Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ጆሮዬን ወይስ ዓይኔን

  በአዲስ አበባ ተወላጅ (ዲ) ኢትዮጵያዊት   

  የግል ማስታወሻዬ

  ዓርብ ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከጠዋቱ 12 ሰዓት ከቤት ወጥቼ ወደ ቦሌ አየር ማረፊያ አመራሁ፡፡ በዝና እንጂ በውን የማላውቃቸውን የትግራይ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች አክሱም፣ ዓድዋ፣ ይሓና አድ አቡንን  በእግረ መንገዴም በአድ አቡን የሚኖሩ ወ/ሮ መብራት ጎበናና ሚስተር ኒልስ ካይ (የዴንማርክ ተወላጅና በጡረታ ዕድሜያቸው በዚሁ ክልል የሚኖሩ) አበልጆቼንም ለመጎብኘት ነበር ዕቅዴ፡፡ በአጋጣሚ የጥምቀት በዓል ዓርብ ቀን ውሎ ቅዳሜና እሑድም በተከታታይ ገጥመው ረዘም ያለ ዕረፍት ቀን ሆኗል፡፡

  በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአገር ውስጥ በረራ የሚገባውን ፎርማሊቲ አሟልቼ ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት በተነሳው አይሮፕላን ተሳፍሬ ወደ አክሱም በረራ ጀመርኩ፡፡ አይሮፕላኑ ሙሉ ተሳፋሪ ይዞ ነበር፤ መንገዱም ሰላማዊና የማያንገጫግጭ ስለነበረ በሐሳቤ ብዙ የተወራለትን በዕድገቷ በተለይ ከሌሎች ክልሎች በተሻለ ሁኔታ መጥቃለች፣ አሁን ባለው የገዥ ፓርቲ ተጠቃሚ ሆናለች እየተባለ በአገር ውስጥና በውጭ ቀጥተኛ ካልሆኑ ምንጮች ሲወራልኝ የሰማሁትን እንዲሁም ከልጅነቴ እስከ ዕውቀት በትምህርት ቤትና በተለያዩ ሁኔታዎች በታሪክ የማውቃቸውን የአክሱም፣ የዓድዋ እንዲሁም ጥንታዊ ቤተ መቅደስ የሚገኝበትን የይሓንን አካባቢ በዚህ አጋጣሚ ለማየት ያለውን እውነተኛ ገጽታ በዓይኔ ለማየት፣ በጆሮዬ የሰማሁትን ለማረጋገጥ ይህንንና ሌላውንም እያሰብኩ ሳይታወቀኝ የካፒቴኑ ድምፅ ወደ መዳረሻችን ወደ አክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አየር ማረፊያ መድረሳችንንና ቀበቷችንን እንድናስር፣ የመቀመጫ ወንበራችንን ቀና አድርገን የምግብ ጠረጼዛዎችን አጥፈን እንድንቀመጥ ይነግረን ጀመር፡፡ ከተወሰኑ ደቂቃዎችም በኋላ መሬት ነካን፡፡ የአውሮፕላኑ መሬት መንካት/ማረፍ ለስላሳና ያልተወረወረ ያላስደነገጠኝ በመሆኑ በአገሬ ካፕቴን የበረራ ብቃት ተደነቅኩ/ኮራሁ፡፡ በዚሁም አብረውኝ የነበሩ የውጭ ዜጎች እንደሚያደንቁን ተስፋና እምነት ነበረኝ፡፡ በውጭ አገር በተለያየ ምክንያት ለኖረ ኢትዮጵያዊ ወይም አፍሪካዊ እኮ ይኼ ሁሉ የራስ የሆነ ነገር ያኮራል፡፡ ብዙ አንገት የሚያስደፉ ነገሮች ተከትለውን ስለሚሄዱ ይህንን ዓይነት ችሎታ ሁሉ ኮራ ያደርጋል፡፡ ሻንጣዬን ሰብስቤ ከአፄ ዮሐንስ አየር ማረፊያ ስወጣም የአየር ማረፊያውን ፅዳትና አያያዝ አደነቅኩ፡፡ ተቀባዮቼን አበልጆቼን ወ/ሮ መብራትና ሚስተር ኒልስ ካይ በሩቁ አይቼ ወደ እነሱ አቅጣጫ ተራመድኩ፡፡ የአየር ማረፊያው አካባቢም በጥሩ ሁኔታ መያዙን የመኪና ማቆሚያው አካባቢም ባለቤት እንዳለው ቤት መጠበቁም በአጽንኦት ተመለከትኩ፡፡

  ከተቀባዮቼ ጋር የናፍቆት ሰላምታ ከተለዋወጥን በኋላ ብዙ ዘመን ባገለገለች ቶዮታ ፒክአፕ መኪናቸው ሆነን በሚስተር ኒልስ ካይ ሾፌርነት ወደ አክሱም ጉዞ ጀመርን፡፡ በነገራችን ላይ ሚስተር ኒልስ ካይ ከወ/ሮ መብራት ኃይሉ ጋር ከሦስት አሠርታት ላላነሰ ጊዜ በጋብቻ በውጪ አገር የኖረና ስለኢትዮጵያ ታሪክ በሰል ያለ ዕውቀት ያለው ነው፡፡ ኒልስ ከኔ በጣም በተሻለ ሁኔታ ስለ ትግራይና አካባቢው ስለ ጥንታዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ሰፋ ያለ ዕውቀትም አለው፡፡ በመንገዳችንም ላይ ስለ አክሱም የእርሻ መሬትና የሕዝብ ቁጥር ስለታሪካዊ ቦታዎችና ስለ ከተማዋ ዕድገት ጭምር ያስረዳኝ ጀመር፡፡ እኔም በጥሞና እያዳመጥኩ በዓይኔም አካባቢውን በስስትና በጉጉት ዓይን አይ ነበር፡፡ ስለ አክሱም ካነበብኩት በስተቀር ምንም ዕውቀት አልነበረኝም፡፡ አዲስ አበባ ተወልጄ አድጌ ብዙም የገጠር ወይም የሌሎች ክልሎች ዕውቀት ስለሌለኝ ለኔ ትልቅ ተሞክሮ ነበር፡፡ ባህር ዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ሐዋሳ፣ ደሴና ድሬዳዋን በጥልቀት ባይሆንም በተወሰነ መልኩ አይቻለሁ፡፡ በደሴ ከተማ መግቢያ አካባቢው ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ተራራማ፣ ገደላማ ምድራዊ ትዕይንት ተደንቄም ነበር፡፡ ባህር ዳር፣ ጎንደርና ላሊበላ አይቼ በወቅቱ በሶሻል ሚዲያ ያየሁትን የተሰማኝን እንዲሁ ብያለሁ፡፡ ወደ መጣሁበት ልመለስና ዕለቱ የጥምቀት በዓል የሚከበርት ቀን ስለነበረና ታቦት የሚሸኝበት ሰዓት ስለደረሰ ወደ ማረፊያ ሆቴሌ የምንጓዝበት መንገድ ዝግ ሆነና መንገዳችንን ቀይረን ወደ ዓድዋ ከተማ መንገዳችንን አቀናን፡፡ እኔም የዓድዋ ስም ሲጠራ ከልጅነቴ እስከ ዕውቀት በትምህርት ቤት፣ በሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንና በመጽሐፍ ስሰማና ሳነብ በልቤ ውስጥ በብዙ ምክንያቶች ትልቅ ሥፍራ ያለው የኢትዮጵያዊነት ኩራት የአፍሪካዊ የነፃነት ምሳሌ በየውጪው አገር ስኖር ስሄድ ልቤን ከፍ፣ አንገቴን ቀና የማደርግበት ጉዳይ ስለሆነ ልቤ ሽብርብር አለ፡፡ “ዓድዋ” ትልቅ ቦታ የምሰጠውን ጉዳይ በአካል በዓይኔ በብረቱ ላይ ልጎበኝ ነው፡፡ አልኩ ለራሴ፡፡

  ታሪካዊው የዓድዋ ከተማ ከገባን ጊዜ ጀምሮ ኒልስ እያንዳንዱን ነገር ያስረዳኝ ነበር፤ ከሱ ሲጎድል እትዬ መብራት ታብራራልኝ ነበር፡፡

  በመሀከሉ ስለ ዓድዋ ጦርነት ቦታ ስለ መታሰቢያ ሐውልት ስለ ሙዚየም አሰብኩና የታለ አልደረስንም እንዴ? አልኩ፡፡ “ምኑ?” ሙዚየሙ፣ ሐውልቱ፣ ቦታው የዓድዋ መታሰቢያ የሚጎበኘው ቦታ! “ምንም የለም! ምንም ይኸው ቦታው እዚህ ጋ ምንም የለም” አለኝ፡፡ ኒልስ እትዬ መብራትም አረጋገጠችልኝ፤ ዓይኔንም ጆሮዬንም ማመን አቃተኝ፤ ልረዳው አልቻልኩም! የዓድዋ ጀግኖች ምን ይሉን? አፍሪካውያን እንዲያው የዓለም ሕዝብ ምን ይለን?

  ዓድዋ ላይ የመታሰቢያ ሐውልት፣ ሙዚየም፣ የሰማዕታት መታሰቢያ፣ እንዴት? እንዴ ዓድዋ ዓድዋ እያልን ስንዘምር ስናወራ ሕይወታቸውን የሰዉልንን ጀግኖች የምናስብበት መታሰቢያ ሳይቆም የዓድዋ ጦርነት 122 ዓመት አለፈው! ኧረ ጉድ! ምን ዓድዋ ብቻ “ማይጨውም” አለ የራሴ አዕምሮ “መቼ አየሽውና” ይኖር ይሆን? ጉርዓ፣ ጉንደት፣ መተማ፣ ሶማሊያና ባድመ ወዘተ. እንዲሁ ብዙ ጀግና ተሰዉቶ አልፏል፡፡ ታዲያ የዚህ ሁሉ ጀግና መስዋዕትነት መክፈል መታሰቢያ የለውም? ታሪክ የለውም? ለልጅ ልጅ በቅጡ በአግባቡ መተላለፍ አልነበረበትም?

  ያለፈ ታሪካችንን እንዲሁ በስም ብቻ ያለ መስዋትነት ያለ ጀግና ኢትዮጵያዊ ሕይወት የተከወነ ይመስል ታሪካችንን መርሳት ምን ማለት ይሆን? የአዕምሮዬ ጥያቄ ነበር፡፡ የዓድዋና የሌሎች ጀግኖቻችንን ስም ዝርዝር ቢቻል የሁሉንም ካልሆነ ያልታወቁት ጀግኖች ብለን ሐውልት አቁመን፣ ሙዚየም ሠርተን ማቆየት ሲገባን በዜና በወሬ ላልተወሰነ ጊዜና ሰዓት ስንዘክር ቦታው አልባሌ ቦታ፣ ያለ ምልክት ባዶ ሆኖ መቅረቱ በጣም አሳዘነኝ፤ አሳፈረኝ፡፡ ይኼ የኢትዮጵያን ታሪክ የዓድዋን ገድል የሚነግረኝ የዴኒሽ ዜጋ ተወላጅ በልቡ ምን ይል ይሆን?

  የዓድዋ ጦርነት እንዲሁ እንደተፎከረበት እንደተዘመረለት፣ ኧረ ልብ በሉ ኢትዮጵያውያን፣ ጦርነት በጦርነት እየተተካ እንደ ዳማ ጨዋታ እያለፈ እንደገና እየተደገመ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ጦርነት ታሪክ ሠርተው አገራቸውን ከነክብሩ ያስረከቡንን ጀግኖች መዘከር ማሰብ ማስታወስ ያኮራናል እንጂ አያሸማቅቀንም፡፡

  ይገርማል! በግል ኑሮዬ ምክንያት ብዙ የባዕድ አገሮችን ጎብኝቻለሁ፤ ኖሬም አይቻለሁ፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ  በቬትናም በጦርነት ለወደቁት ጀግኖች በዋሽንግተን ዲሲ በስምንት ሺ ካሬ ሜትር በሚገመት ቦታ ከ58 ሺሕ በላይ ጀግኖች ስም ተዘርዝሮ ሲገኝ፣ የኮሪያ ጦርነት ዘማቾች መታሰቢያ ደግሞ በዋሽንግተን ዲሲ ምዕራብ ፖቶማክ ፓርክ ይገኛል፡፡ ሌላው የጀርመን የ”Mountain Troops in World War II’’ ከፍራንኮ ሩሲያን ጦርነት ዘመቻ የነበሩትን ወታደሮች የሚዘክር ይገኛል፡፡

  በሌሎችም አገሮች እንዲሁ ስም ተዘርዝሮ ወይም ያልታወቀ ወታደር ተብሎ ሲዘከር ሲጎበኝ አይቻለሁ፡፡ በጣም በሚገርም ሁኔታ በደቡብ ኮሪያ የኢትዮጵያ ኮሪያ ዘማቾች የሰማዕታት ሙዚየም “Ethiopian Korean Man Vitreous Memorial” በሚል በቹንቾን ከተማ መገኘቱ ነው፡፡ ሙዚየሙ የፍቅር ቦታ ወይም “Romantic City” በምትባለው የቹንቾን ከተማ በኢትዮጵያ የሳር ጎጆ ቤት አሠራር ዓይነት ሙዚየም ተሠርቶ የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ፎቶግራፍ ተለጥፎ፣ ሐውልት ቆሞ፣ በምስል ቪዲዮ ተደግፎ የጦርነቱ ማስረጃ እየታየ “Thank you Ethiopia”  በሚል ፕሮግራም ለጉብኝት እንዲመች ሆኖ ተዘጋጅቶ ይገኛል፡፡

  ከጉብኝቱ በኋላ የደቡብ ኮሪያ ተወላጅ የሆነው ሚስተር ዴቪድ (የኮሪያ ስሙን አላስታውስም) የኢትዮጵያን ቡና በእኛ በባህላዊ አፈላል እያፈላ ቡና ጎብኝዎችን ይጋብዛል፡፡ የኢትዮጵያን ቡና በጥሬውና በተቆላ እየሸጠ ያስተዋውቃል፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ቡና እና ስለ ጦርነቱ ታሪክ ያስረዳል፡፡ በመጨረሻም በመዝገብ ስማችንን አስፍረን ፎቶ ግራፍ ተነስተን በጎብኝዎች ቦታ ላይ ለጥፈን ሄደናል፡፡ ይህንን በደቡብ ኮሪያ ቆይታዬ አይቼዋለሁ፡፡

  ያለውን ክብርና በኛ አባቶች አያቶች የጀግንነት ገደብ “Thank You” ተብያለሁ፡፡ ተመስግኜ ተከብሬ አይቻለሁ፡፡ የአገሬን የኮሪያ ጀግኖች ታሪክ በቅጡ ያልሰማሁት በወጉ ያልተማርኩትን በሰው አገር በጥሩ ሁኔታ ተጠብቆ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ባለፉ ባገደሙ ቁጥር “ኢትዮጵያዊ/ት ነህ/ነሽ” ተብሎ ሲመሰገን አይቻለሁ፡፡

  በደቡብ ኮሪያ በኢትዮጵያዊነቴ በጀግኖቼ ገድል ኩርት ብዬ ኖሬአለሁ፡፡ አልፌ ተርፌም “ኢትዮጵያዊት” ነኝ ብዬ ቀድሜ ተናግሪያለሁ፡፡ እኛ እኮ ለናንተ ነፃነት መስዋዕትነት ከፍለናል፤” ብዬ “Thank You“ ተብያለሁ፡፡ በተለይ በዕድሜ የገፉ የደቡብ ኮሪያ ተወላጆች ኢትዮጵያዊት መሆኔን ሲያውቁ “ኢትዮጵያ ቺንጉ” (ኢትዮጵያ ጓደኛ) ይሉኛል፡፡ በሰው አገር ፈገግ ብዬ አንገቴን ቀና እንዳደርግም ረድቶኛል፡፡

  በወቅቱ የዓድዋንና የሌሎቹን የጦር አውድማዎች ጉዴን ስላላየሁ በኛ አገር እንደ አቅማችን የክብር ቦታ ይኖራል ብዬ አስብ ነበር፡፡ በተለይ በተለይ “ዓድዋ!”

  በሌሎች አገሮች ያለውን የታሪክና የጀግና ሰማዕታት ክብር ዘርዝሬ አልዘልቀውም፡፡ ወደኛ አገር ወደ አክሱም፣ ዓድዋና ይሓ ጉብኝቴ ስመለስና እኛ የአፍሪካንና የዓለም ሕዝብ ጉድ ያሰኘ ብለን የምንፎክርለትን “የዓድዋ ድል” ቦታና ከተማ እንደዚሁም እንደ አልባሌ መተዋችን አሳዘነኝ፡፡ በነሱ ደረጃም ባይሆንም እንደ አቅማችን የጦርነት የነፃነት ትግል የአለመደፈር መስዋዕትነት ደም የፈሰሰበት፣ አጥንት የተከሰከሰበትን ቦታ ሙዚየም ሠርተን ሐውልት ገንብተን ለትውልድ ለጎብኚ ማቆየት ይጠቅመናል ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህም ከተማው፣ የከተማውና የአካባቢው ነዋሪ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ለትውልድም ትልቅ የአዕምሮ ኩራት ይሆናል፡፡ አገር ጎብኚ የአክሱምን ሥልጣኔ ለመጎብኘት ይተማል፡፡ በእግረ መንገዱ የዓድዋን ዝና የሰማውን በዓይኑ ለማየት ይጓጓል፡፡ ነገር ግን በቦታው ምንም የተመዘገበ፣ ለማየት የተመቻቸ ነገር ባለመኖሩ ባዶ ቦታ አይቶ ለመሄድ ይገደዳል፡፡

  ይህ ከሚሆን በጥሩ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ለአፍሪካ ምን ማለት እንደሆነ ግንዛቤ አግኝቶ እንዲሄድ ቢደረግ ከኢኮኖሚ ጠቀሜታው በተጨማሪ ለአገራችን ያላቸው አመለካከት ተስተካክሎ በተሻለ ሁኔታ እንዲገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ በስደት፣ በሥራ፣ በዲፕሎማሲና በተለያየ ሁኔታ በባዕድ አገር ያለው ኢትዮጵያዊም አንገቱን ቀና ያደርጋል፡፡ የአገር ፍቅርም ያዳብራል፡፡

  መቼም የቅርብ ትዝታ ሆኖብኝ ዓድዋ ዓድዋ አልኩ እንጂ ሌሎችም የጦርነት የታሪክ ቦታዎች በዚህ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡ የቱሪዝም ዕድገትም በሌሎች አገሮች እንደምናየው ትልቅ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሚሆን አቅም አለው፡፡

  በአገር ውስጥም ትምህርት ቤት፣ ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ሲዘጋ ጥናትና ምርምር ለማድረግ በብዙ መልኩ ጉብኝት የሚደረግበት ሁኔታና ሥፍራ ይመቻቻል፡፡ ይህ በመሆኑም የተለያየው የኅብረተሰብ ክፍል ስለ አጎራባች ክልሉ ታሪክና ባህል ዕውቀት ይገበያል፡፡ ይህም የኔነትን፣ አንድነትን፣ መተሳሰርንና የአገር ፍቅርን ያዳብራል፡፡ በኢትዮጵያዊነት መኩራት ይጎለብታል፡፡ ሌላው በጉብኝት ወቅት የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊን የትውልድ ቤት (የቤተሰብ ቤት) አይቻለሁ፡፡ አጥርና በሩን ያሠራችው አንዲት የውጭ ዜጋ መሆኗን ከአካባቢው ሰዎች ተረድቻለሁ፡፡  የአቶ ኢሳይያስ አፈወርቂ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ቤተሰብ ቤትም ዓይቻለሁ፡፡ ፎቶግራፍ አንስቻለሁ፡፡ ቤቱ ያለበትን አይቻለሁ፡፡ ያም ሆነ ይህ ይኼም እኮ ታሪካዊ ቦታ ነው፡፡ ቢጠበቅ መጎብኘት የሚገባው ቦታ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

  የሰሜኑ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ተራራማ፣ ድንጋያማና ሞቃታማ በመሆኑ የውኃ ችግር በዓድዋ፣ አክሱምና ይሓ አካባቢ የከፋ ነው፡፡ በውኃ ዕጦት በተለይ በይሓ ሕፃናትና እንስሶች ሲንገላቱ አይቻለሁ፡፡ በሌላው የኢትዮጵያ ክልል ረሃብ፣ ድርቅና የውኃ ዕጦት የለም ለማለት ሳይሆን ይኼ ብዙ የተወራለት “ተጠቃሚ” የተባለ አካባቢ ግን ምንም ያላገኘ ከአቧራና ድንጋይ በስተቀር ምንም የሌለው መሆኑን ከጆሮዬ ዓይኔ ስላሳመነኝ ያየሁትን ልጽፍ ፈልጌ ነው፡፡ ወደ ይሓ ሳቀና ከዓድዋ ወደ ይሓ መገንጠያ ድረስ የአስፋልት መንገድ (ከአዲስ አበባ ሁመራ የሚሄደው) ይሆንና እስከ ይሓ ድረስ አቧራማና ጠጠራማ ጥርጊያ መንገድ ይገኛል፡፡ አክሱምና ዓድዋን ጎብኝቶ ወደ ይሓ የዘለቀው ጎብኝ ሁሉ ይኼንን ጥርጊያ መንገድ ማለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ይሓ ደርሰን የንግሥተ ሳባን ቤተ መንግሥት (ቁፋሮው ያልተጠናቀቀ) እና የአቡነ አፍፄ ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረውን ታሪካዊ ቦታ ከጎበኘን በኋላ አስጎብኝዎቼን በይሓ “ሎጅ” ወይም “ሆቴል” መኖሩን ጠየኳቸው፡፡ ያገኘሁት መልስም ምንም እንደሌለና በውኃ ችግር ምክንያት እንደሆነ አስረዱኝ፡፡

  ይሓ በተራራ ሰንሰለት የተከበበች በጣም ለዓይን የሚስቡ በተፈጥሮ የተለያየ ቅርፅ የያዙ ተራሮች የሚገኙባት (ሹርባ የተሠራች ሴት ፀሎት የሚያደርስ ሰው፣ መሶበ ወርቅ፣ አንበሳና መንትዮች) የመሳሰሉ የሚደንቁ ቅርፅ ተራሮች የተቀጣጠሉባት ቦታ ናት፡፡

  ተራራማ መልክዓ ምድር እኮ በራሱ ትልቅ የቱሪስት መስህብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ ተራሮች “ስብሰባ” የተጠሩ ይመስል ማለቂያ የሌለው የተራራ ሰንሰለት ይታያል፡፡ ወይ ተዓምር ብዬ አድንቄአለሁ፡፡ ከባዕድ አገር የመጡ ጎብኝዎችም ተደንቀው ሲያዩ ፎቶና ቪድዮ ሲቀርፁ አይቻለሁ፡፡

  ይህችን ድንቅና ታሪከ ብዙ፣ እጅግ የተለያየ የታሪክ መስህብ ያላት አገራችን በቅጡ ባለመያዛችን ታሪካችን እንደ አልባሌ ተረት፣ ቅርፃ ቅርፃችን እንደ ልጆች መጫወቻ፣ ይህንን ያቆዩልን ጀግኖቻቸችን እንደ ማንም ሳይቆጠሩ እዚህ ደርሰናል፡፡ አሁንም አልዘገየንም፤ እኔ በራሴ በትንሽዋ የጉብኝት ዕይታዬ ለህሊናዬ ዕረፍት ስል ይህንን ብያለሁ፤ ኧረ እንደውም “ታሪካዊዋን የሃይማኖት ቦታ ኢየሩሳሌምን ለመጎብኘት ብዙ ብር ከፍለን እንሄዳለን፤ የኛ “አክሱም፣ ላሊበላ፣ አል ነጃሺ መስጊድ እኮ ከኢየሩሳሌምና መካ መዲና ያልተናነሰ የሃይማኖት ባለታሪክ ሲሆኑ፣ የበለጠ የሃይማኖት ጎብኝዎችን (Pilgrimage) ሊስቡልን ይችላሉ፡፡ ጠንክረን የሚገባንን ትኩረት ሰጥተን ከሠራን በቱሪዝም የምናገኘው ገቢ ለኢትዮጵያ ትልቅ የኢኮኖሚ ዕገዛ፣ ለሕዝብም ለከተማዎችም ዕድገት ይበጅ ነበር፡፡ የአካባቢው ተወላጅ ወጣቶችም በሥራ ምርጫ ማጣት ከቀየው ባልተሰደዱም ነበር፡፡

  እንግዲህ ያየሁትን የታዘብኩትንና የቆረቆረኝን ጸሐፊ ባልሆነ ብዕሬ እንካችሁ ብያለሁ፡፡ በተሻለ ሁኔታ የሚያስረዳ የሚመክር ደግሞ ይጨምርበት፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -