Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናደኢሕዴን ሦስት አዳዲስ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላትን በመምረጥ ስብሰባውን አጠናቀቀ

ደኢሕዴን ሦስት አዳዲስ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላትን በመምረጥ ስብሰባውን አጠናቀቀ

ቀን:

ዋናና ምክትል ሊቃነ መናብርቱን የመረጠው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ለ24 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ፣ ሦስት አዳዲስ የኢሕአዴግ ምክር ቤት አባላትንና አንድ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል በመምረጥ አጠናቋል፡፡

የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ ማክሰኞ የካቲት 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ደኢሕዴን የተጓደሉ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና ምክር ቤት አባላትን በመምረጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡ የተመረጡት ግለሰቦች እነማን እንደሆኑ አቶ ተስፋዬ ተጠይቀው፣ ‹‹ስማቸውን ለጊዜው አላስታውስም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ሆነው የተመረጡት በአውሮፓ ኅብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ መሆናቸውን፣ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ ሰኞ የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ደኢሕዴን ለ24 ቀናት ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅም አቶ ሽፈራው ሽጉጤን የድርጅቱ ሊቀመንበር፣ አቶ ሲራጅ ፈጌሳን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ መምረጡ ይታወሳል፡፡  

በጉባዔው ወቅት የተሰጠውን አገራዊና ክልላዊ ተልዕኮ በመወጣት ረገድ ተገምግሞ ከኃላፊነት የወረደ አመራር እንደሌለም አቶ ተስፋዬ አክለው ጠቁመዋል፡፡

የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ያደረገውን ስብሰባ ሲያጠናቅቅ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቷል፡፡ ማዕከላዊ ኮሚቴው እንደተለመደው ችግርን በመዘርዘር ብቻ ሳይሆን ለችግሮቹ ባለቤት በመለየት፣ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂነትና ኃላፊነት በመውሰድ ስበሰባው እንደተካሄደ በመግለጫው ጠቁሟል፡፡

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፣ በመጀመርያ ደረጃ ድምዳሜ ላይ የደረሰበት ጉዳይ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከኢሕአዴግና ከደኢሕዴን ሊቀመንበርነትና ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸውን ያደነቀ ሲሆን፣ ይህም የአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ድሎችና የአቶ ኃይለ ማርያም ብቃት ያመጣው መሆኑን በአግባቡ እንደሚገነዘብ አስታውቋል፡፡ ‹‹አሁንም ሥልጣን የሕዝብ አገልጋይነት መሣሪያ ከመሆን ይልቅ ለራስ ጥቅምና ክብር መጠቀሚያ የማድረግ ዝንባሌ ገኖ ባለበት አገርና አኅጉር ሥልጣንን በራስ ፍላጎት በመልቀቅ ለአገሪቱም ሆነ ለአኅጉራችን አዲስ ታሪክ በማስቀመጡ በመሪያችን በእጅጉ ኮርተናል፤›› በማለት መግለጫው አትቷል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በአመራርነት ዘመናቸው ላስመዘገቧቸው አመርቂ ድሎችና ውጤቶች ተገቢውን ክብር ድርጅቱ እንደሚሰጣቸውም ተገልጿል፡፡

የድርጅቱ ሁለተኛው የውሳኔ ሐሳብ ባለፉት ዓመታት ለተመዘገቡ ልማቶችና በአገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ዘላቂና ሰላም ለማስፈን በተደረገው ርብርብ ደኢሕዴን የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረጉ በመግለጫው የተብራራ ሲሆን፣ ጉድለቶችም እንደነበሩና ደኢሕዴን ለእነዚህ ጉድለቶች የራሱ ድርሻ እንዳለውና ጉድለቶችን ተቀብሎ ለወደፊት ለማረም ዝግጁ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

ሦስተኛው የውሳኔ ሐሳብ ደኢሕዴን በሚመራው ክልል ተመሳሳይ ብሔራዊና መደባዊ ጭቆና ሲፈራረቅባቸው የኖሩ 56 ብሔር ብሔረሰቦች በድርጅቱ ፖለቲካዊ አመራርና በሕዝቡ መልካም ፈቃድ የፈጠሩት አንድነት፣ አሁን ላለው ጠንካራ ትስስር አስተዋጽኦ እንደነበረው መገምገሙን ተገልጿል፡፡ ‹‹በክልላችን የሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሲመሩ የነበሩትን 21 ድርጅቶች በራሳቸው ፈቃድና ይሁንታ በመዋሀድ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በመፍጠራችን በክልሉ ዴሞክራሲያዊ አንድነት እንዲያብብ በማድረግ ረገድ ሁነኛ ታሪካዊ ድል መሆኑን እንገነዘባለን፤›› ሲል መግለጫው ያብራራል፡፡ መግለጫው አክሎም፣ ‹‹የክልላችንን አንድነት የሚፈታተኑ ችግሮች ያጋጠሙንና እያጋጠሙን ያሉ ቢሆንም፣ ዋናው ችግር ግን የኪራይ ሰብሳቢነት ሽፋን የሆነው ጠባብነት ነው፤›› ሲል መግለጫው አስረድቷል፡፡

አራተኛው የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ የ24 ቀናት ስብሰባ ውሳኔ፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት ረገድ ያጋጠመ ችግሮችን የተመለከተ ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ከመላ ዜጎች ነፃና የነቃ ተሳትፎ ውጪ ሊታሰብ እንደማይችል ያብራራው መግለጫው፣ በዚህ በኩል የዜጎችን የነቃ ተሳትፎ የሚገድቡ በርካታ ችግሮች እንዳሉ መገምገሙን መግለጫው ጠቁሟል፡፡

አምስተኛው የውሳኔ ሐሳብ ደኢሕዴን የክልሉንም ሆነ የአገሪቱን ሕዝብ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ለማውጣት እያደረገ ያለውን አስተዋጽኦ የተመለከተ ሲሆን፣ ዛሬም ይህ ችግር ከሕዝቡ ጫንቃ እንዳልወረደ መገምገሙንና ለወደፊት በተጠናከረ ሁኔታ ይህን ችግር ለመፍታት መወሰኑን ጠቁሟል፡፡

ስድስተኛው ጉዳይ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የተመለከተ ነው፡፡ ደኢሕዴን በተግባራዊ እንቅስቃሴ በርካታ እጥረቶች እንዳሉበት፣ በቀጣይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ካሉ በአገርና በክልል ደረጃ ከሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራትና በክልሉ ያለምንም ተፅዕኖና እንቅፋት እንዲንቀሳቀሱ፣ በሚያግባቡ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ተደጋግፎ ለመሥራት መወሰኑን በመግለጫው ተብራርቷል፡፡

ሰባተኛውና የመጨረሻው የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተከሰተ ያለው ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት፣ እንግልትና ስደት የተመለከተ ነው፡፡ ደኢሕዴን ይህን ችግር አምርሮ እንደሚቃወምና ለወደፊት ችግሩ እንዲቀረፍ ከፍተኛ ርብርብ እንደሚያደርግ በመግለጫው አስረድቷል፡፡

ደኢሕዴን ለክልሉ ሕዝቦች፣ በየደረጃው ለሚገኙ የአመራር አካላትና ለድርጅቱ አባላት፣ ለክልሉ ሴቶችና ወጣቶች፣ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለሕዝብና ለሙያ ማኅበራት፣ በመላው ዓለም ለሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች፣ ለአገሪቱ ሕዝቦችና ለፖለቲካ ፓርቲዎች መልዕክት አስተላልፏል፡፡ በክልሉ የተጀመሩ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት ቁርጠኛ እንደሆነና ችግር ሲከሰትም በመነጋገር ለመፍታት ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውቋል፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...