Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ማሪታይም ባለሥልጣን በወደብና በሎጂስቲክስ ላይ ያተኮረበትን የአምስት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ይፋ አደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ኢትዮጵያውያንን በወደብ ሥራዎች ይሠማራሉ ተብሏል

የማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ የሚያከናውናቸውን ተግባራት የሚጠቁም ዕቅድ ይፋ አደረገ፡፡ የአገሪቱን የወደብና  የሎጂስቲክስ አጠቃቀም ይቀይራሉ ያላቸውን ዕቅዶች ለውይይት አቀረበ፡፡

ባለሥልጣኑ ያለፉትን አምስት ዓመታት ክንውኖችና የመጪዎቹን አምስት ዓመታት ጠቋሚ የዕቅድ አቅጣጫዎች በማስመልከት በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በጠራው ስብሰባ ይፋ እንዳደረገው፣ እስካሁን ድረስ በወደብ ሥራዎች ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎች የሉም፡፡ በመሆኑም በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን 300 ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በተለያዩ ወደቦች ተሠማርተው አገልግሎት እንደሚሰጡ ለማድረግ መታቀዱን፣ የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን አበራ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር በዕቃ አስተላላፊነትና በመርከብ ውክልና የሚሠሩ ባለሙያዎች ቁጥርም ከ140 ወደ አምስት ሺሕ እንደሚያድግ አቶ መኮንን አስታውቀዋል፡፡

የባለሥልጣኑ ዕቅዶች ከሆኑት መካከል፣ በገቢና ወጪ ዕቃዎች ላይ የትራንዚት ጊዜና ወጪን ለመቀነስ ካሰባቸው ሥራዎች መካከል በዓለም አቀፍ የሎጂስቲክስ አፈጻጸም መለኪያ አገሪቱ የምትገኝበትን ዝቅተኛ ደረጃ በግማሽ ለማሻሻል ያቀደበት ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም ያላት ደረጃ 104ኛ መሆኑን የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ ወደ 57ኛ ደረጃ ለማድረስ እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

የወጪ ንግድ ጭነትን በአገር ውስጥ በኮንቴይነር አሽጎ ወደ ውጭ ለመላክ የታሰበበት ግብ ከሚጠቀሱት አንዱ ሲሆን፣ አሁን ከሚገኝበት የሰባት በመቶ መጠን ወደ መቶ በመቶ ደረጃ ለማድረስ ታቅዷል፡፡ በኮንቴይነር ታሽገው ከሚላኩ ምርቶች መካከል በተለይ ቡናን በብትን በኮንቴይነር ለመላክ የታቀደው ይገኝበታል፡፡ ለአራት ዓመታት ያህል ቡናን በዚህ መንገድ ለመላክ የታሰበው ዕቅድ ሳይሳካ ቆይቷል፡፡ ቡና ላኪዎች ‹ቡናን በብትን በኮንቴይነር መላክ አመቺ አይደለም፣ ደንበኞቻችን አይቀበሉትም› በማለት ሲቃወሙት እንደነበር አይዘነጋም፡፡

የሎጂስቲክስ ወጪ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ (ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ) በ2007 ዓ.ም. 30 ከመቶ መድረሱን ባለሥልጣኑ አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በመጪው ዕቅድ ዘመን ወደ 22 ከመቶ ዝቅ ለማድረግ እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ በገቢና በወጪ ንግድ ላይ የሚታየው የሎጂስቲክስ ወጪም በ20 ከመቶ ይቀነሳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት የጠቅላላ ካርጎ ሽፋን አሁን ከሚገኝበት 51 በመቶ ወደ 90 በመቶ ለማድረስ መታቀዱን፣ የደረቅና የብትን ጭነቶች መርከብ ዲመሬጅና የመጋዘን ኪራይ ወጪን ዜሮ ማድረግም፣ የባለሥልጣኑ የአምስት ዓመት ዕቅዶች ከሆኑት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ ባሻገር ለገቢና ወጪ ዕቃዎች ትራንዚት የሚጠየቀውን የሰነድ ብዛት ከአሥር ወደ አራት የመቀነስ ዕቅድ የታዘ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ አቅም ዕቃዎችን ከወደብ ወደ አገር ውስጥ የሚጓጓዝበትን የ390 ሺሕ የመርከብ ጭነት መጠን ወደ 881 ሺሕ የጭነት መጠን ከፍ የማድረግ ዕቅድም ይፋ ሆኗል፡፡

በሌላ በኩል ባለፉት አምስት ዓመታት በማሪታይም ጉዳዮች ባለሥልጣን የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራትን ሲጠቅስ፣ ከጂቡቲ ወደብ በተጓዳኝ አማራጭ ወደቦችን ለመቀጠም የሚያስችሉት ሐሳቦችን ከማቅረብ ባሻገር የሙከራ ሥራዎች መሠራታቸውን አካቷል፡፡ በርበራና ፖርት ሱዳን በዋናነት ተጠቅሰዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ባለሥልጣኑ በተቋቋመ ማግሥት አከናውኗቸው ከነበሩ ሥራዎች መካከል ስድስት ወራት ከዚያ በላይ በወደብ ቆይተው ይወረሱ የነበሩ ዕቃዎችን፣ በስምምነት ወደ አገር ውስጥ ማምጣት የጀመረበት የሚታወስ ነው፡፡ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰባቸው ንብረቶች በወደብ ቆይታ ሳቢያ ይወረሱ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ከዚህም በሻገር በወደብ ትራንዚት ክፍያና በወደብ አጠቃቀም ላይ ከጂቡቲ ወደብ አስተዳደር ጋር ስምምነት በመፈጸም ለውጦች ማስመዝገቡን ባለሥልጣኑ ይዘረዝራል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች