- Advertisement -

የዓድዋ ድል 122ኛ ዓመት

‹‹እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለኔ ሞት አላዝንም፡፡ ደግሞ እግዚአብሔር አሳፍሮኝ አያውቅም ወደፊትም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም፡፡ አሁንም አገር የሚያጠፉ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልንን ባህር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሬን ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡ አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም፡፡ አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ ዕርዳኝ፣ ጉልበት የሌለህ ለልጅህም ለምሽትህም ለሃይማኖት ስትል በሐዘን ዕርዳኝ፡፡ ወስልተህ የቀረህ ግን፣ ኋላ ትጣላኛለህ አልተውህም ማርያምን ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬ በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡››

ይህ የአዋጅ ቃል ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ሕዝቡንና የየአካባቢውን መኳንንትና ገዢዎች በኢጣሊያ ላይ ያነሳሱበት የክተት አዋጅ ነበር፡፡ በዚህም አዋጅ መሠረትም 122 ዓመታት በፊት፣ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ድል ተመቶበታል፡፡ ኢትዮጵያውያን እርመኛ አርበኞች በጠቅላይ አዝማቹ በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ምኒልክ አማካይነት ሕያው ታሪክ ያስመዘገቡበት ዓድዋ፡፡

ከነገ በስቲያ፣ የካቲት 23 ቀን 2010 .ም. በመላው ኢትዮጵያዓድዋ ድል መታሰቢያ ይከበራል፡፡ ‹‹ዓድዋ በአብሮነት የአሸናፊነት ተምሳሌት!›› በሚል መሪ ቃል የካቲት 22 እና 23 በክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንደሚከበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ በዐውደ ውጊያው ቦታ በዓድዋ በሶሎዳ ተራራ አካባቢ ከዋዜማው ጀምሮ ሲምፖዚየም፣ ዐውደ ርዕይና ሥነ ጥበባዊ መሰናዶ ይኖራል፡፡ በተለይ በቦታው ስለሚገነባው ሙዚየም እየተከናወነ ስላለው ተግባር ውይይት ይካሄዳል፡፡ በሌላም በኩል አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት የዓድዋ ኮንፍረንስ ሐሙስ የካቲት 22 ቀን፣ በአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ከ2፡30 ሰዓት ጀምሮ ቀኑን ሙሉ እንደሚያካሂድ አስታውቋል፡፡ በኢትዮጵያ መንግሥት መናገሻ ከተማ በአዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ በሚገኘው ዳግማዊ ምኒልክ ሐውልትና አደባባይ እንደሁሌም በልዩ ሥነ ሥርዓት እንደሚከበር ይጠበቃል፡፡

ታሪኩ

1888 .ም. ኢጣሊያ የቅኝ ግዛት ሕልሟን እውን ለማድረግ በተነሣች ጊዜ ሰበበ ጦርነት የሆነው የውጫሌው ውል ነበር፡፡ በአንቀጽ 17 በኢጣሊያንኛ ትርጉሙ ኢትዮጵያ የኢጣሊያ ጥብቅ ግዛት ነች፤ የውጭ ግንኙነቷ በርሷ በኩል ይሆናል የሚለው የተጭበረበረ ሐረግ ነበር ፍልሚያ ውስጥ የከተታቸው፡፡

ኢትዮጵያውያንም የውስጥ ችግራቸውን ወደጎን ትተው ከየማዕዘኑ ተጠራርተው በአፄ ምኒልክ መሪነት ከፍልሚያው አውድማ ተሰለፉ፡፡ በታሪክ ጸሐፊው በአቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ አገላለጽ፣ የኢጣሊያንንም ወታደር ከበው እየተፏከሩ በጥይትና በጎራዴ ሲደበድቡት የኢጣሊያ ጦር አራት ሰዓት ከተዋጋ በኋላ ሽሽት ዠመረ፡፡ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን እየተከታተሉ ሲወጉት፣ አዝማቹ ጄኔራል አልቤርቶኒ ተቀምጦበት የነበረው በቅሎ ተመቶ ወደቀ፡፡ ወዲያው ተነሥቼ አመልጣለሁ ብሎ ለመነሣት ሲጥር ከቅምጡ ሳይነሳ እየተሽቀዳደሙ የሚሮጡት ኢትዮጵያውያን ደርሰው ጄኔራሉን ማረኩት፡፡

- Advertisement -

1ኛው ክፍለ ጦር አዛዡ ተማርኮ፣ ሠራዊቱ በጭራሽ ከጠፋ በኋላ ሁለተኛው ክፍል የጦር ሠራዊት ራአዮ ከሚባለው ስፍራ ላይ ሆኖ፣ ካራት እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ የሦስተኛውን ክፍል የጄኔራል ኤሌናን ጦር ጨምሮ ተዋግቶ በመጨረሻ የጦር አዛዡ ጄኔራል አሪሞንእዚያው እጦርነቱ ላይ ሞቶ ተገኘ፡፡

ከዚህም በኋላ በመጨረሻ ያለው የኢጣሊያ ጦር በተለይ ማርያም ሸዊቶ ከሚባለው ስፍራ ላይ ተጋጥሞ ከቀድሞው የበለጠ ጦርነት ተደረገ፡፡ ይልቁንም የመጨረሻው ድል የሚፈጸምበት በመሆኑ የሁለቱም የጦር ሠራዊት ተደባልቆ በጨበጣ በሚዋጉበት ጊዜ፣ በጨበጣ በሚደረገው ዘመቻ ከኢጣሊያኖች ይልቅ ኢትዮጵያውያን በጎራዴ አነዛዘር የቀለጠፉ ነበሩ፡፡

ይሁን እንጂ ኢጣሊያኖች ተስፋ ቆረጠ ኃይል እስከ አሥራ ሁለት ሰዓት ድረስ በጉብዝና ሲዋጉ በመጨረሻ አዛዣቸው ጄኔራል ዳቦርሚዳ በጥይት ደረቱን ተመቶ ወድቆ ባንዲት ጠብታ ውሃ ማነው አፌን የሚያርሰኝ እያለ እንደ ተኮነነው ነዌ ሲጮኽ ጥቂት ቆይቶ ሞተ፡፡

«ጣልያን ገጠመ ከዳኛው ሙግት

አግቦ አስመስለው በሠራው ጥይት

አሁን ማን አለ በዚህ ዓለም፣

ጣልያን አስደንጋጭ ቀን ሲጨልም

ግብሩ ሰፊ ነው ጠጁ ባሕር

የዳኛው ጌታ ያበሻ ሕር»

ተብሎም ስለዓድዋ ድል ስንኞች ታሰሩለት፡፡

የታሪክ ጸሐፊው ቤርክሌይ ስለ ዓድዋ ዐውደ ውጊያ የጻፈውን ጳውሎስ ኞኞ «ዐጤ ምኒልክ» ብሎ ባሳተመው መጽሐፉ እንደሚከተለው ገልጾታል፡፡

«ሃያ ሺሕ ያህል ወታደሮች ያሉበት የአውሮጳ ጦር በአፍሪቃ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ተሸነፈ፡፡ በእኔ እምነት መሠረት በዘመናችን ታሪክ ውስጥ እንደ ዓድዋው ያለ ጦርነት የለም፡፡ በእልቂቱ በኩል 25,000 ሰዎች በአንድ ቀን ጀምበር የሞቱበትና የቆሰሉበት ነው፡፡ ፖለቲካና ታሪክ አበቃ፡፡ . . . አበሾች አደገኛ ሕዝቦች መሆናቸው ከኦሪት ዘፍጥረት ጀምሮ ተጽፎላቸዋል፡፡ የእኛ ዓለም ገና ቶር እና ኦዲዮን በሚባሉ አማልክት ሲያመልክ በነበረበት ጊዜ አበሾች የክርስትናን ሃይማኖት የተቀበሉ ቸው፡፡»

የዓድዋውን ጦርነት ከመሩት የጦር አዛዦች መካከል እቴጌ ጣይቱ፣ ራስ መኰንን፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ራስ አሉላ፣ ራስ አባተ፣ ፊታውራሪ ገበየሁ ይገኙበታል፡፡

በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የነበሩት ፊታውራሪ ተክለ ሐዋርያት ተክለ ማርያም በዓድዋው የጦር ግንባር በመሰለፍ ያዩትን በሕይወት ታሪካቸው ጽፈው አቆይተውልናል፡፡

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ባሉት ሳምንታት የአካባቢው እረኞች ሲጫወቱ ደበሎ እየሰቀሉ አዋጅ ይናገሩ እንደነበር አዋጁንም ጠቅሰው ለዘመናችን አድርሰውልናል፡፡  «እሽ ስማ ብለውሃል መስማሚያ አይንሣህ «ያድባርን ያውጋርን ጠላት… «ሐማሴንን ለራስ አሉላ፣ አጋሜን ተምቤንን ለራስ ስብሐት፣ እንደርታን ዋጀራትን ለደጃዝማች ሐጎስ፣ እንዳመኾኒ ሰለሞንን ለፊታውራሪ ተክሌ፣ «ዋድላን ደላንታን ለፊውታራሪ ገበየሁ፣ ሰጥቻለሁ ብለውሃል! ይበጅ ያድርግ፤

«በየካቲት ጣጣችን ክትት «በመጋቢት እቤታችን ግብት

«በሚያዛሳ ያገግም የከሳ

«ይበጅ ያድርግ…» እያሉ ይተነባሉ፡፡

የዓድዋ ጦርነት ሲነሳ ሁሌም የሚነሳው ባሻዬ አውአሎም ሐረጎት ነው፡፡ በስለላ ሙያው ተጠቅሞ የኢጣሊያን የጦር እቅድ በማሳከር አኩሪ ተግባር አከናውኗል፡፡ የባዕዳኑ አገልጋይ የነበረው አውዓሎም በቁጭት በመነሳሳትና በብላታ ገብረእግዚአብሔር ጊላ አማካይነት ከራስ መንገሻ ዮሐንስ ጋር ይገናኛል፡፡

እንደ ቀኛዝማች ታደሰ ዘወልዴ ጽሑፍ ራስ መንገሻም ከአፄ ምኒልክና ከእቴጌ ጣይቱ ጋር ይገናኙና የጦርነቱ ጊዜ ሲቃረብ የተሳከረውን እቅድ ለዤኔራል ባራቲየሪ እንዲደርስ ይደረጋል፡፡

አውዓሎምና ብላታ ብረ እግዚአብሔር ከኢጣሊያውያን ተለይተው ወደ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ገብተው ጦርነቱ ሲፋፋም ከኢጣሊያ መኰንኖች አንዱ ነገሩን ተገንዝቦ «አውዓሎም አውዓሎም» እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምቶ፣ «ዝወኣልካዮ ኣያውዕለኒ» (ከዋልክበት አያውለኝ) ብሎ አፌዘበት ይባላል፡

ኪነ ጥበብ

የዓድዋ ድልን አስመልክቶ በተለያዩ የጥበብ ሰዎች የተሠሩ ኪነጥበብ ተኮር ሥራዎች በፊልም፣ በተውኔት፣ በሥነ ሥዕል፣ በሥነ ግጥም፣ በቅኔ ወዘተ. የቀረቡት በርካታ ናቸው፡፡

ከ20 ዓመታት በፊት ታዋቂው የፊልም ዳይሬክተር ኘሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ «ዓድዋ» በሚል መጠሪያ የደረሰው ፊልም በበርካታ ታሪካዊ ፎቶግራፎች የታጀበ ነበር፡፡ በተውኔት ዘርፍ ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ነፍስ ኄር ጸጋዬ ገብረመድኅን «ዓድዋ» ከተሰኘውና 1964 ዓ.ም. ከደረሰው ግጥም ሌላ አሜሪካ ውስጥ ለእይታ የበቃው «ምኒልክ» ተውኔት ዓድዋን ያጎላበት ነበር፡፡ አዲስ አበባ ከተማ 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩዋን በ1979 ዓ.ም. ስታከብር ታዋቂው የቴአትር ዳይሬክተር አባተ መኩሪያ በአጋጣሚው የዓድዋውን ዘመቻ ክተት የሚያሳይ ትርኢት ‹‹ክተት ወደ ዓድዋ ዘመቻ›› በሚል ርእስ አሳይቶ ነበር፡፡ ይኸው ታዋቂ አርቲስቶችን ጨምሮ 4000 ሰዎች የተሳተፉበት ትርኢት በምስል ተቀርፆ በየጊዜው በቴሌቪዥን መስኮት ከመታየት አልተቋረጠምም፡፡ የደጃዝማች ግርማቸው ተክለሐዋርያት ካለፉ በኋላ የታተመው «ዓድዋ» ተውኔታቸውም ይጠቀሳል፡፡ የድምፃዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የ‹‹ጥቁር ሰው›› ዓድዋ ተኮር ቅንቀናውም የቅርብ ዘመን ሥራ ነው፡፡

«! . . . ያቺ ዓድዋ» የጸጋዬ ገብረመድኅን «እሳት ወይ አበባ» ከተሰኘው የሥነ ግጥም መድበሉ ውስጥ የሚገኝ ስለ ዓድዋ የዘከረበት ነው፡፡

ሥነ ሥዕልን በተመለከተ ድሉን የሚያሳዩ በተለያዩ ሠዓልያን የተሣሉ ባህላዊና ዘመናዊ ሥዕሎች የመኖራቸውን ያህል ኢጣሊያናውያንም የምኒልክን ታላቅነትና ድል አድራጊነት፣ የክሪስፒን ተሸናፊነትና ውድቀት የሚያሳይ የካርቱን ሥዕል አሰራጭተዋል፡፡ ሥዕሉ « ፐቲት ጆርናል» የታተመ ሲሆን፣ ምኒልክ ክርስፒን በታላቅ ዱላ ሲጎሽሙትና ሲጥሉት ያሳያል፡፡

የዓድዋ ጦርነት ድልን በሥዕል በመግለጽ በኩል የቤተ ክርስቲያን ሠዓሊዎች ዓይነተኛ ሚና እንደነበራቸው ይገለጻል፡፡ ‹‹Ethiopian Paintings on Adwa›› በሚል ርእስ ጥናት የሠሩት በሙኒክ አትኖሎጂካል ሙዚየም የኢትዮጵያ ክፍል ኃላፊ የነበሩት አቶ ግርማ ፍሥሐ፣ ትውፊታዊ ሠዓልያኑ የዓድዋውን ድል በሥዕላቸው የዘከሩበት መንገድ ለኢትዮጵያ ባህላዊ አሣሣል ዕድገትን አስተዋጽኦ አድርጓል ይላሉ፡፡

አንዳንዶቹ ሥዕሎች የዐፄ ምኒልክ አማካሪ በነበሩት አልፍሬድ ኢልግ ስብስብ ውስጥ በስዊዘርላንድ ሲገኙ፣ የሆልትዝ ስብስብ በበርሊንና የሆፍማን ስብስብ በዋሽንግተን ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ. በ1905 አካባቢ የተሣሉት ከነዚህ ሥዕሎች መካከል የአለቃ ኤሊያስ፣ የአለቃ ኅሩይና የፍሬ ሕይወት ይገኙበታል፡፡

በሥዕሉ ጐልተው ከሚታዩት ከጠቅላይ አዝማቹ ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በተጨማሪ አዝማቾች፣ መካከል ፊታውራሪ ገበየሁ፣ ራስ መንገሻ፣ ራስ አሉላ፣  ራስ አባተ፣ ደጃዝማች ባልቻ ይጠቀሳሉ፡፡ ከአዝማሪዎች መካከልም አዝማሪ ፃዲቄ እየሸለለችና እየፎከረች ስታዋጋ የሚያሳይ ሥዕልም የዘመኑ ትሩፋት ነው፡፡

አዝማሪዎች ለኢትዮጵያ ሠራዊት ይሰጡት የነበረው ወኔ ቀስቃሽ አዝመራ ጉልህ ነበር፡፡ ስለነዚያ አዝማሪዎች ቤርክሌይ ከጉዞው ጋር አያይዞ የጻፈው የሚጠቀስ ነው፡፡

«. . . በሠራዊቱ መሀል አዝማሪዎችም አብረው ይዘምታሉ፡፡ በዚያ ሁሉ ሁካታ አዝማሪዎቹ ዘማቹን እያጫወቱ ይሄዳሉ፡፡ አብሮአቸው የሚጓዘው ሠራዊትም ለአዝማሪዎቹ ግጥም ይነግሩዋቸዋል፡፡ አዝማሪዎቹ የደከመውን በግጥም እያበረታቱ ይጓዛሉ»

ወንድሜ ራበህ ወይ? ወንድሜ ጠማህ ወይ

አዎን የናቴ ልጅ እርቦህ ጠምቶሃል

ታዲያ የናቴ ልጅ አዳኝ ወፍ አይደለህም ወይ?

ግፋ ብረር ወደፊትህ ሂደህ ጠላትህን አትበላም ወይ?

ግፋ ወደፊት ከበዓሉ ቦታ ፈጥነህ ድረስ

የምታርደውን ሥጋ የማቆራርጥልህ እኔ ነኝ

ግፋ የናቴ ልጅ ውሃ ጠምቶሃል

ጠጅ ብታጣ ደሜን እንድትጠጣ እሰጥሃለሁ

ቅዳሜ የካቲት 22 ቀን 1888 .. ሌሊት ለእሑድ 23 አጥቢያ ወታደሩ እየሸለለ አዝማሪዎችም ማዘመር ጀመሩ፡፡

«ኧረ ጉዱ በዛ ኧረ ጉዱ በዛ

        በጀልባ ተሻግሮ አበሻን ሊገዛ» ይሉ ነበር፡፡

ለጦር አዝማቾችም ማንቂያም ተገጥሟል፡፡

‹‹ክፉ አረም በቀለ በምጥዋ ቆላ

አሁን ሳይበረክት አርመው አሉላ፡፡

እነዚያ ጣሊያኖች ሙግት አይገባቸው

አሉላ አነጣጥረህ ቶሎ አወራርዳቸው፡፡

ዳኘው ወዴት ሄዷል እስኪ ወጥተህ እይ

አክሱም መንገሻዬ እስኪያዝ ነወይ፡፡

ዓድዋ ላይ ጣሊያኖች የዘፈኑለት

       ምኒልክ ጎራዴህ ወረደ ባንገት፡፡››

የዓድዋ ጦርነት የተካሄደበት ዕለት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የበዓላት ትውፊት መሠረት የቅዱስ ጊዮርጊስ ቀን ነው፡፡ ከቀደመው ጊዜ አንስቶ እስካሁን «ጠባቂ ቅዱስ» ( ፓትረን ሴንት) ተብሎ ይታወቃል፡፡ እስከነ ዝማሬውም

«የዓድዋ አርበኛ ቅዱስ ጊዮርጊስ

ከምኒልክ ጋር አብሮ ሲቀድስ፤

ምኒልክ በጦሩ ጊዮርጊስ በፈረሱ

ጣልያንን ድል አደረጉ ደም እያፈሰሱ» እየተባለ እስካሁን ይዘመራል፡

- Advertisement -

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን

ከ ተመሳሳይ አምዶች

ለጤና ተቋማት አክሬዲቴሽን ለመስጠት ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑ ተገለጸ

የኢትዮጵያ አክሬዲቴሽን አገልግሎት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ለጤና ተቋማት አክሬዲቴሽን ለመስጠት ዝግጅቱን እያጠናቀቀ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የሊያና ሔልዝ ኬር (ያኔት ሆስፒታሎች) አራት ዓለም አቀፍ የዕውቅና ምስክር...

ሴት ሥራ ፈጣሪዎች በብሩህ እናት 2017 ውድድር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

ሴት ሥራ ፈጣሪዎች  የፈጠራ ሥራቸውን ለማጎልበት፣ የቢዝነስ ክህሎታቸውን ለማሳደግና የገንዘብ ድጋፍ ለማግኘት በሚረዳቸው የብሩህ እናት 2017 የንግድ ሥራ ፈጠራ  ውድድር እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ፡፡ የሥራና ክህሎት...

