ኢሕአዴግ አሥረኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ነሐሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ያካሂዳል፡፡ ኢሕአዴግ በጠቅላላ ጉባዔው በተለይ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፌርሜሽን ዕቅድና በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ ሙሉ በሙሉ ከአጋሮቹ ጋር በሚቆጣጠረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ አንድምታዎች ላይ ይመክራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በባህር ዳር ከተማ ከተካሄደው ዘጠነኛው ጠቅላላ ጉባዔ በኋላ አሥረኛውን ጉባዔ እንድታስተናግድ የተመረጠችው መቐለ ስትሆን፣ እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅቷን እያካሄደች መሆኑ ከሥፍራው የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡
የኢሕአዴግ የውጭና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው ኢሕአዴግ ጠቅላላ ጉባዔውን ነሐሴ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ለመጀመር ጊዜያዊ ቀጠሮ መያዙን አረጋግጠው፣ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ግን ጊዜው ገና ነው ብለዋል፡፡
ይህንን ጉባዔ ለማካሄድ አስቀድሞ የተያዘው ፕሮግራም እንደሚያሳየው፣ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አዲስ አበባና ድሬዳዋን ጨምሮ በዘጠኙ ክልሎች ሕዝብ እንዲወያይ ይደረጋል፡፡
በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመሩት ውይይት ከለጋሾች፣ ከምሁራንና ከንግዱ ኅብረተሰብ ጋር በቀጣይነት እንደሚካሄድ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በነሐሴ ወር ግምገማዎች ከተካሄዱ በኋላ የአመራሮች ሹም ሽር ተደርጎ የኃላፊነት ምደባ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ በነሐሴ ወር የመጀመርያ ሳምንት ደግሞ ኢሕአዴግን የመሠረቱት አራቱ ፓርቲዎች የየራሳቸውን ጉባዔ በማካሄድ የሁለት ዓመት ዕቅድ እንደሚያፀድቁ፣ ለኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴ እንዲሁም ፓርቲያቸውን በቀጣይነት የሚመሩ አመራሮችን እንደሚመርጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ይህ እንደተጠናቀቀ ኢሕአዴግ በሚያካሂደው አሥረኛው ጉባዔ በዕቅዱ ላይ ውይይት በማድረግ እንደሚያፀድቀው፣ ጉባዔው ያፀደቀው ዕቅድ በመስከረም ወር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔው እንደሚያገኝም ተገልጿል፡፡
ሌላኛው የጉባዔው አጀንዳ ይሆናል የተባለው በግንቦት 2007 ዓ.ም. የተካሄደው አገራዊ ምርጫ ነው፡፡ በዚህ ምርጫ ኢሕአዴግና አጋር ፓርቲዎች ለመጀመርያ ጊዜ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች ሙሉ መቀመጫ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
ጉባዔው ይኼ ሙሉ መቀመጫ እንዴት ሊገኝ እንደቻለ? በቀጣይ የፓርቲው ሥራዎች ላይ የሚያስተላልፈው መልዕክት ምን ሊሆን ይችላል? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሏል፡፡
ኢሕአዴግ በሕገ ደንቡ ጠቅላላ ጉባዔውን ከሁለት ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ተኩል ድረስ ባለው ጊዜ እንደሚያካሂድ ተቀምጧል፡፡ ኢሕአዴግ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሕልፈት ምክንያት ዘጠነኛውን ጉባዔ ያካሄደው በሁለት ዓመት ተኩል ሲሆን፣ ከዚያ በፊት የነበሩትን ጉባዔዎች በየሁለት ዓመቱ ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