Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሰኔ 30 የደረሰባት ካዛንቺስ

ትኩስ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ በመልሶ ማልማት ፈርሰው እየተገነቡ ካሉት ሰፈሮች ግንባር ቀደሟ ካዛንቺስ ናት፡፡ ከአሠርታት በፊት ከፊል ካዛንቺስ ከሱፐር ማርኬት እስከ ዮርዳኖስ ሆቴል አካባቢ አዳዲስ ግንባታዎች ታይተውባታል፡፡ ዘንድሮም ከፊሏ ካዛንቺስ ከዑራኤል እስከ ስድስተኛ ፖሊስ ጣቢያ መገንጠያ ድረስ በስተግራ ያሉት ከወራት በፊት የፈረሱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ በጆሴፍ ብሮዝ ቲቶ መንገድ በ‹‹ባቢሎን›› አካባቢ የሚገኙ ቡና ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎችና ፋርማሲ ወዘተ. ቀነ ገደባቸው ሰኔ 30፣ 2007 ዓ.ም. ደረሰባቸውና ከመፍረሳቸው በፊት እሸጋው ከማለዳ ጀምሮ ተከናውኗል፡፡ ፎቶዎቹ ይኸንኑ ይዘክራሉ፡፡

(ፎቶ በሔኖክ ያሬድ)

********

ላልታወቀ አህያ ነጂ
ባሮጌው ጎዳና፤ በጮርቃው ማለዳ
ጋልቦ እንዳልደከመ፤ እንደ ጥቁር ፈርዳ
አቤ እየሠገረ
ከኋላው የሚሳብ፤ አህያ እየነዳ
ስሙ ማን ነበረ?
የመንደር ወፍጮ ቤት፤ ቅሪቱን ሲተፋ
ዱቄት የሚለብሰው
በዝነኞች ፊት ላይ፤ ካሜራ ሲያካፋ
ጠብታ ሚደርሰው
ማን ይሆን ይሄ ሰው?
እኛ የምናዘው፤ እሱ የሚሰማን
ሰው እያደረገን፤ ከሰው የማንቆጥረው
አህያ እየነዳ፤ ኣስፋልቱን ሲሻማን
የምንገፈትረው
በጥሩምባ እሩምታ፤ ምናስደነብረው
በኑሮው ምንቀልድ፤ በሞቱ ምንተርት
በፈረሰ ጎጆው፤ ፓርቲ ምንመሠርት፤
ፊቱ ቢልቦርድ ላይ፤ ወጥቶ ባይሰጣ
ጀግና የማይባል
ግና ለጀግኖቹ፤ ጉልበት የሚያዋጣ፡፡
ካበበ ሰሀን ላይ፤ በሶው እንዳይጠፋ
በተራ ክንዶቹ፤ ተራራ ሚገፋ
ለናቀችው ዓለም፤ ላቡን የገበረ
ስሙ ማን ነበረ?

(በዕውቀቱ ሥዩም)

*****

‹‹ክረምት ላይ ቆሜ መስከረምን ሳስበው››

ለአዲስ አበባ ሰው መቼም ዝናብ በጸሎት የተገኘ ድንቅ የአምላክ ስጦታ አይመስልም። መስከረምን ልዩ ወር ያደረጋት ይህ ዛሬ የምናማርረው ዝናብ ነው። አደይ አበቦችን ዛሬ ላይ ቆመን ካሰብናቸው የዚህ የአባት ዝናብና የእናት መሬት የወሩ (መስከረም) የበኩር ልጆች ናቸው።

መስከረም ላይ ቆመን፣ በአደይ አበባ ታጅበን እነ ሐምሌን ካሰብናቸው ያኮረፉ ወራት ይመስላሉ። ‹‹ይህን ሁሉ ደስታ ሰጥተናቸው። ምድሪቱን በአበባ አጅበን ለመስከረም ወር አስረክበናቸው ዘፈናቸው ምነው ለኛ አልሆነ›› የሚሉ ይመስሉኛል።

መስከረም የወር መጀመርያ ከመሆኑ በፊት ዝናብ የነበረ አይመስለኝም። ዝናብ በጊዜ ዑደት እነ ሐምሌ ሠፈር ላይ ሲከትም መስከረምም ከፀሐይ ጋር ጋብቻ ሲፈጽም ያኔ አዲስ ዘመን የተባለ ይመስለኛል። የኖህ መርከብ ዕረፍቱ፣ የወር መጀመርያ መስከረም ላይ እንዲሉ።

ጳጉሜን እንኳን ከመስከረም የተጠጋችው የነ ሐምሌን ክብር ለመውረስ ነው። አሁን እንደው ከስድስት ቀን አንሳ፡፡ ወር ተብላ ስሟ ተጠርቶ ይባስ ብላ የመስከረም ጎረቤት ሆነች።

ነሐሴ ታጋሽ፣ ዝምተኛ ወር። በቡሔ ተማምኖ ድግስ ይበቃኛል ብሎ እኩሌታውን በጾም በጸሎት ሱባኤ ይዞ ድምፁን አጥፍቶ ኗሪ።

የመስከረም ድግስ ብዛቱ። ‹‹እንቁጣጣሽ›› ብለን ሳንጨርስ ‹‹መስቀል ተተኮሰ›› ይገርማል። ወርሀ ጽጌ መስከረም 26 ደግም ዛሬ ላይ ቆሜ ይናፍቀኛል። ‹‹አክሊለ ጽጌ ማርያም፡ ቀጸላ መንግሥቱ ለጊዮርጊስ። ክበበ ጌራ ወርቅ… አክሊለ ጽጌ›› ማለት ያምረኝና የነ ሐምሌ ስጦታ መሆኑን ሳስብ ካለምክንያት ወራትን ያልሠራ አምላክ ጠቢብነትን አደነቅሁ።

‹‹በምድር ዘመን ሁሉ መዝራትና ማጨድ ብርድና ሙቀት በጋና ክረምት ቀንና ሌሊት አያቋርጡም፤›› እንዲል ዘፍጥረት፡፡

ያሬድ ሹመቴ በገጹ እንደጻፈው

*******

ትዝታ  ሰኔ 30 እና. . . ልጅነት

‹‹ቆይ ሰኔ 30 እንገናኝ›› የምትለዋ የተማሪዎች ማስፈራሪያ በእኔ ዘመን (ከሃያ እና 30 ዓመት በፊት) ብቻ የሚነገር ቃል ይመስለኝ ነበር። እንዲያውም ትንሽ ሪሰርች ቢጤ ሳደርግ ዛሬም የመንግሥት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ‹‹ሰኔ 30 እንገናኝ›› እንደሚባባሉ አረጋገጥሁ፡፡

ዛሬ ሰኔ 30 ስለሆነ እስቲ ከትዝታው እንቋደስ፤
መቼም ሁሉም እንደየ ዕድሜውና ዘመኑ የራሱ የልጅነት ትዝታ አለው።

 እስቲ የእኔን ላካፍላችሁ። ልክ የመጀመርያ የፍቅር ደብዳቤ የደረሰኝ የአምስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ ነበር። ያኔ ትምህርት ቤታችን እስከ ስምንተኛ ክፍል ብቻ ስለነበር፣ የፍቅር ደብዳቤው የደረሰኝ ስምንተኛ ክፍል ከሚማር ቀለሜዋና በትምህርት ቤታችን ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዋች ከሆነ ልጅ መሆኑ የኔን ለየት ያደርገዋል መሰለኝ። . . . ምክንያቱም ያኔ አምስተኛ ክፍሎች ስምንተኛ ክፍልን እንደ ኮሌጅ እንቆጥር ስለነበር፣ ወዲህም ልጁ ጎበዝና ዝነኛ በመሆኑ የቅርብ ጓደኞቼ ሳይቀሩ ‹‹ታድለሽ›› ነበር ያሉኝ።

ይህ ታዋቂና ቀለሜዋ ልጅ ስሙ እስክንድር ይባላል። (እንዲያውም አንዳንድ መምህራኑ ‹‹ታላቁ እስክንድር›› እያሉ ነበር የሚጠሩትና የተላከልኝን ደብዳቤ ከጓደኞቼ ከሐረግ፣ ሲሲ (ሲሳይ) ፎዚያና ጽጌ ጋር ሆነን አነበብን። ልጁ ደብዳቤውን የጻፈልኝ በግጥም ሲሆን ዛሬ ብዙውን ብረሳም ሁለቱን ስንኞች ግን እንኳን እኔ ጓደኞቼ ዛሬም ያስታውሱታል።

ግጥሟ እንዲህ ትነበባለች፡-

‹‹ኢትዮጵያ አገሬ አንቺ ለምለሚቱ

ታድዬ ገብርዬ የፀጉርሽ ውበቱ››

የሚል ነበር።

በወቅቱ አሪፍ ግጥም መስሎኝ ነበር አይ ልጅነት። ኋላ ላይ ግን ቤት እንዲመታለት ነው ለካ ኢትዮጵያ አገሬን የጨመራት። ከግጥሙ በተጨማሪ ከደብዳቤው መጨረሻ ላይ ‹‹ፍቅሬን ለመግለጽ ጣቴን በእስፒል ወግቼ በደሜ ፊርማዬን አኖራለሁ›› ብሎ በደሙ ነጠብጣብ ፈርሟል።

እኔና ጓደኞቼ የታላቁ እስክንድርን ደብዳቤ በግጥምና በስድ ንባብ በደንብ አድርገን አዘጋጀን። ፖስታው ከመታሸጉ በፊት ጓደኞቼ አንድ ሐሳብ አነሱ። አንቺም እንደርሱ ጣትሽን በስፒል ወግተሽ አድሚና ፈርሚበት የሚል። እኔ ደግሞ በተፈጥሮዬ መርፌ ነገር አልወድም። ዛሬም ክኒን እቅማታለሁ እንጂ ብታመም መርፌ በጣም እፈራለሁ። በእምቢታዬ መጽናቴን ሲያረጋግጡ ከጓደኞቼ አንዷ የራስዋን ጣት በስፒል ወግታ ለመፈረም ፈቃደኛ ሆነች። ደብዳቤው ላይ አበባ የመሰለ ነጠብጣብ ሠራንና እኔ ፊርማዬን አኖርኩ።

ትዝ ይለኛል ድሮ ወደ ትምህርት ቤት ስንሄድ ተሰባስበን፣ ተጠራርተን ነው። በማግሥቱ እኔ ከጓደኞቼ ጋር ፊት ፊት፣ ወንድሜም ከራሱ ጓደኞች ጋር ከኋላ እየተጫወትን እንሄዳለን። የጻፍኩት ደብዳቤ ደብተሬ ውስጥ ነው። ይሁን እንጂ ታሪካዊው ደብዳቤ ለካ ከደብተሬ ውስጥ ወድቆ ከኋላዬ ከሚሄዱት ወንድሜና ጓደኞቹ እጅ ወድቋል። ዓይናችን እያየ ደብዳቤውን ከፍተው አነበቡት፣ ልንቀማቸው ብንወራጭም አልቻልንም . . . በኋላ ወንድሜና ጓደኞቹ ከሠፈር እስከ ትምህርት ቤት ድረስ እስክንድር . . . እስክንድር. . . እስክንድር በሚል ዜማ አጀቡኝ ሌሎች ውሪዎችም ተቀላቅለው ጩኸቱ ደምቆ ትምህርት ቤት ደረስን። በኋላ በዕረፍት ሰዓት ተጨማሪ ሊያበሽቁኝ ተቀጣጥረው ሄዱ።

በዕረፍት ሰዓት ግን ታላቁ እስክንድር ነገሩን ሰምቶ ወንድሜን ‹‹ሰኔ ሠላሳ ያበቃልሃል›› ብሎ አስፈራርቶ ደብዳቤውን እንደተቀበለው ሰማሁ። ይሁን እንጂ ወንድሜ በዚያች ደብዳቤ የተነሳ ለቤተሰብ እነግራለሁ እያለ እያስፈራራኝ ለረዥም ጊዜ የከረሜላና የብስኩት ጉቦ ሲቀበለኝ የነበረው አይረሳኝም። አይ ልጅነት ደጉ ደስ ሲል!

(በታደለች ገብሩ)

********

ከደካማ ተማሪዎች ታላላቅ ብዕረኞች

ቻርለስ ዲከንስ፣ ማርክ ትዌን፣ ማክሲም ጎርኪ፣ አልቤርቶ ሞራሺያና ሲንኦኬሲ መደበኛ ትምህርታቸውን በፍፁም ሊያጠናቅቁ ካልቻሉ ደራስያን መካከል ይገኛሉ፡፡

መደበኛ ትምህርት መጨረስ ካቃታቸው ሌሎች ደራስያን መሃል በተለይ ጃክ ለንደን፣ ዊል ሮጀርስና ዊሊያም ሳሮያን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ለመፈጸም ያልቻሉ ናቸው፡፡ የኮሌጅ ትምህርት ይከታተላሉ ተብለው ሲጠበቁ ሳይማሩ ከቀሩት መካከል እንግሊዛዊቷ ደራሲት ቨርጂኒያ ዎልፍና ጆርጅ ቤርናርድ ሾ ይገኙበታል፡፡

አያሌ ደራስያንና የብዕር ሰዎች ቀደም ሲል በትምህርት ቤት ይሰጣቸው የነበረውን የሥነ ጽሑፍ ትምህርት ማለፍ አቅቷቸው እንደወደቁ ብዙ የሚነገር አለ፡፡
ይህ ዕድል ካጋጠማቸው ውስጥ ታዋቂው የፈረንሣይ ደራሲ ኤሚሊ ዞላ ይገኝበታል፡፡ ዞላ በሊሴ ቅዱስ ሉዊስ ትምህርቱን ሲከታተል ይሰጠው በነበረው የፈረንሣይኛ ሥነ ጽሑፍ ትምህርት ዜሮ አግኝቷል ይባላል፡፡ ይሁን እንጅ በዕድሜ ዘመኑ 20 ተከታታይ (ሴሪያል) የልቦለድ መጽሐፎችን በመጻፍ ከፈረንሣይ ሥነ ጽሑፍ ባለውለታዎች አንዱ ተጠቃሽ ለመሆን በቅቷል፡፡

  • ንጉሤ አየለ ተካና ደጀኔ ጥላሁን ‹‹ጣዝማ አስደናቂው የደራስያን ሕይወት›› (1979)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች