Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርትየመቐለ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ጉዞ

የመቐለ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ውድድር ጉዞ

ቀን:

ስፖርት ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የማስተሳሰር ትልቅ አቅም አለው፡፡ ስፖርታዊ በዓለም ዙሪያ ሲዘጋጁ ኅብረተሰቡ እንዲገናኝ ሰፊ ዕድል ከመፍጠራቸውም በተጨማሪ የተለያዩ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ትውፊታዊ የልምድ ልውውጦች የበለጠ እንዲቀሳሰሙ መንገድ ይፈጥራሉ፡፡ በስፖርቱም ተተኪዎችን ለማፍራት አስተዋጽኦውም የጎላ ነው፡፡ ከዚህ መሠረተ ሐሳብ የሚነሳው ዘጠነኛው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ከሰኔ 24 እስከ ሐምሌ 2 ቀን 2010 ዓ.ም. በመቐለ ዩኒቨርሲቲ ይካሄዳል፡፡ አዘጋጅነቱ ከኡጋንዳ የተቀበለው የመለ ዩኒቨርሲቲ በ11 የስፖርት ዓይነቶች ውድድሩን ያከናውናል፡፡ ከአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎቻቸውን ወክለው የሚመጡ ከ2,500 በላይ ተወዳዳሪዎች ይታደማሉ፡፡ ዶ/ር ከሳቴ ለገሰ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዳይሬክተርና በስፖርት ሳይንስ መምህር ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የስፖርት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንትም ናቸው፡፡ በመቐለ ስለሚዘጋጀው የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድር ዝግጅት ዳዊት ቶሎሳ አነጋግሯቸዋል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ዘጠነኛውን የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርታዊ ውድድርን ለማዘጋጀት  ዕድሉን እንዴት አገኛችሁ?

ዶ/ር ከሳቴ፡- ውድድሩን ለማዘጋጀት ከኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ፈቃድ አገኘን፡፡ ከዚያም በስምንተኛ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ላይ ካምፓላ በመገኘት ውድድሩን ማዘጋጀት እንደምንፈልግ፣ ዩኒቨርሲቲያችን ስላለው መሠረተ ልማት ለመድረኩ ባቀረብነው መሠረት ከናይጄሪያ፣ አልጄሪያና ጋና ተሽለን ስለተገኘን የማዘጋጀት ዕድሉን ማገኘት ችለናል፡፡  

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- ይኼን ውድድር በኢትዮጵያ ለማሰናዳት የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ያደረገው እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?

ዶ/ር ከሳቴ፡- የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ውድድሩን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት ሰፊ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ በዚህም መሠረት በአፍሪካ ደረጃ ቀደም ብሎ ከተሰናዱ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር የተለያዩ ልምዶች ለመቅሰም ሞክረናል፡፡ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር የተለያዩ ኮሚቴዎችን በማቀናጀት ዝግጅቱን ለማጠናቀቅ በሰፊው እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡ በመለ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አንድ ዓመት ስንዘጋጅ ቆይተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በዩኒቨርሲቲው ለሚከናወነው ውድድር ምን ዓይነት ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል?

ዶ/ር ከሳቴ፡- በአጠቃላይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥና ውጭ የሚደረጉ ሁነቶች ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ከዶርሚተሪ ከምግብ፣ ከመረጃና ቴክኖሎጂ ጋር በተያያዘ ኮሚቴ በማቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል፡፡  

ሪፖርተር፡- ለውድድሩ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተወጣጡ ከ12 በላይ አገሮች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ተብሏል፡፡ ከተወዳዳሪው ቁጥር ብዛት አንፃር እንዴት ማስተናገድ ይችላል?

ዶ/ር ከሳቴ፡- በማንኛውም ዓለም አቀፍም ሆነ አህጉር አቀፍ ውድድሮች ላይ የበጎ ፈቃደኞች ሚና ትልቅ ነው፡፡ በተወዳዳሪው ቁጥር አንፃር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ለማግኘት ከባድ ነው፡፡ ስለዚህ እኛም የተለያዩ ልምዶችን 15ኛው የዓለም ዩኒቨርሲቲዎች ውድድር ካስተናገደችው ደቡብ ኮሪያ ለመቅሰም ሞክረናል፡፡  ኢትዮጵያ በተሳተፈችበት ውድድር ላይ ስምንት ሺሕ በጎ ፈቃደኞች ነበሩ፡፡ ሻምፒዮናው እንዲሳካ የበጎ ፈቃደኞች ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡ ስለዚህ እኛም ያንን መንገድ በመከተል ከደቡብ ኮሪያ በጎ ፈቃደኞች ማኅበር ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ ከዩኒቨርሲቲው ለተውጣጡ 600 በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች፣ እንዲሁም ከከተማው ነዋሪና ከቀይ መስቀል በማቀላቀል የተወጣጡ 200፣ 200 ግለሰቦች ሥልጠና እንዲሰጣቸው ተደርጓል፡፡ ሥልጠናውንም ከሥፍራው በመጡ ባለሙያዎች ሲሰጥ ቆይቷል፡፡ ሦስት ጊዜ መጥተው ሁለት ሳምንታት የፈጀ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የበጎ ፈቃደኞች ሥልጠና ምን ይመስላል?

ዶ/ር ከሳቴ፡-  ሥልጠናው በተለያዩ ጊዜያት እስከ ሦስት ቀናት ሲሰጥ ነበር፡፡ የተሰጠው ሥልጠናም ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ሲሆን፣ ልዑካን ቡድን ከኤርፖርት ጀምሮ እንዴት መቀበል እንደሚገባቸው፣ ምግብ ቤት አካባቢ የሚሰጡት ድጋፍ፣ በስታዲየም አካባቢ ጭምር በቂ የሆነ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ይኼም ሥልጠና ከአስተሳሰብ ለውጥ ጀምሮ ሲሰጣቸው ቆይቷል፡፡ በተጨማሪም ይኼ ሥልጠና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የበጎ ፈቃደኝነት ትርጉም የበለጠ እንዲዘምን ያደርጋል፡፡ በውድድሩ ላይ የሚገኙት ወጣቶች ዓለም አቀፍ የበጎ አድራጎትን ዕውቀት ይቀስማሉ፡፡ ውድድሮች ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች የበጎ አድራጊ ወጣቶች ሚና ትልቅ ነው፡፡ ስለዚህ ይኼ ሥልጠና ለሌሎች ተማሪዎች የበለጠ ልምድ ማካፈል ያስችላል፡፡

ሪፖርተር፡- የስታዲየሞችና የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች ዝግጅት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ከሳቴ፡- በቂ ዝግጅት እያደረግን ነው፡፡ ለምሳሌ ለእግር ኳስ ስፖርት በተለያዩ የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ውስጥ ስታዲየሞች ተገንብተዋል፡፡ ከዚያ ውጭ ሦስተኛ ስታዲየም  ቀደም ብሎ መቐለ ከተማ ላይ ግንባታው የተጀመረው ስታዲየም ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ስታዲየሙን የመቐለ ከተማ ለዩኒቨርሲቲው በሰጠው መሠረት እሱም ለውድድሩ በተወሰነ መጠን ዝግጁ ነው፡፡ በተጨማሪ በአንድ ሜዳ ላይ ሦስት የጨዋታ ዓይነቶችን ማስተናገድ የሚችሉ መወዳደሪያ ቦታዎች በአራቱም ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ውስጥ ተገንብተዋል፡፡ በቤት ውስጥ ለሚደረጉ ውድድሮችም እንዲሁ ጂምናዚየሞች ተሰናድተዋል፡፡ ለአትሌቲክስ ውድድርም የመም (ትራክ) ነጠፋ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ዝግጅቱን በተመለከተ ከሚመለከታቸው የአፍሪካ አካላት ጋር ያላችሁ ግንኙነት ምን ይመስላል?

ዶ/ር ከሳቴ፡- የሚመጣው እንግዳ ቁጥር ብዙ ስለሆነና ከተለያዩ አፍሪካ አገሮች ስለሚመጡ በጉዞ ላይ እንዳይንገላቱና አስፈላጊው ክትትል እንዲደረግላቸው ከኢትዮጵያ ኤርፖርት ድርጅት ጀምሮ ያለውን ሒደት እያስረዳናቸው እንገኛለን፡፡ በአፍሪካ ደረጃ የሚገኙ አመራሮችም የሒደቱን ሪፖርት ስለሚፈልጉ ያሉትን እንቅስቃሴዎች ሪፖርት እያደረግን ነው፡፡ ከአንድ ሳምንት በኋላ ደግሞ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ስፖርት ማኅበር ፕሬዚዳንትና የአስተዳደር ኃላፊው በዩኒቨርሲቲው ያለውን እንቅስቃሴ ምን ይመስላል? የሚለውን ይገመገማሉ፡፡ እስካሁን የተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች ምዝገባቸውን እያደረጉ ይገኛሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ከተለያዩ የአፍሪካ ዩኒቨርሲቲዎች የሚመጡት ተወዳዳሪዎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው፡፡ እነዚህን እንግዶች ለማስተናገድ አስቸጋሪ አይሆንም?

ዶ/ር ከሳቴ፡- የተለያዩ ዓለም አቀፍ ልምዶች እየተመለከትን ቢሆንም አስተርጓሚ ትንሽ አስቸጋሪ ሆኖብናል፡፡ ቋንቋዎች ከእንግሊዘኛም ባሻገር ስዋሂሊ፣ ዓረብኛና ፈረንሣይኛ የሚናገሩ አሉ፡፡ ስለዚህ ይኼን ችግር ለመቅረፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቀው የወጣቶች ፌሎውሺፕ በ128 አገሮች ጽሕፈት ቤት አለው፡፡ በአፍሪካም ጽሕፈት ቤት ስላለው የተለያዩ አስተርጓሚዎች እንዲያቀርብልን ተነጋግረናል፡፡

ሪፖርተር፡- ውድድሩን በኢትዮጵያ ማከናወኑ ምን ዓይነት ፋይዳ ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

ዶ/ር ከሳቴ፡- በዚህ መደረጉ በቀዳሚነት ተማሪው ያለውን ባህል ለሌሎች ማጋራትና የሌሎቹን ወደ ራሳቸው በማምጣት ልምድ መለዋወጥ ያስችላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችም አህጉር አቀፍ ውድድሮችን ማሰናዳት እንደሚችሉ እናሳያለን፡፡ ከስፖርት ባሻገርም በዩኒቨርሲቲዎቻቸው ያለውን የትምህርት ሒደት፣ ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች እንዴት ናቸው? የኅብረተሰቡ አኗኗርና ባህል ምን ይመስላል? የሚለውን ይጋራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ላይ የሚገኙና ከተወዳዳሪዎቹ ጋር ወደ ውድድር መድረኩ የሚመጡ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች የሚደረገው ውይይት በሴሚናር፣ በጥናትና ምርምር፣ በኅብረተሰብ ጉዳይና በአገሪቱ ውስጥ ያሉትን ጉዳዮች ለማመቻቸት ዕድል ይፈጥራል፡፡ የቱሪስት መስህቦች የመጎብኘት ዕድል ይኖረዋል፡፡ በውድድሩ ላይ የሚሳተፉ ተተኪዎች ደግሞ በአገሪቱ ውስጥ ላሉ ክለቦች ግብዓት ይሆናሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...