Thursday, September 21, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ የግል ድርጅቶች በነበረው እንዲቀጥሉ ተወሰነ

በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ የግል ድርጅቶች በነበረው እንዲቀጥሉ ተወሰነ

ቀን:

የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003ን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ቀደም ሲል በፕሮቪደንት ፈንድ የታቀፉ ሠራተኞች ወደ ጡረታ እንዲዞሩ በሚል የተቀመጠውን አንቀጽ ፓርላማው ሙሉ በሙሉ በመሰረዝ፣ ሌሎች ማሻሻያዎችን ካካተተ በኋላ አፀደቀ፡፡

ፓርላማው የሥልጣን ዘመኑ ከማብቃቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ሰኞ ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባው፣ እጅግ አወዛጋቢና በርካታ የግል ድርጅቶች አቤቱታቸውን ባቀረቡበት የግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ላይ፣ የግል ድርጅቶቹ ያቀረቡትን አቤቱታ የሚደግፍ ማስተካከያ በማድረግ አፅድቋል፡፡ ሕጉን ያመነጨው የግል ድርጅት ሠራተኞች የማኅበራዊ ዋስትና ኤጀንሲ ማሻሻያውን በተመለከተ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት አላወያየም ተብሎ በፓርላማው ወቀሳ ቀርቦበት ነበር፡፡

ረቂቅ አዋጁ በግንቦት ወር መጨረሻ የቀረበለት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ረቂቁን መርምሮ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያቀርብ፣ በዋናነት ለማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በተባባሪነት ደግሞ ለሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ ይታወሳል፡፡

የፓርላማው ማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በረቂቅ አዋጁ ላይ ከተወያየ በኋላ፣ በፕሮቪደንት ፈንድ ብቻ የተሸፈኑ ከ300 በላይ ሠራተኞችን የቀጠሩ ድርጅቶችን በመጋበዝ ውይይት ማድረጉን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡

በዚህ ውይይት ላይ አስረጂ ሆነው የቀረቡት የኤጀንሲው የሥራ ኃላፊዎች፣ በአዋጁ 715/2003 መሠረት በፕሮቪደንት ፈንድ ለመቀጠል ስምምነታቸውን የገለጹ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች፣ በዚህ ማሻሻያ አዋጅ መሠረት ያጠራቀሙት ገንዘብ ወደ ግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ይዛወራል የሚለውን አንቀጽ እንደተሰረዘ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ለመሳተፍ ተገኝተው የነበሩት ከሁለት መቶ በላይ ድርጅቶች ይህ መደረጉን በቅድሚያ አመስግነው፣ አሁንም የፕሮቪደንት ፈንድ በአማራጭነት ሊቀጥል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ካቀረቧቸው ምክንያቶች መካከል በዋናነት የጠቀሱት በሥራ ላይ የሚገኘው አዋጅ ባስቀመጠው አማራጭ መሠረት ዴሞክራሲያዊ የሆነ ውይይት አድርገው፣ በፕሮቪደንት ፈንድ ለመቀጠል መስማማታቸውና መወሰናቸውን ነው፡፡ ይህ ሆኖ ሳለ ዴሞክራሲያዊና ነፃ በሆነው ውይይት የተወሰነን ውሳኔ መደፍጠጥ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

በሌላ በኩል የቀረበው ሐሳብ ደግሞ ፕሮቪደንት ፈንድን አሁንም የዜጎች አማራጭ አድርጎ መተው የሚጎዳ አለመሆኑን የሚገልጽ ነው፡፡ ከ2003 ዓ.ም. ሐምሌ ወር በኋላ በፕሮቪደንት ፈንድ ማኅበራዊ ዋስትናን ማቋቋም የማይቻል በመሆኑ፣ ቀደም ሲል በፕሮቪደንት ፈንድ የተቋቋሙት እየተዋጡና ሥርዓቱም እየሞተ ይሄዳል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በወቅቱ ከተደረገው ውይይት ጠቃሚ ሐሳቦችን እንዳገኙ የገለጹት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳብ ወ/ሮ አበባ ዮሴፍ፣ ይህንኑ የሚገልጽ የውሳኔ ሐሳብ ይዘው ሰኔ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ለፓርላማ አቅርበዋል፡፡

ባቀረቡት የውሳኔ ሐሳብ ሪፖርት፣ ‹‹የሥራ ውላቸው ባልተቋረጠና በነበራቸው የፕሮቪደንት ፈንድ ሽፋን ተጠቃሚነታቸው ለመቀጠል ወስነው በነበሩ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ስም የተጠራቀመ መዋጮ፣ ይህ አዋጅ ከፀናበት ቀን ጀምሮ ወደ ግል ድርጅት ሠራተኞች ጡረታ ፈንድ ገቢ ተደርጎ በዚህ አዋጅ የሚሸፈኑ ይሆናል፤›› የሚለው ረቂቅ ማሻሻያ ተሰርዟል ብለዋል፡፡

ከዚህ ውጭ በረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ተካቶ የነበረውና የግል ድርጅት ሠራተኛ ማለት በግል ድርጅት ውስጥ ከአንድ ወር ላላነሰ ጊዜ የተቀጠረ ነው የሚለው አንቀጽ በውይይቱ ወቅት ቀርቦ በነበረው ሐሳብ መሠረት በማሻሻል፣ ‹‹ከአርባ አምስት ቀናት ባላነሰ ጊዜ ደመወዝ እየተከፈለው ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ፣ ወይም የተወሰነ ሥራ ለመሥራት የተቀጠረ ሠራተኛ ሲሆን፣ የሥራ መሪውንም ይጨምራል፡፡ ሆኖም ለጥጥ ለቀማ፣ ለሸንኮራ አገዳ ቆረጣና ለሌሎች መሰል በየዓመቱ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ እየተደጋገመ የሚሠራ ሥራን ለመሥራት የተቀጠረ ሠራተኛን አይጨምርም፤›› በማለት እንዲሻሻል አድርጓል፡፡

የፓርላማው የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ በመጨረሻ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለሁሉም ዜጎች ማኅበራዊ ዋስትና የማረጋገጥ ግዴታውን ለመወጣት ያቀረበው ማሻሻያ እንጂ፣ በከተማው ሲወራ እንደነበረው የተጠራቀመ ገንዘብ ለመውሰድ አቅዶ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ረቡዕ ሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው ዕትም፣ የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ወደ ጡረታ እንዲጠቃለል ተወስኗል መባሉ ስህተት መሆኑን፣ በፕሮቪደንት ፈንድ የተሸፈኑ ድርጅቶች በነበረው ዐቅድ እንዲቀጥሉ መወሰኑን እየገለጽን ለተፈጠረው ስህተት ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...