Wednesday, June 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ኪንና ባህልለተዘነጋው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት የሚደርስለት ማን ነው?

ለተዘነጋው የአባ ጅፋር ቤተ መንግሥት የሚደርስለት ማን ነው?

ቀን:

አሥራ ሁለት ተሳፋሪዎችን ብቻ ለመጫን የተዘጋጀው ሰማያዊ ታክሲ ተጨማሪ 13 ሰዎችን አሳፍራለች፡፡ አራተኛው ወንበር ላይ የተቀመጡ ሰዎች ሳይቀሩ ሌላ አምስተኛ ሰው ይጋፋቸው ይዟል፡፡ ረዳቱ በሚቀመጥበት አግዳሚ ወንበርም አምስት ሰዎች ተጨናንቀው እንዲቀመጡበት ተደርጓል፡፡ ሁለት ሰዎች የሚጭኑ ወንበሮችም ለሦስተኛ ሰው ቦታቸውን አጋርተዋል፡፡

በወጉ ያልተጠረገውን የጠጠር መንገዱ አቋርጦ የሚሄዱ ታክሲዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ብቅ የሚሉ ሲገኙ ተጋፍቶ ቦታ መያዝ ነው፡፡ ትርፍ መጫኑ፣ በጠባብ ቦታ ላይ ተዛዝሎ መሄዱ አያሳስባቸውም፡፡ መኪናው በተንገጫገጨ ቁጥር አንዱ መንገደኛ ሌላኛው ላይ መውደቁ አያስጨንቀውም፡፡ ሾፌርና ረዳቱ ፈላጭ ቆራጭ በሆኑበት በዚህ መስመር ክፈሉ የተባሉትን ከመክፈል ውጪ ታሪፉን ጠቅሶ መከራከርም አይታያቸውም፡፡ ከዚህ ውጭ በታሪፉ መሠረት ነው የምከፍለው ብሎ የሚከራከር ተሳፋሪ የጭቅጭቅ ፍቅር ቢኖርበት እንጂ ሕጉን ተከትሎ የሚቀንስለት እንደሆነ የለም፡፡

እንደ ኅብረተሰቡ አገላለጽ፣ ሕግ የማይገዛው ይህ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጠው ከተቆረቆረች ከ180 ዓመታት በላይ ባስቆጠረችው ጅማ ከተማ ውስጥ ነው፡፡ እንዲህ ያለ ሕገወጥነት የሚታየው ደግሞ መነሻቸውን ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ሪፈራል ሆስፒታል ከፍ ብሎ ከሚገኘው የታክሲ ተራ ተነስተው ከተማዋን ወደ ቆረቆሩት ንጉሥ አባጅፋር መንደር ጅሬን የሚሄዱ ታክሲዎች ናቸው፡፡

- Advertisement -

በአንድ ወቅት የሥልጣኔ ዘውግ፣ ሥነ ሥርዓት አብዝቶ የሚከበርባት፣ የታፈረች የንጉሡ መንደር የነበረችው ጅሬን እንደ ቀድሞው የመናገሻ ሥፍራነቷ ሳይሆን አስፋልት እንኳን የማታውቅ የገጠር መንደር ሆናለች፡፡ የጠጠር መንገድ እንኳን እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ብርቋ ነበር፡፡ ከከተማው ሦስት ኪሎ ሜትሮች ያህል ርቃ የምትገኝ ሳይሆን መቶ ኪሎ ሜትሮችን ርቃ እንደምትገኝ አነስተኛ የገጠር መንደር ሆና ቆይታለች፡፡ እንደ መንገድ ያሉ ወሳኝ የመሠረተ ልማት አውታሮች ቀርቶ የትራፊክ ሕግ እንኳ በጅምር ላይ እንደሚገኘው የጠጠር መንገዷ ርቋታል፡፡

ጅሬንን የቆረቆሩት የንጉሥ አባጅፋር ቤተ መንግሥት የተገነባው በዚሁ ተራራማ ሥፍራ ላይ ነው፡፡ የከተማው አናት ላይ የተገነባው ቤተ መንግሥቱ በአራቱም አቅጣጫ ከተማዋን ወለል አድርጎ ያሳያል፡፡ በ6,666 ጂፒኤስ ላይ ያረፈ ሲሆን፣ የተገነባው ከ140 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ ልዩ የኪነ ሕንፃ ጥበብ የሚታይበትን ይህንን ቤተ መንግሥት ለመገንባት ያልተለመዱ ነገሮች በጥቅም ላይ ውለዋል፡፡

 በወቅቱ ሕንፃ የሚገነባበት እንደ ሲሚንቶ ያሉ ግብዓቶችን ማግኘት አይታሰብም ነበር፡፡ ስለዚህም መሰል ቤተ መንግሥቶችን ለመገንባት የተለያየ ዘዴዎችን ጥቅም ላይ ይውላሉ፡፡ የአባጅፋር ቤተ መንግሥት የተሠራውም ጭቃና ጭድ በእግር ተረግጦ ለሦስት ወራት እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ እንደ የሲሚንቶ ሚና እንዲጫወት ደግሞ የስንዴ ዱቄትና እንቁላል በአንድነት ከጭቃው ጋር ተለውሰዋል፡፡ አንግሎቹም በቄንጠኛ ድንጋዮች የታነፁ ናቸው፡፡

65 በሮች፣ 54 መስኮቶችና 29 ክፍሎች ኖረውት የተገነባው ቤተ መንግሥቱ ባለ አንድ ፎቅ ሲሆን፣ ከአናቱ ላይ ደግሞ አንድ ማማ አለው፡፡ እንደ ኮርኒስና ወለል እንዲሁም እንደ ምሰሶ ሆነው ውስጡን ያዋቀሩ ከዋንዛ የተፈለፈሉ አሥር በአሥር ሳንቲ ውፍረት ያላቸው ጠንካራ ጣውላዎች ነው፡፡ ከአናቱ ላይ ያለው ማማ ውስጡ ሙሉ በሙሉ ከጣውላ የተሠራ ሲሆን፣ አራት የጥበቃ በሮች አሉት፡፡ በምሥራቅ ሸዋ በር፣ በምዕራብ ከፋ በር፣ በደቡብ ዳውሮ በርና በሰሜን ደግሞ ሊሙ በርን ያስቃኛሉ፡፡ በእነዚህ አቅጣጨዎች ወታደሮች በአራቱም በሮች በተጠንቀቅ ቆመው ቅኝት ያደርጋሉ፡፡

ከማማው ላይ ሲወጡ ጥንታዊነቷን የለቀቀችውና የዛጉ ቆርቆሮ ክዳኖች የበዙባት ጅማ ከተማ ቁልጭ ብላ ትታያለች፡፡ በዚያው መጠን ያረጀውን የቤተ መንግሥቱን የላይኛውን ክፍል እንዲመለከቱ ዕድል ይሰጣል፡፡ ቤተ መንግሥቱ በ1870 ዓ.ም. ሲገነባ ከህንድ፣ ከፓኪስታን፣ ከፈረንሣይ፣ ከእንግሊዝና ከሌሎች የዓረብ አገሮች ጋር ዲፕሎማቲክ ግንኙነት የነበራቸው ንጉሡ አባጅፋር ለግንባታው የሚሆኑ አንዳንድ ግብዓቶችን ያስገቡት ከባህር ማዶ ነበር፡፡

ለምሳሌ እንደ ብረት የሚጠነክረው የጣራው ክዳን የተጫነው ከእንግሊዝ አገር ነበር፡፡ በወቅቱ የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት አልነበረምና ቆርቆሮዎች በግመል ተጭነው በኬንያ በኩል ነበር ወደ ኢትዮጵያ እንዲገባ የተደረገው፡፡ የመብረቅ መከላከያ ብረቱም እንደዚሁ ከፈረንሣይ አገር የተላከ ነበር፡፡

አጠቃላይ የቤቱ ዲዛይንና በመግቢያ በሮች ላይ ከአንድ እንጨት ተፈልፍሎ የተሠራው ጌጠኛ ቅርፅ የተላከው ከህንድ አገር ነበር፡፡ ማማው ላይ ወተው ሲመለከቱ ታዲያ በእርጅና ምክንያት የተበጣጠሰው የጣሪያው ከፈፍ፣ ጉራማይሌ የሆነው የቆርቆሮው ንጣፍ፣ የሕንፃው ድጋፍ የነበሩ ነገር ግን በእርጅና ብዛት ደጋፊ የሚያስፈልጋቸው የጣራው ምሰሶዎች፣ መዝናኛ የነበሩ አልጌ የበቀለባቸው በረንዳዎችና ሌሎችም ቤተ መንግሥቱ ያለበትን አደገኛ ሁኔታ ያስታውሳሉ፡፡

በአጠቃላይ ቤተ መንግሥቱ ግርማ ሞገስ ያለው ከርቀት እንጂ ቀርበው ሲመለከቱት ወደ መጨረሻው የተቃረበ ነው የሚመስለው፡፡ ሕንፃው ብቻ ሳይሆን ከዋንዛ የተሠሩ ምሰሶዎች ሳይቀሩ ተዳክመዋል፡፡ ከአንዳንዶቹ በስተቀር አብዛኞቹ ምስጥ እንዳልነበር አድርጎ አስቀርቷቸዋል፡፡ የተወሰኑት ደግሞ መሠረቱን የያዘው የታችኛው ክፍላቸው በመበላቱ ጣራውን በመደገፍ ፈንታ ተንጠልጥለው በተቃራኒው ሸክም ሆነውበታል፡፡ ከጣውላ የተሠራው የበረንዳው ክፍል በአንደኛው ጎን አልጌ በቅሎበታል፡፡ ጎብኚዎች እንዳይጠጉ አደገኛ ተብሎ በሽቦ የተከለለ ክፍልም አለ፡፡

እንደነገሩ ተደርጎ በዛገ ሽቦ የተከለለው ቦታ ወደ አንድ ጎን አጋድሏል፡፡ በአንዱ ጎን ያለው ከጣውላ የተሠራ መወጣጫ ደረጃም እንዲሁ ወደ አንድ ጎን ዘሟል፡፡ የቀን ውሎውን በቤተ መንግሥቱ ያደረገው አስጎብኚው አቶ ከድር ተማም ጎብኚዎቹን ወደ ኋላ ትቶ አደገኛ ተብሎ የታጠረውን ሽቦ አልፎ በመግባት ማብራሪያ መስጠት ጀመረ፡፡

አቶ ተማም በቤተ መንግሥቱ መሥራት ከጀመረ ስምንት ዓመታት ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከአንዳንድ አልተመዘገቡም በሚል ከሚያልፋቸው ጥያቄዎች በስተቀር ስለ ቤተ መንግሥቱና ጅማን ያስተዳድሩ ስለነበሩት ንጉሥ ያነበበውን አንድም ሳያስቀር በቃሉ ይዟል፡፡ ገለጻ መስጠት ሲጀምር በሬዲዮ ፕሮግራም የመጽሐፍ ትረካ እንደሚያቀርብ ሁሉ ድምፁ ለስለስ ይላል፣ በዜማዊ ቃና ሲያነበንብ አንድም አይሳሳትም፡፡ ከጎብኚዎች የሚሰነዘርለትን ጥያቄ በተለመደው ድምፅ መልስ ይሰጥና ወደ ትረካው ሲመለስ ዜማዊ ቃናው አብሮት ይመለሳል፡፡

በዕድሜው ማምሻ ላይ ከሚገኘው ያረጀው ሕንፃ ውስጥ ከአንዳንድ መገልገያ ዕቃዎች በስተቀር ምንም የሚታይ ነገር የለም፡፡ አቶ ከድርም ከሕንፃው በተጨማሪ ብዙ የሚያስጎበኘው ነገር የለም፡፡ ከበር ሲገቡ ከፊት ለፊት የሚቀበልዎ በትልቅ በርጩማ ላይ በፍሬም ተደርጎ የተቀመጠው የንጉሡ ፎቶግራፍ ነው፡፡ አቧራ የጠጣው የመስታወት ፍሬም ተሰነጣጥቋል፡፡ በውስጡ አቅፎ የያዘው ምስል በአንድ ወቅት ንጉሥ የነበሩን ባለታሪክ ቀርቶ ዘመድ ያለው የአንድ ተራ ሰው ፎቶግራፍ አይመስልም፡፡

አቶ ከድር በያዘው መጠቆሚያ ወደ ፎቶግራፉ እያመለከተ ‹‹ይህ ፎቶግራፍ በፓኪስታን የተሠራ ነው፡፡ ይህኛው የዋናው ኮፒ ሲሆን፣ ኦርጅናሉ በጅማ ሙዚየም ነው የሚገኘው፤›› አለ ዜማዊ የድምፁ ቃና ሳይለውጥ፡፡ አቶ ከድር ማነብነቡን ቀጠለ ‹‹አባጅፋር አባ ጉመል በ1852 ዓ.ም. ተወለዱ፡፡ ሦስት ስሞች ነበሩዋቸው፡፡ የልጅነት ስማቸው ቱሉ ነው፡፡ ቱሉ የተባሉት ቁመታቸው 2 ሜትር ከ10 ሴንቲ ሜትር ይደርስ ስለነበር፣ ደረታቸውም አንድ ሜትር ስፋት ስለነበረው ክብደታቸውም 150 ኪሎ ስለነበር ነው፤›› ነው ሲል ፎቶውን እየተመለከተ ስለ ንጉሡ ታሪክ ይተርክ ጀመረ፡፡

ከቱሉ ቀጥሎ በእስልምና ስማቸው ብለው ይጠሯቸውም ነበር፡፡ ሦስተኛ ስማቸው ደግሞ ቀላ ያለ ገጽታቸውን ተከትሎ የተሰጣቸው አባ ዲማ ነው፡፡ አባ ጅፋር የሥልጣን ስማቸው ሲሆን፣ ሥልጣንን የወረሱት ከአባታቸው ነው፡፡ አባ ጅፋር ጅማን ለ56 ዓመታት አስተዳድረዋል፡፡ ባደረባቸው ሕመም ለሰባት ዓመታት የአልጋ ቁራኛ ሆነው ቆይተው በ1926 ዓ.ም. በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

በሥልጣን ጊዜያቸው ይህንን ቤተ መንግሥት ከመገንባት ባለፈ ሌሎች ብዙ ነገሮችን አድርገዋል፡፡ ለሥልጣኔ የቀረቡም ነበሩ፡፡ አገሬው የጉድጓድ ውኃ ሲጠጣ ቀርከሃን እንደ ቱቦ በመቀጠም በአቅራቢያ የሚገኝ ውኃ በቧንቧ ጠልፈው ቤተ መንግሥት ድረስ እንዲገባ አድርገዋል፡፡ ከ139 ዓመታት በኋላ ዛሬ ምን ያህሉ የጅሬን ነዋሪዎች ንፁህ ውኃ ያገኛሉ? የሚለው ነገር ግን አሁንም አጠያያቂ ነው፡፡

የንጉሡ ጥረት ከእሳቸው ጋር አብሮ የጠፋ ይመስላል፡፡ ሌላው ቢቀር የአገሪቱ የታሪክ አካል የነበሩ ይገለገሉባቸው የነበሩ በሚገባ በቅርስነት እንኳ ተገቢው ጥበቃና እንክብካቤ አይደረግላቸውም፡፡ ያለ ሚስማር ከበሬ ቆዳ፣ ከእንጨት የተሠራው 2.50 በሁለት ሜትር ርዝመትና ስፋት ያለው የጠፈር አልጋቸው ተገቢው ጥገና እንኳን አልተደረገለትም፡፡ መሀሉ ከተቦጨቀ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ለዘመናት የከረመበት አቧራ እንኳን በወጉ አይጠረግም፡፡ የልጆቻቸው አልጋም እንዲሁ ተመሰቃቅሏል፡፡ ከአንድ እንጨት ተፈልፍለው የተሠሩ የልብስ ማስቀመጫ፣ የብርዝ መጥመቂያና ሌሎችም በተመሳሳይ አደጋ ውስጥ ከወደቁ ቆይተዋል፡፡

በአንድ ክፍል ውስጥ ከሚገኙ አልጋዎችና ከእንጨት የተሠሩ መገልገያዎች ውጪ ሌሎች የሚታዩ ንጉሡ ሠርተው ያለፉትን ታሪክ፣ መገልገያ ቁሳቁሶች፣ የጦር ሜዳ ውሎ የሚያሳዩ ነገሮች የሉም፡፡ እንደ አቶ ከድር ገለጻ መሰል ቁሳቁሶች ከቤተ መንግሥቱ ወጥተው ወደ ከተማው ሙዚየም እንዲገቡ የተደረገው ከ30 እና 40 ዓመታት በፊት ነው፡፡

የሚጠፋና የሚሰረቅ ነገር ባለመኖሩ የሚደረግለት ጥበቃ ይህን ያህል ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ጎብኚዎች በየግድግዳው ላይ ስማቸውን ሲያሰፍሩ ሀይ ባይ ያጡት፡፡  28 ክፍሎች ኦና ሆነው ይውላሉ ያድራሉ፡፡ ኦና ሆነው የሚውሉት ክፍሎች የነበራቸው የኤሌክትሪ መስመር በመበላሸቱ ጨለማ ውጧቸዋል፡፡ የሌሊት ወፍ ማደሪያ በመሆናቸው በኩስ ተበላሽተዋል፡፡

ሕንፃው መሀል ላይ ለመዝናኛነት ተብሎ የተተወው ሜዳማ ክፍል ሳይቀር ላልሆነ ተግባር እየዋለ ይገኛል፡፡ ይህ መጠነኛ ሜዳ ግራና ቀኙ በመኝታ ቤቶችና በማብሰያ ክፍሎች የተከበበ ሲሆን፣ የዛሬን አያድርገውና በረንዳዎቹ ደግሞ የንጉሡ ወዳጆቻቸው አረፍ ብለው የሚዝናኑበት ቦታ ነበር፡፡ አንደኛው ፎቅ ላይ ተቀምጠው  እንደ ግላዲያተር ሜዳው ላይ የሚታገሉ አገልጋዮቻቸውን ቁልቁል እየተመለከቱ ይዝናኑ ነበር፡፡

ትናንት መዝናኛ የነበረውን ይህንን መዝናኛ በአሁኑ ወቅት የቀዬው ሰዎች እንደ ኩሽና እየተገለገሉበት ይገኛሉ፡፡ ሪፖርተር ቦታው ተገኝቶ በጎበኘበት ወቅት በአንደኛው ጥግ ሦስት ቦታ ጉልቻ ተጥዶ ነበር፡፡ ‹‹የአካባቢው ሰዎች የመውሊድን በዓል እዚህ  ነበር ያከበሩት፡፡ ለዛ ፕሮግራም የተጣዱ ጉልቻዎች ናቸው፤›› አለ አቶ ከድር ጉዳዩን ቀለል አድርጎ፡፡

‹‹የኤሌክትሪክ መስመር አለው፡፡ ነገር ግን ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ ከአንዳንድ ክፍሎች በስተቀር አይሠራም፡፡ ተበላሽቷል፤›› ይላል ጨለማ የዋጣቸውን ኦና ክፍሎች ሲያስጎበኝ፡፡ ከዓመታት በፊት ብዙ ነገር ማለት የነበረው ቤተ መንግሥቱ ጭር ብሏል፡፡ አደገኛ ተብሎ ከተከለለው በረንዳ በተለየ የውስጥ ክፍሎቹ ያስፈራሉ፡፡ ቤተ መንግሥቱን ሕይወት እንዲዘራ ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት ሙከራዎች መደረጋቸውን አቶ ከድር ይናገራል፡፡

የመጀመርያው ዕድሳት የተደረገለትም በ1984 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ የተደረገለት ዕድሳት ታሪክ እንዳለው የአገር ቅርስ ሳይሆን እንደማንኛውም ግለሰብ ቤት አዲስ የማስመሰል ነገር ነበር የተደረገው፡፡ ኮርኒሱ የነበሩት ከዋንዛ የተሠሩ ጣውላዎች ተነስተው በምትኩ እንደነገሩ በሆነ ኮምፐርሳቶ ተተክቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ ኮምፐርሳቶው በተለያዩ ቀለሞች እንዲደምቅ ተደርጓል፡፡ በቀለም ቢደምቅም ቤተ መንግሥቱ ጉራማይሌ ገጽታ እንዲኖረውና በሁለት ዘመናት የነበሩ የሕንፃ ፋሽን ማሳያ እንዲሆን ያደረገው ነው፡፡ ፈገግ የሚያስብለው ነገር እሱም እያረጀ መሆኑ ነው፡፡

በተደረገው ዕድሳት ነባሮቹ ከእንግሊዝ የመጡ ቆርቆሮዎች በመናኛ ቆርቆሮዎች ነበር የተተኩት፡፡ ከተወሰነው የሕንፃው አካል በስተቀር አብዛኛው በሌላ ቆርቆሮ መተካቱን አቶ ከድር ሲናገር በሐዘን ነው፡፡ ከዚያ በኋላም ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ የዕድሳት ሙከራዎች ሳይሳኩ ቀርተዋል፡፡ በእነዚህ ፕሮጀክቶች የተጀመሩ ሥራዎች ሳይገባደዱ በጅምር ቀርተዋል፡፡ በቤተመንግሥቱ አንደኛው ክፍል ውስጥ ለታችኛው ክፍል እንደ ኮርኒስ ለላይኛው ደግሞ እንደ ወለል ያገለግሉ የነበሩ ጣውላዎች ተነቃቅለው እንዲሁ ከቀሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡      

‹‹ከ140 ዓመታት በፊት የተገነባው ቤተመንግሥቱ በጣም አርጅቷል፤›› ያሉት የጅማ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ኃላፊ ወ/ሮ ተወዴ ኑረዲን ናቸው፡፡ ጎብኚዎች አደገኛ ተብለው በተከለሉ በአንዳንድ የሕንፃው ክፍሎች ውስጥ እንዳይንቀሳቀሱ መታገዱን ተናግረዋል፡፡ ዕድሳት ለማድረግ በተለያዩ ጊዜያት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ መቅረቱን አምነዋል፡፡ ጉዳዩን የሚመለከተውም የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅትም እድሳት ለማድረግ ሌላ እንቅስቃሴ መጀመሩን፣ ለዚህም ከወር በፊት ጥናት መደረጉን ኃላፊዋ ተናግረዋል፡፡

የተጀመረው እንቅስቃሴ ምን ያህል ውጤታማ ሊሆን ይችላል የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡ የቤተመንግሥቱ ዕድሳት በዙሪያው ላሉ የመንደሩ ነዋሪዎች የመሠረተ ልማት ተደራሽነት ችግር ምላሽ የሚሰጥ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ጎብኚዎች የሚመላለሱበት ደረጃውን የጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎትና የትራፊክ ቁጥጥር መኖርም ወሳኝ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅና የሚስተጋቡ ሥጋቶች

ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ...

የመጨረሻ የተባለው የንግድ ምክር ቤቱ ምርጫና የሚኒስቴሩ ውሳኔ

በአገር አቀፍ ደረጃ ደረጃ የንግድ ኅብረተሰቡን በመወከል የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ...

ሚስጥሩ!

ጉዞ ከካዛንቺስ ወደ ስድስት ኪሎ፡፡ የጥንቶቹ አራዶች መናኸሪያ ወዘናዋ...