Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቱሪዝም ድርጅት ኃላፊ ‹‹ከሕግ ውጪ ሁለት ደመወዝ›› በመቀበልና በአስተዳደር ድክመት እንዲከሰሱ ተጠየቀ

የቱሪዝም ድርጅት ኃላፊ ‹‹ከሕግ ውጪ ሁለት ደመወዝ›› በመቀበልና በአስተዳደር ድክመት እንዲከሰሱ ተጠየቀ

ቀን:

  • ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከባድ ወቀሳ ቀርቦበታል

የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅትን ላለፉት ዘጠኝ ወራት በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የቆዩት አቶ ዮሐንስ ጥላሁን፣ መንግሥት ከመደበላቸው ደመወዝ በተጨማሪ በየወሩ ስምንት ሺሕ ዶላር ከሕግ ውጪ ሲቀበሉ እንደነበር በማስታወቅ በሕግ ሊጠየቁ ይገባል ሲል የድርጅቱ ቦርድ ጥያቄ አቀረበ፡፡

ሪፖርተር እንዳረጋገጠው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በጻፉት ደብዳቤ፣ አቶ ዮሐንስ ከመንግሥት ዕውቅና ከሕግ ውጪ በሆነ መንገድ ሁለት ደመወዝ ሲቀበሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ቦርዱ የማያውቀውና ሕገወጥ በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ፣ የባከነው ሀብትም በሕግ እንዲጠየቅ፤›› በማለት አሳስበዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ በመንግሥት ከሚከፈላቸው ደመወዝና ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ለተቋሙ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት ከሚሰጠው ድጋፍ ስምንት ሺሕ ዶላር ሲከፈላቸው ነበር የሚል ውንጀላ ቀርቦባቸዋል፡፡

የቦርድ ሰብሳቢው በደብዳቤያቸው በተቋሙ አመራር ከፍተኛ የአሠራር ችግር እንዳለና የሕግ ጥሰት መኖሩን ጠቅሰው፣ ‹‹አስቸኳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ፣ አሠራር ተጥሶ የተፈጸሙና እየተፈጸሙ ያሉ ክፍያዎች በሕግ እንዲጠየቁ፤›› በማለት ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቀዋል፡፡ 

በቱሪዝም ድርጅት ውስጥ ስለሚፈጸሙ አስተዳደራዊና ሌሎች ያልተገቡ ተግባራት የካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. በተካሄደው የቦርዱ መደበኛ ስብሰባ ወቅት የቀረቡ መረጃዎች በተቋሙ የሚፈጸሙ ድርጊቶችን በማቅረባቸው የተነሳ፣ ጉዳዩ በአስቸኳይ እንዲጣራ ኮሚቴ መሰየሙን ቦርዱ ለሚኒስቴሩ ከጻፈው ደብዳቤ ለመረዳት ተችሏል፡፡

‹‹የቀረቡት መረጃዎች እጅግ አስደንጋጭና የሕግ ተጠያቂነት የሚያስከትሉ ናቸው፤›› ያለው የአቶ ተወልደ ደብዳቤ፣ ሐሙስ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት በአጣሪው ኮሚቴ የቀረበውን ሪፖርት አዳምጦ፣ ስምንት ነጥቦች ላይ ያጠነጠኑ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ጠቅሷል፡፡

ከውሳኔዎቹ ውስጥም እንዲህ ያሉ አስተዳደራዊና በሕግ የሚያስጠይቁ ጥሰቶች ለወራት ሲፈጸሙ ከቦርዱ ‹‹ሚስጥር ተደርገው መበደቃቸው›› እንዳሳዘነው በማስታወቅ፣ በሚኒስቴሩ የቀጥታ ትዕዛዝ ከመንግሥት ሹመት፣ ደመወዝ፣ ጥቅማ ጥቅም በተጨማሪ ከሰኔ 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ለዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮሐንስ ጥላሁን ከዩኤንዲፒ የተቋሙ አቅም ግንባታ ፕሮጀክት እንዲከፈል እየተደረገ ያለው 8,000 ዶላር ሁለተኛ ደመወዝ የቦርዱ ዕውቅና የሌለው በመሆኑ በአስቸኳይ እንዲቋረጥ፤›› በማለት የባከነው ሀብትም በሕግ እንዲጠየቅ ለሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡

