ባልና ሚስት ምግባቸውን የሚያዘጋጁት በተለያየ ዕቃ ለየራሳቸው ነበር፡፡ አንድ ቀን ማታ ለራታቸው የሚሆን አጥሚት በተለያዩ ማሰሮ አዘጋጁ፡፡ ቀኑ እየመሸ ሲሄድ የከብቶቹ በር በአጉራ አልተዘጋም ነበርና፡፡ ‹‹አንተ ዝጋ›› በመባባል ተፋጠጡ፡፡ በመጨረሻ ሴትየዋ ወጥታ ለመዝጋት ፈቃደኛ ባለመሆኗ ባልየው አጥሚቱን እንዳትሰርቅበት ማሰሮውን በጭንቅላቱ ተሸክሞ ወደ በሩ ሄደ፡፡
በአንድ እጁ አጉራውን በሌላ እጁ ማሰሮውን ደግፎ ለመዝጋት ሲታገል የሆነ ነገር አወላከፈውና ከበሩ ጋር ተላተመ፡፡ ትኩሱ አጥሚት በሰውነቱ ላይ ተደፍቶ ቢያቃጥለው ኡኡታውን ለቀቀው፡፡ በዚህ ጊዜ ጐረቤቶቹ ተሰብስበው አጥሚቱን ከሰውነቱ ላይ እየጠረጉ ወደ መሬት ሲፈነጥቁ ‹‹ኧረ እባካችሁ ወገኖቼ ሌላ እራት የለኝምና ወደ አፌ በሉት፤›› በማለት ሁሉንም አሳቃቸው፡፡