Friday, March 24, 2023

ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ፍለጋ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበርነትና ከአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርነት  ለመልቀቅ የካቲት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ይህን ጥያቄያቸውንም የኢሕአዴግና የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች እንደተቀበሏቸው መናገራቸው አይዘነጋም፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኃላፊነት የመልቀቀያ ጥያቄ ማቅረብ የአገሪቱ መነጋገሪያ በሆነ በአንድ ቀን ልዩነት ደግሞ፣ በመላ አገሪቱ ለስድስት ወራት ተግባራዊ የሚሆን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታውጇል፡፡ መንግሥት በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት አገሪቱን ማስተዳደር እንዳልቻለ፣ በአገሪቱ እየተከሰተ ባለው ቀውስ ሳቢያም የሰው ሕይወት እየጠፋና የአካል ጉዳት፣ እንዲሁም የንብረት መውደም እያስከተለ እንደሆነና ይህን ችግር ለመፍታት ሲባልም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. ታውጇል፡፡

መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለማስወገድ እስረኞችን እንዲሚፈታ በገባው ቃል መሠረት በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ ዜጎችን ከእስር ለቋል፡፡ ወደፊትም በርካታ የተፈረደባቸውና ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ ያሉ ዜጎችን እንደሚፈታ ይጠበቃል፡፡ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት የሚወሰዱ ዕርምጃዎች ይፋ በተደረጉ በቀናት ልዩነት ደግሞ የአዋጁ ዝርዝር መመርያዎችና ክልከላዎች በኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ኃላፊና በመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈጌሳ ረቡዕ የካቲት 14 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአገሪቱ ሕዝብ ይፋ ተደርጓል፡፡ ይህ አጀንዳ መነጋገሪያ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ባልተጠበቀ ሁኔታ የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የአመራር ሽግሽግ ማድረጉን ሐሙስ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ገልጿል፡፡ በዚህ መሠረትም የድርጅቱ ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዚዳንት አቶ ለማ መገርሳ አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው የደርጅቱ ምክትል ሊቀመንበርና የክልሉ ፕሬዚዳንት፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ደግሞ የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው እንዲሠሩ የድርጅቱ ማዕከላዊ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ መምረጡ ይፋ ተደርጓል፡፡ የዶ/ር ዓብይ የኦሕዴድ ሊቀመንበርነት ቦታን ማግኘት ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር በዕጩነት ለማቅረብ የታለመ እንደሆነ በስፋት እየተነገረ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለስድስት ዓመታት ያህል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከአቶ መለስ ዜናዊ ሕልፈተ ሕይወት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆኑት አቶ ኃይለ ማርያም በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ስድስት ዓመታት በተለይም ባለፉት ሁለት ዓመታት ገደማ፣ በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ ቀውስ ተከስቷል፡፡ ይህን ተከትሎም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ለመልቀቅ እንደተገደዱ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ በኢሕአዴግና በደኢሕዴን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴዎች ተቀባይነት ማግኘቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ገዥው ፓርቲ ቀጣዩን ሊቀመንበር በብሔራዊ ምክር ቤት ለመምረጥ ደፋ ቀና እያለ ነው፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል ማለት ነው፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚኖሩ ዲፕሎማቶች ጋር የካቲት 13 ቀን 2010 ዓ.ም. በሸራተን ሆቴል ውይይት ባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ገዥው ፓርቲ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ሥራ ላይ እንደሆነ፣ ሒደቱም በጥሩ ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለው መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

አሁን ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆን ይችላል የሚለው አነጋጋሪ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ከዚህም በላይ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር በትክክል የአገሪቱን ችግር መፍታት ይችላል? አዳዲስ የፖሊሲ ለውጦች ያደርጋል? በአገሪቱ ጉዳይ ያገባኛል ከሚሉ ወገኖች ጋር ውይይት በማድረግ አገሪቱን ካለችበት ቀውስ መታደግ ይችላል? የኢትዮጵያን ሕዝብ ማዕከል ያደረገ መፍትሔና የጋራ መግባባት ይፈጥራል ወይ? የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አብላጫ መቀመጫ ያለው ፓርቲ አገሪቱን ያስተዳድራል፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 73 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተደነገገው፣ የሚመረጠው ጠቅላይ ሚኒስትር ግን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል መሆን አለበት፡፡

በዚህ መሠረት የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች ማለትም ሕወሓት፣ ብአዴን፣ ኦሕዴድና ደኢሕዴን ለግንባሩ ሊቀመንበርነት ያጯቸውን ግለሰቦች ለብሔራዊ ምክር ቤት በማቅረብ በድምፅ ብልጫ ያስመርጣሉ፡፡ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት 180 ተወካዮች ያሉት ሲሆን፣ እያንዳንዱ ብሔራዊ ፓርቲ 45 ተወካዮች አሉት፡፡

በ2007 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ኢሕአዴግ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ከአጋር ፓርቲዎች ጋር መቶ በመቶ አሸንፏል፡፡ ኢሕአዴግ በሚቀጥሉት ጥቂት ቀናት የድርጅቱን ብሔራዊ ምክር ቤት ስብሰባ በማካሄድ አዲስ የግንባሩን ሊቀመንበር እንደሚመርጥ፣ ሊቀመንበሩን ደግሞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቦ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመት እንደሚያሰጥ ይታወቃል፡፡ አዲሱ የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማን ሊሆኑ ይችላል? የሚለው ጉዳይ አሁንም አነጋጋሪነቱ እንደ ቀጠለ ነው፡፡

አገሪቱ ያለችበት ቀውስ እየታወቀ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ቶሎ አለመሾም የመንግሥት ንብረት እንዲመዘበር ዕድል ከመክፈቱም በላይ፣ የአገሪቱን ሕዝብ አለመረጋጋት ከፍ ያደርገዋል የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ጊዜ ወስዶና ተመካክሮ የአገሪቱን ችግሮች ለመፍታት ቁርጠኛ የሆነ መሪ መምረጥ እንዳለበት የሚከራከሩ ወገኖችም አሉ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ የጂኦ ፖለቲካ ተንታኝና ምሁር መድኃኔ ታደሰ (ፕሮፌሰር) ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢሕአዴግ የራሱ አሠራር እንዳለውና ሊቀመንበሩንና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለመምረጥ የሚደረገው ጥረት ተጋኖ መቅረብ የለበትም ባይ ናቸው፡፡

ፖለቲከኛው በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) በበኩላቸው፣ ኢሕአዴግ በአገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ካወጀ በኋላ ሊቀመንበሩንና የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመምረጥ ሲጣደፍ አለመታየቱ ችግር ውስጥ እንዳለ ማሳያ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ደግሞ ፓርቲው አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ ነው ይላሉ፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አቶ ሙላቱ ገመቹ በበኩላቸው፣ ኢሕአዴግ የአገሪቱን ችግሮች በመፍታት ረገድ አሁንም የሚታዩበት እንከኖች እንዳሉ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አገሪቱን የሚመራ ሰው ከሥልጣን ለመነሳት ጥያቄ ሲያቀርብ ወዲያውኑ ሌላ ጠቅላይ ሚኒስትር መመረጥ ነበረበት፡፡ ይህ ክፍተት በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ከባድ ሙስና፣ የሕገ መንግሥትና የግለሰቦች የሰብዓዊ መብት አለመከበር ችግሮች ሊፈጠሩ ይችላሉ፤›› ብለዋል፡፡

የጂኦ ፖለቲካ ተንታኙ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ ግን በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አሁንም ሥራቸውን እያከናወኑ መሆኑን፣ ከዚህ አንፃር በዚህ ወቅት የተለየ ችግር ይፈጠራል ብለው እንደማያስቡ ገልጸዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን ለመውረድ ጥያቄ ማቅረባቸው ሁለት ነገሮችን እንደሚያሳይ ጠቁመዋል፡፡ የመጀመርያው ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ታሪክ በሰላማዊ መንገድ ለመውረድ ጥያቄ ማቅረባቸው ያልተለመደ እንደሆነ፣ ሁለተኛው ደግሞ የአገሪቱ ትልቁ ሥልጣን (ጠቅላይ ሚኒስትርነት) በፓርቲ አባላት ፍላጎት ላይ የተመሠረተ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ይህ ማለት የአንድ ሰው ጠቅላይነት (ተፈሪነት) እየቀረ መምጣቱን ይጠቁማል ብለዋል፡፡  

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ተከስቶ የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል፣ አካል ጎድሏል፣ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ባለፉት ሳምንታት የሰው ሕይወት መጥፋቱና መፈናቀሉ ረገብ ያለ ቢመስልም፣ የተፈናቀሉ ዜጎችን ከማቋቋም አኳያ እስካሁን ተጨባጭ ሥራ አለመሠራቱ ይነገራል፡፡ የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ የማቋቋም ሥራው አልተጀመረም፡፡ ነገር ግን በኦሮሚያ ክልል ተፈናቃዮችን ለማቋቋም በክልሉ መንግሥት፣ በረድኤት ድርጅቶችና በፌዴራል መንግሥት በርካታ ሥራዎች እየተሠሩ እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነገር ተደምጧል፡፡

በአገሪቱ ከተከተሰው መፈናቀል በተጨማሪ ከፍተኛ ሥጋት እየሆነ የመጣው የብሔርተኝነት ስሜት እንደሆነ የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም አገሪቱ ቀውስ ውስጥ በመግባቷ ሳቢያ ሥልጣናቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ካቀረቡ በኋላ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ዓይነት ፖሊሲ ሊከተሉና የአገሪቱን ችግር ሊፈቱ ይችላሉ? የሚለው የብዙዎች መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡

ፕሮፌሰር መድኃኔ አሁን ዋናው ጉዳይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ምን ዓይነት የፖሊሲ ለውጥና የፖለቲካ ሒደት ይከተላሉ የሚለው ነው ይላሉ፡፡ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ማንበብና የችግሮቹን ጥልቀትና ስፋት በትክክል መረዳት የሚችል ከሆነ መልሱ ቀላል እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ ይህ ከተደረገ አዲስ የፖለቲካ ሒደት በማምጣት አገሪቱን ማዳን እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡ ‹‹ዋናው የትኛውም የፖለቲካ መሪ ማድረግ ያለበት አገርን ማስቀጠል ነው፡፡ መጀመርያ ያለውን ሁኔታ በትክክል መረዳትና ማወቅ፣ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት በትክክለኛው ሚዛን ማስቀመጥ ከተቻለ ሌላው ቀላል ነው የሚሆነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ ደግሞ፣ ኢሕአዴግ አሁን እያወራ ያለው የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት አስገብቶ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ቢሆኑ ከሥልጣን ለመውረድ የወሰኑት በገዛ ፈቃዳቸው ሳይሆን በፓርቲው ግፊት እንደሆነ ገልጸው፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑትም በማሟያ ምርጫ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የፓርላማ አባል በነበሩ ጊዜ አንድ ትውስታ እንደነበራቸው ፕሮፌሰር በየነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹አቶ ኃይለ ማርያም የክልል ተመራጭ ነበሩ፡፡ እሳቸውን ወደ ፓርላማ ለማምጣት ሲፈለግ ከወላይታ ተመርጠው የመጡ የፓርላማ አባል ለቅቄያለሁ እንዲሉ አሰኙ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ከደቡብ ፓርላማ ለቅቄያለሁ እንዲሉ ተደረገ፡፡ ለሁለቱም ልዩ ማሟያ ምርጫ እንዲካሄድ ተደርጎ አቶ ኃይለ ማርያም ለፌዴራል ተወዳድረው መጡ፣ ያኛው ደግሞ ለክልል ተወዳደሩ ተባሉና ክልል ገቡ፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ አኳያ አሁንም ገዥው ፓርቲ የሚፈልገው ሰው ካለ በዚህ መንገድ ወደ ፓርላማ እንዲገባ ማድረግና ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የመሾም ዕቅድ ሊኖረው እንደሚችል ፕሮፌሰር በየነ አስረድተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ይህን ያሉት የኦሕዴድ ሊቀመንበር የነበሩትና አሁን ምክትል የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የሚፈልጉ ግለሰቦች እንዳሉ አስታውሰው መሆኑን፣ አሁን ግን ይህ ስሜት መቀየሩን ተናግረዋል፡፡ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኦሕዴድ ሊቀመንበር ከሆኑ በኋላ እነዚህ ስሜቶች እየጠፉ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በበኩላቸው፣ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ችግር ተረድቶ በችግሮቹ መጠን መፍታት የሚችል ይሆናል? ወይስ አይሆንም? የሚለው ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኦፌኮው አቶ ሙላቱ ደግሞ ኢሕአዴግ በ27 ዓመት የሥልጣን ዘመኑ ባልተለመደ ሁኔታ ችግር ውስጥ በመግባቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሳቸውን ማግለል ደረጃ ላይ መድረሳቸውን አስታውሰው፣ አሁንም በኦፌኮ እምነት አገሪቱን ከገባችበት ቀውስ ያወጣታል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ተተኪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የሚመረጠው ግለሰብም የአገሪቱን ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቁመዋል፡፡

