Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከቻይና በኮንቴይነር ታሽጎ ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ዘይት የድንጋይ ንጣፍ ሆኖ ተገኘ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጎበታል

– የጋላፊንና የሚሌን ፍተሻ ጣቢያዎች ማለፉ ግርምት ፈጥሯል

– ተጠያቂዎቹ ንግድ መርከብና የቻይና ድርጅት መሆናቸው ተጠቁሟል

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሚገኘው አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ከቻይናው ዌይፋንግ ሹኦፌንግ ኢምፖርትና ኤክስፖርት ኩባንያ ገዝቶ ወደ ኢትዮጵያ ያስመጣው በአራት ኮንቴይነሮች የአኩሪ አተር ዘይት፣ ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም. መቐለ ደረቅ ወደብ ደርሶ ሲከፈት ኮንክሪት የድንጋይ ንጣፍ ሆኖ ተገኘ፡፡

የሪፖርተር ምንጮች ከደረቅ ወደብ አስተዳደር የመቐለ ቅርንጫፍ እንደገለጹት፣ አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ከቻይናው ኩባንያ የገዛውን አራት ኮንቴይነሮች አኩሪ አተር ዘይት አጓጉዞ ወደ አገር ውስጥ እንዲያስገባለት፣ ከኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጋር ተስማምቷል፡፡ ድርጅቱም በገባው ውል መሠረት ሲአይኪው የተባለው የቻይና ድርጅት አረጋግጦና ሠርተፊኬት አሳይቶት ዕቃው መጫኑን ሰነዶች እንደሚያስረዱም ምንጮች ተናግረዋል፡፡

አሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ዘይቱን ለሚልከው የቻይናው ኩባንያ እስከ ወደብ ማድረሻና የዘይቱን ዋጋ 67,860 ዶላር ከፍሏል፡፡ ለመርከብ ማጓጓዣ ደግሞ ከቻይና እስከ ጂቡቲ 7,684 ዶላር ከፍሏል፡፡ ከጂቡቲ እስከ መቐለ ደግሞ የማጓጓዣ 6,433.75 ዶላር ከፍሏል፡፡ በድምሩ 81,977.75 ዶላር ወይም 1,861,550.87 ብር መክፈሉን ምንጮች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

አራት ኮንቴይነር አኩሪ አተር ዘይት በኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅት የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ተጭኖ መቐለ ደርሶ ሲከፈት፣ በኮንቴይነሮቹ ውስጥ የተጫነው ንፁህነቱ የተረጋገጠና የተመሰከረለት የአኩሪ አተር የምግብ ዘይት ሳይሆን፣ መንገድ ላይ የሚነጠፍ (በተለይ ለውኃ ማስተላለፊያ ቱቦዎች ከላይ ሽፋን የሚውል ጠፍጣፋና ረዘም ያለ መዝጊያ ድንጋይ) ኮንክሪት ንጣፍ ድንጋይ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

በሥፍራው የነበሩ የደረቅ ወደቡ ሠራተኞችም ሆኑ ስማቸው ያልተገለጸው የድርጅቱ ባለቤት ከመደንገጣቸው የተነሳ፣ ለደቂቃዎች በፀጥታ ውስጥ ሆነው እርስ በርስ ሲተያዩ መቆየታቸውን ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ኤክስፖርት የሚያደርገው የቻይናው ኩባንያ ኮንቴይነሮቹን ሲወስድ ባዶ መሆናቸው ተረጋግጦና ማሸጊያ (ሲል) አብሮ እንደሚሰጠው የጠቆሙት ምንጮች፣ ኩባንያው ምርቶቹን በገባው ውል መሠረት ጥራታቸውን የጠበቁና ጉድለት እንዳይኖርም ሲአይኪው የሚባለው የጥራት ተቆጣጣሪ የቻይናው ድርጅት መከታተል እንደነበረበት፣ የመጫን ኃላፊነቱን የወሰደው የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክ አገልግሎት ድርጅትም ቁጥጥር ማድረግ ይገባው እንደነበር ተናግረዋል፡፡ የመጫኛው ትዕዛዙ (ቢል ኦፍ ሎዲንግ) ዘይት ቢልም፣ ሲከፈት ግን ድንጋይ መሆኑን አክለዋል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ መንግሥት የተወከለው የቻይናው ሲአይኪው ድርጅት ተከታትሎ ማሳሸግና ማስጫን ሲገባው፣ የማይታወቅ ዕቃ እንዲላክ ማድረጉ ግራ እንዳጋባቸው ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ጊዜው አስፈሪ ከመሆኑ አንፃር፣ ማለትም አሸባሪ መላ ዓለምን እያሰጋ ባለበት ‹‹የተጫነው ዕቃ ፈንጂ ቢሆንስ?›› በማለት የሚጠይቁት ምንጮች፣ የድንጋዩ ጉዳይ ሕጉን ተከትሎ መፍትሔ የሚያገኝ ቢሆንም፣ መንግሥት ግን ችግሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላው ምንጮችን ያስገረመው ኮንቴይነሮቹ የባህር ላይ ጉዞአቸውን ጨርሰው መቐለ ደረቅ ወደብ ከመድረሳቸው በፊት፣ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ቅርንጫፍ መፈተሻ ጣቢያዎች የጋላፊንና የሚሌን የፍተሻ ጣቢያዎች የመፈተሻ እስክሪን ውስጥ ሲያልፉ፣ የታየውን የዕቃ ዓይነት ሪፖርት አለማድረጋቸው ወይም እዚያው አለማስቆማቸው ነው፡፡ በስክሪን ውስጥ ስለሚታይ ጥብቅ ቁጥጥር አድርገው ቢሆን ኖሮ እዚያው ሊይዙት ይችሉ እንደነበር ምንጮች ገልጸዋል፡፡

ዕቃውን ያስጫኑትን የአሚድአብ ጄኔራል ቢዝነስ ድርጅት ባለቤትን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ ችግሩን የፈጠረው ወይም ቁጥጥሩን በአግባቡ ያልተከታተለው ማን እንደሆነ፣ በአስጫኙ ላይ ለደረሰው ኪሳራ ተጠያቂው ማን እንደሆነ፣ በተለይ ጥብቅ ቁጥጥር መደረግ ያለበት የባህር ላይ ትራንስፖርትን በሚመለከት ምን መደረግ እንዳለበት ማብራሪያ እንዲሰጥ የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅትን ለማነጋገር የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ በጋላፊና በሚሌ የፍተሻ ጣቢያዎች እንዴት ኮንቴይነሮቹ ሊያልፉ እንደቻለም ማብራሪያ ለመጠየቅ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣንን የኮሙዩኒኬሽን ኃላፊዎችን ለማግኘት የተደረገው ጥረትም እንዲሁ አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች