Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ አጭበርብረዋል የተባሉ እስራት ተፈረደባቸው

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የተቀጡት በሌሉበት ነው

መንግሥታዊ ሰነዶችን በሐሰት በማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሰባራ ባቡር ቅርንጫፍ፣ ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ማጭበርበራቸው የተረጋገጠባቸው የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅና ሁለት ግለሰቦች፣ ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአምስት እስከ 12 ዓመታት ከስድስት ወራት የሚደርስ ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው፡፡

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ሕግ በሙስና ወንጀል ክስ የመሠረተባቸው፣ የቅርንጫፉ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት አበጀ፣ ይፈመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ የተባለ ድርጅት ተወካይ አቶ ብርሃኑ አዳፍሬና የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይትባረክ አፈወርቅ ናቸው፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ክስ እንደሚያስረዳው፣ የባንኩ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት በ2005 ዓ.ም. የተለያዩ ሀሰተኛ የባንክ ዋስትና ሰነዶችን አዘጋጅተዋል፡፡ ያዘጋጁትን ሐሰተኛ ሰነድ ይፍመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ ለተባለው ድርጅት በመስጠት ወንጀሉን መፈጸማቸውን ያስረዳል፡፡

በሥራ አስኪያጁ የተዘጋጀውን ሐሰተኛ ሰነድ የድርጅቱ ተወካይ አቶ ብርሃኑ በመቀበልና ሐሰተኛ የሽያጭ ዋስትና በማስያዝ፣ ከአንድ የማደያ ድርጅት ውል ተዋውለው 900,000 ብር የሚያወጣ የሞተር ዘይት፣ ቅባቶችና የነዳጅ ኩፖን ወስደው በወንጀሉ መሳተፋቸውን ክሱ ያስረዳል፡፡

የይፈመን ቲምበር ፕሮሰሲንግ ሥራ አስኪያጅ ናቸው የተባሉት አቶ ይትባረክ፣ ከአቶ ብርሃኑ ጋር በመተባበር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ላደረጉት የእንጨት ምሰሶዎች አቅርቦት ውል፣ ሐሰተኛ ሰነዱን በዋስትና በማቅረብ 4,908,623 ብር ቅድመ ክፍያ ከኢትዮ ቴሌኮም በቼክ መውሰዳቸውን ይገልጻል፡፡ ገንዘቡንም ወደ ድርጅታቸው አካውንት በማስገባትና አውጥተውም ለግል ጥቅማቸው ማዋላቸውም በክሱ ተጠቁሟል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ ሦስቱም ተከሳሾች ድርጊቱን መፈጸማቸውን በምስክሮችና በሰነድ በማረጋገጡ፣ የባንኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ መኳንንት በሌሉበት በስምንት ዓመታት ጽኑ እስራት፣ አቶ ብርሃኑ አዳፍሬ በ12 ዓመት ከስድስት ወራት ጽኑ እስራትና አቶ ይትባረክ አፈወርቅ በአምስት ዓመታት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 18ኛ ወንጀል ችሎት ሰኔ 25 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ሰጥቷል፡፡  

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች