ቅዳሜ ረፋድ ላይ ነው፡፡ ዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤትን አልፈው በስተቀኝ ሲሻገሩ በርካታ ድንኳኖች ይገኛሉ፡፡ በአካባቢው ወዲያ ወዲህ የሚሉ ግለሰቦችም ጥቂት አይደሉም፡፡ ከድንኳኖቹ በአንዱ በእንስሳት አምሳያ የተዘጋጁ ሙሉ ልብሶች (ማስክ) ያደረጉ ወጣቶች ይታያሉ፡፡ በርካታ ታዳጊዎች ማስክ ያደረጉትን ወጣቶች ከበው ተቀምጠዋል፡፡ እንቅስቃሴያቸውን በግርምት ተሞልተው የሚከታተሉ ሕፃናትም ነበሩ፡፡ እንደአጋጣሚ በአራት ኪሎ ጎዳና ሲያልፉ የሕፃናትን መበራከት አስተውለው ወደ ድንኳኑ ጐራ ያሉ ወላጆችና ልጆቻቸውም ከድንኳኑ በቅርብ ርቀት ሆነው ክንውኑን ይመለከታሉ፡፡
ከታዳጊዎቹ መካከል ተረት፣ መነባንብና ቀልድ ያቀረቡ ነበሩ፡፡ ሌሎች ደግሞ መዝሙሮች አስደምጠዋል፤ እንስሳትና ታዋቂ ሰዎችን የማስመሰል ትርዒት ያቀረቡ ታዳጊዎችም ይጠቀሳሉ፡፡ በቦታው ለተገኙ ታዳጊዎች ከሕፃናት መጻሕፍት ልብ ወለድ ታሪኮች ተነበውላቸዋል፡፡ የእንዳለ ጌንቦ የትርጉም ሥራ ‹‹ዶ/ር አንኮና ሌሎችም ተረቶች››፣ የፀጋዬ ሽንቦዬ ‹‹ግድየለሹ ቀበሮና ሌሎችም ተረቶች›› እና ‹‹ድመቴን ምን ላብላት?›› የተሰኘው የዓለም እሸቱ መጻሕፍት ጥቂቱ ናቸው፡፡ ታዳጊዎቹ ከእያንዳንዱ ተረት ምን እንደተገነዘቡ ተጠይቀዋል፡፡ ያገኙትን ፍሬ ነገር ለሌሎች ታዳጊዎች አካፍለዋል፡፡ ታዳጊዎቹ ልዩ ልዩ የሕፃናት መጻሕፍትም ተሸልመዋል፡፡
ለታዳጊዎቹ የተሰናዳው ዝግጅት እዛው አራት ኪሎ በነጋታው እሑድ ጠዋትም ተካሂዷል፡፡ ዝግጅቱ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ከተካሄደው የ‹‹ሰኔ 30 የንባብ ቀን›› መሰናዶዎች አንዱ ነው፡፡ ‹‹ሰኔ 30 የንባብ ቀን›› ሕዝብን ለንባብ ለማነሳሳት እንዲሁም የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚካሄድ ንቅናቄ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችና መሥሪያ ቤቶች የየዓመቱን ክንውን በሚያጠናቅቁበት ወርኃ ሰኔ ማገባደጃ ላይ ይካሄዳል፡፡
ዓምና በእግር ጉዞና ልዩ ልዩ ለንባብ የሚቀሰቅሱ ክንውኖች አዲስ አበባ ውስጥ መከበሩ ይታወሳል፡፡ ዘንድሮ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ በሐረር፣ በጎንደር፣ በሰመራ፣ በደሴ፣ በመቐለና በባሕር ዳር ከተሞች ተካሂዷል፡፡ አራት ኪሎ አካባቢ የተከናወነው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይ ይጠቀሳል፡፡ ከሰኔ 26 እስከ 30፣ 2007 ዓ.ም. በየከተማው የሥነ ጽሑፍ ምሽቶችና የሥነ ጽሑፍ ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡
በአገር አቀፍ ደረጃ መሰል እንቅስቃሴዎች በብዛት ባይስተዋሉም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በዐውደ ርዕዮቹ ለሕፃናት እንዲሁም ለሕፃናት መጻሕፍት ጉልህ ቦታ ይሰጣቸዋል ለማለት ግን አያስደፍርም፡፡ በዚህ ረገድ የዘንድሮው ‹‹ሰኔ 30 የንባብ ቀን›› የተሻለ ይመስላል፡፡
በርካታ ትርጉምና ወጥ የሕፃናት መጻሕፍት ለገበያ ቀርበው ነበር፡፡ ሕፃናት እንዲያነቡ ሊያነሳሱ የሚችሉ የንባብ መርሐ ግብሮችም ተዘጋጅተዋል፡፡ ወቅቱ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ዕረፍት የሚወስዱበት በመሆኑ ክረምቱን በንባብ እንዲያሳልፉ የሚያነሳሱ ዝግጅቶች ቀርበዋል፡፡ በዝግጅቶቹ ቤተሰቦች ተካፋይ ሆነው ልጆቻቸውን ለንባብ እንዲገፋፉ ቅስቀሳ ተደርጓል፡፡
ዝግጅቱን ያሰናዳው የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር (ኢደማ) ነው፡፡ የማኅበሩ ተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይታገሱ ጌትነት እንደሚናገረው፣ የንባብ ባህል እንዲዳብር ቅስቀሳ ከሚደረግባቸው መንገዶች አንዱ ነው፡፡ ‹‹ሰኔ 30 ትምህርት ቤቶች የሚዘጉበት በመሆኑ በተለምዶ ከንባብም ዕረፍት የሚደረግበት እንደሆነ ይታሰባል፤›› የሚለው ይታገሱ፣ ክረምት እንደማንኛውም ወቅት የንባብ ወቅት መሆኑን ለማስገንዘብ እንዳለመ ያስረዳል፡፡
በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱት መርሐ ግብሮች የየአካባቢውን ነዋሪ ለንባብ የሚያነሳሱ እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ ታዳጊዎችን ያማከሉ ዝግጅቶች ልጆችና ቤተሰቦቻቸውን በኅብረት ለመቀስቀስ ሁነኛ መንገድ እንደሆኑ ያክላል፡፡ ዝግጅቱ አብዛኛውን የማኅበረሰቡን ክፍል እንዲሁም የመንግሥት አካላት እንዳሳተፈ ይገልጻል፡፡ በየከተማው ባሉ ከፍተኛ የትምህርት ተቋሞች የተካሄዱት የሥነ ጽሑፍ ምሽቶች፣ የአደባባይ ቅስቀሳዎች እንዲሁም የውይይት መድረኮች የንባብ ባህልን ለማዳበር የሚያስፈልጉ እንቅስቃሴዎችን አመላካች ናቸው ይላል፡፡
ወጣትና አንጋፋ ደራስያን፣ የሥነ ጽሑፍ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላትን ያሳተፉ ውይይቶች በንባብ ዘርፍ ያሉ ክፍተቶችን በመጠቆም፣ የመፍትሔ አቅጣጫ ጠቋሚ እንደሚሆኑ ያምናል፡፡ ውይይቶቹ በተለይም ፖሊሲ አውጪዎችን በማሳተፍ፣ ፖሊሲ በመቅረጽ ረገድ የጎላ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል በማለት ይገልጻል፡፡
ይታገሱ እንደሚለው፣ የማኅበረሰብ ድረ ገጽን ጨምሮ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ መካሄዱ ዝግጅቶቹን ለብዙኃኑ ተደራሽ ስላደረጋቸው ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ፡፡ ለጥቂት ቀናት የሚካሄድ ቅስቀሳና ሥነ ጽሑፉን ያማከሉ መርሐ ግብሮች ማካሄድ የንባብ ባህልን ለማዳበር በቂ አይሆንም፡፡ ‹‹ዝግጅቱ እንደ ማነሳሻ ያገለግላል እንጂ የንባብ ባህል በጥቂት ቀናት የሚዳብር አይደለም፤ ሰዎች ክረምትን ለንባብ እንዲያውሉ በማነቃቃት ያግዛል፤›› ይላል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ለዝግጅቱ የገንዘብ ድጋፍ የሚያደርጉ ተቋሞችን ማግኘት አዳጋች ነበር፡፡ ስፖንሰሮች አለማግኘት የመሰል ዝግጅቶችም ዋነኛ ፈተና ነው፡፡ ስለ ንባብ ያለው ግንዛቤ ሲዳብር ስፖንሰር ለማግኘት የተሻለ ዕድል እንደሚኖር ተስፋ ያደርጋል፡፡ በዚህ ዓመት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በተጨማሪ የግል ቢዝነስ ተቋሞች ስፖንሰር አድርገዋል፡፡ ዝግጅቱ በየዓመቱ በሰኔ ወር መጨረሻ የሚካሄድ ይሆናል፡፡