Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመርያ በሚጥሱ ኃይሎች ላይ ኮማንድ ፖስቱ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመርያ በሚጥሱ ኃይሎች ላይ ኮማንድ ፖስቱ ዕርምጃ እወስዳለሁ አለ

ቀን:

የሕዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መመርያ በሚጥሱ ኃይሎች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ማክሰኞ የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. መግለጫ አውጥቷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምቴና በምዕራብ ወለጋ ዞን ደምቢዶሎ ከተሞች፣ ሕገወጥ ኃይሎች የሕዝቡን ሰላምና መረጋጋት ለማደፍረስ ጥረት ከማድረጋቸውም በላይ በፀጥታ ኃይሎች ላይ የእጅ ቦምብ በመወርወር አደጋ ለማድረስ ሙከራ አድርገዋል ሲል ጽሕፈት ቤቱ አስታውቋል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች ሰላምና መረጋጋት ለማረጋገጥ በሚያደርጉት ጥረት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ መመርያ እንደተሰጣቸው የጠቆመው መግለጫው፣ በዚህ መሠረት የፀጥታ ኃይሎች እየተቸገሩና አልፎ ተርፎም ራሳቸውን ለአደጋ እያጋለጡ ናቸው ብሏል፡፡ እነዚህ ኃይሎች ከድርጊታቸው የማይቆጠቡ ከሆነ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በመመርያው መሠረት የፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ዕርምጃ እንዲወስድ ትዕዛዝ መሰጠቱን አስታውቋል፡፡

የአስቸኳይ ኮማንድ ፖስቱ ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት በመግለጫው ‹‹ፀረ ሰላም ኃይሎች በኦሮሚያ ክልል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የመኖሪያ ቤትና አድራሻ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደሚያሠራጩና በአካል ቤታቸው ድረስ በመሄድና ስልክ በመደወል እያስፈራሩ ነው፤›› ብሏል፡፡ ‹‹የሕዝብ ተመራጮች ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው ለኮማንድ ፖስቱ ተደጋጋሚ አቤቱታ በማቅረብ ላይ ናቸው፤›› ያለው መግለጫው፣ ይህን ፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄድና ፍላጎት በኃይል ለመጫን የሚደረግ አፍራሽ እንቅስቃሴ ኮማንድ ፖስቱ በቸልታ እንደማይመለከተው፣ በዚህ ተግባር በተሰማሩ ኃይሎች ላይ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ሕጋዊ ዕርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ ማስጠንቀቁን አስታውቋል፡፡

የአገሪቱ ሕዝብ የራሱን ሕይወትና ንብረት ከጥቃት ለመጠበቅ ከፀጥታ ኃይሎች ጎን ተሠልፎ መስዋዕትነት ጭምር እየከፈለ እንደሆነ የጠቆመው መግለጫው፣ ይህን ጥረት ሕዝቡ አጠናክሮ አሁንም እንዲቀጥል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ሴክሬታሪያት ጽሕፈት ቤት ጥሪውን አቅርቧል፡፡

በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠረውን የፀጥታ መደፍረስ መነሻ በማድረግ በመላ አገሪቱ ተግባራዊ የሚሆን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 9 ቀን 2010 ዓ.ም. መታወጁ የሚታወስ ሲሆን፣ አዋጁ ከወጣ በኋላ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች መረጋጋት መፈጠሩን በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

በአገሪቱ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93 መሠረት በሚኒስትሮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከታወጀ በ15 ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ መፅደቅ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በእነዚህ ቀናት አዋጁ ካልፀደቀ ተግባራዊ እንደማይሆን የአገሪቱ ሕገ መንግሥት ይገልጻል፡፡

ሰሞኑን እየወጡ ያሉ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከነበሩበት የዕረፍት ጊዜ ተጠርተው አዋጁን ለማፅደቅ፣ ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባ ያካሂዳሉ፡፡ በዚህ ወቅትም አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ፀድቆ ወደ ሥራ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...