Saturday, December 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናፓርላማው የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበርን በሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነርነት ሾመ

ፓርላማው የምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበርን በሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነርነት ሾመ

ቀን:

–  በሥራ ላይ የሚገኙት የሕዝብ እንባ ጠባቂዋ በድጋሚ ተሹመዋል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ተቋማት ለሚባሉት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ሹመት ሰጠ፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሊቀመንበር የነበሩት ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. ገዥው ፓርቲና አጋሮቹ መቶ በመቶ ያሸነፉበትን የምርጫ አፈጻጸም ሪፖርት ለፓርላማው አቅርበው፣ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፓርላማው በሙሉ ድምፅ የሰብዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር አድርጎ ሾሟቸዋል፡፡

በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች የሚሾሙት በዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ አቅራቢነት እንደሆነ ይደነግጋል፡፡

በዚሁ መሠረት አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የሚመሩት ዕጩ አቅራቢ ኮሚቴ ከአምስት ወራት ቀደም ብሎ ተቋቁሞ የነበረ ሲሆን፣ የዕጩ ምልመላ ሒደቱም በአፈ ጉባዔው አማካይነት ቀርቧል፡፡ ብቃት ያላቸው ዕጩዎችን ለማግኘት ይረዳ ዘንድ ዜጎች በጥቆማው እንዲሳተፉ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ስቱዲዮ በመገኘት የአንድ ሰዓት የፓናል ውይይት በማድረግ ግልጽነትና ግንዛቤ ለመፍጠር ኮሚቴው ሞክሯል ያሉት አፈ ጉባዔው፣ በብሮድካስት ኮርፖሬሽንና በፋና ሬዲዮ እንዲሁም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዜጎች ጥቆማ እንዲሰጡ ማስታወቂያ መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት በአጠቃላይ ለዋና መሥሪያ ቤትና ለስምንት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ኮሚሽነርነት 158 ሰዎች የተጠቆሙ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ማስረጃ ያላቀረቡ 62 ሰዎች መሆናቸውን፣ ማስረጃ ያቀረቡ 96 እንደሆኑ፣ ከእነዚህ መካከል መሥፈርቱን አሟልተው ለመጀመርያ ማጣሪያ የተለዩት 74 ግለሰቦች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በመቀጠልም ተጠቋሚዎቹን ለመምረጥ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ መሆኑን፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር ተቆርቋሪ መሆኑን፣ በሕግ ወይም አግባብ ባለው ሌላ ሙያ የሠለጠኑ መሆኑን፣ በታታሪነቱ፣ በታማኝነቱና በሥነ ምግባር መልካም ስም ያተረፈ፣ ከደንብ መተላለፍ ውጪ ባለ በሌላ ወንጀል ተከሶ ያልተፈረደበት፣ ጤንነትና ዕድሜ መመልከታቸውን አፈ ጉባዔው ገልጸዋል፡፡

በዚህ መመዘኛ መሠረት አወዳድሮ 11 ዕጩዎችን መልምሎ እንዲሾሙ መወሰኑን የገለጹት አፈ ጉባዔው፣ በዋና ኮሚሽነርነት ዶ/ር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር አበራን፣ በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት አቶ እሸት ገብሬ ገብረ ማርያም፣ እንዲሁም ለሕፃናትና ለሴቶች ጉዳይ ኮሚሽነርነት ወ/ሮ ኡባህ መሐመድ ሁሴንን ለፓርላማው በዕጩነት አቅርቧል፡፡

ዶ/ር አዲሱ እ.ኤ.አ. በ2002 በዓለም አቀፍ ሕግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የያዙ ሲሆን፣ የ2002 ዓ.ም. እና የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫዎችን በምክትል የቦርድ ሊቀመንበርነት መርተዋል፡፡

ዶ/ር አዲሱ እነዚህን ምርጫዎች በምክትል ሊቀመንበርነት በመሩበት ወቅት፣ በተመዘገቡት የምርጫ ውጤቶች የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ገለልተኝነታቸውን ይተቻሉ፡፡  

በተለያዩ ጊዜያትም የቦርዱን አመራር አካላት ገለልተኝነት በግልጽ የተቹ ሲሆን፣ ይኼንን የሰሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከ2007 ዓ.ም. ጠቅላላ ምርጫ በፊት በሰጡት አስተያየት፣ ቦርዱን የሚዘልፉ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ማለታቸው ይታወሳል፡፡

በምክትል ዋና ኮሚሽነርነት የተሾሙት አቶ እሸት ገብሬ ደግሞ የፓርላማው አባል፣ ከአዲሱ ሹመታቸው በፊት ደግሞ የአፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ የሕግ አማካሪ የነበሩ ናቸው፡፡

ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ተመሳሳይ ሥርዓት የታለፈ መሆኑን፣ 171 ሰዎችም ለዋና መሥሪያ ቤትና ለክልል ቅርንጫፎች መታጨታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ውስጥ የኮሚቴውን መመዘኛ ያለፉት ወ/ሮ ፎዚያ አሚን ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅትም በዋና እንባ ጠባቂነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡ ምክትል ዋና እንባ ጠባቂዋ ወ/ሮ ሠራዊት ስለሺና የሕፃናትና የሴቶች ጉዳይ እንባ ጠባቂ የነበሩት ወ/ሮ ሳኒያ ሳኒ በነበሩበት ቦታ በድጋሚ ተሹመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...