Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንትን ጨምሮ የጣሊያንና የሌሎች አገሮች መሪዎች በፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ይገኛሉ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ የሚካሄደው ፋይናንስ ለልማት ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይ ከሚታደሙ የአገር መሪዎች መካከል፣ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደንን ጨምሮ የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቴዮ ሬንዚ፣ የስዊድን ጠቅላይ ሚኒስትር ስቴፈን ሎፍቬንና ሌሎች በርካታ የአገር መሪዎች በጉባዔው ላይ እንደሚገኙ ከተረጋገጠው መካከል መሆናቸው ታወቀ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ 16 ርዕሳነ ብሔርና ርዕሳነ መንግሥታት፣ ስድስት ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ሰባት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ ሦስት ምክትል ፕሬዚዳንቶችና 66 ሚኒስትሮች በጉባዔው ላይ እንደሚሳተፉ ተረጋግጧል፡፡ በጠቅላላው ከአምስት ሺሕ በላይ ተሳታፊዎች ፋይናንስ ለልማት በተሰኘው ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ ይጠበቃል፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮቶኮል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄኔራል ወ/ሮ የሺ ታምራት ለሪፖርተር እንዳረጋገጡት፣ ከተጠቀሱት መሪዎች በተጨማሪ የቱርክ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የስሎቫኪያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቤልጂም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የቶንጋ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የላይቤሪያ፣ የቤኒን፣ የጉያና እንዲሁም የቻድ ፕሬዚዳንቶች፣ የሲሼልስ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር፣ የሴንት ቬንሴንትና ግሬናዲንስ ጠቅላይ ሚኒስትርን ጨምሮ የሌሴቶ ንጉሥ ከሚጠበቁት መሪዎች መካከል ይገኙበታል፡፡

ከዚህ ባሻገር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙንና በሥራቸው የሚገኙ ልዩ ልዩ የተመድ ኤጀንሲዎችን የሚመሩ ኃላፊዎች፣ እንደ ዓለም ባንክና የዓለም የፋይናንስ ተቋማትን የሚመሩ ፕሬዚዳንቶች፣ የትልልቅ ኩባንያዎች ኃላፊዎችና የታወቁ ምሁራን ስማቸው በተሳታፊነት ከተመዘገቡት ውስጥ ይገኛል፡፡ ከምሁራኑ መካከል ጆሴፍ ስቲግሊትዝና ጄፊሪ ሳክስ ይገኙበታል፡፡

ሦስተኛው ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በአፍሪካ ምድር ሲካሄድ የመጀመሪያው ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ የተካሄዱት ጉባዔዎች 14 ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ የመጀመሪያውን የጉባዔውን ጥንስስ ያስተናገደችው የሜክሲኮዋ ሞንቴሬ ከተማም፣ የሞንቴሬው ስምምነት (ሞንቴሬ ኮንሰንሰስ) የሚል መጠሪያን አትርፋበታለች፡፡ ታሪካዊ በሆነው የሞንቴሬ ጉባዔ የዓለም ሀብታም አገሮች ለታዳጊና ለድሆች አገሮች ልዩ የፋይናንስ ድጋፍ ለማድረግ የስምምነት ቃል ያሰሩበት ነበር፡፡

የበለፀጉት አገሮች ከጠቅላላ ብሔራዊ ገቢያቸው ውስጥ የ0.7 በመቶ መዋጮ በማድረግ ደሃ አገሮችን በመደገፍ የሚሊየሙን የልማት ግቦች እንዲያሳኩ ለማገዝ ቃል ገብተው ነበር፡፡ ሆኖም ላለፉት አሥራ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ሲደረጉ የቆዩትን የልማት ግቦች ያሳኩት ጥቂት አገሮች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ አብዛኞቹን የልማት ዕቅዶች በማሳካት ከተሳካላቸው አገሮች መመደቧ ጉባዔውን እንድታዘጋጅ አግዟታል፡፡

በመጪዎቹ አሥራ አምስት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ረሃብን ከማጥፋት ጀምሮ በልዩ ልዩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አካባቢያዊ ችግሮች መቀረፍ ላይ ያተኮሩት የዘላቂ ልማት ግቦች ትግበራ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከፍተኛ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፎች ካደጉት አገሮች ዘንድ ይጠበቃሉ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2002 ከተካሄደው የሞንቴሬ ጉባዔ በኋላ እ.ኤ.አ. በ2008 በዶሃ ኳታር የተገናኙት የዓለም መሪዎች፣ የቀድሞውን ስምምነት በማደስ ተግባራዊ ለማድረግና ተጨማሪ ድጋፎችን ለማቅረብ ቃል ቢገቡም፣ በጠቅላላው ባለፉት አሥራ አራት ዓመታት ውስጥ የታዩት ለውጦች ይጠበቁ ከነበሩትና ከታቀዱት የተመድ ግቦች አኳያ በእጅጉ ኋላ ቀርተዋል፡፡ ሦስተኛው የአዲስ አበባው ጉባዔ የተገቡትን የልማት ፋይናንስ ድጋፎች ብቻ ሳይሆን አዳዲስ የፋይናንስ ምንጮች የሚጠበቁበት ነው፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች