Wednesday, October 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ለሞጆ – ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ክፍል ለሆነው የመንገድ ግንባታ 370 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፀቀደ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከሞጆ እስከ ሐዋሳ እየተገነባ ለሚገኘው 202 ኪሎ ሜትር የፍጥነት መንገድ አካል ለሆነው 57 ኪሎ ሜትር መንገድ ግንባታ 370 ሚሊዮን ዶላር የብድር ስምምነት ፓርላማው አፀቀደ፡፡

ፓርላማው የሥልጣን ዘመኑን ከማጠናቀቁ ቀደም ብሎ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ፣ ለሞጆ – ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ አካል ለሆነው የባቱ (ዝዋይ) – አርሲ ነገሌ መንገድ ግንባታ 370 ሚሊዮን ዶላር፣ የዓለም ባንክ አካል ከሆነው ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር (IDA) ጋር የተደረገ የብድር ስምምነትን አፅድቋል፡፡

የሞጆ – ሐዋሳ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፎችና በአራት ክፍሎች ተለያይቶ የሚገነባ ነው፡፡ እነዚህም በመጀመርያው ምዕራፍ ከሞጆ – መቂና ከመቂ – ዝዋይ እንደቅደም ተከተላቸው 56.8 ኪሎ ሜትርና 36 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው ናቸው፡፡

ዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር በወቅታዊ የብር ምንዛሪ ያበደረው 370 ሚሊዮን ዶላር፣ በሁለተኛው ምዕራፍ ሦስተኛው የመንገድ ክፍል ማለትም ከባቱ (ዝዋይ) – አርሲ ነገሌ ያለውን 57 ኪሎ ሜትር ግንባታ ለመፈጸም የሚውል ነው፡፡

የመጀመርያው ምዕራፍ ሁለት ክፍሎች የሆኑት ከሞጆ – መቂ 56 ኪሎ ሜትር መንገድ ከአፍሪካ ልማት ባንክ በተገኘ 151.8 ሚሊዮን ዶላር ብድር በመገንባት ላይ ነው፣ የዚህ ምዕራፍ ሌላኛው ክፍል የመቂ – ዝዋይ 37 ኪሎ ሜትር መንገድ ደግሞ  ከኮሪያ ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ በተገኘ ብድር እየተገነባ ይገኛል፡፡ ኪንግናም የተባለው የኮሪያ ኩባንያ የፕሮጀክቱ ሥራ ተቋራጭ ነው፡፡

የመጨረሻው የመንገዱ ክፍል ከአርሲ – ነገሌ ሐዋሳ መንገድ ያለው 51.68 ኪሎ ሜትር መንገድ ነው፡፡ ለዚህ መንገድ ግንባታ የሚያስፈልገውን ብድር ለማግኝት ከቻይና  ኤክስፖርት ኢምፖርት ባንክ ጋር የመግባቢያ ስምምነት ላይ መደረሱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የዚህ የፍጥነት መንገድ መገንባት ኢትዮጵያን ኬንያ ድንበር ከምትገኘው ሞያሌ ብሎም ከኬንያ የሞምባሳ ወደብ ጋር የሚያገናኝ ነው፡፡ በመሆኑም በሐዋሳ የሚቋቋመው የኢንዱስትሪ ዞን ምርቶች ኤክስፖርት ማድረጊያና ግብዓቶች ማስገቢያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ፓርላማው በተጠቀሰው ዕለት ከዚሁ አበዳሪ አካል፣ ለግብርናው ዘርፍ የሚውል 350 ሚሊዮን ዶላር ወይም ሰባት ቢሊዮን ብር የብድር ስምምነትን በተጨማሪነት አፅድቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች