ግሪክ በዕዳ ማዕበል መመታት የጀመረችው እ.ኤ.አ. ከ2009 ማብቂያ ጀምሮ ነው፡፡ የግሪክ የብድር ቀውስ ወይም ‹‹ግሪክ ዲፕረሽን››፣ በዩሮ ከሚገበያዩ 19 የአውሮፓ ኅብረት አባል አገሮች ውስጥ ቀድመው በብድር ዕዳ ከተመቱ አራት አገሮች ቀድሞ የተከሰተም ነው፡፡ ግሪክን ለብድር ቀውስ ተጋላጭ ካደረጓት መካከልም በዓለም አቀፍ ደረጃ እ.ኤ.አ. ከ2007 እስከ 2010 ተከስቶ የነበረው የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የግሪክ ኢኮኖሚ አወቃቀር ደካማነት፣ እንዲሁም የአገሪቱ ብድር ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርት ጋር አለመመጣጠን ይጠቀሳሉ፡፡ በመሆኑም ግሪክ ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት የተበደረችውን ገንዘብ ቃል በገባችው መሠረት ትመልሳለች ወይ? የሚለው አነጋጋሪ መሆን የጀመረው እ.ኤ.አ. ከ2009 ወዲህ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 ግሪክ ከፍተኛ ዕዳ በማስመዝገብ በታሪክ ተጠቃሽ አገር ነች፡፡ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የተበደረችውን 1.6 ቢሊዮን ዩሮ እ.ኤ.አ. እስከ ጁን 30 ቀን 2015 መክፈል ባለመቻል፣ ካደጉ አገሮች መካከል የመጀመሪያዋ ሆናለች፡፡ እ.ኤ.አ. በ2012 አገሪቷ የነበረባት ዕዳም 323 ቢሊዮን ዩሮ ነበር፡፡
ግሪክ አሁን ለገጠማት የፋይናንስ ቀውስ መነሻው እ.ኤ.አ. በ1999 ተግባራዊ የተደረገው፣ በዩሮ ዞን አባል አገሮች የንግድ ዋጋን የሚቀንሰውና አጠቃላይ የንግድ መጠንን የሚጨምረው የጋራ መገበያያ ገንዘብ ‹‹ዩሮ›› ጥቅም ላይ ሲውል ነው፡፡ ይህ ደግሞ በግሪክ የጉልበት ዋጋን በማናር የምርት ዋጋ እንዲጨምር ሲያደርግ፣ ይህም ጀርመንና በዩሮ መገበያየትን ከተቋቋሙት ሌሎች አገሮች በንግድ ተወዳዳሪ እንዳትሆን አድርጓታል፡፡ የአገሪቷ ኢኮኖሚ ከሚያስገባው ገቢ በላይም ወጪ እንዲበልጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ በመሆኑም ግሪክ ብድር ውስጥ ለመግባት ግድ ሆኖባታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ግሪክ ዓመታዊ ገቢዋ 193 ቢሊዮን ዩሮ ቢሆንም ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የተበደረችው ደግሞ ከ342 ቢሊዮን ዩሮ በላይ ነው፡፡ የበጀት ቅነሳ (ኦስተሪቲ ፕላን) በመቅረፅ፣ ማለትም ሕዝቡ ከመንግሥት ያገኝ የነበረውን ጥቅማ ጥቅምና አገልግሎት በመቀነስ ያለፉትን አምስት ዓመታት ዕዳ ለመቀነስ ስትፍጨረጨርም ከርማለች፡፡ ሆኖም ዕዳዋን በተቀመጠላት ጊዜ መክፈልም ሆነ የሕዝቧን ፍላጐት ማሟላት አልቻለችም፡፡
ግሪክ ባለፉት ስድስት ዓመታት ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርቷ 25 በመቶ ቀንሷል፡፡ ሥራ አጥነት እ.ኤ.አ. በ2010 ከነበረው አሥር በመቶ፣ በ2015 መጋቢት ወደ 25 በመቶ አሻቅቧል፡፡ በተለይ ወጣቶች ሥራ አጥ ሆነዋል፡፡ ከ25 ዓመት በታች ከሚገኙትና ለሥራ ከደረሱ ወጣቶች ከሁለቱ አንዱ ሥራ አጥ ሆኗል፡፡ አገሪቷ በገጠማት የገንዘብ ቀውስ ምክንያት እ.ኤ.አ. እስከ 2010 ድረስ ከአገሪቱ ሕዝብ ሦስት በመቶ ያህሉ አገሩን ጥሎ ተሰዷል፡፡ በአገሪቱ ሥራ እየሠሩ ያሉት ደግሞ ከደመወዛቸው አብዛኛው ይቆረጣል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2009 ወዲህ ግሪክ የገጠማት ውድቀት ባደጉ አገሮች በታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው፡፡ በአገሪቱ ያለው የገንዘብ ቀውስ ንግዶች እንዲዘጉ፣ በታሪካዊዋ አቴንስ የሚገኙትም ሱቆች ባዶዋቸውን እንዲውሉ አድርጓል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው በተያዘው ዓመት ብቻ 60 የሚሆኑ ሱቆች ተዘግተዋል፡፡
ለብዙ ዓመታት ውዝግብ ሲፈጥር የቆየው የግሪክ የጡረታ አከፋፈል ሥርዓት ተቀይሯል፡፡ የጡረታ አበል በአማካይ በ60 በመቶ ያህል ተቀንሷል፡፡
የግሪክ መንግሥት በፋይናንስ ቀውስ እየተመታ ባለበት በአሁኑ ወቅት አውሮፓና አይኤምኤፍ ለግሪክ አዲስ የገንዘብ ድጋፍ ሥርዓት አማራጭ አቅርበው ነበር፡፡ በግሪክ የቁጠባ ባህል ግድ እንዲሆን፣ እነሱ ደግሞ ገንዘብ ሊለቁ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡ ይህ ግን በግሪክ መንግሥትም ሆነ ሕዝብ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አሌክሲስ ሲፕራስ በጉዳዩ ላይ ባለፈው እሑድ ሕዝበ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ሕዝባቸው ‹‹ኖ ቮት›› ወይም የአበዳሪዎችን ሐሳብ እንዳይመርጥ ሲማፀኑ ነበር የቆዩት፡፡ ባለፈው እሑድ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔም፣ ከ61 በመቶ በላይ መራጮች የጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ሐሳብ ደግፈዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራሲ፣ ሕዝቡ የአበዳሪዎችን ሐሳብ መቃወሙ አገራቸው ከአበዳሪዎች ጋር ለምታደርገው ድርድር አቅም ይፈጥራል፡፡ በሌላ በኩል ሕዝቡ ብዙ ተጎጂ በማይሆንበት የብድርና የአከፋፈል ሥርዓት እንዲሁም ዕዳ ለማሰረዝ መንገድ ያመቻቻል ብለዋል፡፡
የዩሮ ዞን አባል አገሮች ግሪክ አበዳሪዎች ያቀረቡትን ሐሳብ እንድትቀበል ሲወተውቱ ቢከርሙም አልተሳካላቸውም፡፡ ሪፈረንደሙን ተከትሎ ባለፈው ሰኞ የጀርመን መራሐተ መንግሥት አንገላ መርከል፣ እንዲሁም ከአውሮፓ ብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር መክረዋል፡፡
ግሪክ በቅርቡ ከአውሮፓ ገንዘብ አታገኝም፡፡ አገሪቷ ለጡረተኞችና ለመንግሥት ሠራተኞች የምትገፍለው በኤሌክትሮኒክ ፎርም ይሆናል፡፡ የግሪክ ባንኮች ለሳምንት ያህል ተዘግተው ቆይተዋል፡፡ ባንኮቹ በአውሮፓ ብሔራዊ ባንክ የድንገተኛ ጊዜ የገንዘብ ድጋፍ ላይ ተመርኩዘው ያሉ በመሆናቸውም ባንኩ ተጨማሪ ገንዘብ ካልለቀቀ ተዘግተው ይቆያሉ፡፡
ግሪክ በገጠማት የገንዘብ ቀውስ ሳቢያ መጠቀሚያቸውን ዩሮ ካደረጉ 19 የአውሮፓ አገሮች መካከል ለመነጠል የምትገደድበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ከዩሮ ዞን አባልነት ብቻ ሳይሆን 28 የአውሮፓ አገሮችን ካቀፈውና በንግድና በሌሎች ጉዳዮች አንድ ፖሊሲን ከሚከተለው የአውሮፓ ኅብረት ጋር የመቆየቷም ሁኔታ እያጠራጠረ ነው፡፡
ፈረንሳይ፣ ግሪክ ከዩሮ ዞን አባልነቷ እንዳትወጣ የተቻላትን ሁሉ እንደምታደርግ አሳውቃለች፡፡ ቢቢሲ የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንዌል ቫልስ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ግሪክ ከዩሮ ዞን መውጣቷ አደጋ አለው፡፡ በመሆኑም በብድር አሰጣጥ ስምምነቶች ላይ የዩሮ ዞን አባል አገሮች ድንገተኛ ስብሰባ ከመቀመጣቸው በፊት የማግባባት ሥራ ይሠራሉ፡፡ ጀርመን ደግሞ ለግሪክ አላስፈላጊ የዕዳ ስረዛ እንዳይደረግ እየወተወተች ትገኛለች፡፡
ግሪክ በዕዳ ተዘፍቃ በአጣብቂኝ ውስጥ የምትገኝ ቢሆንም፣ አበዳሪ አገሮችና ተቋማት ያቀረቡትን በሕዝቡ ላይ የሚጫን የቁጠባ ሥርዓት አልተቀበለችም፡፡ በሌላ በኩል የአገሪቱ የገንዘብ ሥርዓት እንደ በረዶ እየቀለጠ ይገኛል፡፡ በአገሪቱ ያሉ ባንኮች በጥሬ ገንዘብ የቀራቸው 500 ሚሊዮን ዩሮ ብቻ ነው፡፡ ይህም ማለት 11 ሚሊዮን ለሚጠጋው የግሪክ ሕዝብ በነፍስ ወከፍ ቢሰጥ 32 ፓውንድ ወይም 45 ዩሮ ይደርሳል ማለት ነው፡፡
የግሪክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራሲ ግሪክ ያለባት 323 ቢሊዮን ዩሮ ዕዳ በ30 በመቶ እንዲቀንስ የ20 ዓመታት የእፎይታ ጊዜ ሊሰጥ እንደሚገባ እየተናገሩ ነው፡፡ በገዛ ፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን በለቀቁት ያኒስ ቫሩፋኪስ ምትክ የተሾሙት የግሪክ የገንዘብ ሚኒስትር አክሊድ ታስካሎቶስ፣ በብራሰልስ ለተሰየመው የአውሮፓ የፋይናንስ ሚኒስትሮች ጉባዔ አዲስ የሚያስማማ ፕሮፖዛል ያቀርባሉ ተብሎ የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በግሪክ በኩል አዲስ ፕሮፖዛል እንደማይቀርብ እየተነገረ ነው፡፡ ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲፕራስ ፕሮፖዛሉን እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡
በቅንጦት መኖር የለመደው የግሪክ ሕዝብ በገንዘብ ቀውስ ከተመታ፣ አገሪቷም በዕዳ ከተጥለቀለቀች ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ አገሪቷ በጥሬ ገንዘብ ያላትን ሀብት እየጨረሰች ነው፡፡ ባንኮችም ተዘግተዋል፡፡ አበዳሪዎች ለግሪክ ገንዘብ ለመስጠት ያቀረቡትን ሐሳብ በሕዝበ ውሳኔ ውድቅ አድርጋለች፡፡ ቀጣይ ዕጣ ፈንታዋ ምን ይሆን?