የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በውድድር ዓመቱ ከሚያከናውናቸው የሩጫ መርሐ ግብሮች መካከል ዓለም አቀፍ ይዘት ያለው የጃንሜዳ ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ይጠቀሳል፡፡ ዘንድሮ ለ35ኛ ጊዜ የተከናወነው ይኼው የሩጫ ውድድር፣ ባለፈው እሑድ በጥሩ የተፎካካሪነት መንፈስ በጃንሜዳ ውድድሩን አድርጓል፡፡
አትሌቲክሱ በተለይም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እያስገኘ ባለው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ሚዛን እየደፋ መምጣቱ ዕውን ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በዚህ የተነሳም የተፎካካሪዎቹ ቁጥርም ጨምሯል፡፡ ለወትሮ የክልሎችም ሆኑ የክለብ አትሌቶች በአገር ውስጥ በሚደረጉ ተመሳሳይ ውድድሮች በግዳጅ ካልሆነ እንዲህ እንደ አሁኑ በፍላጎት የሚወዳደሩ እምብዛም እንደነበር አይዘነጋም፡፡
እሑድ የካቲት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ከ966 አትሌቶች በላይ፣ ከሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከክለብና በግል የቀረቡ ተወዳዳሪዎች በ35ኛው የጃንሜዳው ኢንተርናሽናል አገር አቋራጭ ተሳትፈዋል፡፡ በዚሁ መሠረት በድብልቅ ሪሌ ከቀረቡት ተወዳዳሪዎች የኦሮሚያ ክልል አሸናፊ ሲሆን፣ በክለብ ደግሞ የኦሮሚያ ውኃ ሥራዎችና መከላከያ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን አጠናቀዋል፡፡ ከአራተኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘው ያጠናቀቁት ደግሞ መሰቦ፣ ለገጣፎና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ናቸው፡፡
በሁለት የዕድሜ ክልል በመክፈል ማለትም በሁለቱም ጾታ በወጣትና በአዋቂዎች በተደረገው የሩጫ ውድድር፣ በስድስት ኪሎ ሜትር ወጣት ሴቶች ግርማዊት ገብረ እግዚአብሔር ከጉና፣ ጽጌ ሰለማ ከትራንስ፣ ሚዛን ዓለምና ብርዛፍ ታረቅ ከጉና፣ ብርሃን ምሕረት ከሱር ኮንስትራክሽንና እጅጋየሁ ታዬ ከኦሮሚያ ክልል ከአንደኛ እስከ ስድስተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ የውድድሩ አሸናፊዎች ሆነዋል፡፡
በስምንት ኪሎ ሜትር ወጣት ወንዶች አቢ ጋሻሁንና ንብረት መላክ ከአማራ ክልል፣ ብርሃኑ ወንድሙ ከኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ መኩሪያ ዘለቀ ከአማራ ክልል፣ ሰለሞን በሪሁን ከትራንስ ኢትዮጵያና ጌታቸው ማስረሻ ከአማራ ክልል ተከታትለው በመግባት ያሸነፉ አትሌቶች ናቸው፡፡
በአሥር ኪሎ ሜትር አዋቂ ሴቶች መካከል በተደረገው ፉክክር፣ እናትነሽ አላምረው ከአማራ ክልል፣ ጌጤ ዓለማየሁና ረሂማ ቱሳ ከኦሮሚያ ክልል፣ ልይሽ ካህሳይ ከመሰቦ፣ ዝናሽ እስጢፋኖስ ከኦሮሚያ ክልልና ሻሾ አሰርሞ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ ናቸው፡፡ በወንዶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር እንየው ዓለም ከሲዳማ ቡና፣ ታደሰ ተስፋሁን ከአማራ ማረሚያ፣ ሁነኛው መስፍን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ መካሻ እሸቴ በግል፣ ገብሬ እርቅይሁን ከአማራ ፖሊና ለይኩን ብርሃኑ ከፌዴራል ፖሊስ ያሸነፉ አትሌቶች መሆናቸው ታውቋል፡፡