በአዲስ አበባ ከተማን ንፁህ የመጠጥ ውኃ አቅርቦት አስተማማኝ ለማድረግ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ 95 ባለሙያዎችን ለመቅጠር ላወጣው ማስታወቂያ 13 ሺሕ ተወዳዳሪዎች አመለከቱ፡፡
ባለሥልጣኑ ታኅሳስ 15 ቀን 2010 ዓ.ም. በአምስት የሥራ መደቦች 95 ባለሙያዎችን ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ መሠረት ምዝገባ ለማካሄድ፣ በርካታ ሥራ ፈላጊዎች መገናኛ አካባቢ የሚገኘውን የባለሥልጣኑ ዋና መሥሪያ ቤት አጥለቅለቀው ሰንብተዋል፡፡
ባለሥልጣኑ ለሲኒየር ኦዲት ኦፊሰርና ለኦዲት ኦፊሰር የመጀመርያ ዲግሪ ለያዙ ሁለት ዓመት የሥራ ልምድ ጠይቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መሐንዲስ (ለውኃ)፣ መሐንዲስ (ለፍሳሽ) እና የስታንዳርድ አፈጻጸም ምዘና ክትትል ኦፊሰር የመጀመርያ ዲግሪ እና ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ጠይቋል፡፡
ባለሥልጣኑ የደመወዙን መጠን በማስታወቂያ ላይ ግልጽ ያደረገ ሲሆን፣ ከ10,022 እስከ 13,240 ብር ወርኃዊ ደመወዝ አቅርቧል፡፡
አንድ መቶ ላልሞሉ የሥራ መደቦች ከ13 ሺሕ በላይ ባለሙያዎች መሠለፋቸው ብዙም የተለመደ አይደለም ሲሉ፣ አንድ የባለሥልጣኑ የሥራ ኃላፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አወቀ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራውን ለማግኘት በርካታ ሰዎች ቀርበዋል፡፡
‹‹ምናልባት የደመወዙ መጠን የተሻለ ስለሆነ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ አቶ አወቀ በርካታ ሰዎች ሊያመለክቱ የቻሉበትን ምክንያት ገልጸዋል፡፡
ለተመዝጋቢዎቹ ከዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ፈተና እንደሚሰጥ ታውቋል፡፡ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን ለከተማው ነዋሪዎች ንፁህ የመጠጥ ውኃ ለማቅረብ፣ ፍሳሽ ቆሻሻዎችንም በዘመናዊ መንገድ ለማስወገድ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማካሄድ ላይ ነው፡፡ በቢሊዮን ብሮች በሚቆጠር በጀት እየተከናወኑ ያሉት ፕሮጀክቶች በመልካም አፈጻጸም ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
ነገር ግን ባለሥልጣኑ በተለይ በንፁህ ውኃ አቅርቦት በኩል የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ከፍተኛ ተግዳሮት እንደሆነበት በተደጋጋሚ እየገለጸ ነው፡፡