Saturday, April 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየትምህርት ነጋዴዎችን ማን ይቆጣጠራቸው?

የትምህርት ነጋዴዎችን ማን ይቆጣጠራቸው?

ቀን:

በዚህ ዘመን እንደ ዳቦ፣ ስኳር፣ ሳሙና ሁሉ በገበያ ከሚሸቀጡ ንግዶች አንዱ ትምህርት ሆኗል፡፡ የሸቀጦቹን ዋጋ ገበያ እንደሚተምነው ሁሉ የትምህርት ግብይትንም ዋጋ የሚተምነው ገበያ ሆኗል፡፡ የግል ትምህርት ቤቶች የተጋነነ ትርፍ የሚያገኙበት የትምህርት ንግድ መንገደኛውን ሁሉ እየሳበው ሁሉም በየጥጋጥጉ የሚከፍተው፣ ተሰብስቦ የሚጀምረው ንግድ ትምህርት ሆኗል፡፡ በነሐሴ ወር በመገናኛ ብዙኃን ከሰማናቸው ዜናዎች ውስጥ እከሌ የተባለ የግል ኮሌጅ ያለዕውቅና አንድ ወይም ሁለት ዓመት አስተምሮ ተዘጋ፣ እከሌ የተባለው ደግሞ ዕውቅና ባላገኘበት የትምህርት ዘርፍ መዝግቦ በማስተማሩ ተቀጣ፣ ወዘተ የሚሉት ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ የትምህርት ሚኒስቴር የግል ኮሌጆችን ዕውቅና በመስጠት፣ በመቆጣጠርና አጥፍተው ሲገኙም ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን ቢኖረውም ሊቆጣጠራቸው አለመቻሉ ለዘመናት የታዘብነው ሀቅ ነው፡፡ ከአፀደ ሕፃናት እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የሚነግዱትን ተቋማትማ የሚመለከታቸውም፣ የሚቆጣጠራቸውም አካል ያለ አይመስልም፡፡ የፈለጉትን የትምህርት ዋጋ ይተምናሉ፣ ወላጆች ግርግር ቢያበዙም ከማስፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ እስካሁን ድረስ የወሰኑትን ዋጋ የተቃወማቸው አካል ውጤት አግኝቶ እንደማያውቅ ልባቸው ስለሚያውቅ ያለርኅራኄ ዋጋ በመጨመር ማትረፍ ብሔራዊ ግዴታ ሆኖባቸዋል፡፡ ይህ ፍረጃ ሁሉንም የግል ትምህርት ቤቶች የሚመለከት ባይሆንም ብዙኃኑን ይመለከታል፡፡

ትምህርት ገበያ ውስጥ እንደሚሸጠው ሸቀጥ አይደለም፡፡ ትምህርት የዜጋ የሰብዓዊ መብት፣ ተተኪና አገር ተረካቢ ማፍሪያ፣ የአገርን ዕድገት የሚወስን ጉዳይ ነው፡፡ የዜጐችን የትምህርት መብት የማክበር፣ የመጠበቅና የማሟላት ግዴታ የመንግሥት ነው፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት በነፃና በግዴታ፣ ሁለተኛና ሦስተኛ ደረጃ ትምህርት መንግሥት በየጊዜው ቀጣይ በሆነ በጀት ዜጐች እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታ የመንግሥት መሆኑን አገራችንን ጨምሮ አገሮች የፈረሙት ሁሉ አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነድ (International covenant on social economic and cultural rights) ይደነግጋል፡፡ በእነዚህ ዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት የትምህርት መብት ለሁሉም ተደራሽ፣ ፍትሐዊ የሆነ፣ ለሰዎች ሁለገብ ዕደገት የሚረዳ፣ ተፈጥሮአዊ እምቅ ችሎታቸውን የሚያወጡበት ሊሆን እንደሚገባ በግልጽ ተደንግጓል፡፡ ትምህርት ለዜጐች ተደራሽ ይሁን ሲባል ከቦታ አንፃር እያንዳንዱ ዜጋ በሚቀርበው አካባቢ እንዲማር (Geographical accessibility) ከዋጋ አንፃር ለዜጋው ያልከበደ (Affordable)፣ በዜጐች መካከል መሠረታዊ ልዩነት (Inequality) የማያመጣ፣ በቋንቋ፣ በብሔር፣ በገንዘብ አቅም፣ ወዘተ መድልኦ የማይደረግበት ሊሆን እንደሚገባ የመማር መብትን ስፋትና ወሰን የተነተኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ይገልጻሉ፡፡

የመማርን መብት ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር የግል ሴክተሩ የራሱ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የታመነ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍና ብሔራዊ ዕቅዶች የግል ባለሀብቱ እንደ ባለድርሻ አካል ይሳተፋል፡፡ የግል ተቋማቱ ድርሻ ትምህርት ለዜጐች እንዲዳረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ ቢሆንም አገልግሎቱን በነፃ እንዲሰጡ አይጠበቅም፡፡ ይሁን እንጂ ለትምህርት የሚያስከፍሉት ዋጋ ትርፍን ብቻ መነሻ ያደረገ፣ ኅብረተሰቡ ልጁን ላለማስተማር እስኪወስን ድረስ የተጋነነ፣ የትምህርት ግብዓት፣ ጥራት ያለው ትምህርት በሌለበት ሁኔታ የባለአክሲዮኖችን የትርፍ ድርሻ ለማሳደግ ያለመ ሊሆን እንደማይገባ የታመነ ነው፡፡ ትምህርት በየቦታው ያለማንም ተቆጣጣሪነት በገንዘብ እንደሚገዛ ከታሰበ ግን ትምህርትም፣ መማርም ተማሪም ዋጋ አይኖረውም፡፡ አሁን አሁን እየተስተዋለ ያለው የትምህርት ሁኔታ በትምህርት መነገድ አዋጭ ‹‹ቢዝነስ›› ተቆጣጣሪ የሌለው ትውልድ ገዳይ ሥራ ይመስላል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የመንግሥት ድርሻ ወሰን

የመማር ማስተማር ግንኙነት የተለያየ መነሻ ኃልዮት ሊኖረው እንደሚችል ይታመናል፡፡ ከላይ በመግቢያችን የተመለከትነው ከሰብዓዊ መብት አንፃር የሚታየው አንዱ ነው፡፡ ትምህርት የሰብዓዊ መብት እንደመሆኑ መጠን ትምህርት እንዲሟላና እንዲስፋፋ የማድረግ ቀዳሚ ግዴታ የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ግዴታውን ለመወጣት አቅሙ ስለማይኖረው የግል ሴክተሩን ማሳተፍ ተገቢ ቢሆንም፣ የግል ተቋማቱ ትምህርትን ሸቀጥ ብቻ እንዳያደርጉት ጠንካራና ቀጣይነት ያለው ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡ ሁለተኛው ኃልዮት በትምህርት የግል ተቋማቱ የሚሳተፉ ከሆነ የትምህርት ንግዱን የሚመራው ነፃ ገበያ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተለይ ነፃ ኢኮኖሚ የሚከተል የኢኮኖሚ መርሐ ግብር ባላቸው አገሮች ገበያው የትምህርት አቅርቦቱን፣ የትምህርት ዋጋውን፣ ጥራቱን፣ ወዘተ እንዲወስን መተው ያስፈልጋል የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ ይሁን እንጂ ነፃ ገበያን በልቅ በመፍቀድ ትምህርት የችርቻሮ ንግድ እንዳይሆን መንግሥት ተገቢ የሆነ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል፡፡ ያለቁጥጥር ትምህርት ለነፃ ገበያ የሚተው ከሆነ የውድድር መንፈሱ በኢኮኖሚ ጠንካራ የሆነው ብቻ እንዲማር ወይም እንዲያስተምር (Survival of the Fittest) በመፍቀድ የአጠቃላይ የሕዝቡ ደኅንነት ዋጋ አጥቶ ሁሉም ወደ ድህነት ቁልቁለት እንዲፋጠን ያደርገዋል፣ የአገር ሀብት በፍትሐዊነት አይከፋፈልም፣ ኢኮኖሚውም ቢሆን በኑሮ ውድነት እየተወጠረ የኢኮኖሚ መረጋጋት አይኖርም፡፡ መማርና ማስተማር ፖለቲካዊ አንድምታም ይኖረዋል፡፡ አንዳንድ ምሁራን በአጽንኦት እንደሚናገሩት የኒዮሊብራሊስት የፖለቲካ አስተሳሰብ የኅብረተሰብ የዕለት ተዕለት ኑሮ በገበያና በሽያጭ ሕግጋት እንዲገዛ መፍቀድ ነው፡፡ እንደ ታዋቂው የፖለቲካ ተንታኝ ዌንዲ ብራውን ገለጻ፣ “Neolibralism represents a unique governmental and social rationality – one that extends market principles to every reach of human life”  ኒዮሊብራሊዝም የገንዘብ ዕድገትና ገቢ ጭማሪ ላይ ስለሚያጠነጥን ጤና፣ ትምህርት፣ ትራንስፖርት፣ ተፈጥሮ ወይም ሥነ ጥበብ የገበያ ሸቀጦች አድርጐ የመቁጠር አዝማሚያ አለበት፡፡ ይህም የትምህርት ተቋማት ነጋዴዎች የሚከበሩበት፤ ኩባንያዎች እንጂ ታላላቅ ዜጐች የሚፈሩበት የልህቀት ተቋማት እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል፡፡ ያለው እንዲያስተምር የሌለው የሚማሩትን እንዲመለከት በማድረግ በዜጐች መካከል መሠረታዊ ልዩነት (Structural inequality) እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ እንዲህ ዓይነት የኒዮሊብራሊስት አስተሳሰብ አገራችን እከተለዋለሁ ከምትለው የልማታዊ መንግሥት ፍልስፍና አንፃር መንግሥት ለዜጐች ትምህርት ፍትሐዊ በሆነ መልኩ እንዲስፋፋ ያለበትን ግዴታ መና ያስቀራል፡፡

የግል ተቋማቱ ከፍታና ዝቅታ

ትምህርትን በማዳረስ ረገድ፣ ዜጐች የትምህርት መብታቸው በተግባር እውን እንዲሆን በማድረግ ረገድ የግል ተቋማቱ ሚና ሰፊ ነው፡፡ በአገራችን የግል ትምህርት ቤቶች ባይኖሩ ኖሮ መንግሥት የዜጐቹን የመማር መብት ማስተግበር ይችል ይሆን? ትምህርትን የተመለከቱ ፖሊሲዎች፣ የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወዘተ በበጐ መልኩ እንዲተገበሩ የግል ተቋማቱ አስተዋጽኦ ትልቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከቁጥጥር ማነስ፣ ከአንዳንድ ባለሀብቶች ትርፍ ብቻ የማጋበስ ፍላጐት፣ በገበያው ያልተገባ ስም ባተረፉ ኩባንያዎች ምክንያት የግል ተቋማቱ የትምህርት፣ የተማሪዎችና የወላጆች ጠላት እስኪሆኑ ድረስ መታሰብ ጀምረዋል፡፡ የግል ተቋማቱ ምንም የትምህርት ግብዓት ሳያሟሉ በማስታወቂያ ድምቀት ብቻ ወላጆችን ያሳስታሉ፣ ከመሠረታዊ እውቀት ይልቅ ቋንቋ ላይ ያተኩራሉ፣ እምቅ ባህልና እውቀት ባለባት አገር የራስን የማያደንቅና ምዕራባውያንን የሚያነግስ ዜጋ ይፈጥራሉ፡፡ እነዚህ መደምደሚያዎች በሁሉም የታመኑ ሀቆች ቢሆኑም አልፎ  አልፎ የተደረጉ ጥናቶችም ይህንኑ የግል ተቋማቱን ዝቅታ ያብራራሉ፡፡

ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ እ.ኤ.አ. ጃኑዋሪ 2014 “Pre elementary and elementary education in Addis Ababa” በሚል ርዕስ በግዮን ሆቴል ባቀረበው ጉባዔ አቶ ታደለ ፈረደ የተባሉ መምህር የግል ተቋማቱ በአዲስ አበባ ከ61 በመቶ በላይ እንደሚሆኑ ጠቅሰው ትምህርት ቤቶቹ ውጫዊና ውስጣዊ ውስንነቶች እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የግል ትምህርት ቤቶች መምህራንን በትምህርት ዕድል አለመደገፍ፣ በቂ የትምህርት መጻሕፍትና ሌሎች ግብዓቶች አለመኖር፣ በካሪኩለም ዝግጅት የተቋማቱ ተሳትፎ አነስተኛ መሆን አጥኚው የጠቀሷቸው ውጫዊ ምክንያቶች ናቸው፡፡ ከተነሳንበት ርዕስ አንፃር ውስጣዊ ችግሮች ሰሚ ካገኙ አጽንኦት የሚሰጣቸው ናቸው፡፡ የጸሐፊውን ድምዳሜ እንደ ወረደ ካስመቀጥነው እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

“The private sectors operate with high business mentality, which leads to unaffordable or expensive school fees. There are also unhealthy teacher – administration relationship and everything is unilaterally decided by owners without the participation of parents and teaching staff. Teachers have no professional freedom and job security while teaching in private schools.” 

በግርድፉ ሲተረጐም የግል ተቋማቱ ለትርፍ ብቻ በመጓጓት ሕዝቡ የማይችለው የትምህርት ክፍያ መጫን፣ የመምህራንና የአስተዳደር ግንኙነቶች ያለወላጆችና መምህሩ ምክር በባለቤቶቹ በነጠላ ውሳኔ የሚገዛ፣ የመምህራኑ የሥራ ዋስትናና የሙያ ነፃነት አደጋ ላይ የወደቀበት እንደሆነ ምሁሩ ገልጸዋል፡፡ በውይይቱ ላይ የተገኙ ተሳታፊም እንደገለጹት የግል ተቋማቱ መሠረታዊ ትምህርት ከማስተማር ይልቅ የውጭ ቋንቋ (በተለይ እንግሊዝኛ) ላይ እንደሚያተኩሩና በሰበብ ባስባቡ (በዓላት፣ ልዩ ቀናት፣ ፌስቲቫል፣ ወዘተ) የትምህርት ዓመቱን በአግባቡ እንደማይጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡

እነዚህ ችግሮች ለማሳያ ተገለጹ እንጂ የችግሮቹ ስፋት ከግል ተቋማቱ አስተዋጽኦ በላይ በየዓውዱ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ጸሐፊው በተገኘበት አንድ የግል ትምህርት ተቋም የባለድርሻ አካላት ውይይት ላይ ወላጆች ያለምንም የተሟላ የትምህርት ግብዓትና ጥራት ያለአግባብ መክፈላቸውን የሚቃወሙትን ያህል መምህራኑም የሥራ ዋጋቸው በወቅቱ እንደማይከፈላቸው ሲያማርሩ ሲሰማ በግል ትምህርት ቤቶች ጀርባ የማይታዩ ከባለቤቶቹም ሌላ አትራፊዎች መኖራቸውን አስተውሏል፡፡

የችግሩን ምንጭ ፍለጋ

እስካሁን በተመለከትነው የጽሑፉ ክፍል ትምህርት ንግድ ብቻ እንዲሆን ለማድረጋቸው ተጠቃሽ ተጠያቂዎች የግል ተቋማቱ እንደሆኑ እንዳይታሰብ ጸሐፊው ሥጋት አለው፡፡ የችግሩ ምንጭ፣ መነሻውና መድረሻው የግል ተቋማቱ በትምህርት እንዲሰማሩ የፈቀደው ግን የማይቆጣጠረው የመንግሥት አካል ላይ ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ያለው ችግር በሦስት መልኩ ሊታይ ይችላል፡፡ የመጀመሪያው መንግሥት የትምህርትን ጥራት ሙሉ ለሙሉ ለግሎቹ የተወ አስመስሎታል፡፡ የትምህርትን መብት የማስተግበር ቀዳሚ ግዴታ የመንግሥት ከሆነ መንግሥት የሚቆጣጠራቸውን የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለዜጋው የተመቹ፣ የትምህርት ጥራት ያለባቸው፣ ለሌሎች አርዓያ እንዲሆኑ አለማድረጉ ዜጐች ከመንግሥት ያጡትን አገልግሎት ከግል ተቋማቱ እንዲፈልጉ አስገድጓቸዋል፡፡ አብዛኛው የመንግሥት ሹም፣ ኃላፊ፣ ሠራተኛ ልጆቹን ከመንግሥት ትምህርት ቤት ውጪ ለማስተማር መትጋቱ መንግሥት በራሱ በበጀት የሚያስተዳድራቸው ትምህርት ቤቶች የትምህርት ጥራት እንደሌላቸው በቂ አስረጅ ነው፡፡ ሁለተኛው መንግሥት የግል ትምህርት ቤቶቹ ላይ ቁጥጥር የሚያደርገው ችግሩ ካለቀ ከደቀቀ በኋላ መሆኑ ነው፡፡ ተማሪዎች እውቅና በሌለው ተቋም ሲማሩ፣ ወላጆች ሰሚ አጥተው የተጠየቁትን የትምህርት ክፍያ እየተበዘበዙ፣ ትምህርት ቤቶቹ የእውቀትና የሥነ ምግባር ማዕከል መሆናቸው ቀርቶ ከባህል ያፈነገጡ እሴቶች መፈተሻ እየሆኑ እየተመለከተ ዝምታን መምረጡ ችግሩን ውስብስብ አድርጐታል፡፡ ችግሩ በአደባባዩና በየቤቱ ሲደርስ የትምህርት ቢሮ መገናኛ ብዙኃን አንድ ቀን ወጥቶ ማስፈራሪያ ሲያውጅ ይደመጣል፡፡ የትምህርት ቢሮ ክትትል ወጥነት ያለው ተከታታይና ዘላቂ ባለመሆኑ ችግሩ ከማጡ ወደ ድጡ እንዲከፋ አድርጐታል፡፡

ሦስተኛው የችግሩ ምንጭ የግል ተቋማቱ መንግሥት ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንደማይወስድባቸው ልበ ሙሉ መሆናቸው ነው፡፡ መንግሥት ምንም ቢል ምንም የግል ተቋማቱ ያሰቡትን በአንድም በሌላ ለማስፈጸም አቅሙ እንዳላቸው ያስባሉ፡፡ ለዚህ ማሳያ በዚህ ሰሞን ወላጆች ከትምህርት ዋጋ ጭማሪ ጋር በተያያዘ ያቀረቡትን አቤቱታ መመርመር በቂ ነው፡፡ በመገናኛ ብዙኃን ሲገለጽ እንደሰማነው ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮና ለንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ከ1,500 በላይ ቅሬታዎች ደርሰዋል፡፡ የቢሮዎቹ ተወካዮች በሬዲዮ ቀርበው ጉዳዩን እየመረመርን ነው፣ ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆች ጋር ሆነው ችግሮቹን ለመፍታት እንዲጥሩ በአጽንኦት ሲጠይቁ ሰማሁ፡፡ ትምህርት ቢሮ አወጣው የተባለው መመርያ ‹‹ከሐምሌ 1 በፊት ተማሪዎችን እንዳይመዘግቡ፣ ሰባ በመቶ የሚሆነው ወላጅ ካልተስማማበት የትምህርት ክፍያ ጭማሪ እንዲያደርጉ ወዘተ›› የሚል መሆኑን በስማ በለው ሰምቻለሁ፡፡ ቢሮው ይህን ያደረገው አብዛኛዎቹ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ከመዘገቡ በኋላ ሲሆን፣ ወላጆች ተስማሙም አልተስማሙም የተጠየቁትን ክፍያ በሚከፍሉበት ሁኔታ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ የመጣላቸውን መዝግበው ቢሮው ሲጠይቃቸው ይህንን ያህል ተማሪ መዝግበናል፣ ወላጆች መፍቀዳቸውን አያመለክትምን? በሚል ይሞግቱታል፡፡ ከዚህ በመነሳት የግል ተቋማቱ ከሚቆጣጠራቸው የትምህርት ቢሮ በላይ ናቸው፡፡ ወላጆች ምንም ጩኸት ያሰሙ ቢሮው የግል ተቋማቱን በተመለከተ ምንም እንደማይል በሁሉም የታመነ ነው፡፡

ሕግ ነክ መፍትሔዎች

በግል የትምህርት ተቋማት የሚታየው ያልተገባ የትምህርት ክፍያን ጤናማ በሆነ መልኩ መቆጣጠር የሚቻለው መንግሥት ግልጽ ፖሊሲ ሲቀርፅ፣ ባለድርሻ አካላት በጥሞና በኅብረት ሲመክሩና ሊፈጸም የሚችል ግልጽና ዝርዝር ደንብ ሲዘጋጅ ነው፡፡ እስከዚያው በዚህ ጽሑፍ የምንጠቁማቸው መፍትሔዎች ሕግ ነክ ናቸው፡፡ የግል ትምህርት ቤቶቹ የሚያስከፍሉትን ዋጋ ከመቆጣጠር ጋር በተያያዘ ሊወጡ ስለሚችሉ መመርያዎች፣ የመማር መብትን መነሻ በማድረግ መመርያ ባልወጣበት ሁኔታ ወላጆችና የመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች ሊወስዱት ስለሚገባው መፍትሔ ለመጠቆም እንሞክር፡፡

የመጀመሪያው መፍትሔ የግል ትምህርት ተቋማቱን በጠቅላላው በተለይም የሚያስከፍሉትን ክፍያ ከመቆጣጠር አንፃር ዋጋን የተመለከተ መመርያ የማውጣት ሥራ ነው፡፡ ከላይ የተመለከትነው ሁሉንም የግል ትምህርት ተቋማት ሊመለከት እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ የትምህርት ግብዓትና ጥራት ልዩነት በሌለበት ሁኔታ የጉለሌው 300 ብር፣ የቦሌው 1,500 በወር የሚያስከፍሉበት መነሻ ምክንያት ለቁጥጥር ትዕግስት አይፈልግም፡፡ መንግሥት አነስተኛና ከፍተኛ የትምህርት ክፍያ ዋጋን ከመወሰኑ በፊት ለትምህርት ቤቶቹ ደረጃ ሊያወጣላቸው ይገባል፡፡ እንደ ትምህርት ቤቱ የመምህራን ብዛት፣ የትምህርት ጥራት፣ ለትምህርተ ቤቱ ያቀረበው ግብዓት (ማስተማሪያ ክፍል፣ ቤተ መጽሐፍ፣ በክፍል የሚስተናገዱት ተማሪዎች ቁጥር፣ የትምህርት መርጃ መጻሕፍት፣ ላቦራቶሪ ወዘተ)፣ አደረጃጀትና በሥራ ላይ የቆየበት ዘመን ከፍተኛ፣ መካከለኛና ዝቅተኛ በሚል ተከፍለው ሊያስከፍሉ የሚገባው የክፍያ ወሰንም በዚያው መጠን በዝርዝር ሊታይ ይገባዋል፡፡ የትምህርት ክፍያን የሚወስኑ ደንቦች በአብዛኛው አፈጻጸማቸው አከራካሪ ስለሆነ በአንድ በኩል የግል ተቋማቱን ከገበያ የማያስወጣና ፍትሐዊ ትርፍ የሚያገኙበት፣ በሌላ በኩል ምንም ዓይነት የተደራጀ የትምህርት ማዕከል ሳይኖራቸው በጭፍን የሚያተርፉትን ለመከላከልና ትምህርትን ‹ንግድ› ብቻ በማድረግ ዜጐችን እንዳይጐዱ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሁለተኛው መፍትሔ መመርያው በሌለበትም ጊዜ ወላጆችና የመንግሥት ተቋማት ሊኖራቸው የሚችለው ድርሻ ነው፡፡ ወላጆች ፍትሐዊ ያልሆነን ክፍያ በመክፈል፣ በመቃወም፣ በኅብረት አቋም በመያዝና ለመንግሥት አካል አቤቱታ በማቅረብ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ ወላጆች እስካሁን ተቃውሞዋቸውን ለተገቢው አካል ቢያቀርቡም ምንም ለውጥ እንዳልመጣ፣ እንደማይመጣ መታዘባቸው የመፍትሔው ዋና ምንጭ እንደ ችግሩ ሁሉ የመንግሥት ተቋማት ላይ መሆኑን ያሳየናል፡፡ አሁን ጉዳዩ የቀረበላቸውና በተቋቋሙበት አዋጅ ችግሩን ይፈታሉ ተብለው የሚታመኑት የትምህርት ቢሮና የንግድ ውድድርና የሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ የመጀመሪያው ዝርዝር መረጃዎችንና ተጨባጭ ማስረጃዎችን ባለው አሠራር ከወላጆችና ከመምህራን በማሰባሰብ፤ ሁለተኛው የመንግሥት አካል ደግሞ የቀረበለትን ጥቆማ መሠረት አድርጐ የመመርመርና የወንጀል ክስ የማቅረብ ሥልጣን ወይም ግዴታ አለበት፡፡ በአዋጅ ቁጥር 813/2006 አንቀጽ 30 እስከ 32 በተደነገጉት ድንጋጌዎች መሠረት ፀረ ውድድር የሆኑ የንግድ ተግባራት መፈጸማቸውን በማረጋገጥ የንግድ ፈቃድ እንዲሰረዝ፣ ያለአግባብ የተፈጸመው ወይም ሊፈጸም ያለው የትምህርት ክፍያ እንዲታገድ እንዲሁም ጉዳት የደረሰበት ሸማችም እንዲካስ ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ኤጀንሲው እስካሁን ብዙ ከትምህርት ያለአግባብ ክፍያ ጋር በተያያዘ የቀረበለት ጥቆማ ቢኖርም ተገቢውን ምርመራ አከናውኖ ውሳኔ የደረሰባቸው ጉዳዮች አለመኖራቸውን እናስተውላለን፡፡ የኤጀንሲውን ሕዝባዊ ወገንተኝነት ለመመስከር፣ አስተማሪ ውሳኔ የምንሰማበት ጊዜ ከትናንት ቢዘገይም ከነገ መርፈድ የለበትም፡፡ ትምህርትን በመነገድ፣ በመሸጥ፣ በመለወጥና በመቸርቸር በዜጐች መብት ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት የሚጥሩትን መንግሥት ሃይ ሊላቸው ይገባል፡፡ 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

               

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...