የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት
ኢትዮጵያ በተጋመሰው 2015 ጎርጎርዮሳዊው የዘመን አቆጣጠር (በተለምዶ አውሮፓ አቆጣጠር) የዓለም ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻ ሆኖ መመረጧን የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት መሰንበታቸውን አስታውቋል፡፡
ምክር ቤቱ በሩማኒያ ቡካሬስት ከተማ ሰኔ 18 እና 19፣ 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ዓመታዊ ጉባኤው የዓመቱን ምርጥ የቱሪዝም መዳረሻና ምርጥ የብዝኃ ባህል መዳረሻ ክብር ለመስጠት ካወዳደራቸው 31 አገሮች መካከል ኢትዮጵያን መምረጡን የምክር ቤቱ ድረ ገጽ ይፋ አድርጓል፡፡
በምክር ቤቱ ድረ ገጽ እንደተገለጸው፣ ኢትዮጵያን ምርጥ የቱሪስት መዳረሻነት ለመመረጥ ካበቋት መስፈርቶች መካከል በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ሁሉ ዓይነት ቅርሶቿ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነርሱም የጥንታዊት ኢትዮጵያ እምብርት የሆነችው አክሱም ከተማ ሐውልቶች፣ የ13ኛ ምእት ዓመት 11ዱ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የ16ኛውን የ17ኛው ምእት ዓመት የኢትዮጵያ ነገሥታት መቀመጫ የነበረው የፋሲል ግቢ፣ 82 መስጊዶች፣ 102 አድባራት ያሉበት የሐረር ጁገል፣ የኮንሶ መልከአ ምድር፣ የቅድመ ሰው የሉሲ ቅሪተ አካል መገኛ ታችኛው አዋሽ፣ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ ናቸው፡፡
በተጨማሪም ዩኔስኮ በጊዜያዊ መዝገብ የያዛቸው ባህላዊና ታሪካዊ የኢትዮጵያ ውርሶች የድሬ ሼኽ ሁሴን ሃይማኖታዊ ባህላዊና ታሪካዊ ስፍራ፣ በላይኛው አዋሽ ሸለቆ የሚገኘው መልካ ቆንጥሬ አርኪዮሎጂያዊ ቦታ፣ 15.1 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሶፍ ዑመር ዋሻም ተጠቃሽ ሆነዋል፡፡
ኢትዮጵያ የ2015 ምርጥ የቱሪስት መዳረሻ ተብላ እንድትመረጥና የ2015 ምርጥ የብዝኃ ባህል መዳረሻ ታላቅ ክብርን መቀበል ይገባታል ሲሉ በቀዳሚነት ለዕጩነት ያቀረቧት የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ዶ/ር አንቶን ካራጂያ ናቸው፡፡
ፕሬዚዳንቱ ለሪፖርታቸው የሰጡት ርእስም ‹‹ኢትዮጵያ በፈጣሪ የተመረጠች ምድር፤ ፍጽምት የባህል ቅርሶች መገኛ›› (Ethiopia the Cultural Destination the Land Chosen by God) የሚል ነበር፡፡
ፕሮፌሰር አንቶን ካራጂያ አስረግጠው እንደተናገሩትም፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከአሁን በኋላ ፍጹም ሰላማዊና ለመጎብኘት ልቃ የምትገኝ ከመሆኗም ባሻገር፣ ለዓለም ቱሪዝም በሯን በመክፈቷ የዓለም የቱሪዝም ባለሙያዎች ለወደፊቱ ቱሪዝም ያላትን አቅም የመሰከሩላት ምድር ናት፡፡››
የኢትዮጵያ መንግሥት ቱሪዝምን አንዱ የድህነት መቀነሻ ስትራቴጅ አድርጎ መያዙ፣ የቱሪስት መዳረሻ አካባቢዎች ያሉ ማኅበረሰቦች ተጠቃሚ ማድረጉም ለስኬቱ አንዱ አመላካች ሆኗል፡፡ ከሥነ ምህዳር ጋር የተጣጣሙ ለብዝኃ ሕይወትና ለአካባቢ ጥበቃ ዋስትና የሆኑ ጥብቅ ደኖች ያካተቱ ፓርኮች ባለቤትና በዩኔስኮም ማስመዝገቧ ኢትዮጵያን ለማስመረጥ እንዳበቁ ተጠቅሷል፡፡
የአውሮፓ የቱሪዝምና ንግድ ምክር ቤት የዘርፉን ሽልማት አምና ለዚምባቡዌ ሐቻምና ደግሞ ለላኦስ መስጠቱ ይታወሳል፡፡