Monday, September 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች

  ካናዳና ኢትዮጵያ ከአምስት አሥርት በኋላ

  - Advertisement -spot_img

  በብዛት የተነበቡ

  ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ›› በማለት የጀመሩትን ንግግራቸውን በዚያው በአማርኛ ቋንቋ ይቀጥሉበታል ብለው ያሰቡ ጥቂት ይመስላሉ፡፡ የብዙ ሰዎች ግምት ምናልባት አንዳንድ ሰዎች እንደሚያደርጉት በአማርኛ መግቢያ አድርገው ተጋባዡን እንግዳ ፈገግ ለማሰኘት ይሆናል የሚል ነው፡፡

  የቆዳ ቀለማቸው ነጭ የሆነው ዲፕሎማት ግን የአማርኛ ንግግራቸውን አላቆሙም፡፡ ቁጥራቸው 500 አካባቢ የሆኑት ተጋባዥ እንግዶች ጉድ እስከሚሉ ንግግራቸውን በአማርኛ ቀጠሉበት፡፡

  አምባሳደር ዴቪድ አሸር በአዲስ አበባ ረዘም ያለ ቆይታ ካላቸው ዲፕሎማቶች መካከል የሚመደቡ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የካናዳ አምባሳደር ሆነው በቆዩበት ጊዜ የዲፕሎማሲ ሥራ ብቻ አልነበረም የሚሠሩት፡፡ የአገሩን ባህል፣ ቋንቋና አመጋገብም በደንብ ለምደውታል፡፡ በብዛት ከሚመገቡት ውስጥ እንጀራ ቀዳሚው ነው፡፡ አለባበሳቸው ሙሉ ልብስ ከመሆኑ ውጪ የሰላምታ አሰጣጥ ሥነ ሥርዓት የአንድ ታዋቂ የአገር ሽማግሌ ይመስላል፡፡

  ‹‹እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ለኢትዮ ካናዳ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓለም እንኳን አደረሳችሁ፤›› ቀጠሉ፡፡ ጥርት ያለ የአማርኛ ንግግራቸው ታዳሚዎችን ያስደመመ ሲሆን፣ በከፍተኛ ጭብጨባ የታጀበ ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የካናዳ ግንኙነት እንዴት እንደተጀመረ፣ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝና የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በመልካም መከባበርና የጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አስምረውበታል፡፡

  ‹‹ኢትዮጵያ የካናዳ የልማት ፕሮግራም ግንባር ቀደም ተጠቃሚ አገር ነች፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ እ.ኤ.አ. በ2013 ካናዳ ለኢትዮጵያ የሰጠችው ዕርዳታ 130 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር መድረሱን ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ራሷን ለማበልፀግ በምታደርገው ጥረት ካናዳ ድጋፍ እንደምትሰጥና መቼም ቢሆን ከጎኗ እንደምትቆም አክለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከካናዳ ዕርዳታ ከሚያገኙ አገሮች በቁጥር ትሠለፋለች፡፡ አምባሳደሩ እንዳሰመሩበት፣ አገሪቱ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በምትከተለው የግብርና ፕሮግራም ላይ የምትሳተፍ ብቸኛ ለጋሽ አገር ነች፡፡

  በኢትዮጵያና በካናዳ በከፍተኛ ደረጃ መደበኛ ምክክር እንዳለ፣ ይህ ሁለትዮሽ ግንኙነት እንደ ሌሎች ለጋሽ የአውሮፓ አገሮች እምብዛም በፖለቲካ አስተሳሰብ የሚመዘን እንዳልሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ለዚህ አንዱ አብነት ካናዳ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንዲደረግ የምትፈልገው ምንም ዓይነት የፖለቲካ መርሐ ግብርም ሆነ የሥርዓት ማሻሻያ የለም፡፡

  አምባሳደር አሸር እንደሚሉት፣ በእርግጥ ካናዳና ኢትዮጵያ የሚያመሳስላቸው የብሔር ብዝኃነት ሲሆን፣ ሁለቱም በብሔር ላይ የተመሠረተ የፌዴራል ሥርዓትም ይከተላሉ፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ዙሪያ ሁለቱም አገሮች በጋራ ይሠራሉ፡፡ በተለይ በሽብርተኝነትና በስደተኞች ጉዳይ ላይ በርካታ የጋራ ፕሮግራሞች ያከናውናሉ፡፡

  በብረታ ብረትና በነዳጅ ማውጣት፣ እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች የተሰማሩ በርካታ የካናዳ ድርጅቶች በመኖራቸው፣ አምባሳደሩ የአንዳንድ ድርጅቶችን ስም ጠቅሰው ለማመስገን ዕድሉን ተጠቅመውበታል፡፡

  ለአንድ ዓመት በተለያዩ ፕሮግራሞች የተከበረው የኢትዮ ካናዳ 50ኛ ዓመት ክብረ በዓል ሰኔ 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ላይ በአፍሪካ ኅብረት በተካሄደ ዝግጅት ነበር የተጠናቀቀው፡፡ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ ዲፕሎማቶች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ በዓሉ 148ኛ ዓመት የካናዳ ቀንም የተከበረበት ነበር፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ ካናዳውያንን ለበዓላቸው በ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› ነበር ንግግራቸውን የጀመሩት፡፡ ካናዳ ለኢትዮጵያ የምትሰጠው ዕርዳታና የልማት ድጋፍ የማይተካና የቁርጥ ቀን ወዳጅ መሆኗን የሚያረጋጋጥ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡  

  ‹‹የኢትዮጵያና የካናዳ ስትራቴጂካዊ አጋርነት›› ተግባራዊ ለማድረግ መንግሥታቸው ቁርጠኛ መሆኑና ከሞላ ጎደል ፕሮግራሙ የተሳካ እንደሆነ ዶ/ር ቴድሮስ አስረድተዋል፡፡ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ የቆየው የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በፅኑ መሠረት ላይ የቆመና በእውነተኛ መረዳዳት ላይ የተመሠረተ መሆኑንም አክለውበታል፡፡ ግንኙነቱ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ካናዳ በኢትዮጵያ ያከናወነቻቸውን በርካታ መሠረታዊ ጉዳዮችም ጠቃቅሰዋል፡፡

  ኢትዮጵያን ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ መር ያሸጋግራል ተብሎ የታመነበት የመጀመሪያ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተጠናቆ ወደ ሁለተኛው ዕቅድ በመሸጋገር ላይ እንደሆነ አስረድተው፣ እ.ኤ.አ. በ2025 ኢትዮጵያን መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለማሳለፍ የተያዘውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የካናዳ እጅ ረዥም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ በዓሉን ለማክበር የታደሙ የካናዳ ዜጎችም ‹‹ከጎናችሁ ነን›› የሚለውን ለማረጋገጥ በሚመስል በጭብጨባ ድጋፋቸውን ገልጸውላቸዋል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጭ መኖሩን ገልጸው፣ የካናዳ የግል ድርጅቶች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ግንኙነቱ በንግድና ኢንቨስትመንት ታጅቦ አሁን ካለበት በአንድ ደረጃ ከፍ ያለ ትርጉም እንዲኖረው በማለትም ጥሪ አድርገውላቸዋል፡፡

  ኢትዮጵያና ካናዳ ከግማሽ ክፍለ ዘመን በኋላ

  የካናዳና የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ግንኙነት ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ አስቆጥሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1965 እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ለግንኙነቱ መጀመር እ.ኤ.አ. በ1954 የአፄ ኃይለ ሥላሴ የቶሮንቶ የአጭር ጊዜ ጉብኝት የሚጠቀስ ሲሆን፣ በ1967 ዓ.ም. ለሁለት ሳምንት ያደረጉት ጉብኝት ግን ግንኙነቱ ኦፊሴላዊ መልክ ያስያዘ እንደነበር ሰነዶች ያመላክታሉ፡፡

  አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተመሠረተው በንጉሡ ጥያቄ በካናዳዊው ተወላጅ ዶ/ር ጄሲዩት ሉሲየን ማት አማካይነት እንደሆነም ይነገራል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ2002 የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጂን ክረተይን ኢትዮጵያን በመጎብኘት የመጀመርያው የአገሪቱ መሪ ሲሆኑ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ እ.ኤ.አ. በ2010 ካናዳን መጎብኘታቸው ይታወቃል፡፡

  አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ስደተኛ ኢትዮጵያዊያን በብዛት ከሚኖሩባቸው አገሮች የካናዳ ዋና ከተማ ቶሮንቶ ከግንባር ቀደምቶቹ መካከል ስትሆን፣ በዚች ከተማ ውስጥ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸውን ይነገራል፡፡

  የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት፣ የአየር ኃይል ግንባታና በየባንኪንግ ሥርዓት መልክ እንዲይዝ በማድረግ ረገድ ካናዳውያን ግንባር ቀደም ድርሻ እንዳላቸውም ይነገራል፡፡

  በአሁኑ ወቅት በምሥራቅ አፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ በጋራ ለመሥራት ሁለቱም አገሮች ስምምነት ያላቸው ሲሆን፣ በተለይ የሶማሊያንና የደቡብ ሱዳንን ቀውስ በመፍታት ካናዳ ከኢትዮጵያ ጎን በመሠለፍ መሥራቷን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

  ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በሰላም እንዲያልቅ ይፋ ያልሆነ ድርድርና ዕርቅ ለማድረግ ካናዳ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓ የሚነገር ሲሆን፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈረመው የተኩስ አቁም ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ፣ በድንበር ሰፍሮ ከነበረው የተመድ ሰላም አስከባሪ ኃይሎች መካከል 450 ያህሉ ካናዳዊያን እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

  የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ሲጠቃለል በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን እጅግ ሞቅ ያለ ሆኖ ቆይቶ፣ በደርግ ዘመን እስከ መቋረጥ ደርሶ ነበር፡፡ በኢሕአዴግ ዘመን አንድ የካናዳ ዜጋ በሽብርተኝነት ተፈርዶበት ከአምስት ዓመት በላይ በእስር እስከቆየ ድረስ ግንኙነቱ ሻክሮ የነበረ ቢሆንም፤ ከዚያ በኋላ በመልካም ግንኙነትና በመተባበር ላይ የተመሠረተ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

  - Advertisement -

  ትኩስ ጽሑፎች

  ተዛማጅ ጽሑፎች

  - Advertisement -
  - Advertisement -