Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

መልሶ ማልማትስ አስተሳሰብን ነው!

ሰላም! ሰላም! ሰላም! በያላችሁበት ይሁን፡፡ በዚህ ክፉና ደግ እንደ ዘይትና ውኃ በተቀላቀሉበት ዘመን ሰላምን አስቀድመን ለጋራ ደኅንታችን ካላሰብን፣ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት ሥጋት ይገባኛል፡፡ ይኼንን ሥጋቴን የምትጋራው ውዷ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ (በእርግጥም አትጠገብም) ዓይኖቿን ወደ ሰማዩ ልካ ወደ ፈጣሪዋ ታንጋጥጣለች፡፡ አንደኛው የድለላ ሥራ ባልደረባዬ፣ ‹‹ነገረኞች በሚያንጓጥጡበት በዚህ ጊዜ ወደ ላይ ማንጋጠጥ ሳይሻል አይቀርም…፤›› እያለ ሥጋቴን ማባባስ ሲጀምር የማይታክተውን እግሬን ተንቀሳቀስ አልኩት፡፡ ቆመን ማዳመጥ ከጀመርን እኮ ከተራው ሰው እስከ አገር የሚመሩት ጓዳ ጎድጓዳ ድረስ ምን የማይወራ አለ? በተለይ አሁን መሪ ፍለጋ ስንባዝን፡፡ አናሳዝንም?

መቼ ነው መሰላችሁ? ሰዎች በሰዎች ጉዳይ ምን ጥልቅ አድርጎዋቸው ነው የሚፈተፍቱት ተብሎ ወሬ ይጀመራል፡፡ ይኼ ወግ ጆሮዬ ውስጥ ጥልቅ ያለው፣ አንድ ዶዘር መግዛት የሚፈልግ የዘመኑ ወጣት ኢንቨስተር ቀጥሮኝ ቡና እየቀማመስኩ ካፌ በረንዳ ላይ ስጠብቀው ነው፡፡ አንድ ፀጉሩን እንደ ቦብ ማርሌ ያንጨባረረ ጎረምሳ ጣቱን እየወዘወዘ፣ ‹‹በእኔ የግል ፍላጐት ማን ያገባዋል? የፈለግኩትን ብበላ፣ ብጠጣና ባጨስ የራሴ ጉዳይ ነው…›› እያለ ተንጣጣ፡፡ የመብሉና የመጠጡ ጉዳይ በእርግጥም የራሱ ጉዳይ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ምን ይሆን ሊያጨስብን የሚፈልገው? ከአካባቢ ተቆርቋሪዎች እስከ አገር መሪዎች ድረስ ይኼንን በየቦታው የሚጨስ ነገር ምነው ዝም አሉ? አካባቢን ከመበከል አልፎ እኮ ትውልድ እያጠፋ ነው፡፡ ለዚህም ‹አትነሳም ወይ› እንባባል እንዴ?

ሰላም ለሁላችሁ ይሁን ሲባል ክፉ ነገር ከእናንተ ይራቅ መሆኑን የሚነግሩኝ ባሻዬ ናቸው፡፡ ‹‹አንበርብር ውስጥህ ሰላም ከሌለው ቀልብ አይኖርህም፡፡ ከራስህ ጋር እየተጣላህ ሌላውን ትነጅሳለህ፡፡ ብዙዎቻችን ሰላም ሲርቀን ደም ይሸተናል፡፡ ካገኘነው ጋር ሁሉ ካልተጋደልን እንላለን፡፡ ሰው በውስጡ ሰላም ይኖረው ዘንድ ከፈጣሪው ጋር መታረቅ አለበት፡፡ ያጠፋውን ሁሉ ተናዞ እንደ አዲስ መወለድ አለበት፡፡ በክፋት አዕምሮአቸው የናወዘ ምን እየሠሩ እንደሆኑ እያየህ ለሰላም መቆም ካልቻልክ የዘራኸውን ታጭዳለህ…›› እያሉ ሲመክሩኝ የክፋት አባዜ የሚወልደው ግብዝነት አረመኔነቱ የት ድረስ እንደሚጓዝ ሳስብ ውስጤ ታወከ፡፡ ወይ ነዶ!

ያዘኑትን ማፅናናት፣ የተቸገሩትን መርዳት፣ ግራ የተጋቡትን መምከር የመሳሰሉ የደግነት መገለጫዎች የሆኑ እሴቶች ባሉበት ዓለም ውስጥ እኔ ያልሆንኩትን ለምን አትሆንም ብለው ዕልቂት የሚያውጁ፣ ግዞት የሚሰዱና የሚያፈናቅሉትን ሳስብ ለእነሱ ጭምር እንዳዝን መንፈሴ ሲወተውተኝ ነው የከረመው፡፡ የባሻዬ ልጅ በምሁር አዕምሮው ሞርዶኛል መሰል ሰው መሆን ምን ማለት ነው እያልኩ እንደ ፈላስፋው ዘርዓ ያዕቆብ ማሰብ ይዳዳኛል፡፡ ሐሳቤን በፈለግኩት መንገድ ለመግለጽ ስሞክር አፍ አፌን እያሉ የሚያስፈራሩኝ አሉ፡፡ ጓደኞቼ ‘እንደተገኘ አወራለሁ ብለህ ቂሊንጦ እንዳታመላልሰን’ ሲሉኝ፣ ንግግሬ ያልተመቸው ዘመናይ ደግሞ፣ ‘ምን ለማለት ፈልገህ ነው?’ ብሎ ያጉረጠርጥብኛል፡፡ በፈሪዎችና በኃይለኞች መካከል ትንሽ ሥፍራ ማጣት ምን ያህል አስቸጋሪ እንደሆነ ሳስብ የሰላም ዋጋ ክብደት ጐልቶ ይሰማኛል፡፡ ኦ ሰላም ትናፍቂያለሽ!

የባሻዬ ልጅ በአንድ ወቅት ያዘኑትን ቤተሰቦች ለማፅናናት ሄዶ ነበር፡፡ እሱ ያኔ እንደነገረኝ አንድ አፅናኝ የሃይማኖት ሰው ለሐዘንተኞቹም ሆኑ ለአፅናኞች አደረጉት ያለው ንግግር ልቤን ነክቶት ነበር፡፡ ልበ ብርሃን የሆኑ ሰዎች በጠፉበት በዚህ ዘመን አንድ ሰው ሲገኝ ተመሥገን ቢባል አይበዛም፡፡ ‹‹አንበርብር ልቤ ነበር የተነካው፤›› አለኝ፡፡ ‹‹እኚህ ሰው ‘ሰው ብቻ ማለት ምንድን ማለት ነው ብዬ ሳስብ የሚበላ፣ የሚጠጣ፣ በሚለብሰው ልብስ፣ በሚነዳው መኪና የኑሮን ስኬት የሚለካ ማለት ነው፡፡ እስከ ሞት የሚኖር ማለት ነው፡፡ እንደ እንስሳ፡፡ ታላቁ ሊቅ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዲህ ይላል፡፡ ሰው እግዚአብሔር ሲለየው ፀባዩ እንደ አራዊት፣ አመጋገቡ እንደ እንስሳ ሆኖ መልኩ ብቻ የእግዚአብሔር ሆኖ ይቀራል፡፡ በጣም ቀለል ባለ አገላለጽ ሲም ካርዱ የወጣ ሞባይል ማለት ነው፡፡ ጥሪ የማይቀበል፡፡ ‹ለጉትቻ ማንጠልጠያ ብቻ የተሠራም ጆሮ አለ› ሲሉ ልቤ ከመጠን በላይ ተነካ፤›› ሲለኝ እኔ ራሴ ፈዝዤ ነበር ያደመጥኩት፡፡

የባሻዬ ልጅ እንደነገረኝ ሰውየው ከተማ ፈርሶ እየተገነባ ነው እየተባለ ሲወራ እንደሚሰሙ (ዓይነ ሥውር በመሆናቸው)፣ ነገር ግን ፈርሶ መሠራት ያለበት የሰው አስተሳሰብ ነው ማለታቸውን አከለልኝ፡፡ ‹‹የሰው አስተሳሰብ ፈርሶ ካልተሠራ የተሠራው ከተማ ይፈርሳል፡፡ ጃፓንና ቻይና አገራቸውን ያለሙት መጀመርያ አስተሳሰባቸውን አልምተው ነው፡፡ አስተሳሰቡ ያልለማ ሕዝብ ያለማውን ያወድማል… ብለው ሲያክሉበት እንዲህ ዓይነት መካሪ አያሳጣን ብዬ በሆዴ ምሥጋናዬን አዥጐደጐድኩት፤›› ብሎ ሲነግረኝ ሳይታወቀኝ ባርኔጣዬን አንስቼ እጅ ነሳሁ፡፡ ‹ቃለ ሕይወት ያሰማልን› ማለት አሁን አይደለም?

‹‹ሰባኪው በዝርዝር ለህሊና ጠቃሚ በሆኑ ምክሮች የሰዎችን ነፍስ ሲያረሰርሱ፣ ዓይኖቻቸው ከንዋይ ላይ አልነቀል ያሉ ደግሞ ምዕመኑን በቀደዱት ቦይ እንደፈለጉት ይነዱታል…፤›› እያለ የባሻዬ ልጅ ተብሰከሰከ፡፡ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት ሊቅ ተብዬዎች፣ ምሁራን ነን እያሉ የሚኮፈሱት፣ በየአደባባዩ እዩን እዩን የሚሉት፣ ወዘተ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ነገሮችን ከማበርከት ይልቅ በየተሰማሩባቸው መስኮች ገንዘብ ላይ መረባረባቸው፣ ለዝና መሯሯጣቸው፣ በሐሰት እየመሰከሩ ወገንን የሚያበጣብጡ ገንነው መታየታቸው ያበሳጨዋል፡፡ እንዲህ ሲሆን ደግሞ ያሳዝነኛል፡፡ ውስጡ ብግን ብሎ ደም ሥሮቹ ሲገታተሩ የክፉዎች ተግባር የፈጠረው ሰላም መንሳት ድቅን እያለብኝ አፅናናዋለሁ፡፡ እስቲ ፅናቱን ይስጠን!

ካፌው በረንዳ ላይ ሆኜ ዶዘር የሚገዛውን ደንበኛዬን ስጠባበቅ ስልኬ አቃጨለ፡፡ አንስቼ ‘ሄሎ’ ከማለቴ፣ ‹‹አንበርብር እያየሁህ ነው… መንገዱን ተሻግረህ ና…፤›› ሲለኝ ዓይኖቼ ከዓይኖቹ ጋር ተጋጠሙ፡፡ ዘመናዊው ‘ራቫ ፎር’ መኪና ውስጥ ስገባ ከሰማይ ቁልቁል የሚወረወረው ንዳድ የፈጠረብኝ ትኩሳት በረደ፡፡ ቅዝቃዜው ከምድር የተገኘ ሳይሆን፣ ከሰማየ ሰማያት የተለቀቀ በረከት መሰለኝ፡፡ በእግሬ አዲሳባን እያካለልኩ የምሰበስበውን ሙቀት አጠራቅሜ፣ መብራት ሲጠፋ እንድጠቀምበት የሚያስችለኝ መሣሪያ ቢፈለሰፍ ኖሮ የመጀመርያው ገዥ እኔ የምሆን ይመስለኛል፡፡ ሙቀቱ መተንፈስ እስኪያቅተን ድረስ ሲያንገበግበን ምን የማያሰማን ነገር አለ? ደንበኛዬ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች የያዘውን የስልክ ወሬ ካጠናቀቀ በኋላ ሞተሩን ቀስቅሶ ማርሹን ሲያስገባ አልተነጋገርንም ነበር፡፡ በፀጥታ ውስጥ መሆን ምንኛ መታደል ነው!

‹‹አንበርብር ምነው ብቻህን ታወራለህ?›› አለኝ፡፡ ይህች ዓይነቷ ወሬ አትመቸኝም፡፡ በሐሳብ ውስጥ ሆነን የፊታችን ገጽታ ሲለዋወጥ የሚያነቡን ተንኮለኞች፣ ‘ይኼኔ ይኼ መሠሪ ምን እየጎነጐነ ይሆን?’ እያሉ በሐሜት ይሸረክቱናል፡፡ እኛ ሰባኪ እንዳሉት አንዳንዴ ጆሯችን በካርድ የሚሠራ ቢሆን ኖሮ ሲሰለቅ የሚውለውን ሐሜት ሁሉ እንሰማ ነበር? የምንፈልገውን ብቻ እየሰማን አውርተን ‘ስዊች ኦፍ’ ነበር የምናደርገው ያሉት ታወሰኝ፡፡ አጅሬውም በሐሳብ መመሰጤን አይቶ ‘ብቻህን ታወራለህ’ ሲለኝ ‘እንዴት?’ ማለት አለብኝ፡፡ አለበለዚያ ምን ስል ሰምተህ ነው ብዬ ነገር ባነሳ የእንጀራ ገመዴ ተበጥሶ ሰላሜን አጥቼ መክረሜ አይደለም፡፡ ደስ ይበለው ብዬ ፈገግ አልኩ፡፡ ለስንቱ አግጥጠን እንዘልቀዋለን ግን!

የሚሰማኝን የውስጤን ሐሳብ ነፍጌው የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን ደረስን፡፡ ሻጭና ገዥ ከዚህ በፊት ይተዋወቁ ኖሮ ተቃቅፈው ተሳሳሙ፡፡ ጊዜያዊው የማስመሰል ሰላምታ ካበቃ በኋላ ድርድሩ ተጀመረ፡፡ የዶዘሩ ሻጭ ዋጋውን ሲጠራ ገዥ በአላምንም ዓይነት ‘እንዴ?’ አለ፡፡ እንደገና ተሳሳቁ፡፡ ወይ ማስመሰል፡፡ በሚግባቡበት ፈሊጥ በገደምዳሜ ተነታርከው ሲጨርሱ ተስማሙ፡፡ ድርድሩ አበቃ፡፡ እኔም የድርሻዬን ወሰድኩ፡፡ ገዥ ከሻጭ ጋር ተሰነባብቶ ወደ መጣሁበት ሲመልሰኝ፣ ‹‹ይኼንን ሌባ አውቀዋለሁ፡፡ ስንቱን በደረቅ ቼክ ያጭበረበረ አረመኔ መሰለህ? አሁን ደግሞ ፋብሪካ አቋቁማለሁ ብሎ የተሰጠውን መሬት መቆፈር ጀምሯል፡፡ ትንሽ መሠረት ካወጣ በኋላ የባንክ ብድር በሚሊዮኖች ያፍስና እብስ ይላል…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ‹‹በጨበጣ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ናቸው እኮ ኢንቨስተር እየተባሉ ወይ አይሠሩ ወይ አያሠሩ…፤›› እያለ ሲነጫነጭ፣ የእሱን ጉድ ደግሞ እንዴት እየተወራለት ይሆን እያልኩ አሰብኩ፡፡ ለስንቱ እናስብ!

የባሻዬን ልጅ የቀጠርኩበት ግሮሰሪ ስደርስ አንዱን አጋብቶ ሁለተኛንው ቢራ እየጀመረ ነበር፡፡ እኔም ያላበውን አዝዤ ውሎዬን አወጋሁት፡፡ ‹‹አገር በገጠማት ክው ብላ ቤተሰቦችን የሚያፅናኑ፣ አገርን የሚያረጋጉ፣ ተስፋን የሚዘሩ፣ ከዋሻው መጨረሻ ብርሃን መኖሩን የሚያመላክቱ፣ ከፀብ ይልቅ ሰላም፣ ከጥላቻ ይልቅ ፍቅር፣ ከመንገብገብ ይልቅ መተሳሰብ፣ ከዋይታ ይልቅ ዕልልታ እንዲኖር የሚተጉ ዜጐች ትሻለች…›› አለኝ፡፡ ዓይኖቻችን ሲያጉረጠርጡ ካላዩ፣ ጆሮዎቻችን ሲቀሰሩ ካላዳመጡ ሰው መሆናችን ጥቅሙ ምንድነው? ‘ሰው ብቻ አትሁኑ’ ሲባልም ሙሉ መሆን አለባችሁ ማለት መሆኑ እየገባኝ አስተሳሰቤን በዚህ መንገድ ቃኘሁት፡፡ ይጠቅመኛልና፡፡ ለማንኛውም ደካማ አስተሳሰባችን ፈርሶ እንደገና ቢሠራስ? አገር ብቻውን እየለማ የሰው ልማት ካልታከለበት እኮ እንደተባለው ትርፉ ውድመት ነው፡፡ አፍርሶ መገንባትስ አስተሳሰብን ነው፡፡ መልሶ ማልማትስ አስተሳሰብን ነው እንባባል፡፡ መልካም ሰንበት!    

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት