Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ዜናየአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሠረተ ልማት ተቋማት በሚፈጥሩት ችግር ኅብረተሰቡ ተማሯል አለ

  የአዲስ አበባ ምክር ቤት የመሠረተ ልማት ተቋማት በሚፈጥሩት ችግር ኅብረተሰቡ ተማሯል አለ

  ቀን:

  • ሳትኮንና ትድሃር ኮንስትራክሽን በጥቁር መዝገብ ሰፈሩ
  • የግል ትምህርት ቤት የዋጋ ጭማሪ ኢኮኖሚያዊ መሠረት የለውም አለ
  • በምርጫ ሰሞን ሕገወጥ የመሬት ወረራ መፈጸሙን ገለጸ

  ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱን የመጨረሻ ጉባዔ ማካሄድ የጀመረው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት፣ የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት መስጫ ተቋማት በሚፈጥሩት ችግር ኅብረተሰቡ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረገ መሆኑ ተመለከተ፡፡ በጉባዔው ከንቲባ ድሪባ ኩማ የ2007 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምና የ2008 በጀት ዓመት የዕቅድ አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት አድርገዋል፡፡

  ከንቲባው በዚህ ሪፖርታቸው የአስተዳደሩን ውጤታማ ሥራዎችና ተግዳሮቶች በዝርዝር አቅርበዋል፡፡ በቀረበው ሪፖርት ላይ በመንተራስ የምክር ቤት አባላት ከኅብረተሰቡ የሰበሰቧቸውን ችግሮች አቅርበዋል፡፡ የምክር ቤት አባላት አንኳር ናቸው በማለት ካቀረቧቸው ችግሮች መካከል የዘገዩ የመንገድ ፕሮጀክቶች፣ የኮንዶሚኒየምና የትምህርት ቤት ዋጋ ንረት፣ የተሽከርካሪ አደጋዎችና በምርጫው ዋዜማና ማግሥት የመሬት ወረራ መካሄዱ ይገኝበታል፡፡

  ሳትኮን ኮንስትራክሽን ከአዲስ አበባ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን ሁለት መንገዶችን በመረከብ ግንባታ በማካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ የመጀመርያው ከተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በቴዎድሮስ አደባባይ አድርጎ እስከ ቤተ መንግሥት ያለው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከጎሮ በሲኤምሲ አድርጎ ወንድይራድ ትምህርት ቤት ድረስ የሚገነባው መንገድ ነው፡፡

  እነዚህ ሁለት መንገዶች መጠናቀቅ ካለባቸው ጊዜ በላይ የተጓተቱ በመሆናቸው፣ የምክር ቤት አባላት እንደተናገሩት መንገዶቹ በወቅቱ አለመጠናቀቃቸው ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል፡፡

  ከሳትኮን በተጨማሪ ትድሃር የተባለው የእስራኤል ኮንስትራክሽን ኩባንያ ከመገናኛ ወደ ጉርድ ሾላ የሚያመራውን የቀኝ ክፍል ለመገንባት ቢረከብም፣ ግንባታው እጅግ በመጓተቱ የአካባቢው ማኅበረሰብ ለከፍተኛ ችግር እየተዳረገ መሆኑን የምክር ቤት አባላቱ ተናግረዋል፡፡

  የአዲስ አበባ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ያብባል አዲስ ለምክር ቤት አባላት ማብራሪያ ሲሰጡ፣ እነዚህን ፕሮጀክቶች ከኩባንያዎቹ መንጠቅ አስተዳደሩን ለከፍተኛ ወጪ ስለሚዳርግ መሥሪያ ቤታቸው ዕርምጃ መውሰድ አልቻለም፡፡ በአሁኑ ወቅት አስተዳደሩ ኩባንያዎቹን እያስታመመ ግንባታውን እንዲጨርሱ ለማድረግ እየሞከረ ነው ብለዋል፡፡

  ከንቲባ ድሪባ ግን ለምክር ቤቱ እንደተናገሩት፣ እነዚህ ኮንትራክተሮች ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም ሥራቸውን አጠናቅቀው ሊያስረክቡ አልቻሉም፡፡ ስለዚህ ከዚህ በኋላ አስተዳደሩ በሚያወጣው ጨረታ እንደማይሳተፉና በጥቁር መዝገብ መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡

  የካቢኔ አባላት በቀጣይነት ያቀረቡት የኮንዶሚኒየም ቤቶች የዋጋ ንረት ነው፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ምዝገባ በተጀመረበት ወቅት የነበረው ዋጋ፣ ዕጣ ከወጣ በኋላ እጅግ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ይህም ኅብረተሰቡን ለአላስፈላጊ ወጪ ከመዳረጉ በላይ ዕጣ የወጣላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች የወጣላቸውን ዕጣ ለመጠቀም ፈተና እንደሆነባቸው አስረድተዋል፡፡

  ከንቲባ ድሪባ ለዚህ ጥያቄ ሲመልሱ የዋጋው ሁኔታ በተደጋጋሚ ተመርምሯል፡፡ ነገር ግን ወደ ግንባታ በተገባ በሦስት ዓመት ውስጥ የኮንስትራክሽን ዕቃዎችና በሰው ኃይል ረገድ የዋጋ ንረት ተከስቷል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ከነበረው ዋጋ የተጨመረው 15 በመቶ ብቻ ነው፡፡ ‹‹የሪል ስቴት ኩባንያዎች የሚሸጡት አፓርታማ በካሬ ሜትር ከ16 ሺሕ እስከ 24 ሺሕ ብር ድረስ ነው፡፡ በ20/80 ፕሮግራም ባለ ሦስት መኝታ ክፍል ግን በካሬ ሜትር 4,700 ብር ነው፡፡ ከዚህ ዋጋ ጋር ሲነፃፀር የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋው አነስተኛ ነው፤›› በማለት የገለጹት ከንቲባ ድሪባ፣ ‹‹ነገር ግን ዝቅተኛ ገቢ ላላቸውና ግዢ መፈጸም ላልቻሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሌሎች የመኖሪያ ቤት ፓኬጆች እያጠናን ነው፡፡ በቅርቡም ይፋ ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡

  ሌላው የተነሳው አንገብጋቢ ችግር የግል ትምህርት ቤቶች ለ2008 የትምህርት ዘመን ዋጋ እየጨመሩ ነው የሚለው ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የግል ትምህርት ቤቶች ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ መሆኑን በመጥቀስ፣ የምክር ቤት አባላት ጉዳዩ ሊመረመር እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ለዚህ ጥያቄ ከንቲባው ሲመልሱ፣ በትምህርት ላይ ዋጋ መጨመር የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የለም፡፡ አግባብም አይደለም ብለዋል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶችን የትምህርት ጥራትና ዋጋ የሚቆጣጠር ራሱን የቻለ መንግሥታዊ ኤጀንሲ ለማቋቋም ጥናት መካሄዱን አመልክተዋል፡፡

  በአዲስ አበባ ከተማ እየደረሰ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ ከቀረቡ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ አደጋ ከአዲስ አበባ ውጪ መንጃ ፈቃድ እያወጡ የሚያሽከረክሩ ግለሰቦችና የመንጃ ፈቃድ አወጣጥ ሥርዓቱ ላይ ጥያቄ ተነስቷል፡፡

  ለእነዚህ ጥያቄዎች አቶ ያብባል ሲመልሱ፣ ከአዲስ አበባ ውጪ መንጃ ፈቃድ ማውጣት ችግሩን እንዳልፈጠረ ገልጸዋል፡፡ የችግሩ መንስዔ ‹ፎርጂድ› መንጃ ፈቃድ በሰፊው መሠራጨቱ ነው ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከአዲስ አበባ ውጪ በፌዴራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን አማካይነት የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ላይ ያለው ችግር እየተጤነ ነው ብለዋል፡፡

  ሌላኛው የተነሳው ችግር ከግንቦት 2007 ዓ.ም. ምርጫ ዋዜማና ማግሥት በተለይ በቦሌ፣ በኮልፌና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍላተ ከተሞች የመሬት ወረራ መካሄዱ መገለጹ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም መሬት የወረሩ ግለሰቦች ምሕረት ተደርጎላቸዋል በማለት በርካታ ግለሰቦች መሬት ወረራ ማካሄዳቸውን የከተማው ፍትሕ ቢሮ ገልጿል፡፡ ከንቲባ ድሪባ ይህንን ሁኔታ ‹‹ሕገወጥ ተግባር›› ካሉት በኋላ፣ ‹‹ከ1988 ዓ.ም. እስከ 1997 ዓ.ም. በሕገወጥ መንገድ መሬት ወረው ምሕረት የተደረገላቸው በወቅቱ የመኖርያ ቤት ችግር ስለነበር ነው፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የመኖሪያ ቤት ችግር የቀነሰ በመሆኑ በመሬት ወራሪዎቹ ላይ በአስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...