የሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ሰሞኑን ውይይት ሲደረግ ሰንብቷል:: በመጀመርያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ከፍተኛ ውጤት ተገኝቶባቸዋል የተባሉ ዘርፎች የመኖራቸውን ያህል ከዕቅዱ ጋር ያልተጣጣሙ አፈጻጸሞች የታዩባቸው ዘርፎችም መኖራቸው ተገልጿል::እያኮበኮበ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ከኢንዱስትሪ ዘርፍ በተለይ የማኑፋክቸሪንግ፣ ከግብርና ዘርፍ ደግሞ የእንስሳት ሀብት ተስፋ ተጥሎባቸዋል፡፡
ሰሞኑን ለውይይት የቀረበው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አገሪቱን ወደፊት ማራመድ ካስፈለገ፣ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ትኩረት መስጠት ‹‹የሞት ሽረት ጉዳይ ነው›› በማለት በኃይለ ቃል ደረጃ አስቀምጧል፡፡