Sunday, April 14, 2024

የሞት ሽረት የተባለው የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

እያኮበኮበ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይ የማኑፋክቸሪንግ፣ ከግብርና ዘርፍ ደግሞ የእንስሳት ሀብት ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡

ሰሞኑን ለውይይት የቀረበው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱን ወደፊት ማራመድ ካስፈለገ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት መስጠት ‹‹የሞት ሽረት ጉዳይ ነው›› በማለት በኃይለ ቃል ደረጃ አስቀምጧል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ተብለው በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የተዘረዘሩት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ስኳርና ኢታኖል፣ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ፣ አግሮ ፕሮሰሲንግና ሲሚንቶ ናቸው፡፡

ከእነዚህ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች በተጨማሪ ከግብርና ምርቶች ኤክስፖርት መንግሥት ከፍተኛ ገቢ ቢጠብቅም ዕቅዱን ማሳካት አልተቻለም፡፡

ከገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ እንደሚያስረዳው፣ ከ2003 ዓ.ም. እስከ 2006 ዓ.ም. በነበሩት የዕቅድ ዓመታት የአገሪቱ ኢኮኖሚ በየዓመቱ በአማካይ በ10.1 በመቶ አድጓል፡፡ ለተመዘገበው ዕድገት የግብርናው ዘርፍ በአማካይ በየዓመቱ 6.6 በመቶ በማደግ ዋናውን ድርሻ ይዟል፡፡ ይህም ቢሆን ግን፣ ታቅዶ ከነበረው 11 በመቶ ጋር ሲነፃፀር የተገኘው ውጤት ዝቅተኛ ነው፡፡

የወጪ ንግድ ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ አነስተኛ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ በ2003 ዓ.ም. የወጪ ንግድ አፈጻጸም አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት የነበረው ድርሻ 17 በመቶ ደርሶ የነበረ ሲሆን፣ በ2006 ዓ.ም. ወደ 11.7 በመቶ አሽቆልቁሏል፡፡

ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የተወሰደው የወጪ ምርቶችን በበቂ መጠንና ዓይነት ለገበያ ለማቅረብ ያለው አቅም፣ አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው በማለት የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ያስረዳል፡፡

በ2006 በጀት ዓመት የወጪ ንግድ ከአጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ 11.7 በመቶ ነው፡፡ ነገር ግን የገቢ ንግድ በአንፃሩ 29.5 በመቶ በመሆኑ የንግድ ሚዛን ጉድለቱ 17.8 በመቶ ነበር፡፡ በአጠቃላይ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ መሆንና የገቢ ንግድ ዕድገት ማሳየቱ የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛኑ እየሰፋ እንዲሄድ ማድረጉ በመረጃው ተመልክቷል፡፡

የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በሚጠናቀቅበት 2007 ዓ.ም. ይህ ክስተት በስፋት ታይቷል፡፡ የ2007 ዓ.ም. የበጀት ዓመቱ ተጠናቆ የኢኮኖሚው ሁኔታ ባለመተንተኑ የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም እንደማሳያ ቀርቧል፡፡ በ2007 ዓ.ም. ከወጪ ንግድ የታቀደው ስምንት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ቢሆንም፣ በመጀመርያዎቹ ዘጠኝ ወራት 2.2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ተገኝቷል፡፡ ይህ አፈጻጸም በ2006 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከተገኘው 2.3 ቢሊዮን ዶላር ጋር ሲነፃፀር በ4.6 በመቶ ዝቅ ያለ ነው፡፡ ‹‹እስካሁን በታየው የኤክስፖርት አፈጻጸም ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ በ2006 ዓ.ም. ከተገኘው አይዘልም፤›› በማለት የሁለተኛው ዕቅድ ሰነድ ያመለክታል፡፡

በአንፃሩ በ2007 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ለገቢ ንግድ 16.4 ቢሊዮን ዶላር ወጪ ተደርጓል፡፡ ይህም ከ2006 ዓ.ም. ተመሳሳይ ወቅት ከወጣው በ4.3 ቢሊዮን ዶላር ብልጫ አለው፡፡ በበጀት ዓመቱ ከወጪ ንግድ የተገኘው ገቢ ለወጪ ንግድ የወጣውን ወጪ መሸፈን የቻለው 13.3 በመቶ በቻ ነው፡፡

የወጪ ንግድ አፈጻጸም ዝቅተኛ ሊሆን የቻለው የዓለም አቀፍ የቡናና የወርቅ ገበያ በመቀዛቀዙ ሲሆን፣ በማኑፋክቸሪንግ በኩል ደግሞ በጨርቃ ጨርቅና በቆዳ፣ እንዲሁም ከስኳር ልማት ይጠበቅ የነበረው አፈጻጸም ደካማ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡

የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ለውይይት ያቀረበው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ይህንን አፈጻጸም እንዳለፈ ታሪክ በመቁጠር፣ ፍጹም የተጋነነ ዕቅድ ይዞ ቀርቧል፡፡

አዲሱ ዕቅድ ቀደም ባለው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከተካተቱ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ተጨማሪ አራት የማኑፋክቸሪንግ ልማት ዓይነቶችን አቅፏል፡፡ እነሱም የባዮቴክኖሎጂ፣ የፔትሮ ኬሚካል፣ የቴሌኮምና የኤሌክትሮኒክስ መሥሪያዎች የሚመረቱባቸው ፋብሪካዎችን ማቋቋም ናቸው፡፡ በሚኒስትር ዴኤታ ማዕረግ የብሔራዊ ፕላን ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ጌታቸው አደም ባለፈው ሳምንት መጀመርያ፣ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ባቀረቡት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትንታኔ መሠረት፣ የባዮቴክኖሎጂ ምርምር በማካሄድ ለግብርናውና ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ዕቅድ ስኬት ወሳኝ ሚና የሚኖራቸውን መሣሪያዎች የሚያመርት ፋብሪካ ይገነባል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ወሳኝ ግብዓት በሆኑት ፔትሮሊየምና ኬሚካል ራሳቸውን የቻሉ ግዙፍ ፋብሪካዎች ይቋቋማሉ ብለዋል አቶ ጌታቸው፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር መብራህቱ መለስ በቅርቡ እንደገለጹት፣ ቴሌቪዥንን ጨምሮ በርካታ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች በአገር ውስጥ መመረት ጀምረዋል፡፡ እነዚህ ምርቶች እንዲስፋፉም መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ፕሮግራም ይዟል፡፡ በቴሌኮም ምርቶችም በቅርቡ በተቋቋመው የአይሲቲ ፓርክ በርካታ ምርቶች ይመረታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

እነዚህና ቀደም ብለው የተጀመሩትን የማኑፋክቸሪንግ ምርቶች በሰፊው እንዲመረቱ በማድረግ አገሪቱ ከዘርፉ እጅግ እንድትጠብቅ የሚያደርግ ዕቅድ ተነድፏል፡፡ አቶ ጌታቸው እንዳሉት፣ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አሁን በማበርከት ላይ ከሚገኘው 4.6 በመቶ ወደ ስምንት በመቶ ያድጋል፡፡ ዘርፉ እ.ኤ.አ. በ2017 ደግሞ በአራት እጥፍ እንደሚያድግ መተንበዩን አቶ ጌታቸው ተናግረዋል፡፡

በዚህም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በወጪ ንግድ በኩል ያለው ድርሻ አሁን ካለበት አሥር በመቶ ወደ 25 በመቶ ከፍ እንደሚል ታቅዷል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 ደግሞ በወጪ ንግድ ያለው ድርሻ ወደ 40 በመቶ ያድጋል፡፡

ከዚህ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በ2012 ዓ.ም. አራት ቢሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዷል፡፡ ዘርፉ የሚቀጥረው የሰው ኃይል አሁን ካለበት 350 ሺሕ፣  በ2012 ዓ.ም. ወደ 800 ሺሕ የሰው ኃይል ያድጋል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡

ይህ ዕቅድ እንዲሳካ በዋነኛነት በግሉ ዘርፍ ላይ ተስፋ ተጥሏል፡፡ በተጠናቀቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የግሉ ዘርፍ በኢንዱስትሪ ዘርፍ እንዲሳተፍ ለማድረግ ቢሞከርም፣ በዘርፉ የሚታዩ በርካታ ችግሮች ባለመፈታታቸው ለውጥ በሚያመጣ ደረጃ ተሳትፎው አልቀጠለም፡፡

በሁለተኛው ዕቅድ ላይ ለግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ማነቆዎች ተብለው የተለዩትን ጉዳዮች ለመፍታት መንግሥት መወሰኑን አቶ ጌታቸው አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህ ማነቆዎች መካከል የመሬት አቅርቦት፣ የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥና ፋሲሊቴሽን፣ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ አገልግሎት አሰጣጥ ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ መንግሥት ቁርጠኛ አቋም መያዙ ተብራርቷል፡፡

በዚህ ዘርፍ ቢሰማሩ ውጤት ሊያመጡ ይችላሉ የተባሉ የግል ዘርፍ ተዋናዮች እየተመለመሉ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ባለሀብቶች በንግድና በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የተሰማሩ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ መንግሥት በማስተባበር ላይ ይገኛል፡፡ ከአገር ውስጥ ባለሀብቶች በተጨማሪም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት በርካታ የውጭ አገር ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የሚደረግ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ለሚገቡ ባለሀብቶች መንግሥት የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማቋቋም ላይ ይገኛል፡፡ ዞኖቹ በአዲስ አበባ፣ በሐዋሳ፣ በኮምቦልቻ፣ በመቐለ፣ በጂማ፣ በአዳማ፣ በድሬዳዋ በመገንባት ላይ ሲሆኑ፣ ግንባታውን የሚያካሂደው የኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ቀጣና ኮርፖሬሽን በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ መመርያ ይሰጠዋል፡፡

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር ከፍተኛ ባለሥልጣን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገር በቀል ማኑፋክቸሪንግና በኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ላይ ተስፋ ተጥሏል፡፡ ተስፋ የተጣለበትን ምክንያት ሲያብራሩም፣ በአገሪቱ እየተካሄዱ ያሉ የግንባታ ሥራዎች 60 በመቶ ያህል በአገር ውስጥ አቅምና ፋይናንስ ሊሠሩ የሚችሉ ቢሆንም፣ አብዛኛዎቹ ፕሮጀክቶች እየተካሄዱ ያሉት ግን በውጭ አገር ኩባንያዎችና ከውጭ በሚገኝ ብድር ነው፡፡ ይህን ለመቀየር መንግሥት የግል ዘርፉን ሚና እንደሚያሳድግ ተገልጿል፡፡

በኮንስትራክሽን ዘርፍ ለምሳሌ በመንገድና በግድቡ ሥራዎች ትልቅ ወጪ የሚጠይቀው የሲቪል ኢንጂነሪንግ ሥራ ነው፡፡ ይህም በአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች አቅም ቢካሄድ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርካታ የኢንጂነሪንግ ዕቃዎች በአገር ውስጥ ሊመረቱ የሚችሉ ቢሆንም፣ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እየወጣባቸው ነው፡፡

ይህንን ችግር በመፍታት የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በኃይል ማመንጫ ግድቦች፣ በመንገድና በድልድይ ግንባታዎች፣ በመስኖ ግድብ ሥራዎችና በመሳሰሉት ተሳትፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ዕቅድ መያዙን ባለሥልጣኑ አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የግል ኩባንያዎች ለኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫና ለስኳር ፕሮጀክቶች የሚሆኑ ዕቃዎችን፣ እንዲሁም በአጠቃላይ የኢንጂነሪንግ ምርቶችን ማምረት እንዲችሉ ዕቅድ ተነድፏል፡፡

‹‹ይህ አሠራር የአገሪቱን የብድር ጫና እንዲቀንስ ከማድረጉም በላይ፣ የአገር ውስጥ የግንባታ አቅምን ማሳደግ ያስችላል፤›› በማለት ባለሥልጣኑ ቀጣዩን የመንግሥት አቅጣጫ ጠቁመዋል፡፡

ከማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ባልተናነሰ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተመልክቷል፡፡ የመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የአገሪቱ ዋነኛ የዕድገት ምንጭ የግብርና ዘርፍ እንደሚሆን፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ ከግብርና ዘርፍ በላይ በፍጥነት በማሳደግ ለፈጣን ኢንዱስትሪያላይዜሽንና የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ መሠረት መጣል እንደሆነም አስቀምጧል፡፡ በታቀደው ደረጃ ባይሆንም በ2003 ዓ.ም. በኢኮኖሚ ዕድገት ውስጥ 45 በመቶ የነበረው ግብርና በ2006 ዓ.ም. ወደ 40 በመቶ ዝቅ ብሏል፡፡ የአገልግሎት ዘርፍ በተመሳሳይ ወቅት ከነበረበት 45 በመቶ ወደ 46 በመቶ ከፍ ብሏል፡፡ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማደግ ለግብርና ዘርፍ ዕድገት ወሳኝ እንደሆነ የተተነተነ ሲሆን፣ አነስተኛ ገበሬዎች የማያመርቱት ምርት በ2007 ዓ.ም. ከተተነበየው 270 ሚሊዮን ኩንታል ዋና ዋና ሰብሎች ምርት፣ በ2012 ዓ.ም. 406 ሚሊዮን ኩንታል ማድረስ  ተጠቃሽ ነው፡፡

በዘርፉ ያሉ ችግሮችን በመፍታትም ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በማቅረብ፣ እንዲሁም የመስኖ ሥራዎችን በማስፋፋት በተለይ በቆላማ ቦታዎች ሜካናይዝድ እርሻዎችን በማስፋፋት ምርታማነት ለመጨመር ተስፋ ተጥሏል፡፡

በተለይ ግን በመጀመርያው ዕቅድ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው የእንስሳት ሀብት፣ በሁለተኛው ዕቅድ ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት እንዳላት ይታወቃል፡፡ ይህ ዘርፍ ከቡና ምርት ቀጥሎ አሥር ሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶና አርብቶ አደሮች የሚተዳደሩበት ነው፡፡

በዚህ የእንስሳት ሀብት የምርት ሰንሰለት የወተት፣ የሥጋና  የቆዳ ምርቶች የሚገኙ በመሆናቸው፣ እስካሁንም ትኩረት አለመደረጉ የሚያሳስባቸው በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ የእንስሳት ሀብት በዋነኛነት የሚታየው ችግር የእንስሳት መኖ አቅርቦት አናሳነትና  ዝቅተኛ የአረባብ ዘዴ ነው፡፡

የሉና ኤክስፖርት ስሎውተር ሐውስ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋልደት ሐጎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በዘርፉ ያሉት ችግሮች ቢቀረፉ በወተት ሀብት፣ በሥጋ ምርትና በቆዳ ውጤቶች ከፍተኛ ምርት ማግኘት ይቻላል፡፡

ነገር ግን አቶ ተስፋልደት እንዳሉት፣ ምንም ዓይነት ዘመናዊ የመኖ አቅርቦት ባለመኖሩ በዘርፉ ያለው ሀብት እየባከነ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በዚህ ዘርፍ የሚታየውን ችግር በመቅረፍ ባለሀብቶች የእንስሳት እርባታ ማዕከላት እንዲያቋቁሙ በመደገፍ፣ ከዘርፉ ከፍተኛ ጥቅም ለማግኘት አቅዷል፡፡

በመጀመርያው ዕቅድ እንደተስተዋለው ከፍተኛ የእንስሳት ሀብት ያላት ኢትዮጵያ በርካታ የወተት ተዋጽኦዎችን ከውጭ ታስገባለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሥጋ ምርት የተሰማሩ ስድስት ያህል ዘመናዊ ቄራዎች በእንስሳት አቅርቦት እጦት ምክንያት ከአቅማቸው በታች እየሠሩ ነው፡፡ በርካታ የቆዳና የሌዘር ፋብሪካዎች በአቅርቦትና በጥራት ማነስ ሲማረሩ፣ መንግሥት በመጀመርያው ዕቅድ ዘመን ትኩረት ሰጥቶ የነበረ በመሆኑ፣ ቆዳ ከውጭ ለማስገባት ተገዶ ነበር፡፡

ይህ አካሄድ የሚያዋጣ ባለመሆኑ መንግሥት ዘርፉን በሚገባ ለመጠቀም አዲስ አቅጣጫ ሊይዝ መቻሉን፣ የዘርፉ ተዋናዮች በአዎንታ ተቀብለውታል፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን አንኳር ሆነው ከቀረቡ ነጥቦች መካከል መንግሥት የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ ከፍተኛ ፍላጎት ቢኖረውም፣ ግዙፎቹን የልማት ድርጅቶች ይዞ መቀጠል መወሰኑ ነው፡፡

ከዚህም በላይ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው እንዳሉት፣ የግብርና ምርቶችን እሴት በመጨመር ለውጭ ገበያ ማቅረቡ ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ መንግሥት ስትራቴጂ ያላቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ኢንተርፕራይዝ፣ ባንኮችና ኢንሹራንስ ተቋማት፣ ኢትዮ ቴሌኮም፣ ኤሌክትሪክ ኃይል ተቋማትን ይዞ እንደሚቀጥል ተተንትኗል፡፡ ከእነዚህ በተጨማሪም በፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ሥር የሚገኙትን ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅትና የትምህርት መሣሪያዎች ማምረቻ ድርጅትን ጨምሮ፣ 16 ኢንተርፕራይዞች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ሆነው አምስቱን ዓመት ይሻገራሉ፡፡

የፕራይቬታይዜሽንና የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ 16 ኢንተርፕራይዞች ይቀጥላሉ፡፡ ብሔራዊ አልኮል፣ አዳሚቱሉ ፀረ ተባይ፣ ኮስቲክ ሶዳ፣ አዋሽ መልካሳ፣ ላንጋኖ የሚገኘው ሆቴል፣ አዶላ ወርቅ፣ ሸበሌ ትራንስፖርትን ጨምሮ 15 ድርጅቶች ለሽያጭ ይቀርባሉ፡፡

በተደጋጋሚ ለሽያጭ ቀርቦ የነበረው ግዮን ሆቴል በመንግሥት እንዲለማ መወሰኑን አቶ ወንዳፍራሽ ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ በተካሄደው ውይይት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው ከሰብሳቢዎቹ አንዱ ነበሩ፡፡ አቶ ተፈራ ከተሳታፊዎች መካከል መንግሥት የግሉን ዘርፍ ለማሳተፍ እንደሚፈልግና መንግሥትም የልማት ድርጅቶችን ይዞ ለመቀጠል ማቀዱ የተምታታ አይሆንም ወይ? በአንድ በኩል ሊበራሊዝም በሌላ በኩል አብዮታዊ ዴሞክራሲ የተንፀባረቀበት ዕቅድ አይደለም ወይ? ተብለው ተጠይቀው ነበር፡፡

አቶ ተፈራ ሲመልሱ፣ ‹‹የእኛ መንግሥት ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ነው፡፡ በዚህ የፖለቲካ ፍልስፍና መንግሥት የገበያ ጉድለት ባለባቸው ዘርፎች ገብቶ ክፍተቱን ይሞላል፡፡ በዚህ መሠረት ነው የግሉ ዘርፍ በማይገባባቸው ዘርፎች መንግሥት እየገባ፣ የግሉ ዘርፍ በሚገባባቸው ዘርፎች መንግሥት ደግሞ ድጋፍ እየሰጠ ይቀጥላል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በዕቅዱ ላይ የተለያዩ ስብሰባዎች ባለፈው ሳምንት የተካሄዱ ሲሆን፣ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተናጠል ከከፍተኛ ባለሀብቶችና ከዕርዳታ ሰጪዎች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተካሄዱትና በሚካሄዱት ውይይቶች ጠቃሚ የሚባሉ ሐሳቦች በዕቅዱ ላይ ተካተው በመጪው ዓመት መጀመሪያ ላይ በፓርላማ ይፀድቃል ተብሎ ዕቅድ ተይዟል፡፡ የተዘጋጀው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአጠቃላይ 194 ገጾች አሉት፡፡ ይህንን ዕቅድ ማሳካት ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሠለፍ እያደገች ያለችውን ጥረት ያፋጥናል ተብሎ በከፍተኛ ደረጃ ተስፋ ተደርጎበትል፡፡ ይህ ዕቅድ እ.ኤ.አ. በ2020 የሚጠናቀቅ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከአምስት ዓመታት በኋላ እ.ኤ.አ. በ2025 መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ አልማለች፡፡ ይህም የሞት ሽረት ጉዳይ ሆኗል፡፡

ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሊያሳካ ካለማቸው ግቦች መካከል የሞባይል ተጠቃሚዎችን ቁጥር አሁን ካለው 40 ሚሊዮን ወደ 103 ሚሊዮን ማሳደግ፣ የአገሪቱን የመንገድ ኔትወርክ ሽፋን ከ120 ሺሕ ኪሎ ሜትር ወደ 220 ሺሕ ኪሎ ሜትር ማሳደግ ተጠቃሽ ነው፡፡ የአገሪቱን የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት አቅም ከ2,310 ሜጋ ዋት ወደ 17,347 ሜጋ ዋት መጨመር አንዱ ግብ ሲሆን፣ የባቡር ኔትወርኩን ከዜሮ ኪሎ ሜትር ወደ 2,702 ኪሎ ሜትር ማሳደግም ይገኝበታል፡፡ የግብርና ምርቶችን ከ207 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 406 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግን በዕቅዱ የመጨረሻ ዘመን ለማሳካት፣ ከማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድ አራት ቢሊዮን ዶላር ማግኘት፣ የአገር ውስጥ ምርት ዕድገትን 11 በመቶና ቁጠባን 26.6 በመቶ ማሳደግ፣ የድህነት መጠንን በ16 በመቶ ማድረስ የመሳሰሉት የዕቅዱ ግቦች አካል ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -