Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከእናቶች ጤናማነት ወር ባለፈ

ከእናቶች ጤናማነት ወር ባለፈ

ቀን:

ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሰላም ተመስገን ሦስተኛ ልጃቸውን ሊገላገሉ ቀናት ቀርተዋቸዋል፡፡ ሁለቱንም ልጆቻቸውን የወለዱት በጤና ተቋምና በሠለጠነ ባለሙያ አዋላጅ ታግዘው ነው፡፡ የእርግዝናቸውን ጤንነት በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ በመከታተል ላይ ናቸው፡፡

ወ/ሮ ሰላምን ያገኘናቸው በተጠቀሰው ሕክምና ኮሌጅ ቅጥር ግቢ የእናቶች ጤናማነት ወርን አስመልክቶ በተከናወነው ትምህርት አዘል ፕሮግራም ላይ ነበር፡፡ በፕሮግራሙ ወ/ሮ ሰላምን ጨምሮ ወደ 60 የሚጠጉ ነፍሰጡሮች ፕሮግራሙን በመከታተል ላይ ነበር፡፡

ከተቀመጡበት እንደ መንጠራራት እያሉ በፕሮግራሙ በመሳተፋቸው ‹‹ደም የተቀላቀለ ፈሳሽ፣ ቁርጠትና የራስ ምታት የመሳሰሉ ምልክቶች ሲታየኝ ቶሎ ብዬ ወደ ሕክምና ተቋም መሄድ እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ›› በማለት በእርግዝና ወቅት ከሚያጋጥሙ አንዳንድ የጤና ችግሮች ወደ ሕክምና መስጫ በመሄድ ራሳቸውን ከአደጋ መከላከል እንዳለባቸው ተናገሩ፡፡

የግልና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ፣ ዕረፍት ማድረግ እንዲሁም የተገኘውን ምግብ በሰዓቱ መመገብ ጠቃሚ እንደሆነ፣ ሕመም ሲሰማ ግን በፍጥነት ወደ ሕክምና መስጫ ተቋም አለመሄድ ወይም መዘግየት ለተወሳሰበ ችግር እንደሚዳርግ በፕሮግራሙ ላይ ከተሰጠው ትምህርት ለመረዳት እንደቻሉ ነው የተናገሩት፡፡

‹‹ካረገዝኩበት ማግስት ጀምሮ በአቅራቢያዬ በሚገኘው ጤና ጣቢያ ክትትል ሳደርግ ከቆየሁ በኋላ ሪፈር ተጽፎልኝ ወደ ሕክምና ኮሌጁ ልመጣ ቻልኩ፡፡ በዚህም የተነሳ በየ15 ቀናት ቼክ ያደርጉኛል፡፡ አገልግሎት ለማግኘት በሄድኩ ቁጥር ሐኪሞቹ የሚያሳዩኝ ፈገግታና የሚያደርጉልኝ አቀባበል ደስ የሚል ነው፤›› ብለዋል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ አዋላጅ ነርስ ጥላሁን ዓለሙ ‹‹በወሊድ ጊዜ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥንቃቄ ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ይህ ሁሉ ጥረት ከተደረገ በኋላ እናት ጤናማ ልጅ ስታገኝ ከፍተኛ የሆነ ደስታ ይሰማታል፡፡ እናት ስትደሰት ደግሞ ባለሙያው አብሮ ይደሰታል፤›› ብለዋል፡፡

በወሊድ ጊዜ ከሚደረጉ ጥንቃቄዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ከወሊድ በኋላ ደም እንዳይፈስ መከላከልና በአማካይ እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ የጨቅላውንና የእናቲቱን ጤንነት ደጋግሞ ማየት ይገኝበታል፡፡ ጤንነቷን የማረጋገጥ ሥራ የሚከናወነውም በየሁለት ሰዓት ልዩነት ነው፡፡ በየአንዳንዱ ሰዓት ቼክ የማድረጉ ሥራ ከተከናወነ በኋላ እናቲቱ ምንም ዓይነት የምትወስደው መድኃኒትና የሚያቆያት ነገር ከሌለ ወደ ቤቷ እንድትሄድ ትደረጋለች፡፡

ከሆስፒታሉ ከመውጣቷ በፊት ግን በአቅራቢያዋ ወደሚገኝ የጤና ተቋም ሄዳ ልጇን እንድታስከትብ ይነገራታል፡፡ በቤተሰብ ምጣኔ ላይ ያተኮረ ምክክርም (ካውንስሊንግ) ይካሄዳል፡፡

ለመውለድ የደረሰች የአንዲት ነፍሰጡር ማሕፀን በአማካይ በአንድ ሰዓት አንድ ሳንቲ ሜትር ያህል ይከፈታል፡፡ ለመውለድ ዝግጁ የምትሆነው ግን ክፍተቱ አሥር ሳንቲ ሜትር ሲደርስ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ አንዲት ነፍሰጡር ለመገላገል አሥር ሰዓት እንደሚፈጅባት ተናግረዋል፡፡ እናቶች በምጥና በቀዶ ሕክምና ይገላገላሉ፡፡ የቀዶ ሕክምናውን የሚፈልጉ ካሉ ፍላጎታቸው ይሟላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ፍላጎት ግን ብዙ ጊዜ አያጋጥምም፡፡ የአገሪቱም ሕግ ይህን ፍላጎት አይደግፍም ይላሉ አዋላጅ ጥላሁን፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማሕፀንና ጽንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊው ታደሰ ኡርጌ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ የእናቶች ጤናማነት ወር የዓለም ጤና ድርጅት በ1979 ዓ.ም. ያወጣው ኢንሼቲቭ ነው፡፡ ዓላማውም ከእርግዝና ጋር በተያያዘ የትኛዋም እናት ጉዳት ሊደርስባት ወይም ለሞት ልትዳረግ አይገባም ወይም የእርግዝናው ደኅንነት የተጠበቀ መሆን አለበት የሚል ነው፡፡

የእናቶች ጤናማነት ወር ኢንሼቲቭ ከወሊድ ጋር በተያያዘ የሚከሰት የእናቶችን ሞት ለማስቀረት ወይም ለመከላከል እንደሚቻል፣ ይህም የሚሆነው በሆስፒታል ውስጥ ወይም በሠለጠነ የጤና ባለሙያ የታገዘ የወሊድ አገልግሎት ሲገኝ ብቻ መሆኑን ለማሳየትና በዚህም ዙሪያ ሰፊ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ማከናወን እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል፡፡

ነፍሰጡሮች ላይ በዋናነት ችግር የሚደርሰው በወሊድ ወቅትና ከወሊድ በኋላ ባሉት ጥቂት ጊዜያት ውስጥ ነው፡፡ ይህንንም ችግር ለመከላከል እናቶች በቂ የሆነ እንክብካቤ እንዲያገኙና በሕክምና እንዲታገዙ ማድረግ፣ እንዲሁም ያልተፈለገ እርግዝና እንዳይከሰት መጠንቀቅ ግድ ይላል፡፡

ከወሊድ በኋላ ባሉት ጥቂት ሳምንታት ከእርግዝና ጋር የሚያያዙ ችግሮች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ተገቢ የሆነ እንክብካቤ ሊደረግ ይገባል፡፡ እናቶች ከእርግዝና በፊት እና በእርግዝና ወቅትም ክትትል እያደረጉ እርግዝናቸው፣ የእነሱም ጤንነት በጥሩ ላይ መገኘቱን ማረግገጥ ይኖርባቸዋል፡፡

አገልግሎቶቹን ለማግኘትም እናቶች የግድ ወደ ጤና ተቋም መሄድ ይኖርባቸዋል፡፡ የሚከሰቱ ችግሮች ደግሞ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለሞት ይዳርጋሉ፡፡ ስለዚህም ድንገት የሚከሰቱ እክሎች የከፋ አደጋ አድርሰው እንዳያልፉ በአቅራብያ የሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር በመሄድ አፋጣኝ ምላሽ ማግኘት ወሳኝ ነው፡፡ የሕክምና ተቋሙ በራቀ መጠን የከፋ አደጋ የመከሰት ዕድሉ በዚያው መጠን ስለሚጨምር አስቀድሞ ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡

በእርግዝና ወቅት የሚታዩ ችግሮች የሚመስሉ ምልክቶች ሁሉ (ዴንጀር ሳይን) አደጋ ያስከትላሉ ማለት ግን አይደለም፡፡ ለዚህም ነው አደገኛ የሆኑ ምልክቶችን እናቶች ለይተው እንዲያውቁ ማድረጉ አስፈላጊ የሚሆነው፡፡ ለምሳሌ ያህል ምጥ ሳይጀምራቸው የምጥ ውኃ መፍሰስ፣ ከፍተኛ የሆነ ትኩሳት፣ ራስ ምታት የመሳሰሉት ምልክቶች በምንም መልኩ ጤናማ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ እነዚህ ምልክቶች ሲታይባቸው ቶሎ ብለው ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ሕክምና እንዲያገኙ ይመክራል፡፡

‹‹ልጅ ከተወለደ በኋላ ልጅ ተሸክሞ የነበረው ማሕፀን ቶሎ መኮማተር አለበት፣ ለዚህም እንዲኮማተር የሚያደርግ መድኃኒትም ወዲያውኑ እንዲወስዱ ያደርጋል፡፡ ይህም ሆኖ ግን አንዳንድ ጊዜ ደም ሊፈስ ይችላል፡፡ ነገር ግን ትክክለኛው ሕክምና ከተደረገ ደሙ ይቆማል፡፡ እናቲቱም ከሞት ትተርፋለች፤›› በማለት የደም መፍሰስን መቆጣጠር ካልተቻለ አደገኛ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ገልጸዋል፡፡

አንዲት እናት ቤት ውስጥ ከወለደች ግን እንዲህ ዓይነቱን መድኃኒት እንደማታገኝ፣ ማሕፀኗም እንደማይኮማተር፣ በዚህም የተነሳ ብዙ ደም እንደሚፈሳት፣ ጤና ተቋም ሳትደርስ በሁለት ሰዓት ጊዜ ውስጥ ሕይወቷ ሊያልፍ እንደሚችል ነው ዶ/ር ታደሰ የተናገሩት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የኤርትራ አቪዬሽን ባለሥልጣን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎችን ማገዱን አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል በኤርትራ ትራንስፖርትና...

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...