Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለምን እንደሚሰደዱ ጥናት ተጀመረ

 ዜጎች በሕገወጥ መንገድ ለምን እንደሚሰደዱ ጥናት ተጀመረ

ቀን:

  • ለጥናቱ ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዟል

ለቤት ሠራተኝነት ወይም ለተለያዩ የሥራ መደቦች ከኢትዮጵያ ክልሎች ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች፣ እንዲሁም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና ሌሎችም አገሮች የሚሰደዱ ዜጎች በሕጋዊ መንገድ መሄድ ትተው ለምን ሕገወጥ መንገድ እንደሚመርጡ ለማወቅ ጥናት ተጀመረ፡፡

ጥናቱን የሚያስጠናው የምሥራቅና የደቡብ አፍሪካ ማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ድርጅት ሲሆን፣ ጥናቱን የሚያጠኑት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ከተለያዩ ቦታዎች የተውጣጡ ምሁራን በሦስት ቡድኖች ተከፋፍለው መሆኑ ታውቋል፡፡ ሦስቱም ቡድኖች ለሚያደርጉት ጥናት ለእያንዳንዳቸው አንድ መቶ ሺሕ ፓውንድ፣ በድምሩ ሦስት መቶ ሺሕ ፓውንድ ወይም ከ11 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙም ታውቋል፡፡

ጥናቱ ‹‹ማይግሬሽን ኢንዱስትሪ ጀንደር ኤንድ ጄኔሬሽን፣ ኢንካም ኤንድ ሬሚታንስስ ኢትዮጵያ›› የሚባል መሆኑም ተገልጿል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የማይግሬሽን ኢንዱስትሪ የኢትዮጵያ ቡድን አስተባባሪና አጥኚ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፈቃዱ አዱኛ (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ የጥናቱ መሠረት በአገር ውስጥ፣ ከክልል ወደ አዲስ አበባና ከኢትዮጵያ ወደ ሌሎች አገሮች ዜጎች ለምን በሕገወጥ መንገድ መሰደድን እንደሚመርጡ መሆኑን አጥኚው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ከአራት መቶ በላይ ሕጋዊ ኤጀንሲዎች እያሉ፣ ዜጎች ሕጋዊ ያልሆኑ ደላላዎችን ለምን እንደሚመርጡ፣ ሕጋዊ ያልሆኑት ደላሎችም እንዴት መመልመል እንደሚችሉ ለማወቅ የሚደረግ ጥናት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ አንድ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሌላ አገር የሚሰደድ ዜጋ፣ ከአርሶ አደር ቤተሰቡ እንዴት ገንዘብ ማግኘት እንደሚችልና ቤተሰቡም ያለምንም መጠራጠር በሬውን ወይም ያለችውን ቅርስ በመሸጥ መስጠት እንደሚችል፣ ሕጋዊ ያልሆኑ ደላሎችም ማሳመን እንደሚችሉ ለበርካታ ዓመታት የታየና የሚታወቅ ነገር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቤተሰብ አባሉ መሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ ከኢትዮጵያ ተነስቶ በተለይ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እስከሚደርስ ድረስ ያለውን የጉዞ መስመር ሕጋዊ ያልሆኑት ደላሎች እንዴት እንደሚዘረጉትም ማወቅ አንዱ የጥናት አካል መሆኑን የጠቆሙት አጥኚው፣ ይህ ዓይነት አሠራር ‹‹ማይግሬሽን ኢንዱስትሪ›› ወይም ‹‹ማይግሬሽን ኢንፍራስትራክቸር›› እንደሚባልም አስረድተዋል፡፡

ከ37 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያውያን ምሁራን በኢትዮጵያ የተመሠረተው የምሥራቅና ደቡብ አፍሪካ የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናት ድርጅት ብዙ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸው፣ በተለይ በኢትዮጵያ አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰውን የዜጎችን ስደት በሚመለከት መሥራት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ለጥናቱ መጀመሪያ የሚሆን ገንዘብም በሰሴክስ ዩኒቨርሲቲ በኩል፣ ከእንግሊዝ መንግሥት ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር (ዲኤፍአይዲ) መገኘቱን ጠቁመዋል፡፡

‹‹ስደትን ሕገወጥ ካልነው ነገሩን ማስተካከል ይከብዳል፤›› የሚሉት አጥኚው ደላሎችን፣ ‹‹በሕግ የማይተዳደሩ ብለን እንጠራቸዋለን›› በማለት፣ ድርጊታቸውን ከመክሰስና ወንጀል ከማድረግ ባለፈ፣ ችግሩን በመረዳት እንዴት መሠራት እንዳለበት ለመምከርና ለፖሊሲ አውጪው አካል በማቅረብ የመፍትሔው አካል ለማድረግ ጥናቱ ጠቃሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከ400 በላይ ሕጋዊ ኤጀንሲዎች እያሉ በቀን በሕገወጥ የሚፈልሱ ዜጎች ሕጋዊ መንገድ ከሚጠቀሙት እጥፍ መሆኑ እየታወቀ፣ ‹‹ሕገወጥ ደላሎች›› በማለት ለመክሰስና አስሮ ለማስተካከል መሞከር ነገሩ ድብቅነትና ሚስጥራዊ መሆን ስለሚጀምር ጥፋቱ የበለጠ እንደሚያደርገው ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ተቀራርቦ ነገሮችን ማስተካከል የተሻለ ውጤት የሚያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የሚሰደዱ ዜጎች ሕጋዊ ያልሆኑ ደላሎችን የሚመርጡት ለምን እንደሆነ የጥናታቸው ዋና መነሻ ሐሳብ መሆኑን የገለጹት አጥኚው፣ የሚያስከፍሉት ገንዘብ ትንሽ ስለሆነ ነው? ሌሎች መሥፈርቶችን ስለማይጠይቁ ነው? ወይስ ደላሎቹ ስላልተማሩና ለወገን ግድ ስለሌላቸው? ለምንድነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ከታች የችግሩ ሰለባ ከሆኑት ቤተሰቦችና ሕጋዊ ካልሆኑ ደላሎች በጥናት የሚያገኙትን ውጤት ለመንግሥት በማቅረብ መፍትሔ ማምጣት ተቀዳሚ ተግባራቸው መሆኑንም አክለዋል፡፡

ሕጋዊ ያልሆኑ ደላሎችን ‹‹ወንጀለኞች›› በማለት ከሚደበቁ ‹‹ምን ቢደረጉ ይሻላል? መደገፍስ ካለባቸው እንዴት ነው መደገፍ ያለባቸው? እንዴትስ ማስተማር ይቻላል? ብለው ከፖሊሲ ቀረፃ በፊት መቅደም ያለበት ዕውቀት መፍጠር በመሆኑ፣ ጥናት ለማጥናት የተነሱትም ምላሽ ለመስጠት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ መንግሥት በሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች አካባቢዎች በዜጎች ላይ የደረሰውን አስከፊ ነገር ተመልክቶ ለአራት ዓመታት ጉዞውን ያገደ ቢሆንም፣ ሕገወጥ ጉዞው ግን ልክ እንደ መደበኛው ቀጥሎ መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም በተቀናጀ ሁኔታ ሠርቶ ነገሮቹን ማስተካከል ተገቢ በመሆኑ ሁሉንም ነገር ለማስተካከል የሚረዳ ውጤት ለማምጣት እየጣሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በችግሩ ዙሪያ የሚገኙ የጥናት ውጤቶችን ለመንግሥት በማቅረብ፣ ችግሮቹ የሚፈቱበትን ሁኔታ ለማምጣትም ጭምር መሆኑንም አክለዋል፡፡

በሌላ ቡድን ውስጥ ሆነው ከክልሎች ወደ አዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች፣ እንዲሁም ወደ ውጭ አገሮች የሚሰደዱ (የሚፈልሱ) ዜጎች በቤተሰቦቻቸው ላይ የሚያመጡትን ለውጥ በሚመለከት ጥናት የጀመሩት ደግሞ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዳምነሽ አጥናፉ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ እሳቸው እንደገለጹት፣ ከአንድ ቤተሰብ ውስጥ ሴት ወይም ወንድ ቢሰደድ ወይም የተሻለ ሥራ ፍለጋ ወደ ሌሎች አገሮች ቢሄድ፣ የትኛው ማለትም ‹‹ሴቷ ወይስ ወንዱ›› በቤተሰቡ ውስጥ የተሻለ ለውጥ እንደሚያመጡ ማወቅ፣ ዋነኛ የጥናቱ መሠረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የቤተሰቡ አካል የሚልከውን ገንዘብ በተሻለ ሁኔታ ጥቅም ላይ የሚያውለው ‹‹አባት ወይስ እናት›› ማንኛቸው እንደሆኑ የመለየትና የተላከው ገንዘብ በተለይ ሴት ልጆች ወደ ትምህርት ቤት እንዲሄዱና ወላጅና ልጆች ተመካክረው በሕይወታቸው ላይ ስለሚያመጡት ለውጥ እንደሚያጠኑም አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ቤተሰቡ የተሰደደና ያልተሰደደ ቤተሰብ ያላቸውን የኑሮ ሁኔታ በማነፃፀር የሚላከውን ገንዘብ ጥቅምና በቤተሰብ ላይ ያመጣውን ለውጥም እንደሚያጠኑ ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ በሕጋዊ መንገድ የሚሰደዱና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚሰደዱ የቤተሰብ አባላት ላይ ጥልቅ ጥናት በማድረግ፣ ጥቅሙንና ጉዳቱን በመለየት መንግሥት የፖሊሲው አካል እንዲያደርገው የጥናት ውጤቱን እንደሚያቀርቡም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...