የቀድሞው የቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩትና በአራተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ፓርላማውን የተቀላቀሉት አቶ ያረጋል አይሸሹም፣ የፓርላማው የሥልጣን ዘመን ሊጠናቀቅ ቀናት ሲቀሩት ወደ ፓርላማ ተመለሱ፡፡ አቶ ያረጋል በ2002 ዓ.ም. ምርጫ ተመርጠው የፓርላማ ወንበር ቢያገኙም፣ በ2004 ዓ.ም. ያለመከሰስ መብታቸው ተነስቶ በሙስና ወንጀል ተከሰዋል፡፡ በተከሰሱበት ሥልጣንን ያላግባብ የመጠቀም የሙስና ወንጀል ጥፋተኛ ተብለው ሰባት ዓመታት ጽኑ እስራትና 20 ሺሕ ብር የገንዘብ ቅጣት እንደተጣለባቸው ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጂ አቶ ያረጋል እስር ቤት ሆነው ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ባነሱት የሕግ ስህተት አቤቱታ ተቀባይነት አግኝተው፣ ቅጣቱ ወደ ሦስት ዓመት ጽኑ እስራት እንዲወርድላቸው በመወሰኑ ግንቦት 18 ቀን 2007 ዓ.ም. ከእስር መለቀቃቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ አቶ ያረጋል ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምክር ቤቱ የሥልጣን ዘመኑ ሊያበቃ የአምስት ቀናት ዕድሜ ሲቀሩት ባለፈው ሐሙስ ወንበራቸው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ፓርላማው የአቶ ያረጋል አይሸሹምን ያለመከሰስ መብት ያነሳው በዚሁ በተጠየቁበት ወንጀል መሆኑ ይታወሳል፡፡