በምዕራብ ጎንደር ዞን ባገረሸው የኮሌራ ወረርሽኝ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገለጸ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ቋራ ወረዳ እንደገና ባገረሸው የኮሌራ ወራርሽኝ ምክንያት ስድስት ሰዎች መሞታቸውን፣ የወረዳው ጤና ቢሮ አስታወቀ፡፡ የቋራ ወረዳ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ...

ባለፉት ስድስት ወራት 620 እናቶች በወሊድ ሕይወታቸው ማለፉ ተነገረ

ከ330 በላይ ሕፃናት በምግብ እጥረት ሞተዋል ተብሏል በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ከወሊድ ጋር በተያያዘ 620 እናቶች መሞታቸውን፣ የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ለፓርላማ አስታወቀ፡፡ ተቋሙ ይህንን...

ያለዕድሜ ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ያስችላሉ የተባሉ የተግባር መመርያዎች ይፋ ሆኑ

በኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. እስከ 2030 የልጅነት ጋብቻንና የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት ያስችላሉ የተባሉ ስምንት የተግባር መመርያዎች ይፋ ሆነዋል፡፡ የጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ያስችላል የተባለው የትግበራ መመርያ...

ከራስ ተነሳሽነት የተቀዳ ስኬት

‹‹አሁን እኔ ምኔ አካል ጉዳተኛ ይመስላል›› ትላለች፡፡ አካል ጉዳተኝነቷን በማየት ማወቅ አይቻልም፡፡ ነገር ግን እሷ የመስማት ችግር አለባት፡፡ በልጅነቷ በጣም ጎበዝና በአስተማሪዎቿ እንዲሁም በጓደኞቿ...

አዳዲስ ጽሁፎች

ፖርላማው አስቸኳይ ስብሰባ ጠራ

በአራተኛ ዓመት የፓርላማ ዘመን የግማሽ ዓመት እረፍት ላይ የሚገኘው የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት፣ ከተቋቋመ ሶስት አመታትን ያስቆጠረውን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ሪፓርት ለማዳመጥና በፓርላማ የፀደቀለትን የሶስት...

የጅቡቲ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሆነው ተመረጡ

የ 59 ዓመቱ ዲፕሎማትና የጂቡቲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ማህሙድ ዓሊ ይሱፍ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽንን ሊቀመንበር ሆነው እንዲመሩ ዛሬ የካቲት 8...

በሕክምና መቶኛ ዓመቱንና በማስተማር ሰባኛ ዓመቱን እያከበረ ያለው ጎንደር ዩንቨርስቲ ና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 40ኛ ዙር የሕክምና ተማሪዎቹን አስመረቀ

ጎንደር ዩኒቨርሲቲው  ዛሬ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓ.ም ፣ 254 ወንድ እና 112 ሴት   የሕክምና ተማሪዎቹን ያስመረቀው ለ40ኛ ጊዜ መሆኑንና ይኸም ዩኒቨርስቲው የተመሠረተበትን ምዕተዓመት...

የተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች መንግስት የ60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ሰጠ

በኢትዮጵያ ለዐይነ ስውራን ትምህርት መሠረተ ልማት የሚውል  የ60 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ  ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች መንግስት ዛሬ የካቲት 8 ቀን 2017 ዓም መሰጠቱ ታወቀ። ድጋፉ የተሰጠው ...

ህወሓት ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ ፈቃዱ ታገደ

-የቦርድ ትእዛዝ አክብሮ ካልተገኘ ከሶስት ወር በኋላ እንደሚሰረዝ ተገልጿል የምስረታ 50ኛ በዓሉን ለማክበር ቀናት የቀሩት ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርግ ህጋዊ ፈቃዱ...

የአየር መንገዱን አሠራር ጥሰዋል በተባሉ የአዲስ አበባ ሽያጭ ቢሮ ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መወሰዱ ተገለጸ

- የሕግ ክፍሉ ክስ መመሥረት የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች እየተመለከተ ነው ተብሏል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የማስታወቂያና የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ክፍሎች ዕውቅና ውጪ፣ በቅጥር ግቢው ውስጥ የፎቶና የቪዲዮ...
[the_ad id="124766"]

በማህበራዊ ሚዲያዎች ይከታተሉን