Wednesday, March 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አቢሲኒያ የሱዳን የበረራ ማሠልጠኛ ተማሪዎችን ለማሠልጠን ተዋዋለ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቢሲኒያ የበረራ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ‹‹ሃይ ሌቭል አቪዬሽን አካዴሚ›› የተባለውን የሱዳን የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ተማሪዎች ተቀብሎ ለማሠልጠን የሚያስችለውን ስምምነት መፈረሙ ተገለጸ፡፡

ከአቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ በሰሜን ሱዳን ከሚገኘው ከሃይ ሌቭል አቪዬሽን አካዴሚ ጋር የተደረገው ስምምነት፣ በንድፈ ሐሳብ ሥልጠና የጨረሱ ተማሪዎች ቀሪ ሥልጠናዎቻቸውን በአቢሲኒያ የበረራ ማሠልጠኛ እንዲሠለጥኑ የሚያስችል ነው፡፡ ይህንኑ ስምምነት የአቢሲኒያ በረራ አገልግሎት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ወልደሃና እና የሃይ ሌቭል አቪዬሽን አካዴሚ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሻራፍ አልዲን ሃመድ አህመድ በካርቱም ተፈራርመዋል፡፡

ካፒቴን አማረ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የሱዳኑ የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ተማሪዎች በአቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት የሚሠለጥኑባቸው የትምህርት ዘርፎች በኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዕውቅና ያገኘባቸው ናቸው፡፡

የሱዳን የበረራ ማሠልጠኛ በሦስት የሥልጠና ዘርፎች ሥልጠና ለመስጠት ባለመቻሉ፣ ሥልጠናውን ሊሰጡ የሚችሉ ሌሎች የበረራ ማሠልጠኛ ተቋማት ለማግኘት ካወዳደራቸው ማሠልጠኛ ተቋማት ውስጥ አቢሲኒያ የበረራ ማሠልጠኛ በመመረጡ የተደረገ ስምምነት ነው ተብሏል፡፡

‹‹ሁለታችንም ተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማራን ስለሆነ በጋራ የመሥራት ባህሉን ማዳበር ተገቢ ነው፤›› ያሉት ካፒቴን አማረ፣ የሱዳን የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ዕውቅና ሊያገኝ ያልቻለባቸውና አቢሲኒያ ደግሞ ዕውቅና ያገኘባቸውን የትምህርት ዘርፎች ለማስተማር ስምምነት ማድረግ ተችሏል፡፡

የሱዳን የበረራ ማሠልጠኛ የኮሜርሻል ፓይለት ላይሰንስና ሌሎች የበረራ ትምህርቶችን የሚሰጥ ቢሆንም፣ ከኮሜርሻል ፓይለት ፈቃድ በተጨማሪ ያሉትን አንዳንድ የሥልጠና ዘርፎች ለማሠልጠን በሱዳን አቪዬሽን ባለሥልጣን ፈቃድ ባለማግኘቱ ቀሪዎቹን ትምህርቶች ለሌላ ተቋም ለመስጠት ተገዷል፡፡

የሱዳን ተማሪዎች ፕሮፌሽናል ፓይለት ሆነው እንዲወጡ ደግሞ ፈቃድ ባልተገኘባቸው የሥልጠና ዘርፎች በአቢሲኒያ በረራ ለማሟላት የተደረሰው ስምምነት እንደሚያግዝ፣ ከካፒቴን አማረ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የሱዳን የሃይ ሌቭል የበረራ ማሠልጠኛ ተቋም ተማሪዎች በአቢሲኒያ የበረራ ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት የሚሰጡዋቸው የሥልጠና ዘርፎች ደግሞ፣ ከኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ዕውቅና የተገኘባቸው በመሆኑ የሱዳን አቪዬሽን ባለሥልጣንም ይቀበለዋል ተብሏል፡፡

ሃይ ሌቭል አቪዬሽን አካዴሚ ከእነዚህ የሥልጠና ዘርፎች በተጨማሪ በሌሎች ዘርፎች ላይ ሥልጠና እንዲሰጥለት ፍላጎት እንዳለው ካፒቴን አማረ ገልጸዋል፡፡ አቢሲኒያ የበረራ ትምህርት ቤት በኢትዮጵያ የመጀመርያው የግል የበረራ ማሠልጠኛ በመሆን ይጠቀሳል፡፡ በተለያዩ የበረራ የትምህርት ፕሮግራሞች አስተምሮ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያለው የበረራ ፈቃድ በመስጠት ላይ ሲሆን፣ እስካሁን በትምህርት ቤቱ ሥልጠና ወስደው የበረራ ፈቃድ ከወሰዱ 145 የሚሆኑ ፓይለቶች ውስጥ ስድስቱ ሴቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በማሠልጠኛ ተቋሙ ከኢትዮጵያውያን በተጨማሪ ከተለያዩ አገሮች የመጡ 36 የውጭ ዜጎች እየሠለጠኑ ነው ተብሏል፡፡ ከሰሜን ሱዳን፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጋቦን፣ ከሳዑዲ ዓረቢያ፣ ከየመን፣ ከፈረንሳይና ከአሜሪካ የመጡ ተማሪዎች በአቢሲኒያ የበረራ ማሠልጠኛ በትምህርት ላይ እንደሆኑ ታውቋል፡፡

ትምህርት ቤቱ ለተማሪዎች መማሪያ የሚሆኑት ስምንት አውሮፕላኖች ሲኖሩት፣ ከበረራ ትምህርት ቤቱ ቀደም ብሎ የበረራ አገልግሎት በመስጠትም ይታወቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች