Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናየኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተተኪ ለመሰየም እየተዘጋጁ ነው

የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች የጠቅላይ ሚኒስትሩን ተተኪ ለመሰየም እየተዘጋጁ ነው

ቀን:

በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ለግንባሩ ሊቀመንበርነት ለመወዳደር ሊቃነ መናብርትን ለመምረጥ ስብሰባ ተቀምጠው ከርመዋል፡፡ ኦሕዴድ በአስቸኳይ የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ የአመራር ሽግሽግ ሲያደርግ፣ ብአዴን የነበሩትን አስቀጥሏል፡፡ ደኢሕዴን ግን አለየለትም፡፡ ሕወሓት ደግሞ ተተኪ እንደማያቀርብ በስፋት ተነግሯል፡፡ በኢሕአዴግ አሠራር መሠረት የግንባሩ ሊቀመንበር ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል፡፡

ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ሰሞኑን አዲስ ሊቀመንበር መርጧል፡፡ የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ሐሙስ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. የፓርቲው ሊቀመንበር እንዲሆኑ ተመርጠዋል፡፡

ከዚህ በፊት የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ለማ መገርሳ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ባካሄደው ድንገተኛ ስብሰባ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሆኑ መርጧል፡፡

- Advertisement -

አቶ ለማ ለኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት፣ ኦሕዴድ በፌዴራል ደረጃ አመራር ለመውሰድ የሕዝቡና የድርጅቱ ጥያቄ ነበር፡፡ ‹‹ታሪክ የሚሰጠንን ዕድል በመጠቀም ለክልሉ ሕዝብም ሆነ ለአገሪቱ ጠቃሚ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ ስላገኘው የአመራር ሽግሽግ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡ በፌዴራል ደረጃ የኃላፊነት ዕድል የሚያገኝ ሰው ሁሉንም የአገሪቱን ብሔር ብሔረሰቦች በአንድ ዓይን የሚያይ እንደሚሆን ጠቁመዋል፡፡

የሕዝብ ክብር የሚመጣው እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነ አቶ ለማ ጠቁመው፣ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚም ይህንን በጥልቀት በማየት የክልሉ አመራርና ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግባባትና በመተማመን ውሳኔ ላይ መድረሱን አስረድተዋል፡፡

‹‹በፌዴራል መንግሥት ውስጥ ሥፍራ ሊኖረን ይገባል ስንል የክልላችንን ጉዳይ በመርሳት ሳይሆን፣ በታሪክ ውስጥ የተገኘውን ዕድል የሕዝብ ክብር በጠበቀ ሁኔታ እንዴት መጠቀም ይኖርብናል የሚለውንም በጥልቀት ማዕከላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፤›› ብለዋል፡፡

ዓብይ (ዶ/ር) የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው ሊመረጡ የቻሉት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር እንዲሆኑ ኦሕዴድ በዕጩነት ለማቅረብ በመፈለጉ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከፓርቲው ሊቀመንበርነትና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመውረድ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ ዶ/ር ዓብይ የፓርቲው ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ የሚሉ ድምፆች ከየአቅጣጫው እየተሰሙ ነው፡፡

ዶ/ር ዓብይ በኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን አጋሮ አካባቢ እንደተወለዱ የሕይወት ታሪካቸው የሚያስረዳ ሲሆን፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በኮምፒዩተር ኢንጂነሪንግና ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እንዳገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰላምና ደኅንነት ጥናት የዶክትሬት ዲግሪ እንዳገኙ ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡

በአርባዎቹ መጀመርያ ዕድሜ ላይ የሚገኙት ዶ/ር ዓብይ፣ ኦሕዴድን የተቀላቀሉት በ1980ዎቹ መጀመርያ ላይ ነው፡፡ ከፖለቲካ ተሳትፎአቸው በተጨማሪ በወታደራዊ መስክ ልምድ እንዳላቸው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የመረጃ መረብና ደኅንነት ኤጀንሲ መሥራችና ዋና ዳይሬክተር፣ እንዲሁም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በብዙኃኑ የአገሪቱ ሕዝቦች ዘንድ ተተኪው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ የሚል ግምት እየተሰጣቸው ከሚገኙ ግለሰቦች መካከል ቀዳሚውን ሥፍራ የሚይዙት ዶ/ር ዓብይ፣ ተቀራራቢ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ የሚጠበቀው ከብአዴን ሊቀመንበር አቶ ደመቀ መኮንን ሊሆን እንደሚችል ይነገራል፡፡

አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና የኢሕአዴግ ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ከመሆናቸውም በላይ፣ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ይገኛሉ፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባውን ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም. እንደተጀመረ መዘገባችን የሚታወስ ሲሆን፣ ከአንድ ወር በኋላ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ወደ ስብሰባ ሲገባ በክልሉ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት የሚያስችል ውሳኔ ያስተላልፋል ተብሎ ሲጠበቅ ነበር፡፡ ፓርቲው ጠንካራና ለየት ያሉ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ በፓርቲው አመራሮች በተደጋጋሚ ጊዜ ቢነገርም፣ በኃላፊነት ቦታ ባሉ አመራሮች ላይ የሥልጣን ሹም ሽር አለመደረጉን፣ የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዓለምነው መኮንን ዓርብ የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

አቶ ዓለምነው፣ ‹‹በአገራችን አሁን ያለው ችግር የተፈጠረው እስካሁን በመጡ ለውጦች ማለትም በማኅበራዊና በኢኮኖሚ ልማቶች፣ በዴሞክራሲ ግንባታ ሒደት፣ በመልካም አስተዳደር ለውጥ ሒደት ላይ በመመሥረት ነው፡፡ ይህን የለውጥ ፍላጎት ስኬታማ ማድረግ የሚቻለው ልማትን በማፋጠንና መልካም አስተዳደር በማስፈን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን በማረጋገጥ እንጂ አንድን ሰው በማንሳት በምትኩ ሌላ ሰው በመቀየር አይደለም፡፡ ስለዚህ ብአዴን ያየው በዚህ መንፈስ ነው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለአንድ ወር ያህል ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅም፣ ባለ አምስት ነጥብ ወሳኔዎችን አስተላልፏል፡፡ የመጀመርያው የውሳኔ ሐሳብ፣ በድርጅቱም ሆነ በሕዝቡ የሚታዩ የፀረ ዴሞክራሲ ተግባራትን በፅናት መታገል ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው፣ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተቋማት ማለትም የሕዝብ ምክር ቤቶች፣ ሚዲያዎች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት፣ የእንባ ጠባቂ፣ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ የፍትሕ አካላት፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና አባሎቻቸው ለዴሞክራስያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚጠበቅባቸውን ተልዕኮ እንዲወጡ ለማስቻልና መሠረታዊ ለውጥ እንዲያመጡ በትኩረት እንደሚሠራ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

በሁለተኛው የውሳኔ ሐሳብ የክልሉንና የአገሪቱን ሰላምና የሕግ የበላይነት ከማረጋገጥ አኳያ ክፍተቶች እንደነበሩ፣ እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

ሦስተኛው ደግሞ ሙስናና ብልሹ አሠራርን የተመለከተ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡን የትግሉ አጋር በማድረግ የተጠናከረ ትግል ለማካሄድ መወሰኑን አስታውቋል፡፡ ኅብረተሰቡን ያማረሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ጉድለቶች፣ የፍትሕ መዛባት፣ የመሠረታዊ ሸቀጦች አቅርቦትና ሥርጭት ችግር፣ ሕገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድ፣ ከመሬት ወረራና ከግብር ሥርዓቱ ጋር የሚታዩ ችግሮችን ለመፍታት የእርምት ዕርምጃ እንደሚወሰድ የፓርቲው መግለጫ አመልክቷል፡፡

አራተኛው የብአዴን የውሳኔ ሐሳብ የክልሉ ሕዝብ እንደ ሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸው መረጋገጥ እንዳለበትና ከዚህ ያፈነገጡና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን የሚያጓድሉ ማናቸውም ተግባራት አገራዊ አንድነትን እንደሚጎዱ መገምገሙን፣ እነዚህን ዝንባሌዎች ያለምንም ማመንታት መታገል እንደሚገባ መወሰኑን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

አምስተኛውና የመጨረሻው የብአዴን የውሳኔ ሐሳብ የትራንስፎርሜሽኑን አጀንዳና የፀረ ድህነት ትግሉን የተመለከተ ሲሆን፣ የተጀመረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ሥራዎች ችግሮች እያጋጠሙ መሆኑን መግለጫው ጠቁሟል፡፡ ይህን ችግር በመፍታት የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የማረጋገጥ ጉዳይ ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ተሰጥቶት እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡

ብአዴን በክልሉ የተጀመሩ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚና የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ከዳር እንዲደርሱ የክልሉና የአገሪቱ ሕዝብ፣ የድርጅቱ አባላት፣ የክልሉ አርሶ አደሮች፣ የአገሪቱና የክልሉ የፀጥታ አካላት፣ የክልሉ ወጣቶች፣ ውጭ የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ የድርጅቱ እህትና አጋር ድርጅቶችና የተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከፓርቲው ጎን ተሠልፈው እንዲሠሩና የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፏል፡፡

ብአዴን በሚቀጥለው ሳምንት ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ አቶ ደመቀ መኮንን ለሊቀመንበርነት በዕጩነት ያቀርባቸዋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡

ሦስተኛው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሲሆን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ከዚህ ቀደም ለ35 ቀናት አድርጎት በነበረው ስብሰባ ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤልን (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡ እሳቸው በአሁኑ ወቅት የሕወሓት ሊቀመንበርና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነትም የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ሥራ በኃላፊነት እንዲመሩ መወሰኑ አይዘነጋም፡፡ በዚህም ምክንያት እሳቸው ለተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትርነት ሊቀርቡ ስለማይችሉ፣ ሕወሓት በኢሕአዴግ ምክር ቤት ያለውን 45 ድምፅ ለሚፈልገው የአባል ድርጅት ተወዳዳሪ ይሰጣል ተብሎ ይታሰባል፡፡

አራተኛው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ፓርቲ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሲሆን፣ የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ከጀመረ ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ የፓርቲው ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም በድርጅቱ የሥልጣን መልቀቅ ጥያቄያቸው ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ዓርብ የካቲት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ምሽት ድረስ የፓርቲው ዋናና ምክትል ሊቀመንበር አልተመረጡም ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለመተካት በኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት የሚሳተፉ 180 አባላት (እያንዳንዱ ድርጅት 45 ተወካዮች አሉት)፣ ለግንባሩ ሊቀመንበርነት ድምፅ ይሰጣሉ፡፡ በተገኘው ውጤት መሠረት ደግሞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ይሰየማል፡፡ ይህም ሒደት በቅርቡ ይጀመራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...