አቶ ልዑልሰገድ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ ኢሕአዴግ በራሱ የአገሪቱን ችግር የሚረዳና ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ የሆነ መሪ ለመምረጥ እንደሚችል እምነታቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹እንደ መሪ የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ብዙ ችግር ያለባት አገር ነች፡፡ በተለይ የዕድገት ጎዳናዋ በአሥጊ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ ይህንን የሚቀለብስ መሪ ያስፈልጋል፡፡ አንድነታችን አደጋ ላይ ነው ያለው፡፡ አገራዊ ስሜት ቀዝቅዞ የብሔርተኝነት ስሜት አይሏል፡፡ አዲሱ መሪ የኢትዮጵያ አንድነትን የሚቀሰቅስ እንዲሆን ነው የምንፈልገው፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ሲወጣ የነበረውና አሁን ያለው እውነታ የተለያዩ ናቸው፡፡ የሕዝቡ ንቃተ ህሊናም እየዳበረ ነው የመጣው፡፡ ስለዚህ ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር ይህንን ችግር የተረዳና ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኝነት ያለው መሆን አለበት፤›› ሲሉ አቶ ልዑልሰገድ አስረድተዋል፡፡

ፕሮፌሰር መድኃኔ አዲስ የሚመጣው መሪ የአገሪቱን ችግር ጥልቀትና ግዝፈት በመረዳት፣ በዚያው ልክ ችግሩን ለመፍታት ዝግጁ መሆን እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ ለመፍታትም ገለልተኛና ነፃ የሆነ ተቋም መቋቋም እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ይህ ተቋም ሁሉም ሊሳተፍበት የሚችል፣ ታሪካችንንና የፖለቲካ ችግራችንን፣ የዴሞክራሲ ተቋማቶቻችንን እንደ አዲስ ለማደራጀትና ለማጠናከር፣ ከዚያም በኋላ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ መደላደል የሚፈጥር መሆን አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ከምሁራን፣ ከታዋቂ ሰዎች፣ ከመንግሥት ሠራተኞች፣ ከገዥው ፓርቲ፣ ከተቃዋሚ ፓርቲዎችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጣ አንድ ስትራቴጂካዊ ቡድን መቋቋም እንዳለበት ፕሮፌሰር መድኃኔ አክለው ገልጸዋል፡፡ ‹‹በዚህ አገር የሐሳብ ድህነት ያለ ይመስለኛል፡፡ ይህን ድህነት ደግሞ ይህ ስትራቴጂካዊ ቡድን የመቅረፍ ዕድል ይኖረዋል፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር በየነ በአገሪቱ ሕዝብ አመኔታ አግኝቶ የሚመራ አካል መፍጠር ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ ጠቁመው፣ ይህ ካልሆነ ግን ኢሕአዴግ ብቻውን የአገሪቱን ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡

አቶ ሙላቱ፣ ‹‹አንድነታችን ተጠናክሮ እንዲቀጥል መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ይህች አገር የሁላችንም ነች፡፡ ሁላችንም ተከባብረን የምንኖረው ዴሞክራሲ ሲኖር ነው፡፡ አንድነታችንን ጠብቀን እንድንኖር ሁላችንም ኃላፊነት አለብን፡፡ አገራችን ስትደማ ሁላችንም ነው የምንደማው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ቢሆኑ ጫፍና ጫፍ ይዘው ገመድ መጎተት ሳይሆን፣ ሁሉም ወደ መሀል መጥቶ የቻለውን ያህል እንዲያበረክት መደረግ አለበት፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ የአቶ ኃይለ ማርያምን ተተኪ ለመምረጥ በዝግጅት ላይ ነው፡፡ አራቱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች በሚያቀርቧቸው ዕጩዎች መሠረት አዲሱ ሊቀመንበር ይመረጣል፡፡ በዋናነት የድርጅቶች ሊቀመናብርት ለፓርቲው ሊቀመንበርነት ይወዳደራሉ፡፡ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የካቲት 15 ቀን 2010 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ለማ መገርሳን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር ሆነው እንዲሠሩ ተወስኗል፡፡

ከስብሰባው በኋላ የኦሕዴድ ምክትል ሊቀመንበርና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ለማ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ኦሕዴድ የክልሉን ሕዝብ ሁለንተናዊ ችግሮች ለመፍታትና የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፊ ትግል ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፣ በፌዴራል ደረጃ አመራር መውሰድ የሕዝቡና የድርጅቱ ጥያቄ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹በክልል ደረጃ መሠራት ያለባቸውን በመሥራት፣ ታሪክ የሚሰጠንን ዕድል በመጠቀም፣ ለክልሉ ሕዝብም ሆነ ለአገሪቱ ጠቃሚ ሥራ መሥራት አስፈላጊ ሆኖ ድርጅቱ ስላገኘው የአመራር ሽግሽግ አድርጓል፤›› ብለዋል፡፡

የሕዝብ ክብር የሚረጋገጠው እኩልነትንና ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ሲቻል እንደሆነ ጠቁመው፣ ‹‹የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚም ይህንን በጥልቀት በማየት የክልሉ አመራርና ማዕከላዊ ኮሚቴው በመግባባትና በመተማመን እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብም ሆነ የኦሕዴድ ጥያቄ በክልል ሳይወሰን በአገሪቱ አመራር ቦታ ላይ ተሳትፎ እንዲኖረው ከሕዝቡ ጋር ሰፊ ትግል ሲደረግ መቆየቱን አቶ ለማ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ከዚህም በመነሳት በፌዴራል መንግሥት ውስጥ የአመራር ድርሻ ሊኖረን ይገባል ስንል የክልላችንን ጉዳይ በመርሳት ሳይሆን፣ በታሪክ ውስጥ የተገኘውን ዕድል የሰፊውን ሕዝብ ክብር በጠበቀ ሁኔታ እንዴት መሠራት ይኖርበታል የሚለውን በጥልቀት ማዕካላዊ ኮሚቴው ገምግሟል፤›› ሲሉ አብራርተዋል፡፡   

ገዥው ፓርቲ አዲሱን ሊቀመንበር ለመምረጥ ዋዜማ ላይ ይገኛል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ምትክ ሌላ ተተኪ ለማምጣት አራቱም ብሔራዊ ድርጅቶች ዕጩዎችን በማዘጋጀት ላይ ናቸው፡፡ ይህ ሒደት ተሳክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት እንዲሰናበቱ ውጣ ውረዱ ቀላል ሊሆን እንደማይችል የብዙዎች ግምት ነው፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -