Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሚድሮክ ጐልድ ምንም ዓይነት የመንግሥት ዕዳ የለብኝም አለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  ዋና ኦዲተር ማስተባበያውን አጣጥሎታል

የፌዴራል ዋና ኦዲተር በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት፣ የማዕድን ሚኒስቴር የሼክ መሐመድ አል አሙዲ የወርቅ ልማት ኩባንያ ከሆነው ሚድሮክ ጐልድ በሕግ የተወሰነውን ገቢ ባለመሰብሰቡ፣ አገሪቱ ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ አጥታለች ማለቱን የኩባንያው ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር አርጋ ይርዳው ‹‹ፍፁም ሀሰት›› ነው ሲሉ አስተባበሉ፡፡ ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሶ በበኩላቸው፣ የሚድሮክ ጐልድን ማስተባበያ በማጣጣል ማዕድን ሚኒስቴር ያልሰበሰበውን የመንግሥት ገንዘብ አሁንም ገቢ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል፡፡

በማዕድን አዋጁ 78/2002 መሠረት በከፍተኛ የማዕድን አምራቾች ላይ ስምንት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያ፣ እንዲሁም በከፍተኛ የማዕድን አምራች ኩባንያዎች ላይ መንግሥት አምስት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ እንደሚኖረው ቢደነገግም፣ የማዕድን ሚኒስቴር ከ2004 እስከ 2006 ዓ.ም. ባሉት የበጀት ዓመታት ከሚድሮክ ጐልድ የሰበሰበው የሮያሊቲ ክፍያ አምስት በመቶ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንዲሁም ከመንግሥት ነፃ የአክሲዮን ድርሻ ሁለት በመቶ ብቻ መሆኑን በማዕድን ሚኒስቴር ላይ በተካሄደው የክዋኔ ኦዲት ቁጥጥር መረጋገጡን ዋና ኦዲተሩ ለፓርላማ ሪፖርት አድርገዋል፡፡ ፓርላማው ካፀደቀው የሮያሊቲና የመንግሥት ድርሻ ምጣኔ ውጪ ሚኒስቴሩ ሚድሮክ ጐልድን በዝቅተኛ ምጣኔ በማስከፈሉ፣ በድምሩ 429 ሚሊዮን ብር ገቢ መንግሥት ማጣቱን ሪፖርት በማድረግ ማዕድን ሚኒስቴር በአገሪቱ ሕግ መሠረት ገቢዎችን እንዳልሰበሰበ ገልጿል፡፡

ሪፖርተር ይህንን የዋና ኦዲተሩን የኦዲት ሪፖርት መሠረት በማድረግ በሰኔ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትሙ ዘገባ ያቀረበ መሆኑ ይታወሳል፡፡ የሚድሮክ ጐልድ ዋና ሥራ አስኪያጅና የሚድሮክ ኢትዮጵያ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር አረጋ ይርዳው ለሪፖርተር በላኩት ደብዳቤ፣ ‹‹ኩባንያው ሕግን አክብሮ ኃላፊነቱን የሚወጣ ድርጅት ነው፡፡ አሥር ሳንቲም የመንግሥት ዕዳ የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

ሚድሮክ ጐልድ የማዕድን አዋጅ ቁጥር 52/1985 መሠረት በማድረግ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር የ20 ዓመታት የማዕድን ማውጣት ውል መግባቱን፣ በውሉ መሠረትም አምስት በመቶ የሮያሊቲ ክፍያና ሁለት በመቶ ነፃ የአክሲዮን ድርሻ በኩባንያው ላይ እንዲኖረው መደረጉን በደብዳቤያቸው አብራርተዋል፡፡

ውሉ መሠረት ያደረገበት የማዕድን አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 678/2002 ተሻሽሎ በሐምሌ ወር 2002 ዓ.ም. ሥራ ላይ መዋሉን የሚያስታውሰው የዶ/ር አረጋ ደብዳቤ፣ በዚህ አዋጅ ላይ የሮያሊቲ ክፍያ ወደ ስምንት በመቶ እንዲያድግ፣ የመንግሥት ነፃ ድርሻ ሁለት በመቶ እንዲሆንና ለወርቅ ማምረት ሥራ የቀረጥ ነፃ መብት እንዳይፈቀድም መከልከሉን ገልጸዋል፡፡ ይህንን አዋጅ መሠረት በማድረግም የማዕድን ሚኒስቴር ለሚድሮክ ጐልድ እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 24 ቀን 2011 ክፍያዎች በአዲሱ አዋጅ መሠረት እንዲከናወኑ ማሳሰቡን ጠቅሰዋል፡፡

ይሁን እንጂ ቀደም ብሎ ለ20 ዓመታት የተገባን የውል ስምምነት አዲሱ አዋጅ ሊቀይር አይገባም በማለት፣ ሚድሮክ ጐልድ ከማዕድን ሚኒስቴር ጋር ለሦስት ዓመታት የተከራከረ መሆኑንና በመጨረሻም ሚኒስቴሩ በሚድሮክ ጐልድ አቋም መስማማቱን የሚገልጽ ደብዳቤ ጥር 28 ቀን 2005 ዓ.ም. መላኩን ገልጸዋል፡፡ በደብዳቤው መሠረትም ሚድሮክ ጐልድ በገባው ውል መሠረት እንዲቀጥል መደረጉን አስረድተዋል፡፡

ዋናው ኦዲተር ሪፖርቱን ለፓርላማ ከማቅረቡ በፊት ሙያው በሚጠይቀው መሠረት ከማዕድን ሚኒስቴር ወይም ከሚድሮክ ጐልድ ማግኘት የሚችለውን ሰነድ ሳይመረምር የሰጠው መግለጫ፣ በኩባንያው ላይ ተገቢ ያልሆነ ገጽታ እንዲያጠላበት በማድረጉ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

ጉዳዩን በተመለከተ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ፣ ‹‹በሚድሮክ ጐልድ ላይ የኦዲት ቁጥጥር አናደርግም፡፡ ቁጥጥር ያደረግነው በማዕድን ሚኒስቴር ላይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ይህ ቢሆንም በኦዲት መርህ መሠረት ተገቢው ምርመራ በሚኒስቴሩ ላይ መደረጉንና ለ20 ዓመታት የተደረገውን ውል መሠረት በማድረግ ተደርጐ የነበረውን ክርክርና የተሰጠውንም እልባት መመርመራቸውን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ነገር ግን ፓርላማው ያወጣውን ሕግ ማዕድን ሚኒስቴር በደብዳቤ ሊቀይረው አይችልም፡፡ ፓርላማው ራሱ በአዋጁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ተቋማት ሕግን አክብረው መሥራታቸውን ተቆጣጥሮ ለፓርላማው መረጃ ማቅረብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር በአዋጅ ቁጥር 678/2002 አንቀጽ 81 ላይ፣ ‹‹ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተሰጠ ፈቃድ ወይም የተደረገ የማዕድን ስምምነት ከዚህ አዋጅ ጋር እስካልተቃረነ ድረስ ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ዘመን ተፈጻሚነቱ ይቀጥላል፤›› የሚለውን አንቀጽ ተላልፏል ብለዋል፡፡

በኦዲቱ ወቅት የሚድሮክን ጥያቄም ሆነ ሚኒስቴሩ የሰጠውን ምላሽ የኦዲት ቡድኑ ማየቱን የገለጹት ዋና ኦዲተሩ አቶ ገመቹ፣ ‹‹ተቀባይነት ያለው አሠራር አይደለም፤›› ብለዋል፡፡ በመሆኑም ማዕድን ሚኒስቴር ይህንንና ሌሎች በኦዲት የተለዩ የአሠራር ችግሮቹን ለማስተካከል የድርጊት መርሐ ግብር አውጥቶ ለዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት መላክ የሚኖርበት መሆኑንና መንግሥት ከሚድሮክ ጐልድ ያጣውን ገንዘብ ማስከፈል አለበት በማለት አስታውቀዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፓርላማው በ2006 ዓ.ም. በማዕድን አዋጁ ላይ ባደረገው ማሻሻያ፣ በኢትዮጵያ በከፍተኛ የማዕድን ልማት ብቸኛ የሆነውን ሚድሮክ ጐልድ የመከራከሪያ ነጥብ የተገነዘበ ማስተካከያ አድርጓል፡፡

የማሻሻያ አዋጁ 816/2006 በአንቀጽ 9 ‹‹ይህ አዋጅ በሥራ ላይ ከመዋሉ በፊት የተሰጠ ወይም የተደረገ ማንኛውም የማዕድን ማምረት ፈቃድ ወይም የማዕድን ማምረት ስምምነት ፀንቶ ለሚቆይበት ቀሪ ዘመን፣ ፈቃዱ በተሰጠበት ወይም ስምምነቱ በተደረገበት ወቅት ተፈጻሚ በነበረው ሕግ መሠረት ባለበት ይቀጥላል፡፡ ሆኖም በፈቃዱ ወይም የስምምነቱ ዘመን አብቅቶ ሲታደስ በዚህ አዋጁ ድንጋጌዎች መሠረት ይፈጸማል፤›› የሚል ማስተካከያ አድርጓል፡፡

  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች