የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ራሱን ችሎ እንዲቋቋም የሚያደርግ ማሻሻያ አዋጅ ፀደቀ፡፡
ጽሕፈት ቤቱ በአዋጅ ቁጥር 253/1993 የተቋቋመ ሲሆን፣ ይህ አዋጅ የጽሕፈት ቤቱ ሥልጣንና ተግባርን ሲያስቀምጥ ራሱን እንዲችል አድርጎ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ሥልጣንና ተግባሩ በአፈ ጉባዔው ላይ የተመረሠተ እንዲሆን ማድረጉን የአዋጁ ማብራሪያ ይገልጻል፡፡
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔና አባላቱ ውጤታማ ሊሆኑ የሚችሉት ትኩረታቸውን መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ማድረግ ሲችሉ እንደሆነ የሚገልጸው የማሻሻያ አዋጁ ማብራርያ፣ ጽሕፈት ቤቱም የተለያዩ ጥናቶችንና ምርምሮችን እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ለምክር ቤቱ ማቅረብ በሚችልበት ሁኔታ ማደራጀት ተገቢ መሆኑን ያስረዳል፡፡
አሁን ባለው አዋጅ የጽሕፈት ቤቱ የሥራ ኃላፊዎችና ዳይሬክተሮች ተጠሪነታቸው ለአፈ ጉባዔው በመሆኑ ተጠያቂነትን ከማረጋገጥ ረገድ ክፍተት መፍጠሩን ይገልጻል፡፡ የጽሕፈት ቤትና የአፈ ጉባዔው የተጠሪነት ግንኙነት በዚህ ደረጃ መሆኑ ለውጤታማነትና ምክር ቤቱ አሁን ከደረሰበት ደረጃ የሚያስቀጥል ሆኖ አለመገኘቱን ማብራሪያው ያስረዳል፡፡
በመሆኑም የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ በአፈ ጉባዔው የሚሾምና ተጠሪነቱም ለአፈ ጉባዔው እንዲሆን፣ ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ደግሞ በዋና ጸሐፊው አቅራቢነት በአፈ ጉበዔው የሚሾሙ ሆነው ተጠሪነታቸው ግን ለዋና ጸሐፊው እንዲሆን ማሻሻያ አድርጓል፡፡
ሥራ ላይ የነበረው የጽሕፈት ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ ጽሕፈት ቤቱ የተቋቋመበት ራሱን የቻለ ዓላማ የሌለው በመሆኑ፣ ፓርላማው ሕገ መንግሥታዊ ተልዕኮውን ለማሳካት የሚያስፈልጉትን ሙያዊና አስተዳደራዊ አገልግሎቶችን መስጠት ዓላማው እንዲሆን በማሻሻያው ተካቷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የፌዴራል ጋዜጣን የማስተዳደር፣ የምክር ቤቱን ተቋማዊ ቀጣይነት ማረጋገጥ፣ ለምክር ቤቱ አባላትና አካላት በሕግ የተወሰኑ ጥቅማ ጥቅሞችንና ልዩ መብቶችን ማስፈጸም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመመካከር ፀጥታና ደኅንነት መከበሩን መከታተል፣ ለምክር ቤቱ አባላት የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት፣ የንብረት ባለቤት መሆን፣ ውል መዋዋል፣ መክሰስና መከሰስ የመሳሰሉ ኃላፊነቶች ተሰጥቶታል፡፡