በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸውን ሕንፃ በአንድ አካባቢ ለማድረግ የተለያዩ እንቅስቃስዎችን እያደረጉ ነው፡፡ 19 ከሚሆኑት ባንኮችና ወደ 20 ከሚጠጉት ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ የአብዛኛው የፋይናንስ ተቋማት መናኸሪያ ይሆናል ተብሎ የተመረጠው ደግሞ ሠንጋተራና በዙሪያው ያሉ አካባቢዎች ናቸው፡፡
ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርብ ርቀት ላይ ይገነባሉ ተብለው በሚጠበቁት ረዣዥሞቹ ሕንፃዎች ቀደም ብሎ አዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ግንባታቸውን አጠናቅቀው ገብተውበታል፡፡
በዚሁ አካባቢ ዳሸን ባንክ የሕንፃ ግንባታውን የማጠናቀቂያ ሥራ እያከናወነ ሲሆን፣ በቅርቡ ወደ አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወጋገን ባንክ ከአዲስ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ፊት ለፊት እያስገነባ ያለው ግዙፍ ሕንፃ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡
ከሸራተን አዲስ ወደ ፋይናንስ ተቋማት መንደር የተነሳው ምስል እንደሚያሳየው ከብሔራዊ ስታዲየም ጀምሮ እስከ ሠንጋተራ ያለው አካባቢ አሁንም የአገሪቱ የፋይናንስ ተቋማት ዋና ማዘዣ ስለመሆኑ የሚያመለክትም ነው፡፡
ለምሳሌ ደቡብ ግሎባል ባንክ፣ ኦሮሚያ ኢንሹራንስ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት፣ አዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ፣ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ዋና መሥሪያ ቤቶቻቸው በዚሁ አካባቢ የሚገኝ ነው፡፡
የአካባቢውን ገጽታ በከፍተኛ ደረጃ ይቀይራሉ የተባሉት አዳዲስና ከ30 ወለል በላይ ፎቆች የሚኖራቸው ሕንፃዎችን ለመገንባት የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት ቦታ ተረክበዋል፡፡ ዲዛይን መረጣ ያደረጉና ወደ ግንባታ የገቡም አሉ፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገነቡት ረዣዥም ሕንፃዎች ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይወጣባቸዋል ተብሎ ይገመታል፡፡ በዚሁ አካባቢ የዲዛይን ሥራዎች አጠናቀው ወደ ግንባታ የገቡና ለግንባታ በመዘጋጀት ላይ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት መካከል ሕብረት ባንክ 1.2 ቢሊዮን ብር በሆነ ዋጋ ባለ 32 ወለል ሕንፃ ግንባታ መጀመሩ ይጠቀሳል፡፡ ናይል ኢንሹራንስም ግዙፉን ሕንፃ ለመገንባት የመሠረት ግንባታ ጀምሯል፡፡ ከእሱ ጎን ደግሞ ዘመን ባንክ በተመሳሳይ እየገነባ ነው፡፡ ንብ ባንክም በተመሳሳይ ወደ ግንባታ ሥራ ገብቷል፡፡ አቢሲኒያ ባንክም የራሱን ሕንፃ ይገነባል፡፡ የኦሮሚያ ሕብረት ሥራ ባንክ ዲዛይኑን አጠናቆ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ረዥሙ ሕንፃ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ባለ 42 ወለል ሕንፃ ለመገንባት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የመሠረት ድንጋይ አኑሯል፡፡ ሌሎቹም በዚህ አካባቢ ይከተላሉ፡፡ የእነዚህ ሕንፃዎች መገንባት የአዲስ አበባን ገጽታ በመለወጥ የራሱ የሆነ ድርሻ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአሁኑ ወቅት በዚህ አካባቢ ያሉ የፋይናንስ ተቋማትና የግንባታ ሥፍራዎች
- በመጠናቀቅ ላይ ያለው የወጋገን ባንክ ሕንፃ
- አቢሲኒያ ባንክ ከሃያት ሪል ስቴት የገዛው ሕንፃ
- የኢትዮጵያ መድን ድርጅት አዲሱ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ
- የደቡብ ግሎባል ዋና መሥሪያ ቤት የሚገኝበት ሕንፃ
- በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ ሕንፃ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚገነባበት ሥፍራ
- የአዋሽ ባንክና ኢንሹራንስ ኩባንያ ሕንፃ
- የሕብረት ባንክ የሚገነባበት ሥፍራ
- ንብ ባንክ የሚገነባበት ሥፍራ
- ዘመን ባንክ የሚገነባበት ሥፍራ
- ናይል ኢንሹራንስ የሚገነባበት ሥፍራ
- የኦሮሚያ ባንክ የሚገነባበት ሥፍራ
- ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ
- በቅርቡ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የዳሸን ባንክ ዋና መሥሪያ ቤት
- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