Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየወራሽ  ጠቅላይ ሚኒስትር አሿሿም ሕግ ክፍተትን የመድፈን አስፈላጊነት

የወራሽ  ጠቅላይ ሚኒስትር አሿሿም ሕግ ክፍተትን የመድፈን አስፈላጊነት

ቀን:

በውብሸት ሙላት

በቅርቡ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ሕዝቦች ዴሞክራሲ ንቅናቄ (ደሕዴን) እና ከኢሕአዴግ ሊቀመንበርነት እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን አሳውቀዋል፡፡ በደሕዴንና በኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚም ዘንድ ጥያቄው ተቀባይነት እንዳገኘ ይፋ ሆኗል፡፡ በቀጣይነት ደግሞ በኢሕአዴግ ማዕከላዊ ኮሚቴና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡ የእነዚህን አካላት ውሳኔ ተከትሎ አዲስ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ድንገተኛውን የመልቀቅ ውሳኔ ተከትሎ ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን እንደሚችል ከሕገ መንግሥቱ ብዙም መልስ አናገኝም፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር፣አቶ መለስ ዜናዊም ሥልጣን ላይ እያሉ ሕይወታቸው በማለፉ በቀጣይነት የተተኩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት የሞቱ መርዶ ይፋ ከሆነ ወደ አንድ ወር ገደማ ቆይቶ ነው፡፡ በሕግ ቢያንስ ለአንድ ወር ያህል ጠቅላይ ሚኒስትር አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡

በወቅቱ የኢሕአዴግ ምክትል ሊቀመንበር እንዲሁም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ከሆኑና ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ወስኖ ለሕዝብ ተወካዮች ካቀረበ በኋላ ነው የፀደቀው፡፡

እንግዲህ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣን ላይ እያሉ ሕይወታቸው በማለፉ ከተፈጠረው ክፍተት ባለመማር አሁንም አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመልቀቅ ጥያቄያቸውን የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ከተቀበለ በኋላ እንዴት እንደሚተኩ፣ በምን ያህል ጊዜ መተካት እንዳለባቸው፣ በምን ያህል ጊዜ ቢሯቸውንና ቤታቸውን ሁሉ ማስረከብ እንዳለባቸው የሚገልጽ ሕግ አልወጣም፡፡

በየትም አገር ቢሆን መሪ በተለያዩ ምክንያቶች መሪነቱን ሲያቆም የሚተካው በፍጥነት ነው፡፡ ይኼንን ሁኔታ የሚገዛ ሕግ ወይም ልማድ አላቸው፡፡ በዋናነት በፍጥነት መተካት ያለበት ደግሞ የተለያዩ ወገኖች፣ ቡድኖች፣ ሰዎች ወዘተ የመሪነቱን ቦታ ሊፈልጉት ስለሚችሉ ክፍት ሆኖ በቆየ ቁጥር ፍላጎቱም እየተጠናከረ ስለሚሔድ አገራዊ ትርምስና ቀውስ እንዳይፈጠር በመሥጋት ነው፡፡ 

በእርግጥ የአቶ መለስ ሞት ተከትሎ የተፈጠረ ብዙም የቡድን የሥልጣን ፍላጎት ነበር ማለት አይቻልም፡፡ የአቶ ኃይለ ማርያምን የመልቀቅ ውሳኔ ተከትሎ ግን ከተለያዩ ወገኖች የተለያዩ ፍላጎቶች በመንጸባረቅ ላይ ናቸው፡፡ በአንድ በኩል የጠቅላይ ሚኒስርነቱን ሥልጣን በመፈለግ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ ሥልጣኑን እንዳይዙ የሚፈልጓቸውን ሰዎች የሚመለከቱ ፍልጎቶች ናቸው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት ሕገ መንግሥታዊ ቀውስም ሊያስከትል እንደሚችል ይታወቃል፡፡

የፓርላሜንታዊ ሥርዓትን በሚከተሉ በርካታ አገሮች ዘንድ የተለመደው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በፓርላማ አብላጫ ድምፅ ያለው ፓርቲ ወይም የፓርቲዎች ጥምረት በመምረጥ መሰየም ነው፡፡ በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በቀጥታ በሕዝብ አይመረጥም፤ በፓርቲው እንጂ፡፡

በእኛ ሕገ መንግሥትም አንቀጽ 56 ላይ እንደተገለጸው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው የፖለቲካ ድርጅት የፌዴራሉን ሕግ አስፈጻሚ የማዋቀር፣ የማደረጃትና የመምራት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ፓርቲው የሕግ አስፈጻሚውን የሚያዋቅረው መጀመሪያ ላይ ርዕሰ መስተዳድሩን (ጠቅላይ ሚኒስትሩን) አስቀድሞ በመምረጥና በመሰየም ነው፡፡ ቀጥሎም ሌሎች የሕግ አስፈጻሚዎች ይመረጣሉ ማለት ነው፡፡ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁኔታም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን ሙሉ በሙሉ የተቆጣጠረው ያው በኢሕአዴግና በአጋር ፓርቲዎቹ በአንድነት በመሆኑ የሕግ አስፈጻሚውን የሚያዋቅረው ኢሕአዴግ ነው ማለት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አንቀጽ 73 ላይ እንደተገለጸውም የፌዴራሉን ሥልጣን የሚረከበው በምክር ቤቱ አብላጫ ድምፅ ያገኘው ድርጅት ነው፡፡ ይህ ድርጅት የፓርላማ አባል ከሆነው መካከል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆንለት በማቅረብ ማስፀደቅ ይጠበቅበታል፡፡ የፓርላማ አባል ያልሆነ ሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጭ ያሉት ሌሎች ሚኒስትሮች ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ፡፡ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትም ወይም ሌላ ግለሰብ ሚኒስትር መሆን ይችላል፡፡ ይህ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ይጨምራል፡፡

በእርግጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ካልሆነና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥራ በመልቀቁ፣ በሞት ሲለይ ወዘተ ተክቶ በሚሠራበት ጊዜ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አይሆንም ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ቢሆን ተመራጭ ነው፡፡ ካልሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመሪነት ሲለቅ ተክቶ መሥራት አይችልም፤በመሆኑም የአመራር ክፍተት ይፈጠራል፡፡

ሕገ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞት ወይም በራስ ፈቃድ በመልቀቅ ወይም ወንጀል በመፈጸሙ ያለመከሰስ መብቱ ተነስቶ በመከሰሱ ምክንያት ወንበሩ ባዶ በሚሆንበት ጊዜ ማን እንደሚተካ ሕገ መንግሥቱ በግልጽ መልስ አላስቀመጠም፡፡ እንደውም በመኪና፣ በአውሮፕላን ወይም በሌላ አደጋ ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ምክትሉም በአንድ ጊዜ ሕይወታቸውን ቢያጡ ማን መተካት እንዳለበት አሁንም ሕገ መንግሥቱ በግልጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ የለም፡፡ በሌላ ሕግም አልተገለጸም፡፡

አንዳንድ አገሮች በርካታ ተተኪዎችን የያዘ ሕግ አላቸው፡፡ በተለይ እ.ኤ.አ. በ2001 መስከረም አንዱ ቀን በአሜሪካ የተፈጸመውን የሽብር ጥቃት መነሻ በማድረግ ፕሬዚዳንት ወይም ጠቅላይ ሚኒስትር ከነካቢኔው በአንድ ጊዜ የሽብር ሰላባ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚን በማሰብ የወራሾችን ወይም ተተኪዎችን ቁጥር የጨመሩም አሉ፡፡

በእኛ አገር ሕገ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሞት፣ በግድያ፣ በመባረር፣በመልቀቅ ወዘተ ሥልጣኑን ቢያጣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሊተካው መቻሉን ወይም አለመቻሉን እንመለከት፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 (1) (ለ) ላይ እንደተገለጸው ‹‹ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖርበት ጊዜ ተክቶ ይሠራል፤›› ይላል፡፡ ነገሩን የበለጠ ለማብራራት የእንግሊዝኛውን አገላለጽም አብረን እንመልከተው፡፡ እንዲህ ይላል፡- ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “Act on behalf of the Prime Minister in his absence” እዚህ ላይ ‹‹በማይኖርበት ጊዜ›› የሚለውን ሐረግ አንድምታ ማጤኑ ወሳኝ ነው፡፡ በማይኖርበት ጊዜ ማለት በሞት፣ በራስ ፈቃድ ወይም በወንጀል በመከሰሱ ምክንያት በሚለቅበት ጊዜ ተክቶ መሥራትን ይጨምራል ወይ? የሚለው ላይ ነው ቁምነገሩ ያለው፡፡

ከዚህ ሐረግ መረዳት የሚቻለውና ከላይ ለቀረበው ጥያቄ መልሱ አሉታዊ ነው፡፡  በሌላ አገላለጽ አይጨምርም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አምስት ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ‘በማይኖርበት ጊዜ’ ከሚለው ሐረግ ትርጓሜ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ‘በማይኖርበት’ ማለት የሚመስለው በሕይወት እያለ ነገር ግን በሕመም፣ውጭ አገር በመሔድ፣ ዕረፍት ላይ በመሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቢሮ ሲቀር አንጂ ሙሉ በሙሉ በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ መቀጠል ሳይችል በሚቀርበት ጊዜ ያለውን ሁኔታ የሚሸፍን አይመስልም፡፡

የእንግሊዝኛው “absence” የሚለው ቃል የሚያመለክተው በቢሮ አለመኖርን፣ከሥራ ገበታ አለመገኘትን፣ መቅረትን እንጂ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ከወንበሩ በቋሚነት የተለየን አይደለም፡፡ በመሆኑም፣ ‹በማይኖርበት ጊዜ› ከሚለው ሐረግ መረዳት የሚቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣኑ በራስ አነሳሽነትም ይሁን በሌላ ምክንያት ሲለቅ ወይም በሞት ሲለይ በቀጥታ ሥልጣን የመውረስ መብትን አያመለክትም፡፡

ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ በዚሁ ንዑስ አንቀጽ ላይ ካለው ‘ተክቶ’ ከሚለው ቃል ጋር የተያያዘ ነው፡፡ እዚህ ላይ ‘ተክቶ’ የሚለውን ቃል የበለጠ የሚያብራራው የእንግሊዝኛው “on behalf of” የሚለው ነው፡፡ ‘ተክቶ’ የሚለው ቃል ትርጉሙ ሊሆን የሚችለው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ወክሎ፣ ተተክቶ፣ እንደእሱ ሆኖ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥራትን፣ በሥልጣኑ ላይ ቢኖር ኖሮ የሚያደርጋቸውን ያደርጋል፣ የሚሠራቸውን ይሠራል፣ የሚወስናቸውን ይወስናል ማለት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የእንግሊዝኛው ሐረግ የበለጠ ይገልጸዋል፡፡ በመሆኑም ተክቶ የሚለው ቃል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመኑ ሳይጠናቅቅ ሥልጣን በሚለቅበት ወይም ሕይወቱ በሚያልፍበት ጊዜ የሚተካው መሆኑን አያሳይም ማለት ነው፡፡ እንደውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውክልና አድራጊ ወይም ወካይ (principal)፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደግሞ ወኪል ወይም እንደራሴ (agent) መሆንን ነው የሚገልጸው፡፡

ከላይ የቀረቡት የአተረጓጎምና የማብራራት ስልትም የቃላቱን መደበኛና በሙያው ውስጥ ያላቸውን ትርጉም መሠረት በማድረግ የሚሰጠውን በሕግ ሙያተኞች ዘንድ በሰፊው የሚታወቀውን ቃላዊ (ቴክስቹዋል) የአተረጓጎም ሒደት የተከተለ ነው፡፡

ሦስተኛው ደግሞ የምክትሉ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ የመሆኑ ነገር ነው፡፡ ምክትል በመሆኑ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ተጠሪነቱ በዚህ መልኩ መቀመጡ ተገቢነት አለው፡፡ በመርሕ ደረጃም ለሹመትም የሚመርጠውና የሚያቀርበውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሆነ የመረጠውንና የሾመውን ሰው ማንሳትም ይችላል፡፡ ተጠሪነቱም ለሚሾመው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱም በማናቸውም ሁኔታ የምክትሉ ተጠሪነት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚሆን ፍንጭ አይሰጥም፡፡ ይህ ደግሞ ከላይ የተገለጹትን ሁለት ምክንያቶች ያጠናክራል፡፡

አራተኛው ደግሞ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆንን በቅድመ ሁኔታ አለማስቀመጡ በራሱ ፍንጭ ሰጭ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ለመሾም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን የግድ ነው፡፡ የሕግ አስፈጻሚው የሚመራውና የሚደራጀው በጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካይነት ስለሆነ እንዲሁም የሚያስፈጽመው ሕግ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የወጣውን ስለሆነ ምክትሉ የፓርላማ አባል እስካልሆነ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን የመውረስ ዕድል ሊኖረው አይችልም ማለት ነው፡፡

ምክትሉ የሥልጣን ወራሽ እንዲሆን ታስቦ ቢሆን ኖሮ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሆን በግልጽ ይቀመጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲለቅ እንዲተካው በሕገ መንግሥቱ አልታሰበም ማለት ይቻላል፡፡

 የመጨረሻው ምክንያት ደግሞ በግልጽ አለመደንገጉ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በግልጽ እስካልተደነገገ ድረስ እንደተተወ ወይም ምክትሉ እንዲተካው አልተፈለገም ብሎ መተርጎም ይቻላል፡፡ እንዲወርስ ቢፈለግ ኖሮ በግልጽ ከመቼ ጀምሮ ምንም ሁኔታ ሲያጋጥም የሚሉት ሁኔታዎችም ጭምር ይገለጹ ነበር፡፡ በዚህ መንገድ ሳይገለጽ በመቅረቱ የሚመለክተው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንደመብት ወዲያውኑ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ወራሽ አለመሆኑን ነው፡፡

  ሕገ መንግሥቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን በሚመለከት የደነገገው ከላይ የተገለጸውን ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ቢገለጽም ባይገለጽም ወራሴ መንግሥትነት በፍጥነት ክፍተት ሳይፈጥር መከናወን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ወይም ንጉሥ በግድያም ይሁን በሞት ወንበር ባዶ ሲሆን፣ በሐዘንና በለቅሶ ሰበብ የፖለቲካ ፍትጊያ እንዲፈጠር ምክንያት መሆን የለበትም፡፡

በእስራኤል፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሳቅ ራቢን በተገደሉበት ወቅት ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍተት ተፈጥሮ ነበር፡፡ እርግጥ አንድ ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና ሁለት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ቢኖሩም በሕግ ወራሽ አይደሉም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሳቅ ራቢን በተገደሉበት ጊዜ እስራኤል ፕሬዚዳንት ሽሞን ፔሬዝን ማለትም የወቅቱን ተቀዳሚ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርገው ከሾሙ በኋላ መንግሥት እንዲቋቋም አድርዋል፡፡

ይሳቅ ራቢን እ.ኤ.አ. ኅዳር 4 ቀን ከምሽቱ አምስት ከሩብ 1995 መሞታቸው ተገልጾ ወዲያኑ ሌሊት ላይ ግን መንግሥት መሥርተው ጨርሰዋል፣ ጊዜያዊና ባላደራ መንግሥት ቢሆንም፡፡ ቀን ላይ በጥይት ተመትተው ምሽት ላይ ነው ሕይወታቸው ማለፉ ይፋ የሆነው፡፡ በሽሞን ፔሬዝ የተመራው ባላደራ ጊዜያዊ መንግሥት በ18 ቀናት ውስጥ ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ያለውን ድርድር ጨርሶ የፓርላማውን ይሁንታ አግኝቶ መንግሥት መሠረተ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትርም ሆኑ፡፡ በእስራኤል ማንኛውም ፓርቲ በሦስት ሳምንት ውስጥ መንግሥት መሥርቶ የመጨረስ ግዴታም አለበት፡፡

በዝምባብዌ ፕሬዚዳንቱ በሞት፣ በግድያ፣ በመባረር፣ በመልቀቅም ይሁን በሌላ ምክንያት የፕሬዚዳንትነቱ ወንበር ባዶ ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ ወራሴ መንግሥት እንዲሆን የተፈቀደው ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ወደ ፕሬዚዳንትንት ከፍ ሲል ሁለተኛው ምክትል ወደ ተቀዳሚነት ከፍ ይላል፡፡ ከዚያ ፕሬዚዳንት የሆነው በፍጥነት ሁለተኛ ምክትል ፕሬዚዳንት መሾም ይጠበቅበታል፡፡

በቅርቡ ፕሬዚዳንቱ ሮበርት ሙጋቤ ሥልጣናቸውን ሲያጡ ማን ይተካቸው የሚለው ብዙም አሳሳቢ አልነበረም፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ወዲያውኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ተክተዋቸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የመልቀቅ ጥያቄ ባቀረቡበት ወቅት የሥልጣናቸው የለቀቁት የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ በወዲያኑ በምክትላቸው እንዲተኩ ምርጫውንም የአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ፓርላማ በመገኘት በሰብሳቢነት አስመርጠውና ቃለ መሐላ አስገብተዋል፡፡ እስከ 2019 ድረስም በፕሬዚዳንትነት ይቀጥላሉ፡፡

በአርጀንቲና ሕገ መንግሥት ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በማናቸውም ሁኔታ የፕሬዚዳንቱ ወንበር ባዶ ሲሆን፣ የሚተካው በምክትል ፕሬዚዳንቱ ነው፡፡ የሁለቱም ወንበር በአንድ ጊዜ ክፍት ሲሆን ግን ኮንግረሱ (ሁለቱም ምክር ቤት በአንድነት) ሌላ እስኪመረጥ ድረስ የመሰለውን ሰው ይሰይማል፡፡

በአሜሪካ ደግሞ የፕሬዚዳንቱ መንበር በማናቸውም መንገድ ባዶ ሲሆን ምክትሉ ይተካዋል፡፡ ተተኪው ምክትሉ ላይ አይቆምም፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባዔ፣ የሴኔቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስትር፣ የመከላከያ፣ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የአገር ውስጥ ሚኒስትር እያለ ሁሉም ሚኒስትሮች የሚተኩበትን ቅደም ተከተል የሚያሳይ ሕግ አላቸው፡፡

በናይጄሪያ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በማናቸውም ምክንያት ቢለቅ ምክትል ፕሬዚዳንቱ ወዲያኑ ይተካዋል፡፡ በተለይ ፕሬዚዳንቱ ሥልጣናቸውን የሚለቁ ከሆነ መልቀቂያ እንዳስገቡ ወዲያውኑ ይተካሉ፡፡ መልቀቂያ ካስገቡ በኋላ ፕሬዚዳንታዊ ተግባራትን ማከናወን አይችሉም፡፡ በእኛ አገር የሆነው ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልቀቂያ ካስገቡ በኋላም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ጭምር አውጀዋል፡፡

እሳቸው ባወጁትና እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ በዚሁ መንገድ ሲያስተዳድሩ ከቆዩ በኋላ ለሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር ሥልጣናቸውን እንደምን አድርገው ያስረክባሉ፡፡ እንደሚታወቀው በአስቸኳይ ጊዜ ሕግ አገርን መምራት አስቸጋሪም በከፍተኛ ሁኔታም የዜጎች መብት የመጣስ ዕድሉም ሰፊ ነው፡፡ ለዚያም ነው ሁኔታውን የሚከታተል አጣሪ ቦርድ እንዲሰየም ሕገ መንግሥቱ የሚያስገድደው፡፡ ቦርዱ አጠቃላይ አፈጻጸሙን ይከታተላል፤ ችግሮች ሲኖሩም ዕርምጃ እንዲወሰድ የማድረግ ሕጋዊ ሥልጣን አለው፡፡

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩም በአጠቃላይ እንዴት እንደመሩትም እንዲሁ ሪፖርት አቅርበው ተጠያቂነትም እንደሌለባቸው በአግባቡ እንደመሩ ማሳየት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር በመካከል ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር መተካት የተጠያቂነትን ሁኔታ ያወሳስበዋል፡፡

የሌሎቹን አገሮች ልማድ አነሳን እንጂ በተለይ በጥንቷ ኢትዮጵያም ቢሆን  በሰለሞናውያን ሥርወ መንግሥት ንጉሡ ሲሞት ማን መተካት እንዳለበት በግልጽ ይታወቃል፡፡ የመንገሥ መብት ያላቸውንና ካልነገሥን በማለት ሊያስቸግሩ የሚችሉትን ሰዎች ቀድሞ መለየት የተለመደ ነው፡፡ የመንገሥ ፍላጎት ያላቸውና ተከታይ ማሠለፍ ውስጥ የሚገቡ ሰዎች ‹‹ወሬኛ›› በመባል ይታወቁ ነበር፡፡ በጎንደር የንግሥና ዘመንን ደግሞ በጣም ጎልቶ ነበር፡፡ ብዙ ወሬኞችም ተነስተው ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ንጉሥ በሚሞትበት ጊዜ አስቀድሞ የሚደረገው የሚተካውን ሰው ፈልጎ መሾም፣ ንግሥና ይገባናል ብለው በወሬኛነት ሊነሱ የሚችሉትን ሰብስቦ ማሰር ወይም በጥበቃ ሥር ማዋል ነው፡፡ ተተኪውን በፍጥነት በማንገሥ የንጉሡን ሞት ከሕዝብ ይፋ ማድረግ ደግሞ ቀጣዩ ሒደት ነው፡፡ አዲስ የተሾመው ንጉሥም ሕዝቡንና ሐዘንተኛውን ‹‹የሞትን እኛ ያለንም እኛ›› በማለት ያጽናናል፡፡ እንዲረጋጋም ጭምር ያደርጋል፡፡ ንጉሥ ሳይሾም ሐዘን አይታወጅም፡፡ አገርን ወደ ቀውስ ስለሚወስድ ነው ይህ አሠራር የሰፈነው፡፡

የተሻሻለው የ1948ቱ ሕገ መንግሥት ደግሞ በግልጽና በዝርዝር ንጉሠ ነገሥቱ እንዴት እንደሚተኩ፣ ወራሴ መንግሥቱ እንዴት እንደሚሾም፣ አገርን አንደሚያስዳድር እያንዳንዱ ገጠመኞችን ሁሉ በመዘርዘር መፍትሔ አስቀምጧል፡፡ እንኳን በሞት ሲለይ ይቀርና በሕመም ምክንያት አገር መምራት በማይችልበት ደረጃ ላይ ቢደርስ (ንጉሡም ወራሹም) መምራት መቻል ወይም አለመቻሉን ሁሉ ማን ሊወስን እንደሚችል ዝርዝር ደንጋጌዎች አሉ፡፡

ይሁን እንጂ፣ ሌሎች አገሮች በሕገ መንግሥታቸው ወይም በሌላ ሕግጋት ነገሥታት፣ ፕሬዚዳንት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት መሾምም ሆነ መተካት እንዳለባቸው ወስነዋል፡፡ በእኛ አገርም ከሞላ ጎድል በጥንቱ ልማድ ይኼው አሠራር የተለመደ ነበር፡፡

በአጠቃላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር ሕግ ማውጣት ያስፈልጋል፡፡ ከላይ በተመለከትናቸው አጋጣሚዎች ወንበሩ ባዶ በሚሆንበት ጊዜ እንዴት መተካት እንዳለበት፣ በምን ያህል ጊዜ መተካት እንዳለበት፣ በተግባር ከለቀቁ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥራት የሚችላቸውንና የማይችላቸውን፣ ለቀቀ የሚባለውን መቼ ነው የሚለውን፣ አንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከመኖሪያ ቤቱም ጭምር በምን ያህል ቀን መልቀቅ እንዳለበት ወዘተ ሕግ ያስፈልጋል፡፡ የሕግ አስፈጻሚውን ሥልጣንና ተግባር በሚዘረዝሩ አዋጆችም ላይ ቢሆን የጠቅላይ ሚኒስትሩና የምክትሉ ሁኔታ አልተገለጸም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ላይ ያለው ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ቢያንስ ሁለት ጊዜ መሳሳት ሊበቃ ይገባል፡፡ የሥልጣንን ነገር በአግባቡ ቅርፅ አለማስያዝ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም አገሪቱንም ጭምር ቀውስ ውስጥ ሊያስገባ ይችላል፡፡

አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...