Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

በብቃት ማነስ ምክንያት አገር መቸገር የለባትም!

በብቃት ማነስ ምክንያት የሚታየው የአፈጻጸም ጉድለት አገሪቱን ለበርካታ ችግሮች እየዳረጋት ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የአቅም ግንባታ መርሐ ግብሮች ተዘርግተው ጥረቶች እንደተደረጉ ቢታወቅም፣ በተለይ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚታየው የብቃት ማነስ ችግሮችን በማባባስ ላይ ይገኛል፡፡ በብቃት ማነስ ምክንያት እየታዩ ያሉ ችግሮች አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የብቃት ማነስ የሚፈጥራቸውን ችግሮች በተለያዩ ዓውዶች ማየት ይቻላል፡፡

  1. የተሿሚዎች ብቃት ያሳስባል

የአንድ ተቋም ጥንካሬ ከሚለካባቸው መሥፈርቶች መካከል የተሿሚዎች ብቃት ተጠቃሽ ነው፡፡ አንድ ተሿሚ በትምህርት ዝግጅቱ፣ በሥራ ልምዱ፣ በግላዊ ባህሪውና አብረውት ከሚሠሩት ጋር ባለው መስተጋብር ዝቅተኛ መሥፈርት ሆኖ ሊለካ ይችላል፡፡ በአገራችን በብዙ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በሙያ ብቃታቸው አንቱ የሚባሉ ያሉትን ያህል፣ ብቃት የሌላቸውና ለተሾሙበት ቦታ የማይመጥኑ ብዙ አሉ፡፡ በፖለቲካ ድርጅት አባልነት ወይም በተለያዩ የጥቅም ግንኙነቶች የማይገባቸውን ኃላፊነት ከአቅማቸው በላይ የተሸከሙ ሞልተዋል፡፡

ለገዥው ፓርቲ ታማኝ እስከሆነ ድረስ ማንም ሊሾም ይችላል ስለሚባል ብቻ ሥልጣን ላይ የሚፈናጠጡ ሰዎች በበዙ ቁጥር፣ ውጤቱ ምን እንደሆነ በሚገባ ታይቷል፡፡ ሙያን ከባለሙያ፣ ሥራን ከሚሠራው ጋር ማገናኘት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ በሚታወቅበት በዚህ ዘመን ሥራ መምራት የማይችሉ ሰዎችን መሾም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለተቀመጡበት ወንበር የማይመጥኑ ኃላፊዎች በኮታ ቦታውን ስለሚይዙ በበርካታ ቦታዎች የአፈጻጸም ጉድለቶች ይታያሉ፡፡ መሬት ላይ ካለው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በባለሙያ በመታገዝ አቅዶ ከግብ ማድረስ ባለመቻሉ፣ በርካታ ዕቅዶች የተቀመጠላቸውን ግብ ማሳካት ተስኗቸዋል፡፡

ብዙዎቹን መንግሥታዊ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚመሩ ግለሰቦች የሕዝቡን ጥያቄዎች መመለስ ባለመቻላቸው የምሬት መነሻ ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡ በየዓመቱ መጨረሻ ሪፖርት ሲደረግ፣ የታቀደውና ውጤቱ ለምን አልተጣጣመም ሲባል የአፈጻጸም ጉድለት በመኖሩ ነው ተብሎ ይመካኛል፡፡ የአፈጻጸም ጉድለት ለምን አጋጠመ ተብሎ በጥልቀት ቢገመገም ግን የተሿሚዎች ብቃት በምክንያትነት ቁልጭ ብሎ ይወጣ ነበር፡፡ የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠናቆ፣ ሁለተኛውን ለመጀመር ተፍተፍ በሚባልበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ የመጀመሪያው ዕቅድ ብዙ ሥራዎች የተከናወኑበት ቢሆንም፣ በርካታ መሰናክሎች እንደገጠሙት አሌ አይባልም፡፡ ከአቅም በላይ ከሆኑ ችግሮች ባሻገር አመራር እንዲሰጡ የተሰየሙ ብቃት የሌላቸው ሹማምንት ጉዳይ ቢፈተሽ መልሱን ማግኘት ይቻላል፡፡

የመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግዙፍ ፕሮጀክቶችና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ይዞ በመምጣቱ፣ በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ሳይቀር ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎ በዓይን የሚታዩ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ነገር ግን በሌሎች ወሳኝ በሚባሉ ሴክተሮች ውስጥ የታየው መጓተት የተሿሚዎች አቅምና ብቃት ማነስ ነው ቢባል ማን ያስተባብላል? ለመልካም አስተዳደር ዕጦት መፍትሔ መፈለግ ያልተቻለውና የሕዝቡን ቅሬታ አዳምጦ ለመፍታት ተራራ የሆነው በምን ምክንያት ነው? በተንዛዛው ቢሮክራሲ ምክንያት ሥራን ማቀላጠፍ ዳገት የሚሆነው ለምንድነው? በተሿሚዎች ብቃትና አቅም ማነስ ብቻ ነው፡፡ ሌላ ሰበብ አያስፈልግም፡፡

  1. የተቋማት ብቃት የወረደ መሆን

የተቋማት ጥንካሬ የሚለካው በአመራራቸው፣ በሰው ኃይላቸው፣ በሚመሠረቱበት የሕግ ማዕቀፍ፣ በተወዳዳሪነት ብቃታቸውና በመሳሰሉት ነው፡፡ ብዙዎቹ የመንግሥት ተቋማት የሚመሠረቱት በሕግ ማዕቀፍ ቢሆንም፣ የአመራሮቻቸውና የሰው ኃይል ሥምሪታቸው ላይ ጎልተው የሚታዩ ችግሮች አሉ፡፡ ብቃት የሌላቸው ተሿሚዎች ከሚፈጥሩባቸው ችግሮች በተጨማሪ፣ የሠለጠነ የሰው ኃይል በክፍያ ምክንያት ማቆየት ስለማይችሉ በደመነፍስ ነው ሥራቸውን የሚያከናውኑት፡፡ ለሙስናና ለዝርፊያም የተጋለጡ ናቸው፡፡ ሌላው ቀርቶ በየዓመቱ የሚወጣውን የፌዴራል ዋና ኦዲተር ሪፖርት በጥንቃቄ ለሚያነብ፣ ምን ያህል የተዝረከረኩ አሠራሮች እንደ ወረሩዋቸውም መረዳት ይቻላል፡፡

የተቋማቱ መዳከም በአገልግሎት አሰጣጥ ረገድ ከፍተኛ ችግር ስለሚፈጥር ሕዝቡን ለምሬት ይዳርጋል፡፡ ብዙዎቹ አቅም በሌላቸው ሹማምንት የሚመሩ ደካማ ተቋማት በቅጡ አያቅዱም፡፡ አፈጻጸማቸውም በጣም ደካማ ነው፡፡ በተንዛዛና በተንሸዋረረ አመለካከት የሚመራው ቢሮክራሲ የአገልግሎት አሰጣጡን እየገደለ፣ ግብር ከፋዩን ሕዝብ ያስመርራል፡፡ ለሰሚ ግራ የሚያጋቡ መመርያና ደንብ እያወጡ ትርምስ የሚፈጥሩ ደካማ ተቋማት ችግራቸውን ለመመርመር እንኳን አይፈልጉም፡፡ የጨረታና የግዥ ሕጎችን በመጣስ ሕገወጥ ድርጊት ይፈጸምባቸዋል፡፡ ሒሳባቸውን በወቅቱ አያወራርዱም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት የሚባለው የዘመናዊ አሠራር መርህን አያውቁትም፡፡ በደመነፍስ እየተመሩ በአገርና በሕዝብ ሀብት ላይ ይቀልዳሉ፡፡ በአስቸኳይ ሥር ነቀል ለውጥ ካልተካሄደባቸው አገሪቱን ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

  1. የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መዝረክረክ

የነገውን ትውልድ ይቀርፃሉ ተብለው የሚጠበቁት ብዙዎቹ የመንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጉዳይ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ በመንግሥት የተበጀላቸውን በጀት ማስተዳደር እያቃታቸው ከመሆናቸውም በላይ፣ በሙስና ይታማሉ፡፡ በተደጋጋሚ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሪፖርት ከሚወቀሱት መካከል እነዚህ የትምህርት ተቋማት ይገኙበታል፡፡ በቅጥር፣ በደረጃ ዕድገት፣ በዝውውርም ሆነ በስኮላርሺፕ ሳይቀር ከፍተኛ በደል የሚፈጽምባቸው እነዚህ ተቋማት የአገሪቱን ሲቪል ሰርቪስ አንገት የሚያስደፉ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ ከመሀላቸው ሥርዓት ይዘው ሥራቸውን በአግባቡ የሚያከናውኑ እንዳሉ ባይዘነጋም፣ የትምህርት ተቋማቱ ይዞታ ግን ከፍተኛ የሆነ ክትትል ያስፈልገዋል፡፡ በደካማ አመራር ምክንያት ችግር ውስጥ ናቸው ያሉት፡፡

ብዙዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በእከከኝ ልከክህ ያልተገባ ግንኙነት ሀቀኛና ጠንካራ ሠራተኞችን እየበደሉ፣ የማይገባውን በሹመትና በጥቅማ ጥቅም ማንበሽበሻቸው የታወቀ ነው፡፡ የተቋማቱን ስምና ዝና የሚያኮስስ ተግባር ሲፈጸም እያወቁም ሆነ በደንታ ቢስነት ዝም የሚሉ የሥራ ኃላፊዎች መብዛት ያስተዛዝባል፡፡ ለማስፋፊያና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የተመደቡ ወጪዎች ሲዝረከረኩና ሒሳብ ማወራረድ ሳይቻል ሲቀር እንዴት ዝም ይባላል? በተደጋጋሚ በሙስናና ባልተገባ ተግባር ስማቸው የሚነሳው የትምህርት ተቋማት ምን ዓይነት ትውልድ ያፈራሉ? ተቋማቱን በአግባቡ መምራት ያቃታቸው ደካማ ሹማምንትስ እስከ መቼ በአገር ላይ እየቀለዱ ይኖራሉ? ይኼ አስቸኳይ መፍትሔ የሚያስፈልገው የወቅቱ ጥያቄ ነው፡፡ የነገውን ትውልድ በአግባቡ መቅረፅ ካልተቻለ የምትጎዳው አገር ብቻ ናት፡፡ ደካማና ብቃት የጎደላቸው ዜጎች ለአገሪቷ ፋይዳ የላቸውምና፡፡ በደካማዎች የሚመሩ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለትምህርት ጥራት ትኩረት ስለማይሰጡ አገሪቷን ኪሳራ ውስጥ ይከታሉ፡፡

