Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  የኤርትራ መንግሥትና ኢትዮጵያ – ሥጋትና መልካም አጋጣሚዎች

  ክፍል አንድ

             በአዳነ አበራ

  ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲና ሶማሊያ የሚገኙበት የአፍሪካ ቀንድ ተደጋጋሚ በሆኑ የአገሮች የእርስ በርስ ጦርነት እንዲሁም አገር ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ቡድኖች የእርስ በርስ ጦር መሳበቅ ጎልቶ ይታወቃል። ለረጅም ጊዜያት አካባቢው የሰላም እጦት የነገሠበት ሲሆን፣ በዚሁ ሰበብ አገራቱና ዜጎቻቸው ለተራዘመ ቀውስ፣ ረሃብና ተደጋጋሚ ስደት ይዳረጋሉ። የአካባቢው አገሮች ወሰንን ጨምሮ ሌሎች ተዛማጅ የሆኑ ለምሳሌ እንደ ባህል፣ ልማድ እንዲሁም እሴቶችን እንደ መጋራታቸው በአንዱ አገር የሚከሰቱ ችግሮችም በሌላው ላይ በአንድም በሌላም መንገድ አንድምታ ይኖራቸዋል። በመሆኑም ይህንኑ ከግምት ያላስገባ ፖሊሲና ስትራቴጂ የወረቀት ሲሳይ ሆኖ የመቅረት ዕድል ብቻ ነው ያለው።

  የዚህ ጽሑፍ ዓብይ ትኩረት ከአካባቢው አገሮች በሁለቱ ማለትም በኤርትራና በኢትዮጵያ ላይ ሲሆን፣ ዓላማውም በቀዳሚው አገር የሚከሰቱ በጎም ሆኑ አሉታዊ ክስተቶች በተከታዩ አገር ላይ የሚያመጡትን መልካም አጋጣሚዎች ወይም ችግሮች ማሰስ ይሆናል። ለዚሁ ግብም መላምቶችን እንጠቅሳለን። በማስከተልም የተወሰኑ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን ለመጠቆም ሙከራ ይደረጋል። በቅድሚያ ግን ‘አዲሲቷ’ ኤርትራ በ1991 ዓ.ም ያለሕግ፣ በ1993 ዓ.ም (በዚህ ጽሑፍ የተጠቀሱት ዘመን አቆጣጠር ሁሉም እ.ኤ.አ ነው) በሕግ ከኢትዮጵያ ከተለየች በኋላ ያለውን ሁኔታ ዳሰሳ ማድረግን እናስቀድማለን።

  የኤርትራ ጉዳይ ሦስት አሥርት ዓመታትን በፈጀ የተራዘመ ጦርነት ከኢትዮጵያ በመገንጠል ከተደመደመ በኋላ በሁለቱ አገሮች መካከል በዓለም አቀፉ ማኅበረሰቡ ተስፋ የተጣለበት፣ እንዲሁም ምስጋናን ያገኘ ወዳጅነት ታይቶ ነበር። ይሁን እንጂ በርካታ ጸሐፊዎች በአዲስ ሙሽሮች የጫጉላ ሽርሽር የመሰሉት ይህ ግንኙነት እንደ ጉም ለመበተን የቆየው ሰባት ዓመታትን ብቻ ነበር። አጭር ዕድሜ የቆየው ይህ መልካም ግንኙነት ኢትዮጵያ ልቅ የነበረው የሁለቱን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት ለመቆጣጠር በመሞከሯ መታመም/መሻከር የጀመረ ሲሆን፣ በድንበር አካባቢ ጥቃቅን ግጭቶች በመፈጠራቸው ተጠናክሮ ከፍተኛ ሕይወት በማጥፋት፣ ኢኮኖሚ በማውደምና አያሌ ስደት ከማስከተሉ አንፃር በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ጦርነት ሆኖ ባለፈው የ1998 እስከ 2000 ጦርነት ግባተ መሬቱ ተፈጽሟል። የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንዲሁም የተከሰተውን ጦርነት በቅርብ የሚያውቁ ለጦርነቱ መከሰት መነሾ የነበሩ ሰበቦችን (Casus Belli) በተለያዩ ጊዜያት ጠቅሰዋል። በስፋት ከሚነሱት መካከል የኤርትራ መንግሥት ፀብ አጫሪነትና ብሔራዊ ጀግንነትን በመጠቀም ለውጥ በአንድ ሌሊት ለኤርትራ ለማምጣት የኢትዮጵያን ሀብቶች የመናጠቅ እንቅስቃሴ፣ የ­ዲሞክራሲና የተጠያቂነት አለመኖር፣ በሁለቱ አገሮች የሥልጣን ማማ ላይ ያሉት ቡድኖች ከትጥቅ ትግል ወቅት ጀምሮ የቆየ አለመግባባት መንስዔዎች ሆነው ይጠቀሳሉ። ይሁን እንጂ የድንበር ጉዳይ መሸፋፈኛ ሰበብ (Ostensible Cause) እንደነበር አብዛኞቹ ምሁራን ይገልጻሉ።

  ከሁለቱም ወገኖች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን ሕይወት ያጠፋውን ጦርነት ተከትሎ በመጣው የአልጄርስ ስምምነት ነበር የተቋጨው። ይሁን እንጂ ስምምነቱ መሸፋፈኛ ሰበብ በነበረው የድንበር ጉዳይ ላይ ያተኮረ በመሆኑ ዘላቂ እልባትን ከማምጣት ተጨናግፏል። የወሰን አጥኚ ኮሚቴው ባድመን ለኤርትራ መስጠቱ ቀጣይነት ያለው መግባባት ላይ እንዳይደረስ እንቅፋት ሆኗል። የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ  የወሰን አጥኚ ኮሚቴውን ውሳኔ የፍትሕ መጨናገፍ፣ ኢሕጋዊና ኃላፊነት የጎደለው ሲሉ ገልጸውት ነበር። ስምምነት አለመምጣቱ ሁለቱን አገሮች በበጎ ዓይን እንዳይተያዩ ያደረገ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ የኢሳያስ መንግሥት የኢትዮጵያ መንግሥት ተቃዋሚ የሆኑ ኃይሎችን መሣሪያ በማስታጠቅ፣ በገንዘብ በመደገፍ እንዲሁም አመቺ ሁኔታን በመፍጠር (Harbor) ላይ ይገኛል።

  የተጨናገፈው ተስፋና የአገር ግንባታ ሙከራ

  ከኤርትራ መገንጠል በኋላ ተስፋ ተደርጎ የነበረው ኤርትራን የመገንባት ውጥን ሳይሳካ ይኼው ሁለት አሥርት ዓመታት አለፉ። ዓለም አቀፉ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን (International Crisis Group) እ.ኤ.አ. በ2010 ሪፖርቱ ኤርትራ በሚያስተዳድሯት አካሎች በስንግ የተያዘች ስትሆን፣ መንግሥት የሚያስተዳድራቸው ሕዝቦች ላይ ሳይቀር አመኔታ የለውም ሲል ገልጾታል። የአገር ግንባታ ተስፋም አፈር ድቤ በልቶ መሪው አካል መስዋዕት የሆኑ የኤርትራ ታጋዮችን የነፃነት ዋጋ ረብ የለሽ በማድረግ በአገሪቱ ላይ አበሳን እንዳመጣ በርካቶች ይስማማሉ። ከእነዚህ ውስጥ የኤርትራ ሕገ መንግሥት እ.ኤ.አ 1997 ዓ.ም ሲፀድቅ የሕገ መንግሥት አርቃቂ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ምሁሩ ፕሮፌሰር በረከት ሀብተሥላሴና ኤርትራን በተመለከተ በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ጽሑፎችን የጻፈው ዳን ኮኔልን (Dan Connell) ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። በኤርትራ ያለው የብሔረሰቦችና የሃይማኖቶች አያያዝም ትችቶች የሚሰነዘሩበት ነው።

  የግለሰብ አምባገነንነት ኤርትራን አያላውሳትም

  መቀመጫውን አስመራ ያደረገው መንግሥት በመሪው ኢሳያስ አፈወርቂ እጅግ ከፍተኛ አምባገነንነት መዘውሩ ተይዟል። ግብሩ ከስሙ ፈጽሞ የተራራቀው ራሱን የዲሞክራሲና የፍትሕ ሕዝባዊ ግንባር (ሕግዴፍ) ብሎ የሰየመው የኢሳያስ መንግሥት በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው እንዲሁም በእያንዳንዱ የኤርትራውያን ሕይወት ላይ ቁጥጥር ያደርጋል። ጴጥሮስ ዕቁበዝጊ (Petros B. Ogbazghi) በ2011 ‘Personal Rule in Africa: The Case of Eritrea’ ብለው በጻፉት ጽሑፍ በመሪው ኢሳያስ ከፍተኛ አምባገነንነት በኤርትራ በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለው ግንኙነት አሉታዊ ሆኖ የሚታይ ሲሆን፣ ፕሬዚዳንቱ ብሔራዊ ሸንጎውን ጨምሮ እያንዳንዱ ጉዳዮች ላይ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ ቁጥጥር ያደርጋሉ ብለዋል።

  በተመሳሳይ ዳን ኮኔል ብሔራዊ ሸንጎው ከፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት የተረቀቀውን አዋጅ ማፅደቅ ሁነኛ ተግባሩ ነው ብሏል። በተጨማሪም ከፕሬዚዳንቱ ሌላ በዘርፈ ብዙ ጉዳዩች እጃቸው ረዥም የሆነው የወታደሩ ክፍል ነው። የ2013 የዓለም አቀፉ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን፣ የ2009 የሰብዓዊ መብት ተሟጋች (Human Rights Watch) እንዲሁም “Bertelsmann Stiftung Transformation Index (BTI)” (2014) ሪፖርት እንደሚያመለክቱት ፍርድ ቤቶች በወታደር ክፍል ኃላፊዎች ቁጥጥር ሥር ሲሆን፣ እነዚህ ኃላፊዎች የዳኝነት ተግባራትን ይከውናሉ። ኤርትራ በአምስት ወታደራዊ ዞኖች ተከፍላ በአገሪቱ የፖለቲካ ሕይወት ላይ ወሳኝ ሚና ባላቸው ጄኔራሎች ትተዳደራለች። እነዚህ ጄኔራሎች በጥቁር ገበያ ንግድና ስደተኞችን ማዘዋወር በመሳሰሉ ፍጹም ሕጋዊ ባልሆኑ እንቅስቃሴዎች በስፋት ተሰማርተዋል።

  ዴሞክራሲን ለኤርትራውያን እንደ ቅንጦት የሚያየው የኢሳያስ መንግሥት

  የዲሞክራሲ ተስፋ በኤርትራ ቅዠት ሆኗል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ዴሞክራሲን ለኤርትራ ሕዝብ መስጠት ቅንጦት እንደሆነ ይመለከቱታል። ጴጥሮስ ዕቁበዝጊና ዳን ኮኔል የአስመራ መንግሥት ዴሞክራሲ ከአስተማማኝ የኢኮኖሚ ልማትና ዕድገት በኋላ አግባብ ሆኖ የሚሰጥ እንደሆነ ያምናል ብለዋል። ኤርትራ በታሪኳ አጠቃላይ አገራዊው ይሁን ክልላዊ ምርጫን ለማድረግ አልታደለችም። ሕግዴፍ (PFDJ)ም ብቸኛው ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ሲሆን፣ አንድም ፓርቲ በተቀናቃኝነት የፖለቲካ መድረክን አልረገጠም። አሁን ያለውን ሁነት መቀየር በምንም መንገድ የማይቀበሉት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በ2008 ከአልጄዚራ ጋር ባደረጉት የቃለ መጠየቅ ቆይታ፣ ሀቀኛና ተፈጥሯዊ ሁኔታዎች እስከሚፈጠሩ ድረስ ምርጫ በፍፁም በኤርትራ አይደረግም ሲሉ ተሰምተዋል። 1998­ እስከ 2000 የኢትዮ ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ የመጣው የአልጀርስ ውል ላይ ስምምነት ላይ አለመድረስ የኢሳያስ መንግሥት በ1997 የፀደቀውን ሕገ መንግሥት ተግባራዊ እንዳያደርግ ሰበብ ሆኗል።

  በኤርትራ የሕግ የበላይነት አለመኖር

  የ2013 የዓለም አቀፉ የቀውስ [አጥኚ] ቡድንና “BTI” (2014) ሪፖርት በኤርትራ የፍርድ ሒደት እንደሌለ አስረድቷል። የፕሬዚዳንቱ አዋጅ የሕግ የበላይነትን ተክቶ ተፈጻሚ ይሆናል። የዳኝነት ነፃነት የለም፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጽሕፈት ቤት በዳኝነት አሠራር በቀጥታ ቁጥጥር ያደርጋል። የፖሊሲና የፀጥታ አካላት ከፍተኛ ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። ሒዩማን ራይትስ ዎች በ2009 ሪፖርቱ ፕሬዚዳንቱ የመሻርና የመሾም ሥልጣን በብረት እጃቸው ይዘዋል፡፡ የሕግ አውጪ፣ የሕግ አስፈጻሚና የዳኝነት አካላት ቢኖሩም ማደናገሪያዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል። ፕሮፌሰር በረከት ሀብተሥላሴም በተመሳሳይ መንገድ ገልጸውታል። (‘’The rule of law has gone to the dogs in Eritrea.’’)

  የኢሳያስ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ

  የፀብ አጫሪነትና ወታደራዊ  ነው

  ኤርትራ አምባገነን በሆነ አገዛዝ እግር ተወርች ተይዛለች። አገዛዙ በግዳጅ የወታደራዊ አገልግሎት በመጥፎ መልኩ ታዋቂ ሲሆን፣ ይህ የወታደራዊነት አባዜ በውጭ ግንኙነቱም ላይ ተዛምቷል። ከ1991 ጀምሮ ኤርትራ ከጎረቤት አገሮች ጋር በፀብ አጫሪነቷ ተለይታ ትታወቃለች። ከጥቃቅን የወሰን ግጭቶች እስከ አደገኛ ጦርነት መነሾ ሆና ቆይታለች። በ1996 በሃኒሽ ደሴት ከየመን ጋር፣ በ1996፣ 1998 እና በ2008 ከጂቡቲና ከሱዳን ጋር፣ እንዲሁም ከ1998 ጀምሮ ለሁለት ዓመት ከኢትዮጰያ ጋር አላስፈላጊ ጦርነት ውስጥ ገብታለች። የኤርትራ ፀብ አጫሪ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በአገሪቱ የዴሞክራሲና ተጠያቂነት ከአለመኖር የሚመነጭ ነው። ሳሊህ ኑር (Salih O. Nur) “Foreign Policy of Eritrea: Explained in the Light of Democratic Peace Propostion” (2010) በሚለው ጽሑፋቸው የዴሞክራሲ እሴት አለመኖር፣ የተቋማት የእርስ በርስ ቁጥጥር (Check and Balance) መጥፋትና በሕግ አወጣጥ ወቅት የአሠራር ግልጽነት አለመስፈን አገሪቱ ያለምንም ከልካይ በሽኩቻና ጦርነት ውስጥ እንድትገባ ዳርጓታል ሲሉ ገልጸዋል።

  የሌለን ጠላትነት መፍጠር

  የኢሳያስ መንግሥት ለኤርትራ ሕዝብና ብሔራዊ ጥቅም ጠላት ሆኖ የቆመ አካል ሳይኖር እንዳለ አድርጎ ማቅረብ መታወቂያው ነው። በተለይም ከ1998 ጦርነት በኋላ ኢትዮጵያን በጠላትነት የፈረጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ኤርትራን በወረራ ለመያዝ መሻት እንዳለው ለሕዝቡ ይለፍፋል። በሥልጣን ለመቆየት የአስመራ መንግሥት ይህን መሳዩን ልፈፋ በተደጋጋሚ ያደርጋል። “Eritrea: the Siege State” ብሎ በ2010 ባወጣው ሪፖርት የኢሳያስ መንግሥት ኤርትራ በጠላት እንደተከበበች ያስተጋባል፡፡ ይህም የጦረኝነት ትልሙን ለማሳካትና ብሔራዊ አንድነትን በዚሁ መሠረት ላይ ለማነፅ ሰበብ ሆኖታል ሲል የዓለም አቀፉ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን ገልጿል። በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ ቀዳሚ ተጠቂ ናት፡፡ ምክንያቱም መርከብ ነጋሽ “Eritrea: The Unraveling of Isaias Authored” ብሎ በጻፈው ጽሑፍ (2013) በትክክል እንደገለጸው ኢሳያስ ‘የጠላት ኢትዮጵያ’ ማንነትን (‘Enemy-Villain-Barbarian Ethiopian Identity’) ገንብቷልና ነው።

  የአካባቢውን አገሮች መበጥበጥ የኤርትራ መንግሥት ገጽታ

  ገና ከጠዋቱ ሲንጋፖርን የኢኮኖሚ ዕድገት ሞዴል አድርጎ ፈጣን ኢኮኖሚን ለማምጣት ለአካባቢው አገሮች ምርት የመላክ ዕቅድ የነበረው የኤርትራ መንግሥት  ስኬትን አልጨበጠም። ይኼ ውጥን ሲጨናገፍ ተንኳሹ የኤርትራ መሪ ኢሳያስ ብጥብጥና አለመረጋጋትን ለአካባቢው አገሮች ማሰራጨትን (Exporting Instablity)  ዓብይ ዓላማ አድርጎ ይንቀሳቀሳል። ሳሊህ ኑር (2010) እንደሚስማሙት ይኼ የአስመራ መንግሥት ተግባር አገሪቱ መረጋጋትን የምታደፈርስ አገር (Regional Spoiler) እና ሽብርና ሽብርተኝነትን የምትደግፍ አገር (State Sponsor of Terriorism) የሚል ስያሜ እንድታገኝ አድርጓታል። የኢሳያስ መንግሥት ከፀብ አጫሪነቱ በተጓዳኝ የአካባቢው አገሮች ተቃዋሚ ኃይሎችን እንደሚረዳ እውቅ ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት  በውሳኔ 1907 (2009)፣ 2023 (2011) በኤርትራ ላይ ማዕቀቦችን ጥሏል። ከ2012 እስከ 2013 የፀጥታው ምክር ቤት ባደረገው ምርመራም ኤርትራ አልሸባብን ጨምሮ ለሌሎች ታጣቂ ኃይሎች የፖለቲካዊ፣ የፋይናንስ፣ የሥልጠናና የሎጂስቲክስ ድጋፍ በማድረግ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለማወክ እንደምትንቀሳቀስ የገለጸ ሲሆን፣ ይኼው መንግሥት በ2011 ጥር ወር በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ለማወክ የሽብር ጥቃት ማቀነባበሩን ምክር ቤቱ አውግዟል።

  ኢሳያስ በኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ኃይሎች ተብለው የተሰየሙትን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር፣ የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር፣ ግንቦት ሰባትና የአርበኞች ግንባርን እንደሚረዳ የኢትዮጵያ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲገልጽ ቆይቷል። ከላይ ለመዳሰስ የሞከርነው የኤርትራን መንግሥት ተጨባጭ ሁኔታ ነው። አምባገነንነት፣ የዲሞክራሲ እጦት፣ ወታደራዊ የውጭ ፖሊሲ፣ ፀብ አጫሪነትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፕሬዚዳንት ኢሳያስ መታያ ገጽታ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለ ካለው የአካባቢያዊ ቀረቤታና የባህል ተመሳሳይነት ወደፊት በኤርትራ ላይ የሚከሰቱ መልካምም ሆኑ ክፉ ሁነቶች በኢትዮጵያ ላይ አንድምታ አላቸው። ከዚህ በታች ይህንን እንመለከታለን፡፡

  በኤርትራ የሚከሰቱ ሁነቶች መላምትና በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አንድምታ

  ከፍ ብለን ለመጥቀስ እንደሞከርነው ጎረቤት በሆነችው ኤርትራ የሚከሰቱ ክስተቶች ሰላምም ይሁን ረብሻ፣ የኢሳያስ መንግሥት ለውጥም ይሁን ቀጣይነት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትም አልያም ውድቀት በኢትዮጵያ ላይ በአንድም በሌላም መንገድ ተፅዕኖ አላቸው። ስለሆነም ይህንን ከዚህ በታች መላምቶችን በማንሳት እንመለከታለን። መላምቶቹንም በፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሥልጣን ቆይታና ከፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን መውደቅ በኋላ በማለት በሁለት ዓብይ ክፍሎች ከፍለን በዝርዝር እንመለከታለን። በውጭ አገሮች ሊከሰት የሚችል ጣልቃ ገብነትንም ከግምት ውስጥ እናስገባለን።

  ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሥልጣን ቆይታ

  ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ላለፉት 24 ዓመታት የኤርትራን መንግሥት እየመሩ ነው። ያለተቀናቃኝ የመሪነት ልጓሙን የያዙት ኢሳያስ የአገሪቱ አድራጊና ፈጣሪ (‘Anchor and Creator’) እንደሆኑ ያምናሉ። ከላይ በዳሰሳ እንደተመለከትነው በ24 ዓመታት የሥልጣን ጊዜያት ፕሬዚዳንቱ ወታደራዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲንና ፀብ አጫሪነትን የሙጥኝ ብለው ቆይተዋል። ይህ የመላምት ሐሳብ በፕሬዚዳንቱ ቆይታ ሊከሰቱ ይችላሉ የሚባሉትን ይፈትሻል።

  የጦረኝነት የውጭ ጉዳይ ግንኙነት አዲስ አቅም አግኝቶ ይቀጥላል

  የኤርትራ መንግሥት የግጭት ግንኙነቱን ከጎረቤት አገሮች ጋር አዲስ አቅም አግኝቶ ሊቀጥል እንደሚችል ይታሰባል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የጎረቤት አገሮች የታጠቁ ተቃዋሚ ኃይሎችን በፋይናንስ፣ በሥልጠናና በሎጂስቲክስ መደገፉን አጠናክረው ሊቀጥል ይችላሉ። በዚህም በዋነኝነት የጥቃት ዒላማ የምትሆነው ኢትዮጵያ ነች። የአስመራ መንግሥት ከፍተኛ በጀት በመመደብ የመከላከያ ኃይሉን ማጠናከሩን ሊቀጥል፣ የጠላትነት እሳቤን (Sense of Enmity) በዜጎች ላይ ማስረፁን ሊያጠናክር፣ ጥቃቅን የድንበር ግጭቶችንም ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪም የኤርትራ ወታደሮች አጥቅቶ መሸሽ (Hit and run) ሊያደርጉ ይችላሉ። ይህ መላምት በአገሪቱ ዴሞክራሲና የዴሞክራሲያዊ ተቋማት እስካልተፈጠሩ ድረስ እውነታ ሆኖ ይቀጥላል። ሳሊህ ኑር (2011) እንዳስተዋሉት የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ከገዢው የሕግዴፍ ፓርቲ (ሻዕቢያ) አምባገነን አሠራር መነጠል አይችልም። ጸሐፊው አክለውም የኢሳያስ መንግሥት አምባገነንነትና ዴሞክራሲያዊ ባህርይ አለመኖር የአዲሲቷ ኤርትራን የውጭ ግንኙነት እጅጉን ፀብ አጫሪ አድርጎታል ብለዋል። በዚህ መላምት ሐሳብ በኤርትራ ላይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት የተጣሉ ማዕቀቦች እንዳሉ ይቀጥላሉ። የኤርትራ መንግሥት ከማዕድን ኢንዱስትሪው በሚያገኘው ገቢ ታጣቂዎችን መርዳቱንና መጋጨቱን ሊቀጥል ይችላል። ፕሬዚዳንት ኢሳያስም ማዕቀቦችን የኤርትራን ዕድገትና አንድነት ለማደናቀፍ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ሴራ ነው ማለታቸውን አይተውም።

  የኤርትራ መንግሥት መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ሳያመጣ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳት አደጋ አለው

  በኢሳያስ የሚመራው የኤርትራ መንግሥት ከተደጋጋሚ ፀብ አጫሪነቱ ሳይታቀብ ማዕቀቡ እንዲነሳ በተለያዩ አካላት መጠየቁ ተደጋግሞ ሊስተጋባ ይችላል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኤርትራ መንግሥት  ሰላማዊ  እንደሆነ በመግለጽ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማቲክ ግንኙነት ላይ እየሠራ ነው። ከዚህ በተጨማሪም በኢጋድና አካባቢው ጉዳዩች ላይ መነቃቃትን  ይኼው መንግሥት እያሳየ ነው። ከዚህ በመነሳት የተወሰኑ ምሁራንና (ከእነዚህም መካከል ኸርማን ኮኸን (2013)፣ ዴቪድ ሺን (2013)፣ ዳን ኮኔል (2009) እና ጄሰን ሞስሊን (2014) መጥቀስ ይቻላል)  እና ተቋማት (የዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ ] ቡድን 2010፣ 2013 እና 2014)፣ ለመንግሥቱ ሐዘኔታን እያሳዩ ነው። መነሻቸው ቢለያይም እኒህ አካላት በኤርትራ መንግሥት ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ እየጠየቁ ነው። ለአብነት ኸርማን ኮሀን ኤርትራን አሸባሪዎችን የምትደግፍ አገር ናት ለማለት መረጃዎች የሉም ብለዋል፡፡ እንደ ሌሎች የአካባቢው አገሮች የኤርትራ አመራሮችም የእስልምና አክራሪነትን በሥጋት ዓይን ይመለከቱታል በማለት ማዕቀቡ እንዲነሳ ‘’Time to Bring Eritrea in from the Cold’’ በሚለው ጽሑፋቸው ተማፅነዋል። ሌሎችም በማዕቀቡ የኤርትራ መንግሥት አመራሮች የሚያጡት አንዳችም ነገር የለም፡፡ ሕዝቡ ነው በማዕቀቡ ተጎጂ የሆነው በማለት ተመሳሳይ ተማፅኖ ያቀርባሉ።

  እነዚህ አካላት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ማዕቀቡን እንዲያነሳ፣ የአውሮፓ ኅብረት የልማት ዕቅድ ቀርፆ ድጋፍ እንዲያደርግ፣ እንዲሁም ኢጋድ የኤርትራን እንደገና አባል የመሆን ጥያቄን እንዲቀበል ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ግፊት መሠረታዊ ለውጥ ያመጣል ለማለት አዳጋች ነው። መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ሳያመጣ የኤርትራ መንግሥት ላይ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳት አደጋን ከመጋበዝ እኩል የሚታይ ነው።

  የኢሳያስ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ

  ከእሾህ ወይን፣ ከኩርንችትስ በለስ ይለቀማልን? እንዲል መጽሐፍ የኢሳያስ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል የሚለው የመላምት ሐሳብ እውን መሆኑ ዝቅተኛ ነው። ይህ ከላይ ካነሳነው መላምት ተቃራኒ ሲሆን ለውጥ ሊከሰት እንደሚችል እንገምት። ይህ ለውጥ ከውስጥና ከውጭ በሚነሱ ግፊቶች አስገዳጅነት ሊመጣ ይችላል። ከውስጥ በሚነሳ ግፊት ሳይተገበር የቆየውን ሕገ መንግሥት ተግባራዊ ማድረግ ይኼን ለውጥ ሊያመጣ ሲችል ከውጭ ከኃያላን አገሮች፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት የሚመጣ ጫና ለውጡን እውን ሊያደርገው ይችላል። ከዳያስፖራ የሚገኘው ሁለት በመቶ ታክስ ላይ የተጣለው ማዕቀብ፣ እንዲሁም በማዕድን ሴክተሩ አገሪቱ የምታገኘው ገቢን ለመቆጣጠር የተዘጋጀው መመርያ (Due Diligence Guidelines)፣ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ከመነጠል ጋር ተከትሎ የሚመጣው ኢኮኖሚያዊ ጉድለት ሥጋት ተፈላጊው ለውጥ እንዲመጣ ሊረዳ ይችላል። ይህም ለውጥ ኤርትራ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሌሎች ጎረቤት አገሮች ጋር መልካም ግንኙነት እንድትፈጥር ሊያግዛት ይችላል።

  ኤርትራ ከኢሳያስ አፈወርቂ በኋላ

  የኢሳያስ በሥልጣን መቆየት ዘላለማዊ አይደለም። ዳን ኮኔል የጤና ጉድለት፣ ወይም ሞት አልያም መፈንቅለ መንግሥትና ግድያ ፕሬዚዳንቱን በሥልጣን ላይ እንዳይቆዩ ሊያደርጋቸው ይችላል ብለዋል። የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ሀብታሙ አለባቸው “Before it proves too late for Eritrea…lessons from Somalia’’ (2013) በሚል በጻፉት ጽሑፍ ግን ፍርኃትና በወታደሩ ክፍል ያለው ክፍፍል መፈንቅለ መንግሥትም ሆነ ግድያ የመከሰቱ ዕድሉን አነስተኛ ያደርገዋል ብለዋል። ይሁን እንጂ በጥር 2013 በተወሰኑ ወታደሮች የማስታወቂያ ሚኒስትር (ፎርቶ) መከበብ ለወደፊቱ ይህ አጋጣሚ ፈጽሞ አይኖርም ለማለት አስቸጋሪ ያደርገዋል። ዓለም አቀፍ ተቋማትንና የኤርትራን ፖለቲካ በቅርብ የሚከታተሉትን ሥጋት የገባቸው ግን ከኢሳያስ በአንድም በሌላም መንገድ ከሥልጣን መወገድ በኋላ ሊከሰት የሚችለው ከባድ አደጋ ነው። ዓለም አቀፍ የቀውስ [አጥኚ] ቡድን በ2013 ኤርትራ ከኢሳያስ በኋላ ሊኖራት የሚችለውን ገጽታ በተነተነበት ሪፖርቱ የፕሬዚዳንቱ ከሥልጣን መወገድ በአገሪቷ ላይ መሻሻልን ለማምጣት በቂ እንዳልሆነ ይገልጻል። ለውጥ ለማምጣት የተቀናጀ የፖለቲካ ፓርቲና አንድነት ያላቸው ዳያስፖራዎች አለመኖር ችግር የመፈጠር ዕድሉን ከፍተኛ የሚያደርገው ሲሆን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ለውጥንም አጠራጣሪ ያደርገዋል ሲልም ይተነትናል። ዳን ኮኔልም ተመሳሳይ ሐሳባቸውን ገልጸዋል። ከኢሳይያስ በኋላ ሊከሰቱ የሚችሉ ትንበያዎችን ከዚህ በታች እንመለከታለን። (ሳምንት ይቀጥላል)

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

  spot_imgspot_img
  - Advertisment -