Monday, June 24, 2024

ፓርላማው የሕዝብን ድምፅ በመስማቱ ምስጋና ይገባዋል!

የግል ድርጅቶች ሠራተኞች ጡረታ አዋጅ ቁጥር 715/2003 የወጣው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 90 (1) ላይ የተደነገገውን የዜጎች የማኅበራዊ ዋስትና የማግኘት መብት ለማረጋገጥ ነበር፡፡ በወቅቱ ምንም ዓይነት የማኅበራዊ ዋስትና ሽፋን የሌላቸው የግል ድርጅት ሠራተኞች ይህንን ዋስትና እንዲያገኙ በማሰብ መንግሥት አዋጁን ማውጣቱ አስመስግኖታል፡፡ ምክንያቱም ዘለቄታዊው የማኅበራዊ ዋስትና ማግኘት የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብት ከመሆኑ ባሻገር በአገሪቱ ላይ ሲያስከትል የቆየው ማኅበራዊ ቀውስ ግዙፍ ነበር፡፡ በርካታ የግል ድርጅት ሠራተኞች ለዘመናት በሥራ ላይ ከቆዩ በኋላ ዕድሜያቸው ሲገፋና ምርታማነታቸው በሚቀንስበት ወቅት ከሥራ መሰናበታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ወይም ደግሞ በተለያዩ ምክንያቶች በዘላቂነት ሥራ መሥራት በማይችሉበት ወቅት ለቤተሰቦቻቸውም ሆነ ለአገራቸው ሸክም መሆናቸው አይቀርም፡፡ ለዚህም ነው ዜጎች ማኅበራዊ ዋስትና ሊኖራቸው የሚገባው፡፡ ምክንያቱም ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ዜጎች ሥራቸውን ቢያቆሙም፣ በማኅበራዊ ዋስትና በመታቀፋቸው በሌሎች ላይ ሸክም ከመሆን ያድናቸዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት አዋጅ ቁጥር 715/2003ን ሥራ ላይ ማዋሉ አስመስግኖታል፡፡

ይህ የማኅበራዊ ዋስትና አዋጅ በወጣበት ወቅት ግን የዚህ ሽፋን አንዱ አካል የነበረውና በርካታ የግል ድርጀቶች ሠራተኞች የታቀፉበት የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ነበር፡፡ በወቅቱም በፕሮቪደንት ዐቅድ ውስጥ ተካተው የነበሩ ሠራተኞች እንዴት መቀጠል አለባቸው? በሚለው ሐሳብ ላይ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም መሠረት የግል ድርጀቶች ሠራተኞች በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ይቀጥሉ ወይስ በጡረታ ይታቀፉ? የሚለው ሐሳብ ላይ ባለጉዳዮቹ ራሳቸው ይሻለናል ያሉትን መርጠዋል፡፡ በወቅቱ የነበረው ዴሞክራሲያዊ አካሄድም ከዜጎች አድናቆት ተችሮታል፡፡ ከዚያም ባለፈ የዜጎችን የማኅበራዊ ዋስትና ማረጋገጥ በማስቻሉ ይበል ያሰኘ አዋጅ ነበር፡፡

ሆኖም በቅርቡ በሥራ ላይ ያለውን ይህን አዋጅ ለማሻሻል ተብሎ አዲስ ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁም የፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ውስጥ ተካተው የነበሩ የግል ድርጅቶች ሠራተኞች፣ ሁሉም ወደ ጡረታ ፈንድ ዐቅድ ውስጥ እንዲገቡ የሚያስገድድ ነበር፡፡ ይህ ረቂቅ ማሻሻያ ግን በባለጉዳዮቹ በእጅጉ የተተቸና በጥርጣሬ  ዓይንም የታየ ነበር፡፡ በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ውስጥ ተካተው የነበሩ አብዛኞቹ የግል ድርጅቶች ሠራተኞችም በማሻሻያው ከፍተኛ ቅሬታ እንደተሰማቸው ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡

እርግጥ ነው መንግሥት ይህን አዋጅ ለማሻሻል ያቀደበትን ምክንያቶች ዘርዝሯል፡፡ መንግሥት የግል ድርጅቶች በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ ውስጥ መታቀፋቸው ዘለቄታዊ የማኅበራዊ ዋስትና እንደሚያገኙ ማረጋገጫ መሆኑን ቢያምንም፣ ይህ ፈንድ ግን በአንዳንድ ደንታ ቢስ ድርጅቶች አደጋ ውስጥ ሊገባ ይችላል የሚል ሥጋት ነበረው፡፡  በእርግጥ ይህ የመንግሥት ሥጋት ፍሬ ከርስኪ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ደንታ ቢስ ድርጅቶች ይህን ፈንድ በአግባቡ ላያስገቡ ይችላሉና፡፡ ይህ ደግሞ የማኅበራዊ ዋስትና አዋጁን ዓላማ ከማሳቱም ባለፈ ማኅበራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ እዚህ ላይ ግን ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ እነዚህ ደንታ ቢስ ድርጅቶች ይህን ተግባራቸውን የሚፈጽሙት የአዋጁን ክፍተት ተጠቅመው መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህ ለዚህ ችግር ዋናው መፍትሔ የግል ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው የሚያስገቡትን የፕሮቪደንት ፈንድ መቆጣጠር እንጂ ከነአካቴው ዐቅዱን መሰረዝ አይደለም፡፡

ሌላው ይህ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ይህን አዋጅ ሊያሻሸል ሲያቅድ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ምንም ዓይነት ውይይት አላደረገም፡፡ መንግሥት እንደዚህ ዓይነት ከሕዝብ ህልውና ጋር የተቆራኙ ሕጎችን በሚያረቅበትም ጊዜ ሆነ ማሻሻያ በሚያደርግበት ወቅት፣ ከሚመለከተው የባለድርሻ አካላት ጋር ተገቢውን ውይይት ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ መንግሥት ይህንንም ባለማድረጉ ሕዝቡ ቅሬታ እንዲያድርበት አድርጓል፡፡ ከዚህም ባለፈ ሕጎች ሲረቀቁና ሲሻሻሉ ተገቢው ጥናት ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ ጥናት የተደረገባቸው ነገሮች ውዥንብር እንዳይፈጠር ከማድረጋቸውም ባሻገር፣ መንግሥት የሕዝብን አመኔታ እንዲያገኝ ያስችለዋል፡፡ ይህን ዓይነት አካሄድም ሥርዓት ያለውና ወጥ አሠራርን በመዘርጋት ሕዝብንም ሆነ መንግሥት መጥቀም ይቻላል፡፡ ሕጎች ሲወጡም ሆኑ ሲረቀቁ ተገቢውን ጥናትና ውይይትም ማድረግ ባህላችን ሊሆን ይገባል፡፡

በዚህህ ረቂቅ ማሻሻያ ምክንያት በርካታ ዜጎች መንግሥት ለዘመናት ያጠራቀምነውን ገንዘብ በጠራራ ፀሐይ ሊወስድብን ነው የሚል ከፍተኛ ሁካታ ፈጥሮ ነበር፡፡ በዚህ ረቂቅ ማሻሻያ ምክንያትም  ዜጎች በባንክ ያስቀመጡትን ገንዘብ በማውጣታቸው፣ በባንኮች ሥራ ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ተፈጥሯል፡፡ ይህ የተከሰተበትም ምክንያት መንግሥት ረቂቅ ማሻሻያውን ሲያዘጋጅ ሕዝብን ካለማሳተፉ የተነሳ ቢሆንም፣ የማሻሻያ ምክንያቶቹ ውኃ የማይቋጥሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ከዚያም ባለፈ ይህ ሥጋት በሚነዛበት ወቅት መንግሥት ጉዳዩን እያወቀ ዝምታን በመምረጡ፣ ለዚህ ሁሉ ትርምስ በር ከፍቷል፡፡

ይህ ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ሲወጣ ማሻሻያው ያስፈለገበት ምክንያት ግልጽ ባለመሆኑና ተገቢው ውይይት ያልተደረገበት ከመሆኑም ባሻገር፣ ረቂቁ አማራጮች ያልቀረቡበት በመሆኑ እንዳይፀድቅ ብለናል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ በተጠራው ስብሰባ በርካታ የግል ድርጅቶችና የሲቪክ ማኅበራት ሠራተኞች ተወካዮች በረቂቁ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ለምክር ቤቱ አሰምተዋል፡፡ እኛም ረቂቅ ማሻሻያውን ተገቢው ጥናት ያልተደረገበትና የሕዝብ ይሁንታን ያላገኘ በመሆኑ፣ ረቂቁ ማሻሻያ እንደማያስፈልገው ገልጸናል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሕዝቡ የተነሳው ቅሬታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ በፕሮቪደንት ፈንድ ዐቅድ የታቀፉ ሠራተኞች ወደ ግል ጡረታ እንዲገቡ የተረቀቀውን ማሻሻያ አንቀጽ በመሰረዝ በመረጡት የጡረታ ዐቅድ እንዲቀጥሉ ወስኗል፡፡ ፓርላማው የሕዝቡን ድምፅ ሰምቶ ይህን በማድረጉ ምስጋና የሚያሻው ከመሆኑም በተጨማሪ፣ በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ይህን ዓይነቱ ባህል ይቀጥል እንላለን፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የሕዝብን ድምፅ የመስማት ባህሉን ካዳበረ፣ ሕዝብም በመንግሥት ላይ የሚኖረው አመኔታ እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህ ባህሉን ያዳብር፣ ያጎልብት እንላለን፡፡ ፓርላማው በዚህ ረቂቅ ማሻሻያ ላይም የሕዝብ ድምፅን በመስማቱ ምስጋና ይገባዋል እንላለን፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ሕግ የማጥቂያ መሣሪያ እንዳይሆን ጥንቃቄ ይደረግ!

የሕግ መሠረታዊ ዓላማ ዜጎችን ከማናቸውም ዓይነት ጥቃቶች መጠበቅ፣ ለሕይወታቸውና ለንብረታቸው ከለላ መስጠትና በሥርዓት እንዲኖሩ ማድረግ ማስቻል ነው፡፡ በዚህ መሠረት ሁሉም ዜጎች በሕግ ፊት እኩል...

መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የተንሰራፋው ሌብነት ልዩ ትኩረት ይሻል!

በየዓመቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበጀት ረቂቅ በፊት መቅረብ የነበረበት የፌዴራል ዋና ኦዲተር ግኝት ሪፖርት ማክሰኞ ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ዘግይቶ ሲቀርብ፣ እንደተለመደው...

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የዋጋ ንረትን ለመቀነስ ምን ታስቧል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በጀት ለተለያዩ መንግሥታዊ ወጪዎች ሲደለደል...