት የሚሰጠው በመንግሥት ተደግፎ አልነበረም፡፡ በተለይ ለደሃው ወገን ፍትሕን ማድረስ ክፍተት ነበረው፡፡ ኮሚሽኑ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር ነፃ የፍትሕ አገልግሎት የሚሰጡ 130 ማዕከሎችን ከፍተናል፡፡ ከ20,000 በላይ የሆኑ ደሃ ዜጎች ከማዕከላቱ አገልግሎት እያገኙ ነው፡፡ ይኼን ጥዬ በማለፌ ደስተኛ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖችን የሚመሩ ግለሰቦች በሌሎች አገሮች ከመንግሥት ጋር ተሟጋችና እሰጥ አገባ የማያጣቸው ናቸው፡፡ እርስዎ ግን ይኼ ስለማያስኬድ ከመንግሥት አካላት በተለይም ከአስፈጻሚው ጋር በጋራ መሥራት ይሻላል ብለው እንደሚያምኑ ይነገራል፡፡ ይኼ አቀራረብ ኮሚሽኑ የተሻለ ሥራ እንዲሠራ አድርጎታል ብለው ያምናሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ይኼ ኮሚሽን የተቋቋመለት ዓላማ አለ፡፡ መንግሥትም ይህንን ኮሚሽን በሚያቋቁምበት ጊዜ ያቀደው ዓላማ ይኖራል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች የተቋቋሙበት ታሪካዊ ፋይዳ የተለያየ ሊሆን ይችላል፡፡ ኮሚሽኖቹ ከመንግሥት ነፃ በሆነ ሁኔታ መንግሥት ሰብዓዊ መብት ማስጠበቁንና መጠበቁን መከታተል አለባቸው፡፡ ይኼን ዓላማ ለማሳካት ግን የሚከተሉት መንገድ በአመራሩ ይወሰናል፡፡ ይኼን ለመወሰን አካባቢያዊ ሁኔታውን መገምገም ይጠይቃል፡፡ እኛም ይሻላል ያልነውን መንገድ መርጠናል፡፡ አንዳንድ ባለሥልጣናትና የመንግሥት አካላት ኮሚሽኑ ከመንግሥት ቀጥተኛ ትዕዛዝ እየተቀበለ እንዲሄድ ፈልገው ነበር፡፡ እኛ ይኼን አላደረግንም፡፡ ኮሚሽኑ ውሳኔውን የሚሰጠው በኮሚሽነሮች ጉባዔ እንጂ በሌላ አካል ትዕዛዝ አይደለም፡፡ የውጭ አካላትን ጨምሮ አንዳንድ አካላት እንደሚፈልጉት ከመንግሥት ጋር በየቀኑ አተካሮ ውስጥ አልገባንም፡፡ መሀል መንገድ ላይ ለመሆን ነው የሞከርነው፡፡ ከመንግሥት ጋር ርቀታችንን ጠብቀን አብረን መሥራት የምንችላቸውን ነገሮች ለመሥራት ሞክረናል፡፡ በመንግሥት በኩል ደግሞ ችግሮች ናቸው የምንላቸውን ነገሮችም በገሃድ እያወጣን ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ይጠቅማል ያልነውን ነገር ለመሥራት ሞክረናል፡፡ የምዕራባውያን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ነን የሚሉ ተቋማት የሚከተሉት መንገድ አለ፡፡ የእነሱን አመለካከት የሚደግፉ ሰዎች ላይ የመብት ጥሰት ሲፈጸም ብቻ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኖች ከመንግሥት ጋር አታካራ መፍጠርን የሙሉ ጊዜ ሥራ እንዲያደርጉት ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ ከቀዝቃዛው ጦርነት የቀጠለ ባህላቸው ነው፡፡ እንደ ታዳጊና እየለማ እንዳለ አገር ይኼ ለኢትዮጵያ ያዋጣል ብዬ አላምንም፡፡ ኮሚሽኑ ከምዕራባውያን ጥቅም ይልቅ ለደሃውና ለድምፅ አልባው ሕዝብ ጥብቅና መቆሙ የተሻለ ነው፡፡     

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ከዛሬ አምስት ዓመት በተሻለ ተቋማዊ ጥንካሬ ማግኘቱ የተቋቋመለትን ዓላማ በተሻለ ሁኔታ እንዲወጣ አስችሎታል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የተመኘሁትን ያህል አልሠራም፡፡ ነገር ግን ከነበረበት ሁኔታ አንፃር በርካታ ዓላማዎቹን አከናውኗል፡፡ የሚጠበቀውን ያህል ተፅዕኖ እንዳልፈጠረ ግን እረዳለሁ፡፡ የአራተኛውን ዙር ጠቅላላ ምርጫ በመታዘብ ጥሩ ሪፖርት ያዘጋጀነው በመጣሁ በሦስት ወሬ ነው፡፡ በወቅቱ ኮሚሽኑ ከነበረው አነስተኛ የሰው ኃይል አንፃር አይቻልም ያሉ ነበሩ፡፡ እኔ ያ ልምድ ለቀጣዩና በቅርቡ ለተካሄደው ምርጫ ጠቃሚ እንደሚሆን ነበር የተከራከርኩት፡፡ በአገሪቱ የዴሞክራሲ ሒደት ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር ኮሚሽኑ እነዚህ ሥራዎችን መሥራት አለበት፡፡ ታዝበን ያወጣነው ሪፖርት የተሻለ አቅም ከነበራቸው ታዛቢዎች ሪፖርት የተሻለ ስለመሆኑ ብዙዎች መስክረውለታል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ኮሚሽኑ በዓመት እስከ 300 ሰዎች ብቻ ያስተናግድ ነበር፡፡ አሁን በሺሕ የሚቆጠር ተገልጋይ አለን፡፡ መብቴን ሊያስጠብቅ የሚችል ተቋም አለ ብሎ እየመጣ ነው፡፡ ዘንድሮ ብቻ ከ1,500 ሰዎች በላይ አገልግሎት አግኝተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በጥናት የተደገፈ መረጃ በመስጠት በኩል ከፍተኛ ክፍተት አለ፡፡ ያንን ለመሙላት የምርምር መምርያ አቋቁመን ኢትዮጵያን በሚመለከቱና አንገብጋቢ ናቸው ባልናቸው ጉዳዮች ላይ ጥናት አድርገን እያወጣን ነው፡፡ ይኼ በውስጥም በውጭም ተፅዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ ስለኢትዮጵያ የሚጽፉት የውጭ ዜጎች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ያጋንናሉ፡፡ ሜዳውም የእነሱ ይሆናል፡፡ ስለዚህ እኛ በፎርፌ እንሸነፋለን፡፡ ያንን ለማጥበብ ሞክረናል፡፡ ይኼ ባህል ከሆነና እያደገ ከሄደ ይኼ ተቋም ጥሩ ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑ አይቀርም፡፡   

ሪፖርተር፡- በቅርቡ እንዳደረጋችሁት በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሪፖርት ታቀርባላችሁ፡፡ ከምክር ቤቱ ጋር ያለዎትን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የተመረጥኩት በምክር ቤቱ ወይም በፓርላማው ነው፡፡ በርካታ ተቃዋሚዎች የነበሩበት ፓርላማ በሙሉ ድምፅ ነው የመረጠኝ፡፡ ስለዚህ የፓርላማው ድጋፍ አለኝ ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ፓርላማው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች እንድንከፍትና በጀት እንዲጨመርልን ድጋፉን ሰጥቶናል፡፡ ኮሚሽኑ እንዲያድግ ባይፈልግ ኖሮ ይህን መከልከል ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን የኮሚሽኑ ባህርይና የአገራችን ባህል ስለማይስማሙ ችግር መፈጠሩ አልቀረም፡፡ እንኳን በኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃም መሰል ተቋማት ረጅም ጊዜ አላስቆጠሩም፡፡ ይህን ተቋም ለማቋቋም አገሮች የተስማሙበት የፓሪስ መርህ የተፈረመው እ.ኤ.አ. በ1993 ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የመንግሥት አካላት ፓርላማውንም ጨምሮ በውል ተረድተዋል ማለት ያስቸግራል፡፡ ማንም የመንግሥት አካል ኮሚሽኑን ማዘዝ ወይም መቆጣጠር አይችልም ሲባል ወይም በዚያ አንድምታ በሚሠራበት ጊዜ ግር ሊላቸው ይችላል፡፡ አመራር የሚሰጠው ሰው ይኼ ችግር ሊኖር እንደሚችል መገንዘብ አለበት፡፡ የነበረኝ ግንኙነት መጥፎ የሚባል ባይሆንም አልጋ ባልጋም አልነበረም፡፡ 

ሪፖርተር፡- ባለፉት አሥር ዓመታት ፓርላማው ካወጣቸው ሕጎች መካከል ቁልፍ የሚባሉት አዋጆች ከዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችና ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ጋር አብረው አይሄዱም ተብለው ይተቻሉ፡፡ ኮሚሽኑ ለዚህ ክርክር እልባት የሚሆን አስተያየት የመስጠት ሥልጣን ቢኖረውም ይህን አላደረገም ተብሎ ይወቀሳል፡፡ አንዳንዶች ይህን ጉዳይ ፓርላማው የበቀል ዕርምጃ እንዳይወስድበት ኮሚሽኑ ስለሚፈራ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ምን ያህል እውነት ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ይህን ያላደረግነው ፓርላማውን ፈርተን አይደለም፡፡ እውነት ነው መሥራት ነበረብን፡፡ የጀመርናቸውም አሉ፡፡ ጥቂት ሕጎች የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥትና ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መርህ የተከተሉ አይደሉም የሚሉ ወገኖች ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እንደሚጮሁ አውቃለሁ፡፡ በዚህ ላይ አቋም አለመውሰዳችን ክፍተት ነው፡፡ ይህ ያልተደረገው ግን ከፓርላማው ጋር ባለን ግንኙነት አይደለም፡፡ እርግጥ በፀረ ሽብርተኝነትና በበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጆች ላይ ይህን ሥራ ለመሥራት ዕቅድ ነበረን፡፡ እውነቱን ለመናገር የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ የሚባለውን ያህል ችግር ያስከትላል ብዬ አላምንም፡፡ አንደኛ ኢትዮጵያ ከወደቀችበት ተነስታ እዚህ የደረሰችው ሰላም በመረጋገጡና በመፈጠሩ ነው፡፡ ስለዚህ ሰው ተሯሩጦ ለመሥራት አመቺ ሁኔታዎች ተፈጥረዋል፡፡ በረሃብና በጦርነት የሚነሳ ስማችን ዛሬ በፍጥነት የሚያድግ ኢኮኖሚ እየተባለ ይነሳል፡፡ በዕድገት ብቻ ሳይሆን በዴሞክራሲም ስማችን በመልካም እየተነሳ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጣና ሽብርተኝነት የሚፈለፈልበት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጠር የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ሰዎች ሕጉ ላይ መረባረባቸው ደግ አይመስለኝም፡፡ የበጎ አድራጎትና ማኅበራት አዋጁ ላይ ግን ጥናቱን ጀምረነዋል፡፡ የጀመሩት ኤክስፐርቶች በመልቀቃቸው ገና አላለቀም፡፡ ስለዚህ አንዱ ያልተሠራው በእምነት የተነሳ ሲሆን፣ ሌላው ሁኔታው ባለመመቻቸታቸው ነው፡፡ ሌሎቹ ላይ አላሰብንበትም፡፡    

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ሥራውን የሚያከናውነው በነፃነት ነው እንኳን ቢባል ብዙዎች በተለይ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማት በጫና ውስጥ የሚሠራና ነፃ ያልሆነ ተቋም ነው ብለው ያስባሉ፡፡ ይህን አመለካከት ለመቀየር ባለፉት አምስት ዓመታት ምን ሠሩ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ይኼ አመለካከት ብዙ አልረበሸኝም፡፡ እኔን የሚረብሸኝ ለጥቃት የተጋለጠው ሕዝብ ጉዳት ነው፡፡ የእነዚህን ወገኖች አመለካከት መቀየርና እምነት እንዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ተመራማሪዎችና ዓለም አቀፍ ተቋማትማ የራሳቸው አመለካከት አላቸው፡፡ የእያንዳንዱ አገር የዕድገት ሁኔታ ይለያያል፡፡ በአንዳንድ አገሮች የሚቻል ነገር በሌላው ላይቻል ይችላል፡፡ እነዚህ አካላት ለኢትዮጵያ የሚመኙት የማይሆን ነገር ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ እውነታው ነጭ ሆኖ ሰዎች የምናየው ነገር ጥቁር ነው ሊሉ ይችላሉ፡፡ ይኼ በጊዜ ሔደት እንደሚፈታ አምናለሁ፡፡ ሌሎች ወገኖችም ኮሚሽኑ የመንግሥት ተቀጥላ ነው ብለው እንደሚጽፉ አይቻለሁ፡፡ ይኼ በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት እየተቀየረ እንደመጣ ተገንዝቤያለሁ፡፡ አሁን ከእኛ መረጃ የሚወስዱ አካላት በርካቶች ናቸው፡፡ የእኛን ጥናቶችም ማጣቀስ ጀምረዋል፡፡ ችግሩ ይኖራል፡፡ ወደፊትም ይቀጥላል፡፡ ወደፊትም የሚረከበው አመራር በዚህ ሳይረበሽ የሕዝቡ ችግር ላይ አተኩሮ እንዲሠራ እመክራለሁ፡፡ ሰፊውን ሕዝብ አንቀሳቅሰን መብት የሚባለው ነገር ምን እንደሆነ ለማሳየትና የመብቱ ጠባቂ ራሱ እንደሆነ እንዲገነዘብ መዋቅር እያበጀን ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ፎረም በየቦታው አቋቁመናል፡፡ ፎረሞቹ በሕዝብና በተለያዩ ተቋማት እንዲመሩ እያደረግን ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን የሚሉ አካላት በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብትን እጅግ አጥበው ነው እየተመለከቱ ያለው፡፡ የችግሩን መሠረታዊ መነሻ ከመመርመር ይልቅ ምልክቱ ላይ ብቻ ነው የሚጮኹት፡፡ አንድ ሰው መንግሥትን ተቃውሞ በመታሰሩ መፈታት እንዳለበት ይጮሃሉ፡፡ መፈታቱ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የእሱ መፈታት ብቻውን ሥርዓቱን አይቀይረውም፡፡ ሕዝቡ ስለመብት ያለው ግንዛቤ በብዙ ሺሕ ዓመታት ጫና የተነሳ ችግር ያለበት ነው፡፡ ይኼን መቀየር ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡   

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ ላይ ከሚቀርቡ ትችቶች መካከል ዋነኛዎቹ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ሪፖርት አለማቅረባችሁና በየቦታው ተከስተዋል በሚባሉ የመብት ጥሰቶች ላይ በወቅቱ ምርመራ አድርጋችሁ ሪፖርት አለማቅረባችሁ ናቸው፡፡ ይህ ለምን አልሆነም?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- አንድ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መሥራት ካለበት ጉዳዮች ትልቁ ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ሪፖርት ማዘጋጀት ነው፡፡ ይህን ሪፖርት ለማዘጋጀት ሥራውን የጀመርነው ከሦስት ዓመት በፊት ነው፡፡ ይኼ ሪፖርት ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ተዓማኒነትህን የሚያጠናክር መሆን አለበት፡፡ ለትችት የሚዳርግህን ሪፖርት ማውጣት የለብህም፡፡ ትክክለኛ ሆነህ መገኘት አለብህ፡፡ ረቂቁን ሦስት ጊዜ አይቸዋለሁ፡፡ ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፡፡ ስለዚህ አላሳተምነውም፡፡ አሁን እየሠራነው ነው፡፡ ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ ያለመታደል ሆኖ እኔ ሲወጣ በዋና ኮሚሽነርነት አላየውም፡፡ ቀጣዩ አመራር ያወጣዋል፡፡ ለምሳሌ የእኛ መረጃ ከመንግሥት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ጋር የሚጣጣም አልነበረም፡፡ የእኛ መረጃ ወቅቱን የጠበቀ አልነበረም፡፡ ተቋሙ ወደ ሥራ ከገባ ገና አሥር ዓመቱ ነው፡፡ ስለዚህ ነገሮችን ቶሎ የመሥራት፣ የመመርመርና ሪፖርት የማድረግ ሥራ የሚፈልገው ተቋማዊ ልምድ የለውም፡፡ ዞሮ ዞሮ የምንመረምረው እኮ የመንግሥትን ሰነድ ነው፡፡ መንግሥት ያላየውን ነገር በተሻለ ሁኔታ የማየት አቅም ልትገነባ ይገባል፡፡ ይኼ አቅም ባለመገንባቱ ወደኋላ የመቅረት ነገር አለ፡፡ አሁን ብዙ አዳዲስ መምርያዎች ሥራ ጀምረዋል፡፡ የተሻለ አቅም ያላቸው ኤክስፐርቶችም ኮሚሽኑን ተቀላቅለዋል፡፡ አሁን እኮ ኢትዮጵያ የብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐ ግብር ቀርፃና አፀድቃ ተግባራዊ እያደረገች ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ያሉ ችግሮችን የሚፈትሽና መፍትሔ የሚሰጥ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የተመጣጠነ የኃይል አጠቃቀምን የሚገዛ ሕግ ባለመኖሩ፣ የሰዎች መብት እየተጣሰ መሆኑን መንግሥት አምኖ ይህን ለማሻሻል አሁን ሕግ እያረቀቀ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- መርሐ ግብሩ መዘጋጀቱ ጥሩ ቢሆንም ተግባራዊ ለመደረግ መዘግየቱ መንግሥትን አስተችቶታል፡፡ ሰነዱን ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥት ቁርጠኛ ነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- አዎ ቁርጠኛ ነው፡፡ ዕቅዱ ገና ከጅምሩ አፈጻጸም ላይ ትኩረት አድርጎ የተሠራ ነው፡፡ ዕቅዱን የሚፈጽሙ ተቋማትን እኮ አስቀድመን ለይተናል፡፡ የሚቆጣጠር የበላይ አካል ሁሉ ተቀምጧል፡፡ የእያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትን ኃላፊነት ያስቀምጣል፡፡ ሰነዱ ወደ ሥራ ከገባ ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው እየተገናኘን እየገመገምን ነው፡፡ ማን ምን ሠራ? ምን ያህል ሠራ? እነማን ወደ ኋላ ቀሩ? ምን ደረጃ ላይ ናቸው? የሚሉት ጥያቄዎች አንስተን በፍትሕ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት እንገመግማለን፡፡ ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ ሆኖ ይሳተፋል፡፡ እርግጥ ነው የጀመርነው ዘግየት ብለን ነው፡፡ ነገር ግን በዓለም ላይ የድርጊት መርሐ ግብሩን ያወጡ አገሮች 30 ብቻ ናቸው፡፡ በአፍሪካ ሰባት አገሮች ብቻ ናቸው ይህን ያደረጉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዷ ደቡብ አፍሪካ ስትሆን ዕቅዱ የተጻፈው በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብቻ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የድርጊት መርሐ ግብር የጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮን፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤትን፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን፣ ፓርላማንና ሌሎች ተቋማትን አሳትፏል፡፡ በፓርላማ ካፀደቁት ጥቂት አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ነች፡፡ ይኼ ነገር ገና መጀመሩ ነው፡፡ ወደፊት ባህል እየሆነ ሲመጣና ልክ እንደ ኢኮኖሚው በየአምስት ዓመቱ እየተዘጋጀ ከመጣ ትልቅ ለውጥ ይመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ የአሁኑ መርሐ ግብር አሥራ አንድ ችግሮችን ለይቶ ለመፍታት አቅዷል፡፡ ነገ ደግሞ ተጨማሪ 20 እና 30 ችግሮችን ለመቅረፍ ሊያቅድ ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት አድርጋችሁ ሪፖርት አውጥታችኋል፡፡ ሪፖርቶቹ ርዕሰ ጉዳዮቹ አነጋጋሪ በነበሩት ጊዜ ያልቀረቡትና የዘገዩት ለምንድነው? ሪፖርቶቹ ላይ የቀረቡት ጉዳዮችስ ስለመፈጸማቸው ክትትል ታደርጋላችሁ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ሪፖርቶቹ የዘገዩት በአቅም ማነስ የተነሳ ነው፡፡ ነገር ግን ሪፖርቶቹ ደረጃቸውን የጠበቁና ጥልቅ የሆኑ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በማረሚያ ቤቶች ላይ የሠራነው ሪፖርት በናሙና የተሠራ አይደለም፡፡ ያሉትን ማረሚያ ቤቶች በሙሉ ነው ዞረን ለማየት የሞከርነው፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ብቻ አንድ አራት ማረሚያ ቤቶችን ብቻ ነው መሸፈን ያልቻልነው፡፡ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረግነው ሰፊ ውይይት ሪፖርቱ ከመውጣቱ በፊት ነው 50 በመቶ ችግሮቹ የተቀረፉት፡፡ በጀት እንዲጨምር፣ የአያያዝ ሁኔታው እንዲሻሻል፣ መሠረታዊ አቅርቦቶች እንዲሻሻሉና ለደረሱ ጥሰቶች ካሳ ሁሉ እንዲከፈል ሪፖርቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ አሁን ሁለተኛ ዙር ጥናት እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ በኋላ በየሁለት ዓመቱ የማጥናት ዕቅድ አለ፡፡ አንድ መታወቅ ያለበት ነገር መብቶችን መጠበቅ ለሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ብቻ የተሰጠ ሥራ አይደለም፡፡ ፍርድ ቤትም የሰብዓዊ መብት ጠባቂ ነው፡፡ ፍርድ ቤት የያዘው ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አንችልም፡፡   

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ምሁራን አሁን ሥራ ላይ ካለው የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት ይልቅ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን ያጠናክራል ይላሉ፡፡ እናንተም በታዘባችሁት አራተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ኮሚሽኑ ይህን ለውጥ እንዳመለከተ የሚጠቅሱ አሉ፡፡ ይኼ አስተያየት ተገቢ ነው ይላሉ?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የእኛ ኃላፊነት ሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠውን ነገር በሥራ መተርጎም ነው፡፡ ኮሚሽኑ ለውጥ ይምጣ አላለም፡፡ ኮሚሽኑ ያለው ኢሕአዴግ የፓርላማውን 99.6 ወንበሮች ሊያሸንፍ የቻለው 30 በመቶ ድምፅ ያገኙት ተቃዋሚዎች የተከፋፈሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ይኼን ወስደው አንዳንዶች አገለባብጠው ኮሚሽኑ ተመጣጣኝ ውክልና ይደግፋል አሉ፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ የ‘አንደኛ አላፊ’ የምርጫ ሥርዓት በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱን ጠባቂ እንደሆነ ኮሚሽን እኛ የምንደግፈው ያለውን ሥርዓት ነው፡፡ እንኳን ምሁራን፣ መንግሥት ራሱ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ አደርጋለሁ ቢል አትችልም ነው የምንለው፡፡ እንኳን አሁን ባለኝ ኃላፊነት ከዚህ ከወጣሁ በኋላ በግሌ ራሱ ለውጡን አልደግፍም፡፡ ይኼን ሥርዓት የሚከተሉ እንደ እስራኤልና ጣሊያን የመሳሰሉ አገሮች ብዙ ችግር ነው የሚደርስባቸው፡፡ ይኼን ያህል ወንበር ስጠኝ እየተባባሉ መንግሥት ለመመሥረት ወራት ይፈጅባቸዋል፡፡ ይኼን ሥርዓት ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት አሁን ያለው ሰላም ይደፍርስ እንደማለት ነው፡፡ ይኼንን መፍቀድ ማለት አሁን ያሉት ፓርቲዎች እንደተከፋፈሉ ይቆዩ ማለት ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለ የተወሳሰበ አገር በዚህ ሥርዓት አይገዛም፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች ተስማምተው አንድ ሆነው ቢበዛ አራት ፓርቲ ቢኖርና ፓርቲዎቹ የሕዝብ አመኔታ ቢኖራቸው ጥሩ ነው፡፡ ልዩነትን ተቀብሎ ተስማምቶ የመሥራት ባህል በኢትዮጵያ የለም፡፡ በቅርብ ጊዜም የሚመጣ አይሆንም፡፡ ይኼ ባለበት ሁኔታ የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ይምጣ ማለትን ጆሮዬ አይሰማውም፡፡   

ሪፖርተር፡- ብዙዎች በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደቱ ላይ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሚጠበቅበትን ሚና እንዳልተጫወተ ያምናሉ፡፡ ለአንዳንዶች ይኼ ከተሰጠው ኃላፊነት ይመነጫል ሲሉ፣ ሌሎች መንግሥት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ስለሌለው ሚናውን በተገቢው ሁኔታ እንዳይጫወት ስላደረገው ነው ይላሉ፡፡ በሌላ በኩል የኮሚሽኑ የአቅም ውስንነትን የሚጠቅሱም አሉ፡፡ ለእርስዎ ዋናው ምክንያት ምንድነው?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- የተሰጠው ኃላፊነት በዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሒደቱ ላይ ሚናውን እንዲጫወት የሚያደርግ አይደለም በሚለው አልስማማም፡፡ ፀጉር መሰንጠቅ ካልሆነ በቀር የተቋቋመበት አዋጅ የሚያሠራ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓለም አቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል ለመሆን ባመለከትንበት ጊዜ የሰጡን አስተያየት ‘ኤ’ ማግኘት ከፈለጋችሁ መለወጥ አለባቸው ያሏቸው ድንጋጌዎች አሉ፡፡ እኔ ይኼ ምክንያት ነው ብዬ ነው አስተያየት የሰጠሁት፡፡ ለምሳሌ በፈለጋችሁት ጊዜ ማረሚያ ቤት ለመጎብኘት ሕጉ አይፈቅድላችሁም ነው ያሉት፡፡ እኛ ግን ተከልክለን አናውቅም፡፡ የመንግሥት ተፅዕኖን በተመለከተ መናገር የምንችለው ስለራሴ ብቻ ነው፡፡ ተፅዕኖ በመፍራት ያልሠራሁት ነገር የለም፡፡ ትልቁ ምክንያት አቅም ነው፡፡ ይኼ ወደኋላ ጎትቶናል፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሚሽኑ በሰብዓዊ መብት ይዘት ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች እንዳሉ ያስቀምጣል፡፡ በሌላ በኩል አስተያየት ሰጪዎች ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የሰብዓዊ መብት ይዞታ እየተባባሰ እንደመጣ ይገልጻሉ፡፡ ይኼን ግጭት እንዴት ያስታርቁታል?

አምባሳደር ጥሩነህ፡- ከ1997 ዓ.ም. በኋላ ኢሕአዴግ ምርጫ 97 ፈጥሮት የነበረውን ሥጋት በውል ተገንዝቦ፣ ለዚያ ሥጋት ምን ማድረግ አለብኝ ብሎ የቤት ሥራውን ሠርቶ ነው የመጣው፡፡ መንግሥት ስለሆነ ሁኔታዎቹ ይፈቅዱለታል፡፡ ሀብቱ ሆነ የሰው ኃይል አለው፡፡ ኢሕአዴግ ዲሲፕሊን ያለው ፓርቲ ነው፡፡ ይኼን የሚያስጠብቅ ሥርዓት ገንብቷል፡፡ ጠንካራ አመራርም አለው፡፡ ከዚህ በተቃራኒ የተቃዋሚ ወገኖች ወደ አንድነት መምጣት ሲገባቸው መለያየትና መባዛት ነው የተፈጠረው፡፡ አንዱ ወገን ራሱን ገምግሞ እጅግ ተጠናክሮ ያሉትን ትንንሽ ቀዳዳዎች ሸፍኖ ሲመጣ፣ ተቃዋሚው ወገን ከነበረባት ወደታች ነው የወረደው፡፡ አሁን የተገኘው ውጤት የሚገርም አይደለም፡፡ ለወደፊትስ ምን ይሆናል የሚለው ነው የሚረብሸኝ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መኖራቸው ጥሩ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አሁን የደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ ተቃዋሚዎች ሚና አላቸው፡፡ የሕዝቡንም አመኔታ አግኝተው ተመርጠው ነበር፡፡ ይኼ ኢሕአዴግ ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ አድርጎታል፡፡ አለበለዚያ በያዘው መንገድ እኮ ሊቀጥል ይችል ነበር፡፡

በዲፕሎማሲው ዓለም ለ30 ዓመት በመሥራቴ ብዙ ነገሮችን አይቻለሁ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ተከብራ፣ በትላልቆቹ ዓይን ጎልታ ታይታ የነበረበትን ጊዜ አላስታውስም፡፡ ከአሜሪካ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመርነው እ.ኤ.አ. በ1903 ነው፡፡ የአሜሪካ መሪ በሥራ ላይ እያለ ኢትዮጵያን ሲረግጥ የኦባማ የመጀመሪያ ነው የሚሆነው፡፡ የሚመጣው ስላከበረን ነው፡፡ እዚህ እንድንደርስ ኢሕአዴግ ሚናውን ተጫውቷል፡፡ ከ1997 ዓ.ም. በኋላ የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ወጣቱን በአነስተኛና ጥቃቅን፣ በኮብልስቶን ሥራ ስላስያዘውና ገንዘብ ኪሱ ውስጥ በመግባቱ ሌላው ሁለተኛ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ለመሞት አሁን አይወጣም፡፡ ከሁሉም በላይ ኢኮኖሚውን ለማሻሻል መሥራቱ ለውጥ አምጥቷል፡፡ በተመሳሳይ ለውጥ ለማምጣት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን በሚገባ መፈተሽ አለባቸው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...