Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊባለመፍትሔ ፈጠራዎች እንዲፈጠሩ

ባለመፍትሔ ፈጠራዎች እንዲፈጠሩ

ቀን:

አንድ ነገር እንደየተመልካቹ አተያይ፣ አስተሳሰብ፣ ዕድሜና የብስለት ደረጃ የተለያየ ውጤት አልያም ምላሽ ይኖረዋል፡፡ ልክ በብርጭቆ ውስጥ እንዳለው ግማሽ ውኃ ግማሽ ጎዶሎ፣ ግማሽ ሙሉ አገላለጽ ዓይነት ተቃርኖ ያላቸው ነገር ግን ከእውነታው ያልራቁ አገላለጾች ማለት ነው፡፡ እንደየተመልካቹ አተያይ አጋጣሚው መልካም አልያም መጥፎ ይሆናል፡፡

አምስተኛ ዓመት የኢንጂነሪንግ ተማሪ ሆኖ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከትምህርት ገበታ መቅረት ለበርካቶች መጥፎ አጋጣሚ ምናልባትም በሕይወት ዘመን ከማይሻሩ ክፉ ገጠመኞች አንዱ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ሥራ ፈጣሪ ጭንቅላት ላለው የ25 ዓመቱ ኖህ ፈቃደ ግን እንደ ማንኛውም ተራ ጉዳይ ቀላል ነበር፡፡ እንዲያውም በሁኔታው ከመማረርና ተስፋ በመቁረጥ ፈንታም ሁኔታውን ወደ ትልቅ የሕይወት አጋጣሚ ለመቀየር ቆርጦ ደፋ ቀና ማለት ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይህም ከሌሎች የዕድሜ እኩዮቹ የተለየ ፀጋ ስላለው ሳይሆን ነገሮችን የሚያይበት መነፅር በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሊጠቀምበት የሚችል ዕድል መኖሩን ስለሚያሳየው ነው፡፡

በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ የሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ የነበረው ኖህ አምስተኛ ዓመት ድረስ ተምሮ ድንገት ትምህርቱን ያቋረጠበት አጋጣሚ በአንድ ጎኑ መግለጽ በማይፈልገው የግል ጉዳይ ተገዶ፣ በሌላው ደግሞ ያለው የትምህርት ጥራት ላይ ጥያቄ ስለነበረው እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከኮሌጁ የወጣው የዛሬ ዓመት አካባቢ ሲሆን፣ የኮሌጅ አስኳላውን ማቋረጡ ሌላ የግሉን ሥራ እንዲሠራ ጊዜና ዕድሉን እንደ ፈጠረለት ይናገራል፡፡

በትምህርት ገበታ በቆየባቸው ዓመታት ያስተዋለውን ከባድ የትምህርት ጥራት ችግር በተወሰነ መልኩ መቅረፍ የሚችል ‹‹ኦንላይንና ኦፍላይን›› የሚሠራ ሥርዓተ ትምህርቱን መሠረት ያደረገ ዌብሳይት (ድረ ገጽ) እያዘጋጀ ይገኛል፡፡ ‹‹አብዛኛው የትምህርት ሥርዓት ከመረዳት ይልቅ ፈተና ማለፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፤›› የሚለው ኖህ ዌብሳይቱ ችግሩን መቅረፍ እንዲችል ተደርጎ መዘጋጀቱን ይናገራል፡፡ ይኼንን ማድረግ እንዲቻለውም አስቀድሞ የተለያዩ የዳሰሳ ጥናቶች አድርጓል፡፡

የሰዎች ከሚያነቡት ነገር 10 በመቶውን፣ ከሚሰሙት 20 በመቶውን፣ የሚያውቁትን ለሌላ ሰው ሲያስረዱ ደግሞ ከ90 እስከ 95 በመቶ የሚሆነውን የማስታወስ አቅም እንዳላቸው ባደረገው የዴስክቶፕ ጥናት ተረድቷል፡፡ ዌብሳይቱ ተማሪዎቹ ፈተና ለማለፍ ብቻ ሳይሆን ጠለቅ ያለ ዕውቀት ኖሯቸው እንዲያልፉ የሚያስችላቸው፣ ተምረው ለሌላው የሚያስተምሩበት፣ ባስረዱ (ባስተማሩ) ቁጥር ገንዘብ ማግኘት የሚችሉበት አሠራር የያዘ እንደሆነ ኖህ ይናገራል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም መጻሕፍትና ሌሎች የትምህርት ግብዓቶች በስፋት እንዲገኙ በማድረግ ያለውን የትምህርት ግብዓት ተደራሽነት ችግር እንደ አቅሙ የሚፈታ ይሆናል፡፡

 አንድን አዲስ ሐሳብ ከራስ አልፎ ለሌላ ሦስተኛ አካል ማስረዳት ሲያልፍም አሳምኖ በተግባር እንዲውል ማድረግ ብዙ ድካም ይጠይቃል፡፡ ኖህም በምናቡ የሣለውን ወደ መሬት አውርዶ በተግባር ለማዋል የብዙዎችን ደጅ መርገጥ፣ ባለሀብቶች ማፈላለግ ነበረበት፡፡ ይኼ በራሱ ትዕግስት የሚፈታተን ተስፋ የሚያስቆርጥ ቢሆንም፣ ወደ ኋላ ግን አላለም፡፡ የሚታይበት በራስ የመተማመን ስሜት፣ ቆራጥነት፣ ለሥራ ያለው ተነሳሽነት ደስ ይላል፡፡ አጣው ብሎ ከሚያማርራቸው ነገሮች ይልቅ ስለ ተፈጠሩለት መልካም አጋጣሚዎች ማውራት ያበዛል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ መሰናክል የሚበዛባቸው ታዳጊ አገሮች እንደ ኖህ ያሉ መንፈሰ ጠንካራ ወጣቶች ተስፋዎቻቸው ናቸው፡፡

 እንዲህ ያሉ ተስፋ ያላቸውን ወጣቶች የያዙትን ነገር አምኖበት ለሥራው የሚያዘጋጃቸው፣ ብቁ እንዲሆኑ ሙያዊና የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርግላቸው እንደ ኤክስ ሀብ ያሉ ድርጅቶችም በአንድ አገር ዕድገት ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ከተመሠረተ አራት ዓመታትን ያስቆጠረው ኤክስ ሀብ እንደ ኖህ ያሉ ዲዛይን የሚሠሩ፣ ኮደሮች፣ ሶፍትዌር የሚሠሩ፣ እንዲሁም በማንኛውም ዘርፍ ሥራ ፈጣሪ አዕምሮና የመሥራት ፍላጎቱ ያላቸውና በሐሳባቸው ላይ ኢንቨስት ማድረግ የሚችሉ ገንዘብ ያላቸው ኢንቨስተሮች የሚገናኙበት የማብቂያ (ኢንኪውቤሽን) ማዕከል ነው፡፡

ኤክስ ሀብ  ዘ ኢንተርፕሩነርስ ማይንድ ሴት (የሥራ ፈጣሪው አመለካከት) በሚል በየጊዜው በሚያዘጋጃቸው ፕሮግራሞች ሌሎች ወጣቶችን ለመድረስ ጥረት ያደርጋል፡፡ ስኬታማ ግለሰቦችን በመጋበዝ ልምዳቸውን እንዲያካፍሉ ያደርጋል፡፡ በዚህ ወጣቶቹ በሥራ ሒደት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዴት ማለፍ እንዳለባቸው ከመማር ባለፈ ወደ ሥራ እንዲገቡ፣ በርትተው እንዲሠሩ ቅስቀሳ ያደርጋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም የሚያመጧቸው አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች በአገሪቱ ውስጥ ካሉ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር የተዛመዱ እንዲሆኑ ለማድረግም በተለያዩ ዘርፎች የሚሠሩ ባለሙያዎችና ባለሥልጣናትን በመጋበዝ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ፈታኝ ነገሮች እንዲያቀርቡ ይደረጋል፡፡

በዚህ መሠረት ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ተዘጋጅቶ በነበረው ፕሮግራም የተሳካለት የንግድ ሰው መሆን የቻለው ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴና የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነሩ አቶ ፍፁም አረጋ ተጋባዥ ነበሩ፡፡ የሻለቃ ኃይሌ የአትሌትነት የሕይወት ልምድና ስኬት ለወጣቶች መነሳሳትን የፈጠረ ሲሆን፣ ኮሚሽነሩ ያቀረቧቸው በዘርፉ ያሉ ፈተናዎች ደግሞ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫቸውን የቀየሰ ነበር፡፡

ኮሚሽነሩ ንግግራቸውን የጀመሩት ባለፈው ዓመት ተቀስቅሶ በነበረው አመፅ 315 የሚሆኑ ትልልቅ እርሻዎች ጉዳት እንደደረሰባቸው፣ በዚህም በመቶዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ያለሥራ መቅረታቸውን፣ በአጠቃላይ 1.1 ቢሊዮን ብር የሚገመት ጉዳት መድረሱን፣ የደረሰውን ጉዳት ለመካስ ከባድ እንደነበር በማስታወስ ነበር፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ጉዳቱን የሚክስ በዚህ ዘርፍ የተሰማራ የኢንሹራንስ ድርጅት ቢኖር ነገሮች ቀላል ይሆኑ ነበር፡፡ ስለዚህም ወጣቶቹ በዚህ ረገድ መፍትሔ የሚሆን የፈጠራ ሐሳብ እንዲያመጡ ጠይቀዋል፡፡

 በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሠራተኞችን የደመወዝ ሁኔታ በተመለከተም አንዳንድ የተለያዩ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን፣ በተለያዩ ጥቅማጥቅሞችም የሚታገዙበት መንገድ እየተስተካከለ መሆኑን ከተናገሩ በኋላ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል ያሏቸውን ጉዳዮች ዘርዝረዋል፡፡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ከሚኖራቸው ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች መካከል ለዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ነው፡፡ ግዙፉ የሐዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ብቻውን ለ60,000 ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ሲነገር ቆይቷል፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን በፓርኩ ሥራ ማግኘት የቻሉ ዜጎች 12,000 ብቻ ናቸው፡፡

‹‹ከእነዚህ መካከል 3,000 የሚሆኑት በተለያዩ ምክንያቶች ከሥራ ለቀዋል፡፡ የማርፈድና የመቅረት ነገር ይታያል፡፡ ለምን አረፈድክ ሲባል ይኸው መጣሁ አይደል ብለው የሚከራከሩ አሉ፤›› የሚሉት ኮሚሽነሩ ሠራተኞቹ በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው መኖራቸው ሰዓታቸውን ጠብቀው በሥራ ገበታቸው እንዳይገኙ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ለዚህም መንግስት 1,000 ሰዎችን መያዝ የሚችል የጋራ መኖሪያ ቤት ከአዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ ጋር አብሮ እንዲሠራ አድርጓል፡፡

ይሁንና ተጨማሪ ቤቶች ስለሚያስፈልጉ ከፓርኩ በስተጀርባ በሚገኝ ቦታ ላይ የማይክሮ ፋይናንስ ብድር ተጠቅመው ቤት ገንብተው ለፓርኩ ሠራተኞች ብቻ በተመጣጣኝ ዋጋ የሚያከራዩ አካላት እንዲፈጠሩ ሐሳብ እንዳለው አቶ ፍፁም ተናግረዋል፡፡ ይም በሁሉም የኢንዱስትሪ ፓርኮች ተፈጻሚነት እንዲኖረው የታሰበ ሲሆን፣ በተጨማሪም በኢንደስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሠራተኞች ልጆች ብቻ የሚያገለግሉ የልጆች ማቆያዎች፣ ትምህርት ቤቶች እንደሚያስፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ወጣቶቹም ለተጠቀሱት ችግሮች መፍትሔ የሚሉትን የፈጠራ ሐሳብ ቢያመጡ ተቀባይነት እንደሚኖራቸው አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...