በአገሪቱ የኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤት ላይ ኅብረተሰቡ የሚያሰማው እሮሮ ኤሌክትሪኩ መጥፋቱ ብቻ አይደለም፡፡ መብራቱ ሄዶ ሲመጣ የሚያደርሰው ጥፋት የትየለሌ ነው፡፡ የኤሌክትሪኩ ኃይል መጠን ከመደበኛው ውጭ ከፍና ዝቅ ሲል የሚያደርሰው ጥፋት ቤት ይቁጠረው፡፡ ማቀዝቀዣው፣ ቴሌቪዥኑ፣ አምፖሉ፣ ልዩ ልዩ ‹‹ቻርጀሮች›› የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶች ተቃጠሉብን የሚል የሕዝብ እሮሮ በየጊዜው ይሰማል፡፡ የሚመለከተው መሥሪያ ቤት ፈጣን ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አገልግሎት የማይሰጠውን ‹‹905›› ላይ ደውላችሁ አስመዝግቡ ከማለት ያለፈ መልስ የለውም፡፡ ‹‹የኤሌክትሪክ ምሰሶው ሊወድቅብን ነው፣ ዘሟል፣ ኧረ ድረሱልን›› እያሉ ለሚወተውቱም ፈጣን ምላሽ መስጠት እንዳልተቻለም ማስረጃ ከሚሆኑ ትዕይንቶች (በፎቶዎቹ የሚታዩት) መካከል በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 እንደራሴ አካባቢ ያሉ የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ለአደጋ መጋለጣቸው ነው፡፡ (በዚሁ ሰበብ በሳምንት ውስጥ የአካባቢው ኅብረተሰብ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶቹ ከጥቅም ውጭ ሆነውበታል) ቀደም ሲል ለመውደቅ አስግቶ የነበረው ምሰሶ እንዲደግፈው የተተከለው ጉርድ መበስበሱን ተያይዞታል፡፡ ይህን ያዩት ሰፈርተኞች ‹‹ሙቅ በገንፎ ሲደገፍ›› ብለውታል፡፡ ከራስ ሙሉጌታ መንገድ ወደ ካዛንቺስ ቶታል በሚያመራው መንገድ በስተቀኝ የቆመው የኢትዮ ቴሌኮም ምሰሶ ከዋናው ኤሌክትሪክ መስመር ላይ ተጋድሞበት ይታያል፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ኧረ መላ በሉ ቢል ተቋማቱ ጆሮ ዳባ ብለዋል፡፡ ‹‹የፉክክር ቤት …›› እንዲሉ፡፡
* * *
የልጅነት የእግር ኳስ ሕግጋት
- የኳሷ ባለቤት ማን የማን ቡድን እንደሚሆን ይወስናል
- ወፍራሙ ልጅ ሁልጊዜ በረኛ ይሆናል
- የኳስ ባለቤት ከተናደደ፣ ከተጐዳ ወይም ቤት ከተጠራ ጨዋታው ያቆማል
- የቡድን አባል መረጣ ጊዜ ብዙ ጐል የሚያገኘው ልጅ አንደኛ ይመረጣል
- ሪጎሬ ከተሰጠ በረኛ የመቀየር መብት የተጠበቀ ነው
- ኃይል የተቀላቀለበት ወይም ኃይለኛ ምት ላለበት ጨዋታ ለተጫዋቹ ማስጠንቀቂያ የሚሰጠው የኳሱ ባለቤት ነው
- ኳስ በሚሠራበት ጊዜ ካልተባበሩ ለሳምንታት አብረው እንዳይጫወቱ ይታገዳሉ
- የኳሱ ባለቤት ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት ቅጣት ምት ያሰጣል/ፋውል ካልሆነ ጨዋታውን ያቆማል
- አንድ ቡድን ሦስት ኮርናዎች ካገኘ አራተኛው ሪጎሬ ነው
- የማልያ መመሳሰል ካለ አንዱ ቡድን ከወገብ በላይ ራቁቱን ሊጫወት ይችላል
- ወንድማማቾች አንድ ቡድን መሆን አይችሉም
- አንድ ሙሉ ጨዋታ ጠዋት ጀምሮ ምሳ ሰዓት ሊያልቅ ይችላል
- ጎሉ የድንጋይ ስለሆነ ወደ ላይ የተመቱ ኳሶች በረኛው እጁን ከፍ አድርጎ ካልደረሰባቸው ጎል አይደለም! በረኛው ድንገት ኳሷን ጨረፍ ካደረጋት ግን ጎል ነው!
- ዳኛም ሆነ የመስመር ዳኛ የለም፤ እንደውም ከጎሉ ጀርባ ሁሉ መጫወት ይቻላል
- ከፌስቡክ፣ የሳቅ ምንጭ (ደብሪቱ ተሾመ)
* * *
ከ229 ሺሕ ዶላር በላይ ያስከፈለው የተሳሳተ ጥሪ
የተሳሳቱ የስልክ ጥሪዎች በተደጋጋሚ ሲገጥሟቸው የሚበሳጩ ግለሰቦች ጥቂት አይደሉም፡፡ በተለይም ደዋዩ እንደተሳሳተ ካሳወቁ በኋላ መደወል አላቋርጥ ሲል ዕርምጃ ለመውሰድ ይገደዳሉ፡፡ አሜሪካዊቷ አራሴሊ ኪንግ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 153 የተሳሳቱ የስልክ ጥሪዎች ከአንድ ድርጅት ገጥመዋታል፡፡
ታይም ዋርነር ኬብል የተባለ ድርጅት በመጀመሪያ ለአራሴሊ የደወለው አንድ ግለሰብ ፈልጐ ነበር፡፡ የፈለጉት ግለሰብ አራሴሊ አለመሆኗን በተደጋጋሚ ብትገልጽም ድርጅቱ ከመደወል አልተቆጠበም፡፡ ለድርጅቱ መክፈል የሚገባቸውን ክፍያ በጊዜው ያላጠናቀቁ ግለሰቦችን ታይም ዋርነር ኬብል እየደወለ መወትወቱ የተለመደ ነው፡፡ ምንም መረጃ ስለሌላት የክፍያ ጉዳይ የሚያሳስብ መልዕክት በተንቀሳቃሽ ስልኳ መበራከቱ ያማረራት አራሴሊ ድርጅቱን ትከሳለች፡፡ ሮይተርስ የማንሀተንን ፍርድ ቤትን ጠቅሶ እንደገዘበው፣ ድርጅቱ 229,500 ዶላር እንዲቀጣ ተወስኖበታል፡፡ አራሴሊ ድርጅቱ የሚፈልገው ግለሰብ አለመሆኗን አሳውቃም ጥሪውን አለማቆማቸው ቅጣቱን እንዳከበደው ተገልጿል፡፡
* * *
በቻይናዊ ወታደር አሟሟት የቀለደ ወጣት ተከሰሰ
ሱን ጂ ቻይናዊ ብሎገር ሲሆን፣ ትዊተር ላይ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሉት፡፡ ቻይናዊው ወታደር ኩዊ ሻዩን አሟሟት ላይ ቀልድ አዘል አስተያየት ጽፎ በትዊተር ገጹ ላይ ባሰፈረ በደቂቃዎች ልዩነት ብዙዎች ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ቅሬታ ሲበራከት ፖስት ያደረገውን ከገጹ ቢያወርድም፣ የወታደሩ ወንድም ክስ መሥርቶበታል፡፡
ቻይና ዶት ኦርግ በትዊተር ገጹ እንዳሰፈረው፣ ኩዊ ሻዩን እ.ኤ.አ. በ1952 የሞተ ወታደር ነው፡፡ ወታደሩ ሕይወቱን ያጣው ለኮሪያ ሲዋጋ ነበር፡፡ በወቅቱ 26 ዓመቱ የነበረው ኩዊ፣ በሚዋጋበት ወቅት ቦንብ ይፈነዳል፡፡ በቦንቡ ፍንጥርጣሪም ልብሱ በእሳት ይያያዛል፡፡ ያለበትን ቦታ ለጠላት ላለማሳወቅ ሲል ያለምንም እንቅስቃሴ ይቆያል፡፡ እሳቱ እያቃጠለውም ሕይወቱ ያልፋል፡፡
ሱን ጂ በትዊተር ገጹ ያሰፈረው ጽሑፍ የወታደሩን አሟሟት የሚያቀል መሆኑን የገለጹ ጥቂት አይደሉም፡፡ ጽሑፉ የወታደሩን አሟሟት ከምግብ አዘገጃጀት ጋር ያነጻጸረ ነበር፡፡
* * *
ፊተኞች ኋለኞች ሲሆኑ
በዕዳ የተዘፈቀችው ግሪክ ዜጎች ኑሮ እንዳልነበረ ከሆነ ሰነባብቷል፡፡ የ77 ዓመቱ አዛውንት ጊዎርጎስ ቻዚጎቲዲስ ከዜጐቹ አንዱ ናቸው፡፡ የጡረታ ገንዘብ ጥየቃ የአራት ባንኮችን በር ቢያንኳኩም መልስ የሰጣቸው አልነበረም፡፡ የጡረታ ገንዘባቸውን ማግኘት ያልቻሉት አዛውንት ከአንድ ባንክ በር ላይ ተቀምጠው ስቅስቅ ብለው ያለቅሳሉ፡፡ ሲያለቅሱ የሚያሳይ አሳዛኝ ፎቶ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ ለመሰራጨት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ፎቶውን በፌስቡክ ያዩት ጀምስ ኮፎስ ልጅ ሳሉ ከአዛውንቱ ጋር አብረው ተምረው ነበር፡፡ አውስትራሊያዊና ግሪካዊው ጄምስ ‹‹ኩሩና ታታሪ ግሪካዊ ሲራብ ማየት አልችልም›› ብለዋል፡፡ ለአብሮ አደጋቸው በወር 250 ዩሮ ለአንድ ዓመት ለመስጠት ቃል ገብተዋል፡፡ በአንድ ዓመት ውስጥ ለውጥ ካልመጣ ድጋፋቸውን እንደሚቀጥሉም አሳውቀዋል፡፡
* * *
ከሰማይ የወረደ ሻርክ
አሜሪካ ቨርጂንያ ውስጥ ነው፡፡ ሱ ቦውዘርና ቤተሰቧ የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን እያደረጉ ነበር፡፡ ከመቅጽበት ከሰማይ ወደ መሬት የሚምዘገዘግ ነገር ያስተውላሉ፡፡ ቤታቸው ጓሮ የወደቀውን ነገር ምንነት ለማወቅ ተጠጉት፡፡ ባለ 13 ኢንች ሻርክ ነበር፡፡
ሻርክ ከሰማይ ወደ ምድር መወርወሩ ያስገረማቸው ሱና ቤተሰቦቿ የቨርጂንያ አኳየር ኤንድ መሪን ሳይንስ ሴንተር ባለሙያዎችን በአፋጣኝ ይጠራሉ፡፡ ዌቪ ኒውስ እንደዘገበው፣ አካባቢው ውኃማ በመሆኑ መሰል ክስተቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ሻርኩ ከውኃ ወደ ላይ ተስፈንጥሮ አልያም በግዙፍ ወፍ ወደ መሬት ተወርውሮ ይሆናል የሚሉ መላ ምቶች አሉ፡፡
ሱና ቤተሰቦቿ ሻርኩን በቤታቸው ለማስቀመጥ ወስነዋል፡፡ ስለጉዳዩ ሰምተው ወደ ቤታቸው ለሄዱ ወዳጆቻቸው ሻርኩን እያሳዩ ስለክስተቱ በዝርዝር እያስረዱም ነው፡፡ ሱ ‹‹ቤታችን ሻርክ ቤት እንደሚባል እንጠብቃለን፤›› ብላለች፡፡
* * *
ዱካ ሲዘምን
ዱካ ኢትዮጵያ ውስጥ አገልግሎት ላይ ከሚውልበት ቅርጽ በተጨማሪ በልዩ ልዩ መልኩ ዲዛይን ተደርጐ የቀረበበት አዲስ መጽሐፍ ‹‹ኮንቴምፖራሪ ዲዛይን አፍሪካ›› ይባላል፡፡ በኢትዮ አሜሪካዊው ጆሞ ታሪኩ የተሰባሰቡ የተለያዩ የዱካ ዓይነቶችን የያዘው መጽሐፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪካ የ50 አርቲስቶች ሥራዎች የተሰባሰቡበት ነው፡፡
የመጽሐፉ አሳታሚዎች ታማስና ሐድሰን ‹‹ስብስቦቹ ፈጠራ የተሞላባቸውና ለኢንቲርየር ዲዛይነሮች የተመቹ ናቸው፤›› በማለት ገልጸዋቸዋል፡፡ ታዲያስ ሜጋዚን እንደዘገበው፣ የጆሞ ሥራዎች ባህላዊው የኢትዮጵያ ቁሳቁሶችን ተመርኩዘው ለተለያየ አገልግሎት በሚያመች መልኩ የቀረቡ ናቸው፡፡ ጆሞ ‹‹በመኖሪያ ቤትም ይሁን በመዝናኛ ቦታ ማንኛውም ሰው ሊጠቀምባቸው ይችላል፤›› ብሏል፡፡
በመጽሐፉ ከተካተቱ ቁሳቁሶች መካከል ከደቡብ አፍሪካ የተወሰደው ዘን ዙሉ ይጠቀሳል፡፡ የዙሉ ቁሳቁስ አሠራርን መሠረት ያደረገ ነው፡፡ የናይጄሪያዊው ዲዛይነር ባንኬ ኩኪ ሥራዎችም ተካተዋል፡፡ የሞሮኮ፣ ሞሪታኒያና ኮንጐ ቁሳቁሶችም በመጽሐፉ ይገኛሉ፡፡
አሳታሚዎቹ እንደገለጹት፣ የአፍሪካ ባህላዊ ቁሳቁሶች ከፍተኛ ትኩረት እየተቸራቸው ነው፡፡ አፍሪካውያን ዲዛይነሮች ለገበያ የሚያቀርቧቸው ቁሳቁሶችም የየአገሩን ባህል ተመርኩዘው የዘመኑ ናቸው፡፡
* * *
የአራት ዓመቷን ሕፃን ውኃ ውስጥ የዘፈቀው ጐልማሳ
ቻይና የሚገኝ መዝናኛ ውስጥ የሆነ ነው፡፡ በመዝናኛው በሚገኝ የመዋኛ ገንዳ ከሕፃን እስከ አዋቂ ይዋኛሉ፡፡ ከሚዋኙት አንዷ የአራት ዓመት ሕፃን ነበረች፡፡ በሰውነቷ ላይ ባጠለቀችው ፕላስቲክ እየታገዘች በውኃው ስትንሳፈፍ ከአንድ ጐልማሳ ጋር ትጋጫለች፡፡ ጐልማሳው በሕፃኗ ይበሳጭና ልጅቷን ከወገቧ ከፍ አድርጐ ይወረውራታል፡፡ በገንዳው ይዋኙ የነበሩ ሰዎች ተደናግጠው ሕፃኗን ከውኃው ካወጧት በኋላ ምንም ጉዳት እንዳልደረሰባት ይገነዘባሉ፡፡ የሕፃኗ እናት በንዴት እየተንዘፈዘፈች ሰውየውን ፖሊስ ጣቢያ መውሰዷን ቻይና ዶት ኮም ዘግቧል፡፡ ሰውየው በምግባሩ መጸጸቱን ተናግሯል፡፡ ‹‹ድንገት ውኃ ውስጥ ስትነካኝ ደንግጬ ያደረግኩት ነው፤›› በሚል ቢያስተባብልም፣ እናትየዋን፣ ፖሊሶችንና በመዋኛ ገንዳው ይዋኙ የነበሩትን ሰዎች ንዴት የሚያበርድ ምላሽ አልሆነም፡፡
እኔ ያንቺ መንገድ
ለአገር ሔዋን ሁሉ
እኔ መንገድ ሆኘ – መምጫና መሄጃ
ይጓጓዙብኛል – መች እንደማርፍ እንጃ፤
ተረኛዋ አንቺ ነሽ
በይ ነይ ተመላለሽ – መንገድሽ ነው ልቤ
አጓጉዝሻለሁ – ትዝታን ደርቤ፤
አሁን በዚህ አፍታ
ከፍቅሬ መዝገብ ላይ – ትዝታን ስገልጠው
ያንቺ ገጽ ላይ ነው – ዓይኔ የሚያፈጠው፤
መጥተው እንደሄዱት – በልቤ ጎዳና
ውጪ፣ ውረጅበት – ሳታሰሚ ዳና፤
አንደዜ ሲፈጥረኝ – ካደረገኝ መንገድ
ንጎጅብኝ አንቺም – እስከምንገዳገድ
ዕጣዬ ነውና – ሂያጅን ማስተናገድ፡፡
– በደመቀ ከበደ፣ ካዛንቺስ
* * *
የሥጋ ፍቅር
አንዱ ሥጋ ቤት ይገባና ግማሽ ኪሎ ስንት ነው? ይላል፤ 70 ብር ይባላል፡፡
ይከራከርና ከ 70 ብር አልቀንስም ሲለው በቃ እሺ ይልና አዝዞ መብላት ይጀምራል። እየበላ መብራት ይጠፋል። ሰውዬው ቀስ ብሎ ተነሳና ከአንዱ ቦታ ሥጋ ቆርጦ ይበላል፡፡ ምግቡን በልቶ ሒሳብ ሊከፍል ወደ ሒሳብ ተቀባዩ ይሄድና 70 ብር ሲሰጠው
ሒሳብ ተቀባዩ፦ 5 ብር ጨምር
ተመጋቢ፦ ለምድነው 5 ብር ተጨማሪ የምከፍለው?
ሒሳብ ተቀባዩ፦ በጨለማ ቆርጠህ የበላኸው የሳንባ ሒሳብ ነው!
(ከድረ ገጽ የተወሰደ)