4 የቁጥጥርና የግምገማ ልልነት

በአሁኑ ጊዜ በብዙ ሥፍራዎች ስለቁጥጥርና ግምገማ ብዙ ቢወራም፣ በጥንካሬ ስለማይካሄዱ በርካታ ችግሮች ይድበሰበሳሉ፡፡ ከዕቅድ እስከ አፈጻጸም ያሉ ተግዳሮቶች አሳማኝ በሆኑ መሥፈርቶች ላይ በመመሥረት ስለማይፈተሹ በለብ ለብ ሪፖርት ይታለፋሉ፡፡ አንድ ዕቅድ ከመነሻው ጀምሮ እስከ ፍፃሜው ድረስ ምን ዓይነት ቁጥጥር ተደርጎበታል? ለሚያጋጥሙ ችግሮች ምን ዓይነት መፍትሔ ተቀምጧል? በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ምን ዓይነት ጉዳዮች ተከናውነዋል? ውስጣዊና ውጫዊ ክስተቶች ያሳደሩት ተፅዕኖ ምን ነበር? ወዘተ እየተባለ ቁጥጥር ያልተደረገበት ሥራ እንዴት ውጤት ይኖረዋል? ዕቅድን ከመነሻ እስከ መጨረሻ የሚገመግመው አካል ጠንክሮ እያፋጠጠ ካልጠየቀ እንዴት ተገመገመ ይባላል? እነዚህ ሁሉ ችግሮች በስፋት ይታያሉ፡፡ የቁጥጥርና የግምገማ ልል መሆን የተቋማትንም ሆነ የግለሰቦችን አቅም እያሽመደመዱ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ሐሰተኛ ሪፖርቶች ለዜና ፍጆታነት እየዋሉ መሳቂያና መሳለቂያ ያደርጋሉ፡፡ የብቃት ማነስን ያጋልጣሉ፡፡

በአጠቃላይ እንደ አገር ሲታይ የብቃት ማነስ ጉዳይ ሊያሳስብ ይገባል፡፡ ሰዎች አለን በሚሉት ዕውቀት ኃላፊነታቸውን ካልተወጡ፣ ተቋማት በገጠመኝ ከመመራት ይልቅ በመርህ ካልተንቀሳቀሱ፣ ሕገወጥ ተግባራት ካልተወገዱና ጠንካራ የቁጥጥር ሥርዓት ካልሰፈነ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚለዋወጠው ዓለም ብርቱ ፈተና የሚገጥመው መሆኑን መዘንጋት የዋህነት ነው፡፡ “እንደጀመርነው እንጨርሰዋለን” እያሉ መፈክር የሚያስተጋቡ፣ ነገር ግን በተግባር ጀምረው ዳር ማድረስ የማይችሉ ደካሞች ብቃት ባላቸው ዜጎች መተካት አለባቸው፡፡ ብቃት የሌለው ቤተሰብ መምራት እንደማይችል ሁሉ፣ የአገር ጉዳይን መምራት እንደማይችል መታመን አለበት፡፡ ተሿሚው የፈለገውን ያህል ታማኝነት ቢኖረው እንኳ ከአቅሙ ጋር የሚመጣጠን ቦታ ይሰጠው፡፡ ወይም አቅሙን ገንብቶ ብቃት እንዲላበስ ድጋፍ ይደረግለት፡፡ በብቃት ማነስ ምክንያት አገር መቸገር የለባትም!  

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...

ሕወሓት በትግራይ ጦርነት ወቅት በፌዴራል መንግሥት ተይዘው ከነበሩት አባላቱ መካከል ሁለቱን አሰናበተ

በሕወሓት አባላት ላይ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የነበሩት ወ/ሮ ኬሪያ...

የኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ ለመሸጥ የሚያስችል ስምምነት ለመፈጸም የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ለማከናወን የሚያስችለውን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሰብዓዊ ቀውሶችን ማስቆም ተቀዳሚ ተግባር ይሁን!

በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተወክለው ከመጡ ሰዎች ጋር ያደረጉት ውይይት፣ በአማራ ክልልም ሆነ በሌሎች ሥፍራዎች የሚካሄዱ ግጭቶች ምን...

የበራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ቅርሶችን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተረከበ

በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ የየካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን ተሸላሚ የነበሩ የአየር ኃይል ጀት አብራሪው የብርጋዴር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ...

የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ መብት ዘላቂ መፍትሔ ይበጅለት!

ሰሞኑን በአዲስ አበባ የተካሄደው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ በተጠናቀቀ ማግሥት፣ መንግሥት ልዩ ትኩረት የሚሹ በርካታ ጉዳዮች እየጠበቁት ነው፡፡ ከእነዚህ በርካታ ጉዳዮች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው...