Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአካባቢ ጉዳይ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

–   ግብርና ሚኒስቴር ባለፈው ዓመት ተሞክሮው ተገድቧል

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ያለፉት አምስት ዓመታትን ሲጀምር በአስገራሚ ክስተቶች ታጅቦ ነበር፡፡ አስገራሚው ክስተት ደግሞ አገሪቱ የምትመራበትን የአምስት ዓመት የኢኮኖሚ ዕቅድ ከቀደምቱ ጊዜያት በተለየ ተፈናጥሮ የተዘጋጀበትና ሲተገበር የቆየበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ ብዙ ሲባልለት የከረመው ‹‹ተለጣጩ፣ ሩቅ ዓላሚው›› የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያውን አምስት ዓመት አገዳቦ ሁለተኛውን ለመጀመር ዕቅዶች ከየሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ተሰባስበው በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት መገምገም ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡

ከባለሥልጣናቱ መለስ ሕዝቡ ይወቃቸው የተባሉ መነሻ ዕቅዶችም እዚህም እዚያም የመወያያ ርዕስ መሆን ጀምረዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አክሲዮን ማኅበር ሐሙስ፣ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በዋና መሥሪያ ቤቱ በተጠራ ስብሰባ የሁለት ሚኒስቴሮች ዕቅድ ለውይይት እንዲቀርብ ይጠበቅ ነበር፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ከአካባቢና ደን ሚኒስቴር ጋር የተገባደደውን የአምስት ዓመት ዕቅድ አተገባበርና የመጪውን አምስት ዓመት መነሻ ዕቅድ ዝግጅት የሚመለከት ስብሰባ ተሰናድቶ ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የመጪውን ጊዜ መነሻ ዕቅዶች ከማቅረብ ተቆጥቧል፡፡ በግብርና ሚኒስቴር የኤክስቴንሽን ጄኔራል ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ መንግሥቴ፣ ሁለተኛውን ምዕራፍ የአምስት ዓመት ዕቅድ መነሻዎች ከማቅረብ ተቆጥበዋል፡፡ ያቀረቡት ምክንያትም ገና በዝግጅት ላይ ያለ፣ ያልፀደቀ ዕቅድ በመሆኑ በዚህ ላይ መነጋገር እንደማይቻል የሚያመለክት ነበር፡፡ ይህ ግን በሌሎች መድረኮች ከተካሄዱት አኳያ ሲታይ ተገቢነት የሌለው ምክንያት ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ውይይቱ የተደረገው ለቀጣዩ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብዓት ለማሰባሰብ እንደመሆኑ መጠን የግብርና ሚኒስቴር ይህንን ባለማድረጉ ዓላማውን ስቷል፡፡ የግብርና ሚኒስቴርና የአካባቢና ደን ሚኒስቴር ባለሙያዎችና ኃላፊዎች በታደሙበት መድረክ፣ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር የመጪውን አምስት ዓመት መነሻ መነሻ ዕቅዶች አቅርቧል፡፡ ግብርና ሚኒስቴር ይህን ከማድረግ መቆጠቡ መድረኩን ጉራማይሌ አድርጎታል፡፡

ይህም ቢባል ግን ግብርና ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ያከናወናቸውን ተግባራት አሰምቷል፡፡ አቶ ተስፋዬ ባሰሙት ገለጻ መሠረት የግብርና ዘርፍ ለአምስት ዓመታት የታቀዱለትን ዋና ዋና ግቦች ወደ ማሳካቱ የቀረበ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ ከተመሠረተ ጥቂት ጊዜያትን ያስቆጠረውና የቀድሞውን የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣንን የተካው፣ የአካባቢና ደን ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታትን ያከናወናቸውን ጨምሮ የመጪዎቹን አምስት ዓመታት ዕቅዶች ይፋ ሲያደርግ ካሰፈራቸው ግቦች መካከል ብክለትን ጨምሮ በአካባቢ እንክብካቤና በደን አጠባበቅ እንዲሁም በተራቆቱ ሥፍራዎች ላይ ስለሚሠሩ ተግባራት አትቷል፡፡

የአካባቢና ደን ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኑርመደድ ጀማል ይፋ እንዳደረጉት፣ ሚኒስቴሩ በአምስት ዓመት ውስጥ ከሚያከናውናቸው መካከል የአገሪቱን የደን ሽፋን ወደ 20 ከመቶ ለማድረስ ያቀደው ይገኝበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የሚካሄደው የደን ቆጠራ 60 ከመቶ መድረሱን ይፋ ያደረገው አካባቢና ደን ሚኒስቴር፣ እስካሁን ባለው ግምት መሠረት የአገሪቱ የደን ሽፋን 15.5 ከመቶ ደርሷል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከዚህም ባሻገር በዚህ ወቅት ደን ሀብት ለኢኮኖሚው የሚያበረክተው ድርሻ አራት ከመቶ ላይ ይገኛል ያሉት አቶ ኑርመደድ፣ በመጪው አምስት ዓመት በእጥፍ ለማሳደግ መታቀዱን ጠቅሰዋል፡፡

ከደን የሚገኘው ገቢ ላይ ትኩረት ካደረገው የዕቅዱ ግብ ውስጥ የደን ውጤቶችን ጥቅም ላይ ለመዋል የሚታሰበውም ይገኝበታል፡፡ በዚህ መሠረት አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አድሮችና ከፊል አርብቶ አደሮች ዓመታዊ ገቢ ውስጥ ከደን ውጤቶችም ድርሻ እንዲኖረው ታስቧል፡፡ ከአሥር እስከ 15 ከመቶ ድርሻ እንዲይዝ ይፈለጋል፡፡

አቶ ኑርመደድ እንዳሉት ለኢንዱስትሪ ጥሬ ዕቃነት እንዲውል ከውጭ የሚገባው ጣውላና መሰል ምርት 57,815 ቶን ደርሷል፡፡ በአገር ውስጥ ተመርቶ ግብዓት የሚሆነው መጠን 206,144 ቶን ሲሆን፣ በጠቅላላው 263,959 ቶን የደን ውጤቶች ለኢንዱስትሪ ግብዓትነት እየዋሉ ይገኛል፡፡ ይህንን መጠን ወደ 500 ሺሕ ቶን ለማሳደግ የሚያልመው ሁለተኛው ምዕራፍ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ ከኢንዱስትሪ ባሻገር ሌሎች አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶችንም የደን ውጤቶች ተጠቃሚ የማድረግ ፍላጎት እንዳለ አሳይቷል፡፡

ለማገዶ ፍጆታ አምስት ሚሊዮን ሜትርክ ኩብ እንጨት ይመረታል ተብሏል፡፡ ለግንባታው ዘርፍ አንድ ሚሊዮን ሜትር ኩብ እንጨት ይቀርብለታል፡፡ ለኤሌክትሪክ ኃይልና ለቴሌኮሙኒኬሽን መስመር ተሸካሚ የእንጨት ምሰሶዎች ግማሽ ሚሊዮን ሜትር ኩብ እንጨት ከደን ይቀርባል፡፡ የደን ውጤቶችን ለገበያ ከማቅረብ በተጨማሪ የተራቆቱ አካባቢዎች ላይ ይሠራል በተባለው የሁለት ሚሊዮን ሔክታር ደን ጥበቃና እንክብካቤም ይጠቀሳል፡፡ በትልልቆቹ ግድቦች ዙሪያ የሚገኙና ከንክኪ ነፃ መሆን የሚገባቸው አምስት ሚሊዮን ሔክታር የተራቆቱ መሬቶችን የመንከባከብና የመጠበቅ ሥራም በዕቅዱ ተካቷል፡፡ በዚህም መሠረት ታላቁ የህዳሴ ግድብ፣ ጊቤ 1 እና ጊቤ 3 የኃይል ማመንጫ ግድቦችን ከደለል ሙላት ለመታደግ፣ ረጅም የአገልግሎት ዘመን እንዲኖራቸው ለማድረግና ሌሎች የተራቆቱ አካባቢዎችንም እንዲያገግሙ ይደረጋል፡፡

በአንፃሩ ግብርና ሚኒስቴር ባለፉት አምስት ዓመታት አከናወንኳቸው ካላቸው ተግባራት መካከል የዋና ዋና የምግብ ሰብሎች ምርት ይጠቀሳል፡፡ በአምስት ዓመታት ውስጥ እየጨመረ መጥቶ በ2007 ዓ.ም. መጨረሻ 270 ሚሊዮን ኩንታል የሰብል ምርት ይጠቀሳል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት 190 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበርም አቶ ተስፋዬ አስታውሰዋል፡፡ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የታሰበው የሰብል ምርት 260.7 ሚሊዮን ኩንታል እንደነበርም በሰነዱ የሰፈረው ዕቅድ ያመለክታል፡፡ በዕቅዱ መሠረት የተፈጸመው ሌላው ተግባር ይታረሳል ተብሎ የታሰበው መሬት ስፋት ነው፡፡ ከ11.2 ሚሊዮን ሔክታር መሬት የተነሳው ይህ ዕቅድ፣ በአምስት ዓመቱ ማብቂያ ላይ 12.5 ሚሊዮን ሔክታር ደርሷል፡፡ ይህም ከታቀደው መጠን በላይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዕቅዱ የታሰበው የሚታረስ መሬት መጠን 12.1 ሚሊዮን ሔክታር ነበር፡፡ በአንድ ሔክታር በአማካይ ይገኝ የነበረው መጠን 17 ኩንታል እንደነበር የገለጹት አቶ ተስፋዬ፣ በአሁኑ ወቅት በሔክታር 21.5 ኩንታል ምርት ይመረታል ብለዋል፡፡

በጠቅላላው በግብርና ዘርፍ በተለይ በአርሶ አደሩ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ ዕቅዶች በአምስቱ ዓመት ዕቅድ መሠረት እንደተሳኩ ለማመላከት የሞከሩት አቶ ተስፋዬ፣ ለገበያ በሚውሉ የግብርና ውጤቶችና በሰፋፊ እርሻዎች የተከናወኑ ሥራዎችን ከመጥቀስ ተቆጥበዋል፡፡ የግብርና ዘርፍ በእነዚህ መስኮች ላይ ያሳየው አፈጻጸም ዝቅተኛ እንደነበር ዓምና በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው የ2005 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ያመላክታል፡፡

በሪፖርቱ መሠረት እስከ 2005 በጀት ዓመት በድምሩ 3.31 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ከክልሎች ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ የተደረገው ለሰፋፊ እርሻዎች ነበር፡፡ ከዚህ ውስጥ ግን እስከ 2005 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ 473 ሺሕ ሔክታር መሬት ወደ ባለሀብቶች ተላልፎ  መልማት የቻለው 11 ከመቶ ብቻ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ‹‹መረጃው በቀጣይ አቅሙና ዝግጁነቱ ያላቸውን ልማታዊ ባለሀብቶች በጥንቃቄ በመመልመል የግብርና ኢንቨስትመንትን በከፍተኛ ደረጃ ማስፋፋት የሚቻልበት ዕድል እንዳለ ያመለክታል፤›› ያለው ሪፖርቱ፣ በአበባ፣ አትክትልትና ፍራፍሬ ዘርፍም በዕቅዱ መሠረት የታሰበውን ያህል ውጤት አለመገኘቱን ይጠቁማል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች