የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከረቡዕ የካቲት 21 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚሰበሰብ ታወቀ፡፡ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ስብሰባ ከተጠናቀቀ በኋላ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት በቅርቡ ይሰበሰባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የስብሰባዎቹ ዓላማም ተተኪውን የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ለመምረጥ ነው፡፡
ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከረቡዕ ጀምሮ ያደርጋል ተብሎ በሚጠበቀው ስብሰባ፣ በሚቀርቡለት የመወያያ ሰነዶች ላይ እንደሚመክር ለማወቅ ተችሏል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ከአራቱም የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች በእኩል የተውጣጡ በአጠቃላይ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ብሔራዊ ምክር ቤት እንደሚሰበሰብ ታውቋል፡፡
ብሔራዊ ምክር ቤቱ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚያቀርብለትን የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በቅድሚያ እንደሚያዳምጥ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በመቀጠል የተያዙት አጀንዳዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሥራ መልቀቂያ ጥያቄ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፍ፣ እንዲሁም በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ምትክም የግንባሩን ሊቀመንበር እንደሚሰይም መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
ይህንን ተከትሎም ኢሕአዴግ ተተኪውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለፓርላማ በማቅረብ እንደሚያሰይም ሲጠበቅ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ፓርላማው የአገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትር የመምረጥ ሥልጣን የለውም፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 73 መሠረት በፓርላማው አብላጫ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሰይም መሆኑን ይደነግጋል፡፡ በ2008 ዓ.ም. ጥር ወር የተሻሻለው የፓርላማ አባላት የሥነ ምግባርና የአሠራር ሥነ ሥርዓት ደንብ አንቀጽ 107፣ ከሕገ መንግሥቱ በመነሳት የጠቅላይ ሚኒስትሩን አሰያየም ይደነግጋል፡፡
በደንቡ አንቀጽ 107(2) መሠረት በፓርላማው አብላጫ ወንበር የያዘው ፓርቲ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ከምክር ቤቱ የሚመርጠውን በአፈ ጉባዔው ጋባዥነት የሚያስተዋውቅ መሆኑን የሚገልጽ ሲሆን፣ በንዑስ አንቀጽ 3 ሥር ደግሞ የፓርላማው አባላት የቀረበውን ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጥታ ተቀብለው እንደሚያፀድቁ ይደነግጋል፡፡
በዚህም መሠረት የፓርላማ አባላት በኢሕአዴግ የሚቀርብላቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብለው እንደሚሰይሙ የሕግ ባለሙያዎቹ ገልጸዋል፡፡