አዲስ አበባ ሦስተኛው ‹‹ፋይናንስ ለልማት›› ወይም ‹‹ፋይናንሲንግ ፎር ዴቨሎፕመንት ኮንፈረንስ›› የተሰኘውን ትልቁን የዓለም ጉባዔ ለማስተናገድ ሽር ጉድ እያለች ትገኛለች፡፡ የተመድ ሹማምንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለጉባዔው ታዳሚዎች በአዲስ አበባ እንገናኝ ጥሪያቸውን ካስተላለፉ ቀናት መቆጠር ጀምረዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አዘጋጅነት በአዲስ አበባ ሊካሄድ ቀናት የቀሩት ይህ ግዙፍ ጉባዔ የዓለም መንግሥታትን፣ የዓለም ባንክ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅትን ጨምሮ ትልልቅ ኤጀንሲዎች፣ ኩባንያዎች፣ የሲቪል ማኅበረሰብ መሪዎችን ሌሎችም የሚሳተፉበት ነው፡፡ ይህ ጉባዔ በኢትዮጵያ መካሄዱ ከሜክሲኮዋ ሞንቴሬ፣ ከካታሯ ዶሃ ከተማ ቀጥላ በሦስተኛ ደረጃ ቁልፍ ቦታ እንድታገኝ ካስቻሏት መካከል ኢትዮጵያውያን የተመድ ባለሟሎች ሚናም ይጎላል፡፡
በሜክሲኮዋ፣ ሞንቴሬ ፋይናንስ ለልማት የተሰኘው ጉባዔ እ.ኤ.አ. በ2002 ሲጠነሰስ መነሻው የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን ለማስፈጸም በታዳጊ አገሮች ዘንድ የሚታየውን የፋይናንስ እጦት ለመሙላት ከ14 ዓመት በፊት ስምምነት ተደርጎበት ነበር፡፡ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ውስጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል ድኅነትን ማስወገድ፣ ቀጣይነት ያለው ልማት ማስመዝገብና ይህንንም ማስፋፋት የሚሉት ስምምነቶች ላይ የፋይናንስ ድጋፍ መደረግ እንደሚገባ የሚገልጸውን ጨምሮ ባለ 73 ነጥብ የአቋም መግለጫ የወጣው ከ14 ዓመት በፊት በሞንቴሬ ጉባዔ ሲሆን፣ ይህም ‹‹የሞንቴሬ ስምምነት›› ወይም ‹‹ሞንቴሬ ኮንሴንሰስ›› እየተባለ ዛሬም ድረስ ይጠቀሳል፡፡
በታዳጊ አገሮችና በበለጸጉት መካከል አዲስ አጋርነት እንዲፈጠር የሚጣራው የሞቴሬው ስምምነት፣ አምስት ዋና ዋና ይዘቶችን ለዓለም ማስተዋወቁን የተመድ የወቅቱ ሪፖርት አሳይቷል፡፡ የመጀሪያው መሠረተ ሰፊ የልማት አጀንዳን ይዞ ብቅ ማለቱ ሲሆን፣ የልማት ዘላቂነትና አካባቢ ጥበቃ ላይ ያተኮሩ ሐሳቦች ለውይይት ቀርበው ስምምነት የተደረገበት ነው፡፡ ታዳጊ አገሮችን በሚመለከት የሞንቴሬ ስምምነት ከሚጠቅስበት ሌላው ነጥብ የውጭ የልማት ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው አገሮች፣ በተለይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የማይችሉ መሆናቸውና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው መሆናቸው የሚታወቁ አገሮችን ለመደገፍ የሚያስችሉ ስምምነቶችም ይፋ ተደርገውበታል፡፡
‹‹ንግድ ወሳኙ የዕድገት ሞተር ነው›› የሚለው የስምምነቱ አካል ድሃ አገሮች የገበያና የፋይናንስ አንቨስትመንት በማግኘት የንግድ እንቅስቃሴያቸው እንዲጨምር ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸውም በ50 የዓለም መሪዎች ስምምነት የተደረገበት ስምምነት አስፍሯል፡፡ ልዩ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ከተባሉት መካከል አፍሪካ ድሃ አገሮች፣ ትንንሽ የደሴት አገሮችና የባህር በር የሌላቸው አገሮች ኦፊሴላዊ የልማት ዕርዳታ ከሚደረግላቸው መካከል ቅድሚያ የሚያገኙት ወይም ደግሞ ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው መካከል እንደሆኑ የሞንቴሬው ስምምነት አስፍሯል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ ማሰሪያው የስምምነቱ አካልና ለታዳጊ አገሮች ትልቅ ፋይዳ ያለው ደግሞ ሀብታሞቹ አገሮች ለድሆቹ የሚያዋጡት የልማት ፋይናንስ መጠን ነው፡፡ የተመድ የ‹‹ሚሊኒየሙ ዴክላሬሽን›› እየተባሉ የሚታወቁትን የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችን በታዳጊ አገሮች ዘንድ ለማሳካት ለጋሽ አገሮች ከጠቅላላው ብሔራዊ ገቢያቸው የ0.7 ከመቶ መዋጮ እንዲያደርጉ ተስማምተው ነበር፡፡
እንዲህ ያሉ ወሳኝ ውሳኔዎች የተላለፉበት የሞንቴሬው ጉባዔ ከተካሄደ ከ14 ዓመት በኋላ ግን አብዛኞቹ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦችም ሆኑ ቃል የተገቡ የፋይናንስ ድጋፎች ሳይሳኩ፣ የተቀመጠላቸው የአሥራ አምስት ዓመት የልማት ዘመንም ተገባዷል፡፡ በመሆኑም ለተጨማሪ ዓመታት የልማት ግቦችን ለማሳካትና ፋይናንስ ለማድረግ ስምምነት ተደርጎ ተመድ ማስተግበር ከጀመረ ጥቂት ሰነባብቷል፡፡
ዶሃና ሁለተኛው የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ
የሞንቴሬ ስምምነት ከተደረገ ከሰባት ዓመት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2008 በካታር ዶሃ፣ ሁለተኛውን ጉባዔ ማካሄድ አስፈልጓል፡፡ በዶሃ የተደረገው ጉባዔም ከሞንቴሬው ብዙም ልዩነት ያልነበረው፣ እንዲያውም ከመጠሪያው አንስቶ የሞንቴሬው ቀጣይ ጉባዔ እየተባለ የሚጠራው ነበር፡፡
የዓለም አገሮች እንደተለመደው ተለቅ፣ ተለቅ ያሉ የስምምነት መግለጫዎችን ቢያወጡም፣ ለድሆቹ አፍሪካና የትንንሽ ደሴት አገሮች ግን ያን ያህል ጠብ የሚል ወይም አንጀት የሚያርስ የፋይናንስም ሆነ የልማት ድጋፍ ያልታየበት ይመስላል፡፡ በዶሃው ስምምነት የወጣው መግለጫ ካካተታቸው ነጥቦች መካከል ለድሃ አገሮች የሚሰጡ ብድሮችና ብድር ቅነሳዎች አንዱ ነው፡፡ የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጀት የዕዳ ማቅለያ ማዕቀፍ፣ ባለብዙ ድርሻ የዕዳ ቅነሳ ስምምነት እንዲሁም የፓሪስ ክለብ የተባሉትን ጨምሮ በርካታ የዕዳ ቅነሳ ተነሳሽነትን የሚያስተጋቡ ስምምነቶች በዶሃው ጉባዔ ተቃኝተዋል፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ዕዳ ያለባቸው ድሃ አገሮች ተብለው ለዕዳ ቅነሳ ብቁ የተባሉ 41 አገሮች የ71 ቢሊዮን ዶላር ቅነሳ እንደሚደረግላቸው በዶሃው ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ ተካቷል፡፡ ባለብዙ ባለድርሻ አካላት ያሉበት የዕዳ ቅነሳ ማዕቀፍም ተጨማሪ የ28 ቢሊዮን ዶላር ቅነሳ እንደሚያደርግ ተጠቅሶ ነበር፡፡
ሆኖም የዶሃውን ፋይናንስ ለልማት ጉባዔም እንዳቀደው ሁሉ የታሰበው ሳይሆን፣ የተፈለገውን የገንዘብ መጠንም ሳይገኝ እንዲያልፍ የሚያስገድዱ በርካታ ቀውሶች በዓለም ላይ ተከስተዋል፡፡ የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ሰበብ እየሆናቸው በርካታ ያደጉ አገሮች ከገቡት ቃል ማለትም ከጠቅላላ የብሔራዊ ገቢያቸው ውስጥ የ0.7 ከመቶ መዋጮን ማድረግ ቀርቶ፣ ድሆች አገሮች የሚያደርጓቸውን መፍጨርጨሮች እንዳላየ መሆን የጀመሩባቸው ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
ይህ ሁሉ ሆኖም የሞንቴሬው ጉባዔ በወሳኝነቱ ይታወሳል፡፡ የዶሃው ጉባዔ የሞንቴሬው ጥላ ሆኖ ይታያል፡፡ በዚያም ላይ ስምምነት የተደረገባቸው ነጥቦች ሳይተገበሩ ዓመታትን ማስቆጠራቸው የሚያስከፍሉት ዋጋም ትንታኔ ቀርቦበታል፡፡ ሳውዝ ሴንተር የተባለው ተቋም በሞንቴሬ ስምምነት መገባደጃ ሰሞን እ.ኤ.አ. በ2008 ባወጣው የትንታኔ ሪፖርት መሠረት፣ በሀብታሞቹና በድሆቹ አገሮች መካከል ያለው የገቢ ልዩነት እየሰፋ ይገኛል፡፡ ባደጉት አገሮች መካከል ባለፉት ግማሽ ክፍለ ዘመን ወደ ላይ እየተመነደገ የመጣው የገቢ መጠን፣ በታዳጊዎቹና በድሆቹ ግን ባለፉት ሃያ አምስት ዓመታት ያሳየው ዕድገት የቁልቁል መሆኑን ይጠቁማል፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም ያወጣውን ትንበያ ያጣቀሰው ሳውዝ ሴንተር፣ ለአብነት ከሰሐራ በታች የሚገኙ አገሮች ከሀብታሞቹ ጋር ለመመሳሰልና በገቢ እኩል ለመሆን የሚወስድባቸውን ዓመታት አጣቅሷል፡፡ ሀብታሞቹ አገሮች ማደጋቸውን ቢያቆሙ፣ ከሰሐራ በታች የሚገኙ አፍሪካውያን ካደጉት እኩል ለመሆን የሚችሉት እ.ኤ.አ. በ2236 ወይም ከ225 ዓመታት በኋላ ይሆናል ማለት ነው፡፡
ከሰባት ዓመታት በፊት ይወጡ የነበሩ ትንታኔዎች እንዲህ ያሉ በመሆናቸው በማደግ ላይ ያሉ አገሮች የቱንም ያህል ዕድገት ቢያስመዘግቡ የገቢ እኩልነትን፣ የልማት ተመጣጣኝነትን ማስፈናቸው የሩቅ ህልም ሆኖ ይታያል፡፡ ሀብታም አገሮች ይበልጥ ባደጉ ቁጥርና ኢኮኖሚያቸውም ከመቼውም እየፈረጠመ በመጣ ጊዜ ለድሃ አገሮች ዕድገትና ልማት፣ ለፍትኃዊና ለዘላቂ ልማት እናዋጣለን ያሉትን የ0.7 ከመቶ መዋጮ ለማሟላት አለመቻላቸውና አለመፈለጋቸውም እያስወቀሳቸው ይገኛል፡፡ ሌላው ቀርቶ ለሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ያስፈልጋል ተብሎ የነበረው 150 ቢሊዮን ዶላር መዋጣት እንደሚያስፈልግም ከሰባት ዓመታት በፊት ይወጡ የነበሩ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡
ምንም እንኳ አፍሪካ እያስዘመገበች ያለችው የኢኮኖሚ ዕድገትና ለውጥ በአሁኑ ወቅት ካለው የዓለም ወቅታዊ ሁኔታ አኳያ ተስፋ የሚጣልበት ነው ቢባልም፣ በመላው አኅጉሪቱ የሚታየው ለውጥ የሕዝቦችን የኑሮ መሻሻል ለማስፈን፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላትና መሠረተ ልማትን ለማስፋፋት ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ በአፍሪካ የኤሌክትሪክ ኃይል የማያገኙ 600 ሚሊዮን ሕዝቦች ይቆጠራሉ፡፡ ጦም አዳሪዎች በሚሊዮኖች ይገመታሉ፡፡ በጦርነትና በድርቅ የሚሰቃዩ ሚሊዮኖች ዛሬም ድረስ የዕርዳታ ያለህ የሚሉባት አፍሪካ፣ በዓለም መድረክ በኢኮኖሚ ዕድገት የሚነገርላትን ያህል በኢንቨስትመንትና በንግድ አልተሳሰረችም፡፡ ከዓለም የንግድ እንቅስቃሴ ውስጥ ከሦስት ከመቶ ያነሰ ድርሻ በመያዝ፣ በአብዛኛው በግብርና፣ በጥሬ ዕቃና በሸቀጥ ንግድ ላይ የተንጠለጠለ እንቅስቃሴ ላይ መሰለፍ ዛሬም አፍሪካ ዕጣ ፈንታ ሆኖ ይገኛል፡፡
ይህም ቢባል ግን በየዓመቱ በአፍሪካ የሚታየው ኢኮኖሚ ዕድገት ቢያንስ ከሩብ ቢሊዮን በላይ ሰዎች ወደ መካከለኛ ገቢ ክልል ውስጥ እንዲሳተፉ፣ ከአሥር ፈጣን ዕድገት ካላቸው የዓለም አገሮች ውስጥ ስድስቱ መገኛቸው በአፍሪካ እንዲሆን ጊዜው የፈቀደ ይመስላል፡፡ ኢትዮጵያ በአፍሪካ አውራ ከሚባሉቱ ገስጋሽ አገሮች ዘንድ ብትመደብም፣ ዕድገቷ በዓለም እጅጉን ድሃ አገሮች ተብለው ከሚጠሩ ተርታ ሊያስወጣት ካስፈለገ በርካታ ዓመታትን መዝለቅ እንዳለበት መንግሥት የሚቀበለው ሀቅ ነው፡፡ ወደ አገሪቱ የሚመጡ የውጭ ኢንቨስተሮችን በማስተናገድ፣ የወጪ ንግድን በማስፋፋት፣ መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት፣ የሕዝቡን የመሠረታዊ ፍላጎቶች የማሟላት፣ የጤና የትምህርት፣ የመንገድ፣ የምግብና የመሳሰሉትን መሠረታዊ አቅርቦቶች ለሁሉም ሕዝብ የማዳረስ ፈተናዎች አሁንም የመንግሥት የቤት ሥራዎች ሆነው ይገኛሉ፡፡
ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ የኢትዮጵያን ጨምሮ የታዳጊ አገሮችን የልማት ሳንካዎች ገምግሞ የመፍትሔ ሐሳቦችን ከማፅደቅ በተጓዳኝ፣ ለአፍሪካ የረጅም ጊዜ ፋይናንስ አቅርቦትን በሚመለከት የሚመክረውን ስብሰባ ጨምሮ ሁለት መቶ የሚደርሱ ተጓዳኝ ስብሰባዎች በአምስት ቀናት ውስጥ እንደሚካሄዱ ሲጠበቅ በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎችም ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ወደ አዲስ አበባ እንደሚጎርፉ ይጠበቃል፡፡
አዲስ አበባ ግን ስለጉባዔው የምታሰማው ድምፅ ጎልቶ የሚሰማ አይመስልም፡፡ የመዲናዋ ጎዳናዎች በመንግሥት መፈክሮችና በጉባዔው መሪ ቃል (‹‹ታይም ፎር ግሎባል አክሽን››) በባነር ማስታወቂያ ላይ በየቦታው ተሰቅለው ይታያሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ከጉባዔው ትልቅነትና በአገሪቱ ከሚታደሙት እንግዶች አኳያ የጉባዔውን ምንነት፣ በጉባዔው ምክንያት አዲስ አበባ ለሳምንት ያህል ምን ዓይነት ገጽታ ሊኖራት እንደሚችልና ሌሎች ጉዳዮችን የሚያሳዩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራዎች ደካማ ሆነው ይታያሉ፡፡