Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርያልገባቸው ያልገባንን ግራ ሲያገቡ

ያልገባቸው ያልገባንን ግራ ሲያገቡ

ቀን:

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሸን (ካፍ) ጋር በተመተባበር በሰው ኃይል ልማት ላይ በጀመሩት የአሠልጣኞች ሥልጠና መሠረት ከሐዋሳ እስከ ድሬዳዋ፣ ከአምቦ እስከ ባህር ዳር፣ ከአዲስ አበባ እስከ መቐለ በተካሄዱ ሥልጠናዎች ላይ የተሳተፍን ባለሙያዎች የረዥም ጊዜ የተጫዋችነትና የአሠልጣኝነት ልምድ ያለን፣ በትምህርት ደረጃ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመማር ላይ የምንገኝ ወይም ትምህርታችንን ፈጽመን በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተን የምንገኝ ነን፡፡ አንዳንዶቻችን ከሥራም አልፎ ቤተሰብ መሥርተን እናስተዳድራለን፡፡

አብዛኛዎቻችን በየሥልጠና ጣቢያዎች ጓደኞች ያሉን በመሆኑ በኮርሱ ወቅት በስልክ ከሥልጠናው ፍጻሜ በኋላ ደግሞ በአካል ተገናኝተን ስለተሰጡን የ‹‹C›› እና የ‹‹B›› ላይሰንስ ኮርሶች ይዘት የሥልጠና ማቴሪያል፣ ኮርሱን ስለሰጡ ኢንስትራክተሮችና የማስተማሪያ ዘዴ፣ ዕውቀት፣ ክህሎትና የግል ባህሪይ በማንሳት (በማማት ሊባል ይችላል) ደረጃ እንነጋገራለን፡፡ በዚህም መሠረት በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ባላቸው ዕውቀት፣ ክህሎና የማስተማር ዘዴና ባህሪ ፍፁም ሞዴል የሚሆኑን እንዳሉ የተሰማን ሲሆን፣ ሌሎቹ ግን ሁሉም በመጠኑ ኖሯቸው ከእኛ ከሠልጣኞች የጎላ ልዩነት ሳይኖረው ግን ፌዴሬሽኑ አበልና ጥቅማ ጥቅም እንዲያገኙ የሚልካቸው ናቸው፡፡ ሦስተኞቹ ደግሞ ተንጠላጥለው እንዲወጡ ካፍና የኢትዮጵያ ፌዴሬሽን መሰላል ያቀረቡላቸው ሠልጣኞችን የሚገላምጡ፣ የሚያንጓጥጡና የሚያዋርዱ ሲሆኑ የኢትዮጵያና የክልል ፌዴሬሽኖች በመሞዳሞድ ኮርሶችን በሥርዓት አልበኛ ኢንስትራክተር መብታችን እንዲደፈጠጥ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ከሚበጀው የሚፋጀው ስለሚባል፣ እንዲሁም ያልገባቸው ሆነው ያልገባንን ግራ ስለሚያጋቡ ከቀጣይ ኮርሶች በፊት ከወዲሁ የመፍትሔ ዕርምጃ እንዲወሰድ አስተያየታችንን እናቀርባለን፡፡

(ኮርሰኞች፤ ከመቐለ)

*********

የፊፋ ማዕበል በካፍና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ይደገም

‹‹ፊፋ አይከሰስ ዙሪክ አይደረስ፤›› ተብሎ ይነገርለት የነበረው ፊፋ ልክ እንደ ዓረብ አገሮች አብዮች፣ በተነሳበት የሰደድ እሳት መለብለብ ጀምሯል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ ብልጭ ቦግ ብሎ ድርግም እንደማይል ተስፋ እናደርጋለን፡፡ እንዲያውም የለውጥ ማዕበሉ በአሠራር ብልሹነትና በንቅዘት የሚወቀሰውን ካፍ (የአፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን) በመናጥ የጎመራ ውጤት እንካችሁ ማለት ይኖርበታል፡፡

 ‹‹የዓሳ ግማቱ ከአናቱ፤›› እንዲሉ የዓለምን ፉትቦል እየመራ የሚገኘው ፊፋ፣ የአፍሪካና የላቲን አሜሪካ የፌዴሬሽን ተወካዮች በተደጋጋሚ በገንዘብና በማቴሪያል እያማለለ ከእርሱ ሥር እንዲሰግዱና መብታቸውን መሬት አንጥፈው እንዲረግማቸው እስከመፍቀድ ደርሰዋል፡፡ ፊፋ ለዓለም ለፉትቦል አጓጉል አካሄድ መከተሉን በማመን ሴብ፣ ብላተር ከዋና ጸሐፊ ባንኪሙን የበለጠ ተቀባይነት እንዳላቸው በማመን ንጉሥ አይከሰስ ሰማይ አይታረስ የሚለውን አባባል ዕውን ሲያደርጉ ታይተዋል፡፡ በተፈጥሮ ሕግ መወለድ፣ ማደግና መሞት ሁሌም ያለ ክስተት በመሆኑ፣ አሁን ጊዜው ሲደርስ የብላተርና የካቢኔያቸው ጓዳ እየተፈተሸ ይገኛል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ጥፋተኝነት ተሰምቷቸው ይሁን ራሳቸው? ከሕጋዊ ተጠያቂነት ለማዳን፣ ባልተጠበቀ ሁኔታ ከሥልጣናቸው በራሳቸው ጥያቄ መልቀቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ይህን አርዓያነት የካፍ ፕሬዚዳንት ኢሳ ሃያቱና ካቢኔያቸውም ራሳቸውን በመፈተሽ የሚታይባቸውን የአሠራር ብልሹነትና ንቅዘት በማመን ከሥልጣናቸው ሊወርዱ ይገባል፡፡ ኢሳ ሃያቱ  ብሔራዊ ቡድናቸው ሲጫወት የሚያንቀላፉ አኅጉራዊ ሳይሆን ብሔራዊ ስሜት የሌላቸው ናቸው፡፡ ይህ የለውጥ ሒደት የኢትዮጵያውን እግር ኳስ ፌዴሬሽን በተለይም የክልል ፌዴሬሽኖችን ሊፈትሽ ይገባል፡፡ አብዛኛዎቹ የክልል ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቶች የሥልጣን ዘመናቸውን ገደብ የተደረገለት አይመስልም፤ ሁሌም ወንበር ላይ አሉ፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቧራ ሲነሳ አንዳንዶቹ ይህን ሁኔታ በማራገብ፣ ከአንዱ ጋር በመወገን ጥቅማቸውን የሚያጋብሱ ናቸው፡፡ እነዚህ ሰዎች በእግር ኳስ ውድቀት ላይ አስተዋጽኦ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ በመሆኑም በፊፋ የታየው የለውጥ መነሳሳት በካፍ፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስና በክልል ፌዴሬሽኖች ላይ ፊቱን በማዞር የሰለቹንን የዕድሜ ልክ ፕሬዚዳንቶች ከእነ ደካማ አሠራራቸው (ካቢኔያቸውን ጨምሮ) ገለል ሊያደርግልን ይገባል እላለሁ፡፡

(የፉትቦል አፍቃሪ አባ ሻረው፤ ከመቐለ)

**********

ይድረስ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገዶች ባለሥልጣን

መንግሥት የኅብረተሰቡን መሠረታዊ ችግሮች የሚፈቱ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የመንገድ ግንባታና ዕድሳት ነው፡፡ ይህም የኅብረተሰቡን የኑሮ ሁኔታ ከሚለውጡ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ ጽሑፌ ስለመሠረተ ልማት ለማስረዳት ሳይሆን፣ በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ በፈረንሣይ ለጋሲዮን አካባቢ ተጀምሮ የቆመው የመንገድ ግንባታ ግራ ስላጋባኝ የሚመለከተው አካል መልስ እንዲሰጥበት ነው፡፡

የፈረንሣይ ለጋሲዮን መንገድ ግንባታ ከታሰበለት የማጠናቀቂያ ጊዜ አልፎ ባለፈው ግንቦት ወር ላይ ‹‹መመረቁ›› ይታወሳል፡፡ መንገዱ በፊት ከነበረበት ችግርና የመኪና አደጋ አንፃር በመሠራቱ ደስተኛ ያልሆነ ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ መልካም ነገርን የሚጠላ ማን ይኖራል? ነገር ግን የመንገድ ግንባታው ወደ ቤላ የሚወስደውን መንገድ ሙሉ ለሙሉ ከጥቅም ውጪ አድርጎታል፡፡ ይህም በጋውን በአቧራ ክረምቱን ደግሞ በጭቃ እንድናሳልፍ ፈርዶብናል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ግን የአካባቢው ሕዝብ ለታክሲ ችግር ተጋልጧል፡፡ በተለይም ከስድስት ኪሎ ወደ ቤላ የሚወስደው መንገድ ሙሉ  ለሙሉ በሚባል መልኩ ከአገልግሎት ውጪ በመሆኑ (በፊት የነበረው አስፋልት ከጥቅም ውጪ ሆኖና ውኃ አቁሮ) ታክሲዎች አልፎ አልፎ ካልሆነ ወደዚያ መስመር አይመጡም፡፡

ከዚያ ይልቅ ከስድስት ኪሎና ከአራት ኪሎ ‹‹በአቋራጭ›› እያሉ የሚጭኑት የትየለሌ ናቸው፡፡ መንገዱ ሳያልቅ ለምን ተመረቀ እላለሁ፡፡ ወደ ቤላ ያለው መንገድ ፈረሰ እንጂ አልታደሰ፤ አልተሠራ፡፡ በተለይማ በርካታ ነዋሪ የሚተላለፍበትና ብዙ ተሸከርካሪ ያስተናግድ የነበረው በተለምዶ ከ‹‹ሕዝብ ሽንት ቤት›› ጀርባ ያለው የዱሮው መንገድ ያሁኑ ትልቅ ጉድጓድ መቼ ሊደፈን ይሆን? አደጋ ወይም ጉዳት ቢያመጣ ማን ሊጠየቅ ነው? ኧረ እባካቹ መላ በሉን፡፡ ሌት ተቀን መንገዱ ተሠርቶ እንዲያልቅ እንዳልተለፋ አሁን ምን ተገኝቶ ነው ሥራው ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ የቆመው?   የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይስጠን፡፡

(ኤርምያስ፤ ከአዲስ አበባ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...