ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የ2008 ዓ.ም. በጀት እንዲፀድቅላቸው፣ አራተኛው ፓርላማ የሥራ ማብቂያ ዕለት በሆነው ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ተገኝተው ነበር፡፡ የምክር ቤቱ አካላት ከበጀት ጉዳይ ውጪ በሆኑ ጉዳዮች ማብራሪያ የሚሹ ጥያቄዎችንም አቅርበውላቸዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል ከኤርትራና ከጐረቤት አገሮች ጋር ያለውን የፖለቲካ ግንኙነት በተመለከተ ጥያቄ ቀርቦላቸዋል፡፡ ለዚህ በሰጡት ምላሽ ‹‹ሁልጊዜ ከአጋም የተጠጋ ቁልቋል ሆነን አንኖርም፤›› ብለዋል፡፡
የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕድል ደርሷቸው መክፈል ስላልቻሉና በአጠቃላይ የቤቶቹ ዋጋ ላይም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ በእነዚህ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ያደረጉት ንግግር እንዲህ ተስተናግዷል፡፡
ፖለቲካ
ምርጫ
የ2007 ዓ.ም. አጠቃላይ ምርጫን በተመለከተ በተደጋጋሚ እንደተናገርነው፣ የዚህ ምርጫ ዋነኛው ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ በምርጫ ወቅትም በዓለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 96 በመቶ የተመዘገበ መራጭ በካርዱ ተጠቅሟል፡፡ ይህ በጣም ትልቅ ውጤት ነው፡፡ ምናልባትም በዓለም ደረጃ በምርጫ ተሳትፎ ትልቅ ቁጥር ተደርጐ ሊወሰድ የሚችልና ምርምርም የሚያስፈልገው ነው፡፡
ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊና ፍትሐዊ ምርጫ ተካሂዷል፡፡ ሌሎች ምን አሉ የሚለው ነገር ብዙ አያሳስበንም፡፡ ምክንያቱም መነሻቸው የተለያየ ስለሆነ፡፡ ዋናው የእኛ ጭንቅ የሚሆነው ሕዝባችን ምን አለ ነው፡፡
ሕዝቡ ኢሕአዴግን በዚህ ደረጃ በሚመርጥበት ጊዜ የሰጠን መልዕክቶች ግልጽና የማያሻሙ ናቸው፡፡ አንደኛ ኢሕአዴግ እስካሁን የሠራቸው ሥራዎች ውጤት ያመጡ መሆናቸውን የሚያሳዩ ናቸው፡፡ ሁለተኛ ሕዝቡ ካለፉት አራት ምርጫዎች የተማራቸውን ተግባራዊ በማድረጉ ነው፡፡
በሦስተኛ ደረጃ ሕዝቡ ሰላምን የሚፈልግ መሆኑን የገለጹበት ነው፡፡ እንደዚሁም የተዛቡ አስተሳሰቦችን፣ ዘለፋን፣ ሥነ ምግባር የጐደላቸው አስተሳሰቦችን የሚጠላ መሆኑንና ለእነዚህ ቦታ የማይሰጥ መሆኑን ያስመሰከረበት ነው፡፡
ኢሕአዴግ ምንም ስህተት የሌለው መልዓክ ስለሆነ አይደለም የተመረጠው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከዚህ አንፃር ራሳቸውን ሊመረምሩና የምርጫው ውጤት ምን ማለት እንደሆነ ሊመረምሩ ይገባል፡፡
ኤርትራ
ዋናው የውጭ ጉዳይ ግንኙነታችን በአካባቢያችን ሰላም እንዲሰፍን፣ የጋራ ጉርብትናንና ልማት እንዲከናወን ነው፡፡ ትስስሩ እየጐለበተ ሄዶ በኢኮኖሚ የመጨረሻውን ደረጃ የያዘ የኢኮኖሚ የጋራ ክንውንና ቅንጅት የመፍጠር ውህደትን እግረ መንገዳችንን የመፍጠር ስትራቴጂ ይዘን በመሥራት ላይ እንገኛለን፡፡
ከሻዕቢያ ውጪ ካሉ ጐረቤቶቻችን ጋር የምናደርገው እንቅስቃሴ እጅግ ውጤታማ ነው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ከኬንያ፣ ከጂቡቲ፣ ከሱዳን ጋር የተፈራረምናቸውና በተግባር እያከናወናቸው ያሉ ሥራዎች በጥሩ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ ስለዚህ ይህንን አጠናክረን መሄድ ይኖርብናል፡፡
ነገር ግን የሻዕቢያ መንግሥት አካባቢውን የማተራመስ አባዜውንና ፖሊሲውን እስካሁን አልቀየረም፡፡ ይህንን ፖሊሲውን የማይቀይርበት መሠረታዊ ምክንያት ደግሞ አለው፡፡ በአገር ውስጥ የተከሰቱ ውስጣዊ ችግሮችን ለመሸፈን ያለው ብቸኛው አማራጭ ሌሎች እያጠቁኝ ስለሆነ፣ ወደ እነዚህ ትኩረቴን አድርጌያለሁ በማለት ሕዝቡን የማታለያ መንገድና ስትራቴጂ ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ተግባሩን በአጭር ጊዜ ውስጥ ያቆማል ተብሎ አይወሰድም፡፡ ይህንን ፖሊሲ መቀየር ያለበት ከሆነ በመጀመሪያ በውስጥ ጉዳዩ በማተኮር በመቶ ሺዎች እየኮበለሉ ያው ወጣቶችን ለማዳን የውስጥ ፖሊሲ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ይህንን ለውጥ ካላደረገ በስተቀር በተለይ ኢትዮጵያንና ጂቡቲን በማተራመስ የውስጥ ችግሩን ውጫዊ ለማድረግ መሥራቱን የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህ ለኤርትራ መንግሥት የሞት የሽረት የሆነ ጉዳይና የመኖሪያ አጀንዳው ነው፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት በኤርትራ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም የያዛቸው አጀንዳዎችን ማጠናከሩ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዋናው ጉዳይ ግን የኤርትራና የኢትዮጵያ ሕዝቦች የሚጠቀሙት ከሰላም በመሆኑ ሰላም ለእኛ የመጀመሪያውም የመጨረሻውም አማራጭ ይሆናል፡፡
ነገር ግን የኤርትራ መንግሥት አሁን በያዘው ፖሊሲ የሚቀጥልና ኢትዮጵያንና ሌሎች ጐረቤት አገሮችን ማተራመሱን የሚቀጥል ከሆነ፣ ተገደን ዕርምጃ የምንወስድበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የኢትዮጵያን ሕዝብ በማማከር ዕርምጃ እንወስዳለን፡፡ የሚያውክ ጐረቤት ባለበት ሁኔታ ‹‹አጋምን የተጠጋች ቁልቋል›› እንዳንሆን ሁልጊዜ መጠንቀቁ ስለሚገባን፣ ጊዜ ወስደን ለኢትዮጵያ ሕዝብ ገልጸን አስፈላጊውን ዕርምጃ ለመውሰድ የምንገደድበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ ይህንን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሳውቀናል፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም እስካሁን ድረስ የዚህን መንግሥት አጥፊ መሆን በመገንዘብ ማዕቀብ ጥሎበታል፡፡ ማዕቀቡ ወደ ተግባር እንዲሸጋገር በየጊዜው እየጠየቅን እንገኛለን፡፡
ይኼ መንግሥት ፖሊሲውን በመቀየር ወደ ሰላም መንገድ እንዲመለስ በጠረጴዛ ዙሪያ ችግሮችን ለመፍታት እንዲገደድና እንዲቀመጥ፣ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ዕርምጃዎችን መውሰድ ይገባዋል፡፡ እኛም ለዚህ ሥራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ካውንስል ያወጣው ሪፖርት በኤርትራ መንግሥት ዙሪያና የኤርትራ ሕዝብ ምን ያህል እየተሰቃየ እንዳለ የሚያሳይ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ይህንን ሪፖርት ተመልክቶ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንደሚወስድ እየጠበቅን እንገኛለን፡፡
ስለዚህ በእኛ በኩል ሰላም ብቸኛ አማራጫችን ነው፡፡ አሁንም ጥያቄያችንና እጃችንን ዘርግተን ስለ ሰላም በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብለን ያለብንን ችግሮች እንድንፈታ ሙሉ ዝግጁነት አለን፡፡ ይህ ሳይሆን ቢቀርና ተገደን ሰላማችንን ለማስከበርና ራሳችንን ለመከላከል ኃይል መጠቀም ያለብን ከሆነ፣ እንደ ወትሮው የኢትዮጵያን ሕዝብ አሳውቀን አስፈላጊውን ዕርምጃ መውሰዳችን የሚቀር አይሆንም፡፡
እስከዚያው ድረስ ለተከበረው ምክር ቤት እንዳሳወቅነው ሁሉ ለእያንዳንዷ ትንኮሳ ዓለም አቀፍ ሕግን የተከተለ ተመጣጣኝ ዕርምጃ እየወሰድን መጥተናል፡፡ አሁንም ይህንን እንቀጥላለን፡፡ በሌላ በኩል እጅግ የሚያሳዝነው የአገሬው ሕዝብ ወይም የኤርትራ ሕዝብ ወጣት አልባ እየሆነ መምጣቱ ነው፡፡
በርካታ ወጣቶች ከኤርትራ እየኮበለሉ በመሆናቸው ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ከዚያም አልፎ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እነዚህን ከፍተኛ ስደተኞች ለማስተናገድ ተገድደዋል፡፡
ለኢትዮጵያና ለኤርትራ ሕዝብ አንድነትና ሰላም እንዲሁም ወንድማማችነት ስንል ይህንን ስደት መሸከማችን ግዴታችን ነው፡፡ ከኤርትራ ሕዝብ ጋር ችግር የሌለብን ሕዝቦች ነን፡፡
ማኅበራዊ ጉዳዮች
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር
ሕገወጥ የሰዎች ዝውውርን በተመለከተ ሕዝቡን የእንቅስቃሴው ባለቤት ማድረግ አለብን፡፡ ከገጠር ቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል መንግሥት ድረስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ወላጆች፣ የእምነት አባቶች፣ መምህራን እንዲሁም ከወጣቶችና ከሴቶች አደረጃጀቶች ጋር በመሆን ነው ለውጥ ሊመጣ የሚችለው፡፡ እስካሁን ካለን ግምገማ ከፍተኛ ለውጥ እንደመጣ እናያለን፡፡ ነገር ግን እነዚህን ሕገወጥ ደላሎች በተመለከተም መንግሥት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ፣ በደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል የተዘረጋውን የደላሎች መረብ ለመበጣጠስ ችሏል፡፡ ይህንን ጥረት አጠናክሮ መቀጠል ነው፡፡ አሁን በሁለተኛው ደረጃ እየተሠራ ያለው ከሰሜንና ከምዕራቡ የአገራችን ክፍሎች በመነሳት እስከ ሊቢያ፣ እንዲሁም ጣሊያንና በዚያ አካባቢ ያሉ ደላሎችን የመበጣጠስ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በቅርቡም የኢንተርፖል ኃላፊ አዲስ አበባ በመምጣት ከእኔ ጋር ውይይት አድርገናል፡፡ ከሚመለከታቸው ኃላፊዎችም ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ስለዚህ ይህንን መረብ እንበጣጥስ የሚል ዓለም አቀፍ ትብብር ተጀምሯል፡፡
ኮንዶሚኒየም
ይህ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ፕሮጀክት በርካታ ዜጐቻችንን የቤት ባለቤት እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋን በተመለከተ ዋጋው ጨምሯል የሚል ጥያቄ ከተነሳ በኋላ፣ በየጊዜው የዋጋው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማጥናት ሙከራ አድርገናል፡፡ ያገኘነው እውነታ ቢኖር ዋጋው የኮንዶሚኒየም ግንባታ ከተጀመረበት ከ1996 ዓ.ም. ጀምሮ በየጊዜው በተወሰነ ደረጃ እያደገ ነው የመጣው፡፡ ያሁኑ ዋጋ የተለየ ጭማሪ አላሳየም፡፡ ስለዚህ የተሳሳተ መረጃ ይዘን እንዳንከራከር ያለው እውነታ ከመጀመሪያው ጊዜ አንስቶ ያለው ዋጋ የተወሰነ ጭማሪ የሚያሳይ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ለተጠቃሚዎች የተላለፈበት ዋጋ ከሌሎች ጊዜያት ሁሉ አነስ ያለ መሆኑን ነው ያየነው፡፡
ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ ዋጋ ጨምሯል የሚባለው ነገር ብዙም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፡፡ ችግሩ የተከሰተው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ እነዚህ ቤቶች እየተላለፉላቸው ያሉት ነዋሪዎች፣ የተወሰኑ ዓመታትን ብቻ ከቆጠቡ በኋላ በመሆኑ ዕድሉ የደረሳቸው ሰዎች የመጀመሪያውን ክፍያ ለመክፈል ቁጠባው በቂ ባለመሆኑ በመቸገራቸው ነው፡፡
ሁለተኛው ምክንያት ብዙዎቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ሰዎች በገቢያቸው መጠን የቤት ዓይነት ፍላጐታቸውን ባለመወሰናቸው ነው፡፡ ብዙዎቹ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ተጠቃሚዎች ባለሦስት መኝታ ቤት ነው የተመዘገቡት፡፡ ስለዚህ የሦስት መኝታ ቤት የመጀመሪያ ክፍያ ዋጋና የስቱዲዮ የመጀመሪያ ዋጋ የተለያዩ ናቸው፡፡ ወይም ባለ አንድ መኝታ ቤት የመጀመሪያ ክፍያ ዋጋ የተለያዩ ናቸው፡፡
ይህ ፕሮግራም በሚቀረጽበት ጊዜ ባለሁለትና ባለ ሦስት መኝታ ክፍል ቤቶች መካከለኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ይሆናሉ ተብሎ ነው የታቀደው፡፡ ስቱዲዮና ባለ አንድ መኝታ ክፍል ደግሞ አነስተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነው የተቀረፁት፡፡ ይኼ ደግሞ ከመክፈል አቅማቸው ጋር ተያይዞ ነው፡፡ እነዚህን ቤቶች ፕሮግራም በምናደርግበት ጊዜ አንደኛው እያንዳንዱ ተጠቃሚ ሊከፍል በሚችለው መጠን እንዲወስን ነው፡፡
አነስተኛ ገቢ እያላቸው ባለሁለትና ባለሦስት መኝታ ቤት የተመዘገቡ የኅብረተሰብ ክፍሎች ወደ የስቱዲዮና፣ ባለአንድ መኝታ ቤት የሚሸጋገሩበት ሁኔታ ካለ የምናየው ይሆናል፡፡ ባለ ሦስትና ባለ ሁለት መኝታ ቤቶች ደግሞ መካከለኛ ገቢ ላላቸውና መክፈል ለሚችሉ ሰዎች ተብሎ የተቀመጠ ነው፡፡ ባለ ሦስት መኝታ ቤት የመያዝ ምኞት ወይም ፍላጐት ቢኖረንም፣ ከገቢያችን ጋር አስተሳስበን ዋናው መጠለያ የማግኘት በመሆኑ ለዚህ መሥራት ይኖርብናል፡፡ በመሆኑም ከተጠቃሚዎቹ ጋር በቅርብ ተነጋግረን ይህንን ሽግሽግ እንዴት ማምጣት እንደምንችል እናያለን፡፡
በተጨማሪ አነስተኛ ገቢ ያላቸው ነዋሪዎች ከ20/80 የቤቶች ፕሮግራም ውጪ የ10/90 የቤቶች አማራጭ አሏቸው፡፡ አብዛኛው አነስተኛ ገቢ ያለው ሰው 10/90 ፕሮግራም ላይ መመዝገብ ሲገባው የተመዘገበው ግን በ20/80 ፕሮግራም ነው፡፡ ስለዚህ 10/90 የሠራናቸው ቤቶች ከተመዝጋቢው ቁጥር በላይ ናቸው፡፡ ምክንያቱም ፍላጐቱ አነስተኛ በመሆኑ ነው፡፡ የ10/90 ቤቶች ፕሮግራም ግንባታዎችን እኔ ሄጄ ተመልክቻለሁ፡፡ በሚገባና በጥሩ ሁኔታ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ሊያኖሩ የሚችሉ ናቸው፡፡ ስለዚህ በገቢያችን መጠን ወደ 10/90 ፕሮግራም ለመምጣት የምንፈልግ ካለን መንግሥት ለማስተናገድ ዝግጁ ነው፡፡ ይህንን ስንል ምክር ቤቱ እንዲገነዘብልን የምንፈልገው ነገር መንግሥት ለቤቶቹ ግንባታ 50 በመቶ ድጐማ አድርጓል፡፡
እነዚህ በቅርቡ ያስተላለፍናቸው ቤቶች 16 ቢሊዮን ብር ነው አጠቃላይ ወጪያቸው፡፡ ከዚህ ውስጥ መንግሥት 7.5 ቢሊዮን ብር ወጪ ሸፍኗል፡፡ ተመሳሳይ ቤቶች በግል ባለሀብቶች የተሠሩ በገበያ ዋጋ እየተሸጡ ያሉት በመንግሥት ከሚገነቡት በአምስት እጥፍ ነው የሚበልጠው፡፡
በዘንድሮው ዓመት የመንግሥት ሠራተኛው ልዩ ተጠቃሚ እንዲሆን በማስፈለጉ ምክንያት 20 በመቶ የሚሆነውን የቤቶች ድርሻ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻቸውን እንዲያወጡ ነው የተደረገው፡፡ ከዚህ አኳያ በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ዕጣው ደርሷቸዋል፡፡
ይህ ዕድል የደረሳቸው የመንግሥት ሠራተኞች ቤቱን ለባለሀብቶች እንዳያስተላልፉት ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ቁጭ ብለን ልንነጋገርበት ይገባል፡፡ ሌሎቹንም የኅብረተሰብ ክፍሎች በተመለከተም እንዲሁ፡፡ ስለዚህ ውስጡን ከመፈተሽ ይልቅ ዋጋው በዝቷል የሚል ነገር ተገቢ አይደለም፡፡ ዋጋው በተመሳሳይ ሁኔታ ነው እየጨመረ የመጣው፡፡ ይኼም የሆነበት ምክንያት አምና የነበረውና ዘንድሮ ያለው የጉልበት ዋጋ እኩል ባለመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ይህ ዋጋ የቤቶቹ ዋጋ ላይ ይንፀባረቃል ማለት ነው፡፡
እንደዚሁ ደግሞ ዋጋቸውን የቀነሱ ግብዓቶች ሲኖሩ ደግሞ ዋጋቸው ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ በዚህ መሠረት የሚፈጸም እንደሆነ ግንዛቤ ቢኖር የሚል አስተያየት አለኝ፡፡