 በአጣሪ ከሚቴው አማካይነት ከተካሄደው የማጣራት ሥራ በኋላ ለቦርዱ በቀረበው ሪፖርት መሠረት አቶ ዮሐንስ፣ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ምሕረት የቻለ (ዶ/ር) እንዲሁም ሌሎች የድርጅቱ ኃላፊዎች አንዱ በሌላው ላይ ያቀረቧቸው ቅሬታዎችና ውንጀላዎች ተካተዋል፡፡

አቶ ዮሐንስ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው የሰጠኋቸውን ሥራ አይሠሩም፣ ውጤት አላመጡልኝም በማለት ቅሬታ ያቀረቡባቸው ሲሆን፣ በተቋሙ ውስጥ ቡድንተኝነት መኖሩን፣ የተቋሙ ሰነዶች ያላግባብ ለሦስተኛ ወገን ይደርሳሉ የሚሉ ቅሬታዎችን ከማቅረባቸውም በላይ፣ እንዲሰናበቱ ያደረጓቸው ሠራተኞች ‹‹በሚኒስትሮች ጣልቃ ገብነት›› ሳይሰናበቱላቸው እንደቀሩ መግለጻቸውን ሪፖርተር ያገኘው የአጣሪ ኮሚቴው ሰነድ አሥፍሯል፡፡

በምክትል ሥራ አስፈጻሚው ምሕረት (ዶ/ር) በኩል አቶ ዮሐንስ ላይ ከቀረቡት ውስጥ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከተቋም ይልቅ ‹‹በግል ጥቅም ላይ ያተኮሩ›› ስለመሆናቸው በማሳያ የተደገፉ ውንጀላዎች ተጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ከመንግሥት 14 ሺሕ ብር፣ ከዩኤንዲፒ 8,000 ዶላር፣ ሁለት ደመወዝ ይቀበላሉ፣ በግል መሬት ኢንቨስተሮችን ያደራድራሉ፣ ያልተገቡ ጉዞዎችን ያደርጋሉ፤›› የሚሉትን ጨምሮ፣ ከሕግ ውጪ የግዥ ተግባራት እንዳሉ ሲገልጹም የጣት አሻራ መሣሪያዎችን፣ የተሽከርካሪ ጂፒኤስ፣ እንዲሁም የ‹‹Cloud Based Office 365›› ሶፍትዌር ከተመሳሳይ ተቋም እንዲገዛ መደረጉ፣ ለሁለት የግል ሬቶራንትና ስፓ ድርጀቶች የባንክ ድጋፍ እንዲደረግላቸው ማድረግ በአቶ ዮሐንስ በኩል የታዩ ጥሰቶች ስለመሆናቸው ተጠቅሷል፡፡

እንዲህ ያሉ ጥፋቶችን ያየው የቱሪዝም ቦርድ ድርጅት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ላይም ከባድ ወቀሳውን ከማቅረቡም በተጨማሪ፣ አቶ ዮሐንስ ከእንግዲህ በአመራርነታቸው ሊቀጥሉ እንደማይገባና ከየካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮም ከሥራ እንዲሰናበቱና በሕግም እንዲጠየቁ መወሰኑን ለባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ሒሩት ወልደ ማሪያም (ዶ/ር) ሪፖርተር ስለአቶ ዮሐንስ ከሥራ መሰናበት ጠይቋቸው፣ ‹‹የደረሰን ነገር የለም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዮሐንስም በስልክ ተጠይቀው ከቦታቸው እንዲነሱ ስለመባሉ የሚያውቁት እንደሌለና በሥራ ገበታቸው ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ሪፖርተር ለኅትመት ወደ ማተሚያ ቤት እስከገባበት እስከ ዓርብ የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በሥራ ገበታቸው ላይ እንደነበሩ ተረጋግጧል፡፡

አቶ ዮሐንስም ሆኑ ምክትላቸው ምሕረት (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ወር ላይ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሹመት እንደተመደቡ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ አቶ ዮሐንስ ከዚህ ቀደም በጄኔራል ኤሌክትሪክ ኢትዮጵያ፣ እንዲሁም በግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ውስጥ መሥራታቸው ይታወሳል፡፡ ምሕረት (ዶ/ር) በበኩላቸው በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በረዳት ፕሮፌሰርነት ማዕረግ መምህር የነበሩ ሲሆን፣ ከመሾማቸው በፊት በተለያዩ የቱሪዝም ሥራዎች ውስጥ ተሳትፎ እንደነበራቸው ግለ ታሪካቸው ይገልጻል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ሔኖክ ያሬድና ታምሩ ጽጌ አስተዋጽኦ አበርክተዋል)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...